Tidarfelagi.com

‹አያሌው ሞኙ›

ደጃዝማች አያሌው በ20ኛው መክዘ ከተነሡት ኃያላን መኳንንት አንዱ ናቸው፡፡ የራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ልጅና የእቴጌ ጣይቱ ዘመድ ሲሆኑ የወገራ አውራጃ ሹም፣ የስሜን አውራጃ ገዥ፣ ልጅ ኢያሱ ከተያዙ በኋላ ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ ጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ደጃዝማች አያሌው ብሩ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ሰዎች መካከል ናቸው፡፡ መኢሶ ላይ ከልጅ ኢያሱ ጦር ጋር በተደረገው ጦርነት ተፈሪ መኮንን እንዲያሸንፉ ደጃዝማች አያሌው ከፍ ያለ ሚና ነበራቸው፡፡ ራስ ጉግሣን ለመያዝ አንቺም ላይ በተደረገው ውጊያም የደጃዝማች አያሌው ጀግንነት ወሳኝ ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ ጦርነት ለሚያበረክቱት ውለታ የራስነትን ማዕረግ እንደሚያገኙ ከንጉሥ ተፈሪ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን በአንድ በኩል የእቴጌ ጣይቱ ዘመድ በመሆናቸው፣ በሌላ በኩልም ከቀድሞዎቹ የዐፄ ምንሊክ ባለ ሥልጣናት ወገን ስለሆኑ ተፈሪ ቃላቸው አጠፉባቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ደጃዝማች አያሌውን ያሳዘናቸው በንጉሡ ግብዣ ላይ የነበራቸው ፕሮቶኮል መወሰዱ ነበር፡፡ እንደ ከፍተኛ መኳንንት በንጉሡ ቀኝ በኩል የነበራቸውን የክብር ወንበር ለራስ ደስታ እንዲለቁ መደረጉ ደጃዝማች አያሌውን ‹እጄ አመድ አፋሽ ነው› እንዲሉ አደረጋቸው፡፡ በኋላም ከንጉሥ ተፈሪ ጋር ይበልጥ ተቃቃሩና በቅጣት መልክ አሩሲ ተመደቡ፡፡

ደጃዝማች አያሌው ከንጉሡ ጋር እንደገና ለመስማማት የሞከሩት የጣልያን ጦርነት እየገፋ ሲመጣ ነበር፡፡ ወደ ኤርትራ ድንበር እንዲዘምቱ ትእዛዝ የተሰጣቸው ደጃዝማች(ፊታውራሪ) አያሌው ብሩ መንገድ ላይ ታመሙ፡፡ በኋላም የንጉሡ ሐኪም ስዊድናዊው ዶክተር ሓራልድ ኒስትሮም በአውሮፕላን ተላከላቸው፡፡ በተደረገላቸው ሕክምና ጤናቸው ሲመለስ ረዥም ጉዞ ወደሚጠይቀው የጦር ግንባር ጦራቸውን ይዘው ተጓዙ፡፡ ስዊድናዊው ሐኪምም አብሯቸው ዘመተ፡፡ የጉዞውንም ማስታወሻ በሚገባ ጻፈልን፡፡

ደጃዝማች አያሌው ብሩ ንጉሥ ተፈሪን አምነው ዘመዳቸውን ራስ ጉግሣን ቢዋጉም ቃል የተገባላቸውን የራስነት ማዕረግ ሳያገኙት በመቅረታቸው የጎንደር ሕዝብ
አያሌው ሞኙ
ሰው አማኙ፣ ሰው አማኙ እያለ ዘፍኖላቸዋል፡፡ ዘፈኑም እስከ ዘመናችን ድረስ ደርሷል፡፡

ይህንን ቅሬታቸው ያወቁት ጣልያኖች በተደጋጋሚ ከጎናቸው ሊያሰልፏቸው ሞክረዋል፡፡ ንጉሥ ተፈሪ ደጃዝማች አያሌውን ባለማመናቸው የተነሣ ወደ ጦርነት ሲዘምቱ እንኳን የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር ይሰልሏቸው ነበር፡፡ አብሯቸው እስከ ጦር ግንባር ዘምቶ፣ የኢትዮጵያ ጦር ተሸንፎ ሲመለስም እስከ ደብረ ታቦር አብሯቸው ተጉዞ A memoir of the Italian – Ethiopian war of 1935-36 የተሰኘውን መጽሐፍ እኤአ በ1938 የጻፈው ዶክተር ሐራልድ ኒስትሮም ምናልባት በንጉሡ ላይ ባደረባቸው ቅሬታ ተገፋፍተው ወደ ጣልያኖች ይገቡ እንደሆን ሲጠይቃቸው ‹‹እውነት ነው ንጉሡ በድለውኛል›› አሉ ደጃዝማች አያሌው ‹‹ነገር ግን እኔ ሀገሬን በምንም ያህል ገንዘብ የምከዳ አይደለሁም፤ ጣልያኖች እኔን ይከዳል ብለው ማሰባቸው የሚያሳፍር ነው›› ብለው ነበር መልስ የሰጡት፡፡

አንዳንዴ መንግሥታት፣ ነገሥታት፣ መሪዎች፣ ባለ ሥልጣናት በግለሰቦች፣ በሕዝቦችና በቡድኖች ላይ የሚያደርሱት ግፍና በደል ይኖራል፡፡ ሀገር ግን አትበድልም፡፡ ሀገርና መንግሥት፣ ሀገርና ንጉሥ፣ ሀገርና ፓርቲ፣ ሀገርና መሪ የተለያዩ ናቸው፡፡ እንደ ደጃዝማች አያሌው መሪዎችን ከሀገር መለየት ሲሳን በየዘመናቱ የተነሡ ባለጊዜዎች የሠሩትን ጥፋት፣ በዘመናት ሁሉ ለምትኖር ሀገር ማሸከምን ያመጣል፡፡

ዶክተር ሐራልድ ኒስትሮም የንጉሥ ተፈሪ የግል ሐኪም ሆኖ የተቀጠረው እኤአ በ1927 ነው፡፡ ዶክተር ሐራልድ በቤተ መንግሥትና በቤተ ሳይዳ ሆስፒታል ይሠራ ነበር፡፡ በኋላም ደጃዝማች አያሌው ብሩን ተከትሎ እስከ ጦር ግንባር ድረስ ተጉዟል፡፡ ዶክተር ሐራልድ ጉዞውን በተመለከተ የዛሬ 77 ዓመት ያሳተመው መጽሐፍ በዶክተር ገበየሁ ተፈሪና በደሳለኝ ዓለሙ ‹የተደበቀው ማስተዋሻ› በሚል ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ርእስ በጥቅምት 2014(እኤአ) ታትሟል፡፡

አንቡት፤ በሌሎች የታሪክ መጻሕፍት የማናገኛቸውን የጦርነቱን መረጃዎች ከቅርብ የዓይን ምስክር እናነባለን፡፡ ዶክተር ሐራልድ አማርኛ አቀላጥፎ የሚናገር፣ የሀገሪቱንም ጠባይ የተረዳ ሰው በመሆኑ የሚነግረን ነገር ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ በተለይም በመጽሐፉ መጨረሻ የኢትዮጵያ ጦር በማይጨው ዐውደ ውጊያ ለምን ሊሸነፍ እንደቻለ የራሱን አምስት የግምገማ ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ ሁላችንም ደግመን ደጋግመን ልናስብባቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡

መልካም ንባብ፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...