Tidarfelagi.com

አንዳርጋቸው ጽጌን በጨረፍታ

አንዳርጋቸው ጽጌ ተፈታ፤እሰይ! በኢትዮጵያ ምድር የበቀለ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሲናፍቀው የነበረ ዜና ነበርና የእሱ መፈታት ለፍትህ ለርትዕና ለሀገር ሲቆረቆሩ ለቆዩና መቆርቆር ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና አፍቃሬ ኢትዮጵያውያን መልካም የምስራች ነው። አንዳርጋቸው የማይሰፈር ዋጋ ከፍሏል።አይተናል፤ሰምተናል። የመፈታቱ ዜና በህይወት ላላሉት ተቃዋሚዎቹ/አሳሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለሞቱትም አስደንጋጭ መርዶ ሊሆንባቸው እንደሚችል ሲገመት የቆየ ነው። እንግልቱ ደግሞ በውስን ዓመታት ብቻ የሚመደብ አይደለም። ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በኢህአዴግ ሲወገዝ፣ አሳዳጆቹ መቆሚያ መቀመጫ ሲያሣጡት የነበረ ሰው ነው። በደርግ ዘመንም አንዲሁ።

አንዳርጋቸው ጽጌን ሳስበው ‹ነጻነት› የሚለው ቃል ብሄራዊ መዝሙር ሆኖ ወደ ጆሮዬ ይገባል። አንዳንዴ ‹ነጻነት› በሚል ርዕስ የሚታወቅ፣ሁላችንም ተቀባብለን ልንዘምረው የምንመኘው ተወዳጅና ዘመን አይሽሬ ነጠላ ዜማ ያለው ሁሉ ይመስለኛል።ነጻነትን በቅጡ ሳያውቁ ነጻ እናወጣለን ስለሚሉ ታጋዮች ስለጻፈ ፣እሱም ለነጻነት በሚከፈል መስዋዕትነት ከመሪ ተዋንያን መካከል አንዱ ስለሆነ እንጂ በሌላ አይደለም።አሁን ተፈታ! አሁንም ምስጋና ለእነ አቢይ አህመድ(ዶክተር)ይሁን!

አንዳርጋቸው የአዲስ አበባ ልጅ ነው – አዲስ አበቤ። ከአዲስ አበባ የወጣው በ1972 ነው – በወርሃ ጥር። በዚያ ሽብር ዘመን፣ በኤርትራ በኩል አድርጎ ትግራይ ገባ። አሲምባ ለመድረስ የሁለት ሰዓት መንገድ ሲቀረው ሕውሃትና ኢህአሰ ጦርነት ገጥመው፣90 የሚሆኑ የኢህአፓ አባላት በሕውሃት ተማርከው ደረሰ። አንዳርጋቸው እንደሚለው፣ ‹በወቅቱ ኢህአፓ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማያደርግና ቁጭ ብሎ ከተማ ውስጥ በሚደረገው ነገር ብቻ አሸንፎ ወደ ከተማ እንገባለን የሚል ኃይል ነበር። በውስጡ የነበረ ዲሞክራቲክ አሰራር ያልነበረ እንደነበረ እንዲያም ከአሲምባ ሲወጣ አስራ አንድ ሰዎችን አንጃ ናችሁ ብሎ ረሽኖ ጉድጓድ ውስጥ ቀብሮ ነበር›

በዚህም የተነሳ፣ በአንዳንድ ሪፖርቶች መነሻነት፣ ኢህአዴግ ለሚነሱ ልዩነቶች ሰፊ የሆነ መድረክ የሚፈጥር ነው ብሎ ስላመነ አዎንታዊ ዕይታ በድርጅቱ ላይ አሳረፈ። ሆኖም አንዳንዶች እንደሚሉት አንዳርጋቸው በትግሉ ሜዳ ተሳታፊ አልነበረም።ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ አብዛኞቹ ባለስልጣናት/በተለይ ተፈራ ዋልዋ/ በትምህርትና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች ያውቁት ነበርና፣ከለንደን መጥቶ እንዲያግዛቸው ጋበዙት። ከነበረው የህይወት ልምድ አንጻር ጋባዦቹ የሰውን ሃሳብ የሚያዳምጡ፣ልዩነት ቢኖር እንኳን በቀላሉ በውይይት መፍታት እንደሚችሉ እምነት አደረበትና ግብዣውን ተቀበለ። ግብዣው ሳይውል ሳያድር ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ሆነበት።‹ከጫካው ሕዝብ ጋር አብረው ታገሉ።ከተማ ከገቡ ስልጣን ከያዙ በኋላ ግን ለጫካው ሕዝብ ጀርባ ሰጡ› በማለት የተቻቸውም ለዚሁ ነው።

