Tidarfelagi.com

አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል…

ትላንት ከአንዷ ጓደኛዬ ጋር ምሳ ለመብላት አንዱ ምግብ ቤት ቁጭ ብለናል።

ምግቡን እየጠበቅን የተገናኘንበትን ብርቱ ጉዳይ ስንወያይ፣ አራት አለባበሳቸውና ነገረ ስራቸው ሁሉ ሃያዎቹን ከጀመሩ እንዳልቆዩ የሚያሳብቅባቸው ወጣቶች መጡና አጠገባችን ያለውን ጠረጰዛ ከበው ተቀመጡ።

በእነሱና በእኛ መሃከል ያለው ርቀት በጣም ቅርብ ስለሆነና ሁኔታቸውን ስለገመትን ‹ጮክ ብለው ሲጫወቱ መረበሻችን አይቀርም። ሚስጥራችንንም ሊሰሙ ይችላሉ›› ብለን ስለሰጋን ሌላ ቦታ በአይናችን ብናማትርም ክፍት ወንበር የለም።

ምርጫ በማጣታችን በተቀመጥንበት ሆነን ጉዳያችንን ማውራት ቀጠልን። ብዙ ደቂቃዎች ቢያልፉም ይረብሹናል ካልናቸው ወጣቶች እንኳን ጩኸት የለሆሳስ ቃላትም ጆሮዬ ስላልገቡ ዞር ብዬ አየኋቸው።

የዝምታቸው ምስጢር ተፈታልኝ።

አራቱም እንደ ሰአት ሰሪ ሞባይል ስልካቸው ላይ አቀርቅረዋል። አንዱ ለብቻው እንደመሳቅ ያደርገዋል። ፌስቡክ ላይ መሆኑን ገመትኩ። የደረፍክን አጭሬ ቀልዶች እያነበበ መሆን አለበት። ሴቷ በአውራ ጣቷ በፍጥነት ገፆችን ወደላይ ትገልጣለች። የሚስባት ነገር አጥታ ፌስቡክ ላይ ላይ ታች እያለች ሊሆን ይችላል። የቀሩት ሁለቱ በከፍተኛ ተመስጦ ስልካቸው ላይ አፍጥጠዋል። የአማላይ ሴቶችን ገፅ እየበረበሩ ይሆናል።

እርግጥ ነው፤ ብዙ የዚህ ዘመን ሰዎች በቁምነገር ለመገናኘት ተቀጣጥረን ፣ ምግብ ቤት ገብተን፣ ቤታቸን እንግዳ ጋብዘን፣ ኬክ ቤት ቁጭ ብለን፣ ቶሞካ ማኪያቶ እየጠጣን፣ ፊልም ቤት ሰልፍ እየጠበቅን፣ መናፈሻ ለመናፈስ ጋደም ብለን፣ ሃይቅ ዳር ተፈጥሮን ለማድነቅ ቁጭ ብለን፣ በቡድን ጥሬ ስጋ እየበላን ከስልካችን መላቀቅ ካቃተን ቆይተናል። ስልካችን ትልቁ ሱሳችን ከሆነ ሰንብተናል።
ስልካችን ባትሪ ሲያልቅበት ሱሳችን ሞልቶ እስኪመለስ መጠበቅ ስለማያስችለን፣ ጣታችን ‹‹ስልኬን ስልኬን›› እያለ ስለሚበላን፣ አንጎላችን ‹‹ፌስቡክ ፌስቡክ፣ ቫይበር ቫይበር›› እያለን ስለሚሞግተን፣ በሰንሰለት እንደታሰረ ውሻ ‹‹ቻርጅ›› ሊደረግ በተሰካ ስልካችን ገመድ ታስረን ሱሳችንን የምናስታግስ ‹‹የስልካችን እስረኞች›› ትንሽ አይደለንም።
በቀኝ እጃችን እንጀራ በምስር እየበላን በግራው ቴክስት የምንፃፃፍ፣
በቀኝ አይናችን ልጃችን ዳዴ እያለ ሲፈነድቅ እያየን በግራ አይናችን ዋትስ አፕ ላይ አዲስ መልእክት እንዳለ የምናይ፣
ስልካችንን ሽንት ቤት ይዘን የምንገባ፣
ከእንቅልፋችን ስንነቃ ባል ወይ ሚስታችንን እንዴት አደርህ እንዴት አደርሽ ሳንል ስልካችን ጋር የምንሮጥ፣ ሲመሽ ከምንወደው ሰው በላይ አስጠግተነው የምንተኛ ትንሽ አይደለንም።

ልጆቹን መልሼ አየኋቸው። በመሃል ጥቂተ ቃላት ተወራውረው አሁንም ወደየ ስልካቸው ያቀረቅራሉ።
በጉጉት ገፅ ይገልጣሉ። ፎቶ እያሽከረከሩ ያያሉ። አልፎ አልፎ ስልካቸው ላይ ያዩትን ነገር ለሌላኛው ያሳያሉ።
ደግሞ እንደገና ያቀረቅራሉ።

የሆነ ቦታ ያነበብኩት ነገር ትዝ አለኝ።

ሞባይል ስልካችን የእጅ ሰአታችንን ተክቷል።
ሞባይል ስልካችን የቀን መቁጠሪያችንን ተክቷል።
ሞባይል ስልካችን ካሜራዎቻችንን ተክቷል።
የምንወዳቸውን ሰዎች እንዲተካ ግን መፍቀድ የለብንም።

ይሄ ማስጠንቀቂያ ለእነሱም ለብዙዎቻችንም እንዳልሰራ ተገነዘብኩ።

ሞባይል ስልኮች ከራቀው ሰው ጋር ሲያገናኙን አጠገባችን ካለው ሰው ጋር ግን ክፉኛ እንዳቆራረጡን ተረዳሁ።

በመሃል የእኛም የእነሱም ምግብ መጣ።

እጆቼን ታጥቤ ስመለስ አንደኛው ልጅ ምግቡን ፎቶ ሲያነሳ ተመለከትኩ። ከመብላቱ በላይ የበላውን በፌስቡክ ማሳየቱ የሚበልጥበት ትውልድ….የማይደገም ኮንሰርት ሄዶ መሃሙድ አህመድን በአይኑ በብረቱ ከማየቱ ይልቅ መሃሙድን እያየ መሆኑን ለማሳወቁ ዋጋ የሚሰጥ ትውልድ…

ከጓደኛዬ ጋር ምግባችንን በልተን ለመነሳት ስንዘገጃጅ አራቱ ወጣቶች በአንዱ ልጅ አስተባባሪነት ‹‹ሰልፊ›› ሲነሱ አየሁ።

ይሄኔ እንደተገናኘ ሰው ‹‹ዛሬ ተገናኝተን ምሳ ስንበላ…ኢት ወዝ ሶ ማች ፈን ሚቲንግ ኦል ማይ ፍሬንድስ….›› ብለው ፌስቡክ ላይ ሊለጥፉት ይሆናል።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...