Tidarfelagi.com

‹አንበሳው› ማን ነው፤ ‹አህያውስ› የምን ምሳሌ?

አንበሳን የማምለክ አባዜ በየጉዳዮቻችን ውስጥ ገንኖ ይታያል፤ የምንወዳቸውና የምንፈራቸው ነገሮች በ‹አንበሳ› ስም እንዲጠሩ እንፈልጋለን፤ የሚያገሱ በሚመስሉ የአንበሳ ሀውልቶች ታጥረን መኖር እንፈልጋለን!

በተቃራኒው ደግሞ፤ አህያን እዩት፤ የውርደት ምልክት ነው፤ አንድም ቦታ ጠላቶቹን ድል ስለማድረጉ የሚተርክ ተረት አጋጥሞኝ አላነበብኩም ፤ በተረቱ ውስጥ አህያ ካለጭነት ሊኖር እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ፤ የሚሸከመው ደግሞ ጭነት ብቻ ቢሆን ባልከፋ፤ግና ውርደት ናላውን እስኪያዞረው ድረስ ይከተለዋል፤ ጌቶቹ እንኳን፤ በእሱ መኖር ኑሮኣቸውን መምራት የቻሉ ገበሬዎች እንኳን፤ እሱ ባይኖር ኖሮ ምን ይውጣቸው እንደነበር የምስክርነት ቃል ከመስጠት ይልቅ፤ በየቦታው ነገር ማሳመር ያ ተረትና ምሳሌ ይፈጥሩበታል።

‹አህያም የለኝ፤ እርግጫም አልፈራ› እያሉ፤ ‹አህያ ሞተች ተብሎ ከጉዞ አይቀርም› እያሉ፤ ‹አህያ ቢረግጥህ መልሰህ ብትረግጠው አህያው አንተ ነህ› እያሉ፤‹አህያ ሲግጥ ደብተራ ሲያላግጥ ይሞታል› እያሉ፤ ‹አህያና ፋንዲያ አራዳና ገበያ›› እያሉ፤ ‹አህያ ከመሞቷ መጐተቷ› እያሉ፤ ‹አህያ ፈረሱን አንተ አህያ ብሎ ሰደበው› እያሉ፤ ‹አህያን በአመድ ካህንን በማዕድ› እያሉ…ወዘተርፈ እያሉ!

ተረትና ምሳሌዎችን ሰብስባችሁ ብታዩ፤ የተረትና ምሳሌዎቹ ቀማሪዎች አህያን ለማዋረድ ታጥቀው የተነሱ ነው የሚመስሉት፤ ተራጋጭነቱን፣ ሆዳምነቱን፣ በየዓመዱ ተልከስካሽነቱን የሚናገሩ እንጂ ከፍ ያለቦታ እንድንሰጠው የሚያደርጉ አይደሉም፤ ድክመቱንና ባህርዩን እየቆጠርንነው የበታች መሆኑን ሌሎች እንዲያምኑልን የምናደርገው!

እስኪ የትኛው አህያ ነው ሚናውን የሚናገር ቅፅል ስም የወጣለት? ለበሬው፣ ለፈረሱና ለውሻው ልዩ ልዩ ስም ያኖራል-ባላገር። እነዚህ የቤት እንስሳት መኩሪያዎቼ ናቸው ይላል፤ በሥራ ሰዓት እንዳይለግሙበት አሞካሽቶ የሚጠራበት ስም አለው፤ ለስራ የሚያነሳሱ የሚያተጉ ዜማዎች አለው፤ ያጨደውን እህል በአህያ አስጭኖ ወደቤቱ ወይም ወደገበያ ሲያመራ ግን ለአህያው ሀዘኔታ የለውም፤ የቁልምጫ ቃል አይመጣለትም፤ ማንቆለጳጰስ አይሆንለትም!

መቸ ነው፤ ለዚህ አህያ ለሆነው ተግቶ አዳሪ ሕዝብ ድካሙን የሚመጥን ዜማ የምናበጅለት?

‹ሃያ አራት ሰዓት› ሙሉ የሚሰሩ አህዮች አሉ፤ የቤት ሰራተኞቻችን ያለእረፍትና እንቅልፍ ለኛ የኑሮ መደላደል የተቻላቸውን ያህል ይተጋሉ፤ ግና በብዙዎቹ ላይ አንበሳ እንሆንባቸውና፤ በጥቂት ጥፋታቸው ምክንያት መቋቋም የማይችሉትን ስድብና ውርደት በጫንቃቸው ላይ እናኖራለን፤ ድካማቸውን የማይመጥን ወርሃዊ ክፍያ እንፈፅማለን፤ ግና ስማቸውን አቆላምጠን ለመጥራት ይተናነቀናል፤ (አህያ መቸ ቅፅል ስም ኖራት?)

ያም ሆኖ፤ ሕይወት ማለት እንዲህ ናት፤ አንበሳው ጐልቶ እንዲወጣ እኛ አህያ እንሆናለን፤ ወይም ተብለን እንሰደባለን፤ ሁሉም አንበሳ መሆን አይችልም፤ ግና‹አህያ› ብንሆንም፤ ተፈጥሮ ደግሞ የዝቅተኝነት ስሜት እንዳይጫወት ብንብላ ነው መሰል፤ ‹አንበሳ› ሆነን የምንተውንባቸውን መድረኮች ትዘረጋልናለች።

ያሳዝናል አህያ መሆን! ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፤ ‹አምስት ስድስት ሰባት› መጽሐፍ ውስጥ‹አሮጊት› የምትል አንዲት ድንቅ አጭር ልቦለድ አለችው፤‹አህያ በጣም ያሳዝነያል› ትላለች እብድ ተደርጋ የተሳለችዋ ገፀባህርይ ‹…ሲጮህ ሰምተህ የለ? የሀዘን ጩኸት ነው፤ የሀዘን ቀፎ፤ የሀዘን ጥሩምባ። እህል ይጫንብያል፤ እንጨት፣ ጥድ፣ ሁሉ ነገር ይጨንብያል፣ ዠርባዬ እስኪቆስል ስድብም ሳቅም ይጫንብያል። መከላከያ ቀንድ የለይ፣ የሚከራከርልይ የለ በምን ፈረድክብይ? ብሎ እግዚአብሔርን ያማርራል። ደሞው እውነቱን ነው። በምን ፈረደበት?› ትላለች።

..
(እንዳለጌታ ከበደ፤ ከያልተቀበልናቸው መጽሐፌ)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...