Tidarfelagi.com

አንበሳ ዙሪያችን ሚዳቅዋ ልባችን!

አንበሳ ዙሪያችን ሚዳቅዋ ልባችን!
(የአንበሳ ልብ ቢጠፋ፣ በአንበሳ ጫማ ሮጦ የማምለጥ ሀገራዊ ጥበብ)
*********

እስቲ ዙሪያችሁን ተመልከቱት? ሁሉ ነገር አንበሳ ነው!!
ተረታችን ሲጀምር፣ “አንድ አንበሳ ነበረ…” ብሎ ነው፡፡ አውቶብሳችን አንበሳ ነው፡፡ ጫማችን አንበሳ ነው፡፡ ዘፈናችን “ቀነኒሳ አንበሳ”፣ “አንበሳው አገሳ” … አይነት ናቸው፡፡ ሳንቲሞቻችንን ገልበጥ አድርጋችሁ ብታዩ አንበሳ ነው፡፡ አንበሳው ቢራ የሚባል ያለበት ሀገር የት ነው? እዚህም አይደል? አንበሳ ባንክ አለ፣ አንበሳ ህንፃ አለ፣ በኢትዮጰያ ታሪክ የመጀመሪያው የተሻለ የሰለጠነ የወታደሮች ስያሜ ማነው? ጥቁር አንበሳ! ሂዱ ቤተ መንግስቱን እዩ፣ በድንጋይ የአናብስት ቅርፃ ቅርፆች ታጥሮ ታዩታላችሁ( ውስጥስ እነማን አሉ? እነ “በኮሽታ ይደንብሩ”) “ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ”፣ አንበሳ ውድም… ወዘተ እያሉ የገዙ ነገስታት ያሉት እዚሕም አይደል? ቃላዊ ግጥሞቻችንን እዩኣቸው፤
“እኚህ ብዙ ናቸው ብሎ ይላል ፈሪ፣
አንድ አንበሳ አይደል ወይ ሺ ላም አሳዳሪ” የሚሉ አይነት አይደሉምንእ?

ምን አንበሳ ያልሆነ ነገር አለ? ሻይ ቅጠል አንበሳ ሆናል፡፡ የነገስታቱ ፎቶ እና ስዕል ስር ድመት ይመስል እግር የሚታከክ አንበሳ አይጠፋም፡፡ ለገሐር ፊት ለፊት ምን ይታያችኋል? አንበሳ! (የሄ ፅሁፍ እራሱ ስለ ምን ያወራል- ስለ አንበሳ ሃሃ… ሳበዛው ማለት ነው)… አንድ ሰው አለ በኢትዮጵያ እና አንበሳ ግንኙነት ላይ የፃፈ የሚል ነገር ሰምቼ ነበር… የተባለውን ፅሁፍ ግን ላገኘሁ አልቻልኩም፡፡

ግን…..
አሁንስ? ይህ በአንበሳ የተከበበ ህዝብ የአንበሳው ምን ያህል ባህሪ ይጋራል? እራሱን እንዲህ አንበሳ አድርጎ የገነባ ትውልድ፣ ባንዴ ምን ወደ ሚዳቋነት አሽመደመደው???
ስለ ፍርሃት እያወራሁ ነው፣ ከፍርሃትም ስለ ብሄራዊ ፍርሃት፡፡ ስለ አጉል ጀብደኝነት ግን አይደለም፡፡ “ፈሪ የእናቱም የአባቱም ልጅ” ስለሚሆንበት አጉል ስሜት ነው፡፡ አጥርህን ሲያፈርሱ እያየህ ወደ እቤትህ ትገባና፣ “ፈሪ የእናቱ ልጅ ነው” ትላለህ፤ የእናትህን አጥር እያስፈረስክ!! …ሲብስብህ ደግሞ ልጅህን “አያ ጅቦ” መጣልህ እያልክ ታሳድገውና “ፈሪ ትውልድ!” እያልክ ትሳደባለህ በያደባባዩ፡፡
ፍርሃት ተፈጥሮኣዊ ነው፡፡ ብዙሃን ጋር ያለው ግን ፈጠራዊ ነው፡፡ ለምን ማለት ይፈራሉ፡፡ የቀበሌውን አመራር ከመንግስት እኩል ይፈራሉ፡፡ ባዶ ሆዳቸውን እያደሩ፣ ጎመን በጠና ይላሉ፡፡ ቀዬው ልብም ጎመንም የሌለበት ይሆናል!

