Tidarfelagi.com

አሜሪካን ፀሀይና የአገሬን ሚድያ ያመነ

“ስሙኝ ልንገራችሁ ታሪኬን ባጭሩ” አለ አለማየሁ እሼቴ የሆነ ጊዜ ! ከዛ ረዘም አድርጎ ዘፈነ።
ስሙኝ ! ትናንት በቤቴ መስኮት መስታወት አሻግሬ ወደ ውጭ ስመለከተ ፀሀይ በሰላሳ ጥሩሷ ፉዋ ብላለች! እሰይ ! Thank you Global warming አልኩ! ወደ ባህር ዳርቻው ወጣ ብየ ልዝናና አሰብኩ! እሚገጥመኝ አይታወቅምና ብየ ብብቴን ተላጨሁ ! ደረቴ መሀል ደግሞ እፍኝ ሙሉ ሂውማን ሄር ተከልኩ! ከዚያ ለሽርሽር ያዘጋጀሁትን ቁምጣየን ቆመጠሁ! ከቁራ የጠቆረ መነፅር ገደገድሁ! አሸዋው ላይ በጀርባየ ተኝቼ መነፅሬን እንደማፍያ መኪና መስኮት ሸርተት አድርጌ የሚዝናኑ ቆነጃጅትን “ሄሎ ሌዲስ! ዋና ባንግ?” እያልኩ ለመልከፍ ተሰናዳሁ! (እመቤቶቼ ! ዋና ትወዳላችሁ ወይ እንደማለት ነው)

ከዚያ የቤቴን በሩን ስከፈት ሳደርግ ..ቆፈን፥ ቁር ፥ ውርጭ ፥ ደከከን የተባሉ የብርድ ዝርያዎች በራፌ ላይ ተሰልፈዋል። አጅሬው ስልታዊ ማፈግፈግ አደረግሁ። ለካ ፀሀዩ ማዘናጊያ ነው! ወይም ውጩን እንድጎበኘው የቀረበ click·bait ነው!

በሀገራችን “እገሌን ብርድ መታው“ ይባላል፤ እኔ ያለሁበት ቦታ ግን ብርድ አይመታም! ብርድ ረመረመው! ብርድ ረሸነው! ብርድ ቶርች አረገው! ብርድ አንጠለጠለበት ቢባል ያስኬዳል! ኢትዮጵያ ውስጥ ስም ሲያወጡ ፀሃይ ጣይቱ ይላሉ፤ ፈረንጆች ሚስ ሰንሻይን ይላሉ፤ “እትየ ፀሀይ-ቅብ“ ብለን ልንተረጉመው እንችላለን !

በነገራችን ላይ ጥቁር ሰው በረዶ ሸርቴቴ ምናምን አያምርበትም! ካቦርት ገድግዶ ከድብ ፀጉር የተሰራ ኮፍያ ለብሶ ፎቶ ሲነሳም አይዋጣለትም ! ጠቋሬ እሚያምርበት በሚንቀለቀል ፀሀይ ስር ፤ ፊቱ ላይ፤ ከተቻለ ወዙ ካልሆነ ላቡ ቸፍፍፍ ብሎ ደሴት የሚያክል ቁምጣ ውስጥ ተጠልሎ ፤አለያም በደንብ ለማናፈስ የሚመች ሽርጥ ሸብ አድርጎ ሲራመድ ነው!

እኔ እኮ እርም የለኝም ! ኮማንዶዎች ፤ አቶ ስብሃት ነጋ ከገደል በሸክም ሲያወርዱዋቸው የሚያይ ቪድዮ” የሚል ርእስ አየሁና ተንገብግቤ ክሊክ አደረግሁ ! እናም እንደተለመደው ተሸወድኩ! ካባ ፍሬምናጦስ ገዳም ላይ አንድ ወጣት አስቀድሶ በገመድ ሲወርድ የሚያሳይ ቪድዮ ነው፤ “ስብሀት ለከ” ብሎ ወደ ቤቱ የተመለሰውን ሰውየ ስብሃት ነጋ ነው ብለው በታሪክ ሲያስመዘግቡት ምንኛ ያዝን? ፤ ምንኛ ልቡ ይሰበር? ከዚህ በሁዋላ ወደ ገዳሙ ከተመለሰ በዚያው እሚቀር ነው እሚመስለኝ !! እኔኮ መጠርጠር የነበረብኝ “ ስብሃትን ተሸክመው አወረዱት ሲባል ነው ! ባይሆን እሱ ይሸከማቸዋል እንጂ ተሸንፎ ከተማረከ በሁዋላ ለምንድነው የሚሸከሙት? ይሄ መቸም፤ ያሸናፊና የተሸናፊን ባህል አለማወቅ ነው፤

የሸክም ነገር ሲነሳ የሆነ ሰው የነገረኝን ታሪክ ልንገራችሁ
ኢህአዴግ ታጋዳይ አዲሳባን በተቆጣጠረ ጊዜ በከተማው ውስጥ መጠነኛ ግርግር ነበር፤ በግርግሩ መሀል አንድምስኪን ወንደላጤ ፒያሳ ከሚገኘው ጎተራ አንድ ኩንታል ጤፍ ዱቄት ሰርቆ አተሸክሞ ወደ ራት ኪሎ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ ! ሰውየው ከሰረቀው ኩንታል ላይ አንዲት እንጀራ የምትሆን ዱቄት አላነሳለትም ! ምጣድ ለመስረቅ አመቺ ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ሳለ በጥቆማ ተያዘ ! በል ተሸከምና መልስ አሉት፤ ከፒያሳ አራት ኪሎ የሄደው ሰውየ ከጉዋዳ ሳሎን ማድረስ አቃተው ! የግቢው በር ላይ ሲደርስማ ዲስኩ ተንሸራተተ፤ ተጋዳላዮችም ዲስኩን ወገቡ ላይ በመርፌ ቁልፍ አስይዘው ! እንደገና ጫኑት !
እና ምን ለማስተላለፍ ነው? ለለውጥ ያክል ዛሬ ምንም አላስተላልፍም!

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...