Tidarfelagi.com

አንዳንድ አሟሟቶች

ሀበሻ አሟሟቴን አሳምረው ይላል። አሟሟት ትልቅ የክብር ሞት ላይ የተንጠለጠለች አላቂ እቃ ነች። የሚደነቅ አሟሟት እንዳለ ሁሉ ግራ የሆነ አሟሟት አለ። ላልቃሽ ቤተሰብ የሚቸግር የሚመስል። ከሞተ የገዘፈ የሚመስል ሰውን ሞት ተኩነስንሶ እና ተልከስክሶ አንሸራቶ ይጥለዋል። ከሞቱ አሟሟቱ አስብሎ ያሳዝናል።

ጊዜው በንግስት ዘውዲቱ የንግስ በዓል ወቅት ነው። ስነስርዓቱ በደመቀ ሰልፍ ከዋለ በኋላ ወደ ቤተመንግስት ተገባ። ግብር ሊገባ፤ሊበላ ሊጠጣ። የትየሌለ ነበር አሉ ለዱንካን ሰበራ የመጣው ሰው። መርስኤ ሀዘንን በእለቱ የሆነውን እንዲህ አስቀምጠውታል፣
«በዚህ ቀን ግብሩን ለመብላት የተሰበሰበው ሠራዊት እጅግ ብዙ ስለ ሆነ ሊጋባ በየነ በበቅሎ አጋፈሩ። ሠራዊቱ ከመብዛቱ የተነሣ እርስ በእርሱ ሲጋፋ ዘጠኝ ሰው በእግር ተጠቅጥቆ ሞተ»
ዘጠኝ ሰው?! ሆድ ለተባለ ስልቻ ዘጠኝ ሰው?! ከተበላ በኋላ ትዝታው እንኳን ሟምቶ ለሚጠፋ የአንድ ቀን ጥጋብ ዘጠኝ ሰው!! ዘመድ ምን ብሎ አለቀሰ ይሆን?
ከዘጠኙ ሰዎች መሃል ምናልባት የተወሰኑት የሸዋ ጦር ከወሎ ጦር ጋር ባደረገው ጦርነት ወቅት ሞት መሃል ገብተው የደነሱ ይሆናሉ። ያኔ ያልሸረፋቸው ሞት እንዲህ በተራ ግርግር ውስጥ መጥቶ ሲነክሳቸው ምን ይባላል?
ዮፍታሄ ንጉሤ፣
«ዋናውስ በሽታ ምንም አልጎዳቸው፣
ካገገሙ ኋላ ግርሻ ገደላቸው» ያለው ይሄን ይሆናል።

መርስኤ ሀዘንን እንድገም፣
በ1909 ነው። የውጊያ ጊዜ ነው። ተማሪዎች ጥይት አያስነካም በሚል አንድ እፅ መሸጥ ጀመሩ አሉ። እንደጉድ ተሸመተ። አንዱ ውብአየሁ የሚባል ዳቆን ነበር። ባምስት ባምስት ብር እየቸበቸበች ንዑስ ከበርቴ ወደ መሆን ተጠግታለች። ደጃዝማች ኃይለማርያም የተባለ ሰው ስለ እፁ ሰማ። ሰምቶ ለራሱ ፈለገው። ውብአየሁን ቤቱ ጠርቶ ጠየቀው። ውብ አየሁ በኩራት እና በመተማመን አብራርታ ዋጋውን ተናገረች።
«ለመሆኑ ከጥይት ማዳኑን በምን አረጋግጣለው አለ ኃይለማርያም (የዘንድሮ ኃይለማርያም ነው እንጂ የድሮ ኃይለማርያሞች ብልጥ ነበሩ ባይ ዘ ወይ 🙂 )
«ይሞክሩብኝ» አለች ውብአየሁ።ከቤት ወጥተው ወደ ሜዳ ሄዱ። ውብ አየሁ እፁን በእጁ ይዞ ፎቶ እንደሚነሳ ሰው ፈገግ እና ኮራ ብሎ ቆመ። ኃይለማርያም ዲሞትፈሩን ጥይት አጉርሶ ሂድ ቢለው የውብ አየሁ ሆድ ውስጥ ሄዶ ተከተተ። ውብ አየሁ ወደቀ። አልተነሳም!!

ሌላኛው አሟሟት በሬድዩ ነው የሰማሁት። በጣም የቆየ ቢሆንም ባስታወስኩት ቁጥር ልጅቷ ታሳዝነኛለች።
ከጓደኛዋ ጋር ሻይ ሊጠጡ ካፌ ይገባሉ። አዘዙ። ቀረበ። በጨዋታ ተጠምደው ስለነበር የጓደኛዋን ዓይን ዓይን እያየች ሻይውን ፉት ትልለታለች።
ወዲያው ፊቷ ተለዋወጠ። ሻዩን ከእጇ ላይ ጣለችው። በጉልበቷ ተንበረከከች። «ንቧ! ንቧ! …ወይኔ! መተንፈስ አቃተኝ» እያለች በጣር ድምፅ ጮኧች። በጉልበቷ አሸበረከች። ጓደኛዋ ግራ ተጋባች። «ውሃ ውሃ እያለች» ጮኧች።
«መተ…ን…ፈ… ስ አ… ቃተ…ኝ» እያለች ወለሉላይ ተዘረጋች። ትንፋሿ ቆመች። ሞተች።
የሆነው እንዲህ ነው…
ከሻዩ ፉት ስትልለት ሻይ ላይ የነበረች ንብ አብራ ወደ ጉሮሮዋ ትገባለች። ንቧ ምን ውስጥ ገባው ብላው ትውተረተርና ሲያቅታት ጉሮሮዋ ላይ ነደፈቻት። ልጅቷ መተንፈስ አልቻለችም። እያጣጣረች አሸለበች። አልተነሳችም።

ሀበሻ ወዶ አይደለም፣ አሟሟቴን አሳምርልኝ የሚለው!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • seifu commented on November 19, 2017 Reply

    በጠምነዉ ደስ ዬሚላዉ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...