በክል 14 መስተዳደር የምክር ጸሐፊ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ ነው፣ ይሆናል ብሎ ተስፋ ባደረገውና ሆኖ በተገኘው መካከል ልዩነት መኖሩን ተገንዝቦ ከኢህአዴግ የተለየው። የራሱን አገላለጽ ልጠቀምና፣ ‹አንድ ነገር ለማንሳት ምን ይሉኛል ብሎ ሁለቴ ሶስቴ ማሰብና መሸማቀቅ› በተጀመረበት ጊዜ ነው ሥልጣኑን የለቀቀው። ያኔ ገና እንደገቡ የኢህአዴግ ሹማንት ጉቦ ለምደዋል የሚል ትችት ሲሰነዝር ‹መሰረተ ቢስ ዘለፋ ነው› ተብሎ እንዲህ በማለቱ የተዘለፈ ሰው ነው። ‹የፖለቲካ ሰዎች እንዴት እንደሚኖሩ ምን እንደሚበሉ ምን እንደሚጠጡ ምን እንደሚለብሱ በዝርዝር የሚያውቅ ሕዝብ መፈጠር አለበት› በማለቱ ተወገዘ። ጉቦ የሀገሪቱ ብሄራዊ መገለጫ ከመሆኑ በፊት በእንጭጩ እንዲቀጭ ያቀረበው ሃሳብ ተለባበሰና ይህን አመለካከቱን የሚቀጭበት መንገድ ለመፈለግ ጉድጉዋድ መማስ ተጀመረ።‹ማኅሌት› መጽሄት(ሀምሌ፣ 1985) እንግዳ አድርጋው በነበረ ጊዜ የተናገረውን ስናነብ፣ሰውየው፣በፊትም እንደ ብረት ጠንካራ ብለን የምንገልጸው ዓይነት ሰው እንደሆነና የፍትህና የነጻነት ጉዳይ ቁርስ ምሳ እራቱ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሰብዓዊ መብት ግድ የሚሰጠው እንደነበር ቀጥሎ የምታነቡት ገጠመኙ አንዱ ማስረጃ ይሆናል።

‹ሁለት ወጣቶች በፖሊስ ጀርባቸውን ተተልትሎ (ተገርፈው) የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋ መጡ። ጀርባቸውን አይተናል። መቼም በተለያየ መንገድ በደርግ ጊዜ ቶርቸር ምን እንደሆነ የሚያውቅ ኃይል የሚገነዘበው ነው። ለማመን የሚያስቸግር ዓይነት ግርፋት ነበር የተገረፉት። የዚያን ጊዜ እኔ ያልኩት ዛሬውኑ በቴሊቪዥን ተቀርጸው ለህዝብ ይቅረቡና ይህን ያደረገው የፖሊስ ሃይል የተወሰደበት ርምጃ የ PUBLIC ማድረግ ነው ( ለህዝብ ማሳወቅ) የሚል ነበር፤ ነገር ግን ይህን ወደኋላ እንሰራዋለን። አሁን ለጊዜው ጉዳዩን እናጣራ የሚለው ሃሳብ የበላይነት አገኘ። አሁን ወደኋላ ተመልሼ ስመለከተው ያንን ሃሳቤን ገፍቼ እንዲቀረጽ ማድረግ እንደነበብኝና ይህ RESIGNATION ISSUE / የስልጣን መልቀቅ ምክንያት/ መሆን ይችል ነበር።ከዚህ ስንነሳ እነዚህ ልጆች አንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከወረዳው የተመረጠ ስላለ ኮሚቴውን ስላወቁት ይዟቸው መጥቶ ታየ እንጂ በዚህ ከተማ ውስጥ በዚሁ አይነት መንገድ የሚገረፉ ሰዎች ስንት ዓይነት ሰዎች አሉ ይህን ያህል ስፋት አላቸው ብዬ ልናገር አልችልም፤ እኛ ላይ ተንጠልጥለናል በየቦታው የሚሰራውን ነገር በስፋት ለማየት የሚያስችል አደረጃጀት የለንም።/…./ብዙ ጊዜ በምክር ቤቱ ውስጥ የሰብዓዊና ዲሞክራቲክ መብቶች መከበርና አለመከበር ሲነሳ ውድድር የሚደረገው ከደርግ ነው፤ ደርግ ለእኔ STANDARD (መለኪያ) አይደለም። ማንም ድርጅት ደርግን STANDARD ማድረግ የሚችል አይመስለኝም። የራሳ ችን እምነትና STANDARD አለን:: ጥያቄው በእኛ STANDARD ተከብሮአል አልተከበረም ነው። በእኛ አልተከበረም ከተባለ ያንን እስከሚያሟላ ድረስ ልንነቅፍ የሚገባን ይመስለኛል። ደርግ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ገድሏልና እኛ ሁለት ብቻ ብንገድል ብናነጻጽር ተሻሽለናል የሚል ነገር የለም። እምነታችን አንድም ሰው እንዳይሞት እንዳይገረፍ ነው…. ›