በከፍተኛ ደረጃ ከሚሰበኩ ነገሮች አንዱ ፍርሃት ሆኗል፡፡ ልክ ነው፣ መፍራት ያስፈልጋል፡፡ በእውቀቱ በእድሜ ቀጥል “እንቅልፍ እና እድሜው” መፅሐፉ ምን አለ? … “ የስልጣኔ መነሻ ፍርሃት ነው እንጂ ጀግንነት አይደለም፡፡መስጠም የማይፈራ ሰው የዋናን ጥበብ አይፈለስፍም”( ገፅ፣72) … የእኛ ግን ውሃ በሌለበት መስጠምን መፍራት ሆነ፡፡ ወገብ ድረስ የማይደርስ ውሃ ዳር ቆሞም ብሰምጥስ ማለት ተለመደ፡፡ አላስፈላጊ ፍርሃት ተፈላጊ ብሔራዊ መዝሙር ሆነ፡፡ አልፈራም የሚል ካለ፣ በሌላ ፈሪ ፈሪ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በፍርሃት ቅባት እየታሸ፣ “የድፍረት ውልቃቱ” እንዲመለስለት ይደረጋል፡፡ የፈራ ይመለስ የሚል እንጂ፣ ፍርሃቱን ሊያጠፋለት የሚሞክር የለም፡፡… ቻው ቻው አንበሳ!!

ድሮ፣ አንበሳዊ ባህሪ ተሞጋሽ ብቻ ሳይሆን ፈሪነትም ተወቃሽ ነበር፡፡ ፈሪ፣ትከሻው አተላ መሸከም እንደሚችል ይነገረው ነበር፡፡ መቆሚያ መቀመጫ እስኪያጣ በግጥም ይጎነተላል፡፡ “ አሁን ለምን ይሆን ፈሪ ማቶንተኑ፣ ቅጠል ላይበጠስ ካልደረሰ ቀኑ” ይባልበታል፡፡ በበዛ እና በከፋ ምልኩም፣ “ወይ ግደልላት ወይ ሙትላት፣ የፈሪ ወዳጅ አታሰኛት” እየተባለ፣ እንዲገል ወይ እንዲሞት ይመከራል( ይገፈተራል)… የዛሬው ህዝብ እንደ ቀደመው ህዝብ ገጣሚ ቢሆን ምን ይል ነበር??? እንዲህ ሊል የሚችል ይመስለኛል…

፩. አትበል ቀደም ቀደም፣ አትበል ደፈር ደፈር
ከቃሊቲ አያልፍም የጀብደኞች ሰፈር፡፡

፪. ሰው መሞቻ ቀኑን ፈፅሞ ባያውቅም
ፈሪ መሰንበቱ አያጠያይቅም፡፡

፫. ሰው ምን ይለኝ በሚል ውጥረት ከመሰነግ
ወዲህም ወዲያ ብሎ፣ ጀግናን ፈሪ ማድረግ!

፬ ለምን ትፈራለህ ይለኛል ሰው ሁሉ
የደፋሮች ዶሮ አትልም ኩኩሉ፤
የማይነጋ ለሊት፣ የማይጮህን ዶሮ ነቅቶ ከመጠበቅ
እጨለማው መሃል በእንቅልፍ መደበቅ፡፡
.
.
.
የሚል የሚል ይመስለኛል….. ገጣሚነቱን “ከቤቴ ውጡልኝ” ብሎ አበረረ እንጂ…

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...