Tidarfelagi.com

“አንቱ አጤ ሚኒሊክ ምን ያሉት ሰው ነዎት ?… “

የዛሬ አመት በዚህ ወቅት ነው …..አዳራሹ ካፍ እስከገደፉ ግጥም ብሎ በተሰብሳቢወች ተሞልቷል ! የኢሃዴግ ወጣቶች ሊግ ..የሴቶች ሊግ …ጥቃቅንና አነስተኛ ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ የቀረ የለም ! ለዩኒቨርስቲ ተማሪወች ከሚሰጠው ስልጠና ጎን ለጎን የአገሪቱን ‹‹ነባራዊ ሁኔታ›› ለነዋሪውም ለማስገንዘብ የተዘጋጀ የሶስት ቀን የመወያያ መድረክ ነው … አዳራሹ ዙሪያውን የአክሱም የላሊበላ ምስሎች ተስለውበታል በቀኝ በኩል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ፎቶ በትልቁ ይታያል በስተግራ የአፄወቹ ምስል ተደርድሯል የአፄ ቴውድሮስ የአፀጼ ሚኒሊክና የአፄ ይኋንስ . . .

ስብሰባው ሶስተኛ ቀኑ ነበር ….ሰብሳቢው እንዳለፉት ሁለት ቀናት ሁሉ ዛሬም እንዲህ ሲል ቀጠለ ‹‹ እና ባለፉት ሁለት ቀናት በስፋት ታሪካችንን እንደዳሰስነው አሁን ላለው የብሄረሰቦች እርስ በእርስ መቃቃር መነሻው አፄ ሚኒሊክ ነበሩ …. አሁን ከኤርትራ ጋር ላለው አንዳንድ ተገቢ ያልሆነ የድንበርና ሌላም ውዝግብም ያው መነሻው የአጼው ስርአት ነበር … ›› እያለ ለድፍን ሶስት ቀናት የአፄ ሚኒሊክን ድክመት ደካማ አስተዳደር እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ያወገዘበትን ትንታኔ አገባደደ …… ከዛም ህዝቡ ጥያቄ ካለው እንዲያቀርብ እድል ሰጠ!

በስብሰባው ላይ የጥንቱ ሲወገዝ እና ሲገዘት የአሁኑ አገዛዝ የፅድቅ ዘይት ሲቀባና ሲሞካሽ ግራ ከገባቸው ታዳሚወች መካከል አንዲት እናት ከወንበራቸው ተነስተው በቀጥታ ወደሚኒሊክ ፎቶ ሄዱና አዳራሹን በሚያናውጥ ድምፅ ሚኒሊክን በጥያቄ አፋጠጧቸው

‹‹አንቱ አጤ ሚኒሊክ …. አሉ የሚኒሊክ ፎቶ ላይ አፍጥጠው …..እንግዲህ የዚች አገር ችግር ሁሉ መነሻ እርሰዎ ከሆኑ …ጥያቄ አለኝ ለእርሰዎ ! ምን ያሉት ሰው ነዎት ግን ?
ለምንድን ነው ላባችንን ጠብ አድርገን ግብር በምንከፍልበት አገር መብራት በየቀኑ የሚያጠፉብን ?
አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….. ለምንድነው የስልክ ኔትወርኩን የማያስተካክሉልን ‹‹ያለዎት ቀሪ ሂሳብ ›› የምትለው እቴጌ ጣይቱ ናት ?›› ለምን አይመክሩልንም …?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….. የውሃ ማማ በምትባል አገራችን ውሃ እንዲህ የሚያጠፉብን ለምንድን ነው ?
አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….ለምንድነው ልጆቻችን ስራ አጥ እንዲሆኑ ያደረጉብን? ያሰሩብን ”””’

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ””’እርሰዎና ጋሻጃግሬዎቾ በአውቶሞቢል እየፈሰሱ ስለምን ህዝብዎት በትራንስፖርት እጦት ፍዳውን እንዲበላ ፈረዱ ?ማንስ ነው ተጠያቂው?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….ለምንድነው የትምርት ጥራቱ ከእጅ አይሻል ዶማ የሆነው ለምን ልጆቻችንን በነቀዘ ቲወሪ ያነቅዙብናል? ››

አንቱ አጤ ሚኒሊክ …..ለምን ምርጫ በደረሰ ቁጥር አገር ምድሩን ያዋክቡታል ?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ …. ለምን ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁትን ሁሉ አሸባሪ እያሉ እስር ቤት ይወረውራሉ? ያስደበድባሉ ያስገድላሉ ?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….. ለምን የህዝቡን የሰቆቃ ኑሮ በመስተዋት ህንፃወች በቀለበት መንገዶች ግርጌ ሊደብቁ ይፍገመገማሉ ?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….. ለምን መርፌ ያነሱ ሙሰኞችን እያሰሩና ከበሮ እያስደቁ በሬ የሚጎትቱትን በዝምታ ያልፋሉ?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ …..ለምን በብሔራዊ ቴሌፊዥናችን ብሔራዊ ውሸት ያልኖርነውን ዝባዝንኬ እየተረቱ ያደነቁሩናል ?ለምን ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ የውሸት ታሪክ ይፈጥራሉ ህዝቦችን የሚያቃቅር ሀውልት ያቆማሉ ….ንፁህ ውሃ ያጣ ህዝብ ከጥላቻ ሃውልት ንፁህ ውሃ ይቅዳ ብለው ነው?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ ….. ለምን ፍትሃዊ ምርጫ አይኖርም … እስከመቸ ከዚህ ሁሉ ችግሮዎት ጋር ዙፋንዎት ላይ ይቆያሉ ?
አንቱ አጤ ሚኒሊክ ……እስከመቸ የከበረ ታሪክን በመንደር ቱሪናፋ ሲያራክሱና ዝቅ ሲያደርጉ ይኖራሉ ?

አንቱ አጤ ሚኒሊክ …..እርሰዎ የጀመሩትን እናስቀጥላለን ! በቃ ለመጭዋም ምርጫ እንመርጠዎታለን አሁን ሰብስበው አይነዝንዙን ….ሲሉ እንደእብድ ጮሁ

ሰብሳቢው
‹‹ሴትዮ ….. አካሄድ አካሄድ ……ከአጀንዳ ወጥተዋል›› ሲል ጮኸ
‹‹ አሃ አጀንዳው የሚኒሊክ መስሎኝ …አካሄድ የምትለኝ ታዲያ ወዴት ሂደን እንጩህ .›› ብለው ቀጠሉ ,,,,
አንቱ አጤ ሚኒሊክ ,,,,,,,,,,

2 Comments

  • Sintayehuyeneabt@gmail.Com'
    ዲያቆን ስንታየሁ commented on July 19, 2017 Reply

    ግን ሴትዮ ዘብትያ አልወረደችም? እውነት አንቱ አጤ ምኒልክ ይህን ሁሉ ሰሩ አይደል…?ግሩም አገላለፅ።

  • binyamtesfaye1224@gmail.com'
    ብንያም ነኝ commented on January 7, 2019 Reply

    አንቱ ምኒሊክ በጎሳ ና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ከየት አመጡት?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...