Tidarfelagi.com

* አልገባኝም አያገባኝም!*

በወግ ደረጃ የመጀመሪያ ወጌ ናት እቺ፣ በትክክል ከተፃፈች አምስት ዓመት ያልፋታል( ከአንዳንድ ቃላት ለውጥ በቀር) እነኋት እራሷ……

* አልገባኝም አያገባኝም!*
^ ^ ^
ከሀገራችሁ ቁስል ይልቅ የአንድ እንግሊዛዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ስብራት የሚጠዘጥዛችሁ የሀገሬ ልጆች ሆይ! እንዴት ናችሁልኝ? ይሄ “ሜስ” የሆነው ኑሯችን እንደ ሜሲ ተጫወተብን አይደል?- አይዞኝ! እስቲ እኛም ትንሽ እንጨዋወትበት፡፡

በዚህች ፅሁፍ ያልገቡኝንና የማያገቡኝን ሀሳቦች በሚያግባባን መንገድ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
በአንደኝነት ያልገባኝ፣ግን የማያገባኝ ጉዳይ የሴቶች “እራቁት መር” አለባበስ ነው፡፡ ይሄ ተወጥኖና ተወጥሮ፣ ሲሻው ተራቁቶ የሚለበስ አለባበስ ሊገባኝ አልቻለም- ልብ አርጉ ግን አያገባኝም!

አንድ ጊዜ አንዷን የሰፈራችን ልጅ “ቆይ ለምንድን ነው እንዲህ የምትለብሱት?” ብዬ ጠየኳት፡፡ …
“ እ.. እ.. እ.. ጣፋጭ ባለበት ዝምቦች ስለማይጠፉ” ብላ ተላጠችብኝ፡፡ በእውነቱ፣ እሷ እና መሰሎቿን ጣፋጭ ብላ፣ ወንዶችን ዝምቦች በማለቷ ንድድ! ብሽቅ አልኩ! በንዴት ፀጉሬም እንትኔም ቆመ፡፡ …. ግን እኮ ዝምቦች ከጣፋጩ ይልቅ ቆሻሻ ባለበት ነው በብዛት የሚገኙት!!” … ልላት ብዬ ተውኩት፡፡ ምን አገባኝ? መቼስ ገባኝ?

በዛ ላይ ልጅቱ እንደው ዝም ብላ ስለጣፋጭ ታውራ እንጂ እልም ያለላት ኢ-ጣፋጭ መሆኗን አውቃለሁ( መች ቀመስካት የሚሉ ወየውላቸው) ….. ይህን ብቻም አይደለም፣ እግሯ የዝሆኔ ተጠቂ፣ ፊቷ እሳት ውስጥ የወደቀ ሃይላንድ እንደሚመስልም አውቃለሁ፡፡የአይኗ ትልቅነትስ ቢሆን፣ በእውነት የተገለጠ ዓይን ሳይሆን ያዛጋ አፍ ነው የሚመስለው፡፡ የታችኛው ከንፈሯ፣ የላይኛው ላይ ተንጠልጥሎ ዥዋዥዌ የሚጫወት ይመስላል፡፡ ሳላጋንን ልንገራችሁ አይደል፤ የግንባሯ ስፋት እንኳን ተካፋች መስኮት ቢሰራበት ሳይጠብ ይበቃል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደመ ግቡ መሆናችን በሚነገርበት በዚህ ሰዓት፣ እንደዚህች ዓይነቷ ሴት የሀገር ገፅታ ልታበላሽ ስለምትችል የሚመለከተው አካል የማያዳግም እርምጃ ቢወስድባት አይከፋም ባይ ነኝ፡፡

…. እንደው ግን እግዜሩ አይቶ የተመኘን ብቻ ሳይሆን አሳይጦ ያስመኘንም ሃጢያተኛ ቢያደርገው ምን ነበረበት? …ለነገሩ የሴትን የኋላ ክፍል አይቶ የመመኘትም ሆነ፣ በሴት የኋላ ክፍል የመሞኘት አባዜ ስለሌለብኝ ምን አገባኝ ? መቼስ ገባኝ?!

^ ^ ^ ^ ^ ^
ሌላው ያልገባኝ፣ ግራ የገባኝ የማያገባኝ ጉዳይ የራፐር ተብዬ፣ “ሱሪ አውርድ፣ ሻሽ ስቀል” ወጣቶች ጉዳይ ነው፡፡ እኚህ ወጣቶች ቋንቋቸው ሁሉ፣ “what`s up” ነው፡፡ ሰላምታቸውም ሆነ ስንብታቸው “what`s up”………ኸረ እባካችሁ ወገኖቼ፣ እስቲ መጀመሪያ ሱሪያችሁን up አድርጉት፡፡ አሁን ማን ይሙት ድህነት ‘‘Down… Down’’ በሚያዘፍናት ሀገር ላይ “up up!” እያሉ መሳለቅ ደግ ነው? ለነገሩ አያገባኝም!