አንዳርጋቸው ጥብብን ከልቡ ያፈቅራታል። ስሜቱን በግጥም መግለጽ የሚችልና የሚወድ ሰው ነው። ትምህርቱም ፍልስፍና ነው። በአንድ ወቅት ባለቤቱ የነበረችውና በአመለካት ልዩነት የተነሳ የተለያዩት ጀማነሽ ሰሎሞን እንዲህ ገልጻዋለች። ‹ፍልስፍና ውስጥ የስነ ውበት (Aesthetics) መሰል ነገር ጋር ስለሚያያዝ ለስነጥበብ ከባድ የሆነ ፍቅር አለው።በርካታ መጻሕፍት አሉት።የንባብ ሰው ነው።ያገናኘን ይሄ ነው። መግባባቱ መዋሃዱ አለ፤ እንደገና ደግሞ በሃሳብ የማንስማማባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ።/…./ ቴአትር መጥቶ ሲያይ ሚስቴ ናት ብሎ አሞግሶኝ የሚሄድ እንዳይመስልህ። የተሰማውንና እውነተኛ የመሰለውን ሂስ ነው የሚሰጠኝ። ለዚያውም የኛ ሰው ክፉ ነገርህን አይነግርህም፤ አዎ ጥሩ ነው፤ ቆንጆ ነው ትባባለህ እንጂ።እና ጥሩ ዓይን ያለው ሰው ቀረብ ሲልህ ይጠቅምሃል።ሌላው የማይነግርህን ጉድለትህን ይነግርሃል።እና እሱ ለኔም ጥሩ ሃያሲ(Critic) ነበር ብዬ አምናለሁ።›(ኢንፎቴይመንት መጽሄት፣ግንቦት 1995)
ሹም በነበረ ጊዜ፣ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ብዙዎች ሲመሰክሩለት እሰማለሁ። ‹ማዕቀብ› በሚለው መጽሐፌ ውስጥ፣ አሮጌ መጽሐፍ በመሸጥ የሚታወቁት አበጀ ጎሹ አስፍሬ ነበር፤ (2006ዓ.ም ገጽ 260) ምስክርነቱን ልድገመውና መጣጥፌን ልቋጨው።
‹‹ኢሕአዴግ ሳይገባ፣ በረሃ እያለ የሚያሰራጨውን የሬዲዮ ፕሮግራም ተደብቀን እናዳምጥ ነበር።ደርግ ገንጣይ አስገንጣይ ቢላቸውም ‹የጭቁኖች ድምጽ ነን፤ መጣንላችሁ!› ሲሉ እውነት መስሎን ነበር፤ መጡ፤ ሲመጡ ምኞታችንን አደፈረሱት፤አስለቀሱን፤አሳቀቁን። ግን ሁሉም አይደሉም። ይህን እፎይታ የገበያ ማዕከል እንድንቆጣጠር በብርቱ የደገፉን ሙሉ አለም አበበ እና አንዳርጋቸው ጽጌ ናቸው። አንዱ ተገደደለ፤ ባህር ዳር በስሙ የባህል ማዕከል ተገነባለት። አንዳርጋቸው ጽጌ ከራሳቸው ወጥቶ፤ ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች ብሎ መጽሐፍ ጽፎ የተቃዋሚ ፓርቲ መስራች ሆነ። ትዝ ይለኛል፤ ይህን የገበያ ማዕከል ሰርተን ስናስመርቅ ከፍተኛ የመንግስት ባለሟሎችን ጠራን። ይህቺን ቦታ ማግኘት ከአንበሳ ቦመንጋጋ ስጋን ፈልቅቆ እንደማውጣት ነበረ። አቶ አንዳርጋቸው ተሟግቶልናል።ለሌላ ባለሀብት ይሰጥ፤ እነዚህ ምን አቅም አላቸው ሲሉ ሌሎቹ ፣ እሱ ግን ‹አይሆንም የሰጠናቸውን አንነጥቅም !› ማለቱን ሰምተን ሽልማት አዘጋጀንለት፤ አይገርምህም፤ ለሽልማቱ አመሰገነን ግን አልተቀበለንም። ‹ አይገባኝም፤ ሥራዬን ነው የሰራሁት፤ ልትሸልሙኝ ያሰባችሁትን ወርቅ ሸጣችሁ አንዳች ነገር አድርጉበት› አለን››

2 Comments

  • አምዴ commented on June 1, 2018 Reply

    በርታ .(አንተም ቃሊቲ እንዳትገባ)

  • mamushguguba@yahoo.com'
    mamush commented on June 8, 2018 Reply

    ማንም ይሁን ምንም,ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ኮርቶ ዘር ቀለም ሳይለየን ኖረናል ገና እኖራለን።ኢትዮጵያዊ ከራሱ አልፎ ሌሎችንም ከጭቆና ለማላቀቅ የሚያደርገውን ለመንገር ጊዜያችሁን አላጠፋም።ግን ማንም የውጭ ዜጋ ለኢትዮጵያችን መልካም አስቦ አያቅም።ስለጠላኝ ጠላሁት ብላችሁ በኢትዮጵያዊነት ደሜ የተሰማኝን ፊትለፊት ተናግሬ ሞቴን እጠብቃለሁ ወይም ቀን እስኪያልፍ እሰደዳለው በፍፁም ዜግነቴን አልቀይርም።የጠላሽ ይጠላ ነው ያለው ዘፋኙ። ማንንም ያገር ልጅ የማንም አገር ዜጋ አይወክለውም።እኛው ለኛ በቂ ነን።ዜግነትህን ጠልተህ ወይም ፈርተህ ከመኖር ሞት ይሻላል። አክ ቱ ..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...