የእነዚህን ራፐር ተብዬዎችን አለባበስ አስተውሎ ለተመለከተ ሰው፣ ወደ መፀዳጃ ቤት እየገባ ያለ፣ ወይም ከመፀዳጃ ቤት እየወጣ ያለ ሰው እየተመለከተ እንዳለ እንጂ የአለባበስ ፈሊጥ ነው ብሎ ለመገመት ያዳግተዋል፡፡
…በራሳቸው አለባበስ ተቸግረው አስሬ ዝቅ ያለ ሱሪያቸውን ከፍ ሲያደርጉ ያዩዋቸው ሰዎች “ሱሪ በእጁ” እያሉ ነው አሉ የሚጠሯቸው-ሱሪ በእጁ! ሃሃ እውነት ነው፡፡ …..አሁን በእግራቸው መሃል ተርፎ የተንጀለጀለውን ጨርቅ ያየ ሰው የሰው ልጅም እንደ ካንጋሮ “ቀረጢት” ተበጀለት እንዴ ብሎ ቢጠይቅ፣ ይፈረደብታል?

…ይሄ በሴቶችም በወንዶችም በኩል ያለው ልብስን ለማውለቅ ያለው መሽቀዳደም በዚህ ከቀጠለ፣ ወደፊት “አበደ” ለማለት፤ “ጨርቁን ጣለ” የሚለው አገላለፅ፣ “ጨርቁን አነሳ” ፤ “ልብሱን ለባበሰ” ተብሎ እንደሚቀየር እምነት አለኝ፡፡

እንደው ግን እንደ አበው አባባል ቢሆን እኮ፣ “ራፐር” መሆን የነበረባቸው አትሌቶቻችን ነበሩ፤ “ሲሮጡ የታጠቁት፣ ሲሮጡ ይፈታል” ስለሚባል፡፡ በእርግጥ ቀበቶ ሲሮጡ ብቻ ሳይሆን `ግብረ ስጋን` ሲወጡም ይፈታል፡፡ ታዲያ እኚህ በቁማቸው የተፈታባቸውን ምን ይሏቸዋል?

አንዳንዴ “እኚህ ራፐር ነን ባዮች ፣ ስብዕናቸው እንደ ሱሪያቸው የወረደ፣ ወገባቸውን ጠበቅ ማድረግ የተሳናቸው ልፍስፍሶች፣ እንደሱሪያቸው የወረደ- የተዋረደ ማንነት ባለቤቶች ናቸው!” ልል ያምረኝና ምን አገባኝ? መቼስ ገባኝ? ብዬ እተወዋለሁ፡፡
¬ ¬ ¬
ሌላው የማይገባኝ ግን የማያገባኝ ጉዳይ፣ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ነገር ነው፡፡ አሁን እንደው ማን ይሙት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕድሜ፣ እንኳን እራስ ለማጥፋት፣ እራስን ማጥፊያ ገመድ ገዝቶ ለመመለስ ይበቃል? – አይበቃም!!
የሚከተለውን እንድፅፍ ያስገደደኝ፣ በቅርቡ እራሱን ያጠፋው የሰፈራችን ልጅ ትዕግስቱ ነው፡፡ ትዕግስቱ ማለት በጎረቤት ሀገራት እንኳን ታይቶ የማጥታወቅ የመጠውለግ በሽታ የያዘው የተጋነነ ቀጫጫ ነው፡፡ ቅጥነቱ በበር ቀዳዳ የገባ ጨረር ይመስላል፡፡ “ቀጭን” የሚለው ቃል፣ አግድም ቢሰመር ከእሱ ይወፍራል፡፡

… መሞቱን የነገረኝ፣ ሚካኤል የተባለ የሰፈራችን ልጅ ነው፡፡ ይሄ ሚካኤል ያልኳችሁ ልጅ ድምፁ በጣም ስለሚቀጥን ሚካኤል የሚል ስሙን ቀይረን “ሚካያ” እያልን ነው የምንጠራው፡፡ ሚካኤል የሰፈራችን፣ እንደ መላዕኩ ሚካኤል ሳጥናኤል ላይ ሰይፍ ባይሰነዝርም፣ ቢላ ይዞ ሸንኮራ አገዳ ላይ ለመሰንዘር ችሏል – የሸንኮራ አገዳ ሻጭ ነው!

ወደ ትዕግስቱ እንመለስ፡፡ ቆይ ግን “ትዕግስቱ” ተብሎ ስም የወጣለት ልጅ፣ እንዴት ትዕግስት አጥቶ እራሱን አጠፋ? ጥፋቱ የአባቱ ይመስለኛል፡፡ ስማቸው “ዘገየ” ነው፡፡ ትዕግስቱ ዘገየ ብለው ሰየሙት፣ ትዕግስት አጣ፣ ራሱን አጠፋ፡፡ ምን ሆኖ? በምን? ለምን? ..አያገባኝም፡፡ ቢነገረኝ እንኳን አይገባኝም፡፡

ሌላው በጣም ያልገባኝና የማያገባኝ ጉዳይ፣ እስካሁን ድረስ ከኔ ምን ለማግኘት እንዳነበባችሁኝና እኔም ለናንተ ምን ለመንገር እዚህ ድረስ እንደለፈለፍኩ ነው፡፡ ስንት እና ስንት የሀገራችን ጉዳዮች አያገቡንም የምንል ሰዎች ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ባያገቡን አያስገርምም፡፡ …ለማንኛውም እግዜር የሚያገቡንን ምርጥ ሃሳቦችና ቆንጆ ቆንጆ ሚስቶች ያድለን፡፡ ለመጨረሻው መጨረሻም፣ በሚያገቡንና በሚያግባቡን ሀሳቦች እስክንገናኝ ድረስ፣የሚሆን ስንብት ልሰናበታችሁ አሰብኩና ምን ብዬ እንደምስናበታችሁ ስላልገባኝ ተውኩት፡፡

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...