Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል 10-11)

(በተጋባዥነት)

ክፍል 10
ማን እንደሆነች አላወቅኩም።ለምን “ማቲ” ብላ ስሜን እንደወዳጇ እንዳቆላመጠችኝ ጭምር። ደግሞስ እንደሷ ያለችን ቆንጆ ለመወዳጀት የሚያበቃ ወኔ ከየት አግኝቼ? ደግሞስ ኤዶምን የምታውቃት ከሆነ አሁን “ማቲ” መሆኔን ካመንኩላት ለእህቴ ተናግራ ልፋቴን ሁሉ ገደል ብትከተውስ?”ይቅርታ የኔ እህት ተሳስተሻል ማቲ አይደለሁም” አልኳት አይኔን በጨው አጥቤ።ሳቅ ብላ “አይይ ረስተኸኛል ማለት ነው ያኔ እነካርሎስ ሲወስዱህ ተላቅሰን እንዳልተለያየን…ሲስተር ቀለሟ ከማሳደጊያው ሻንጣህን ይዛ ስትወጣ አትሄድም ብዬ ገግሜ…” አናቴ በዱላ የተመታ ያህል ደነገጥኩ።ከአፌ አምልጦኝ “እኔ አላምንም ቅድስት ንፍጦ…i mean ቅድስት” ተንተባተብኩ። ከት ብላ ስቃ መጥታ ላዬ ላይ ተጠመጠመች። ከዛ ደግሞ ለቅሶ…ቅድስት ለአንድ አመት አዲስአበባ የሚያስጠጋኝ አጥቼ ህፃናትን የሚረዳ የካቶሊክ ሚሽን ውስጥ ስኖር የነበረች ጓዴ…እናትና አባቷ በጦርነት ተገድለውባት እነዛ ምስኪን መነኮሳት ዘንድ ስትኖር የማውቃት ትንሽዬ ነፍሰ ቀጭን ልጅ…የደረሰብኝ ፆታዊ ጥቃት ሲያስቃዠኝ”ባስማም…ባስማም” ብላ የምታውቃትን ስመ ቅዱስ መንፈስ ጠርታ ልታባርርልኝ የምትደናገጥልኝ የስምንት አመት ህፃን።ትንሽዬ ንፍጥ የማይለያት ልጅ…

ከሆቴሉ ሬስቶራንት ተያይዘን ገብተን መጫወት ጀመርን።እሷም በአመቱ ወደጀርመን በጉዲፈቻ እንደተወሰደች ከአምስት አመት በፊት ወደአገሯ ጠቅልላ እንደገባችና በስራ አጋጣሚ ከሰላም እና ቤተሰቦቿ ጋር እንደተዋወቀች አወራችኝ። “እንዴት እኔን አገኘሽኝ?” አልኳት ተገርሜ። “የለቅሶው እለት ከሩቅ አይቼህ እሱ ነው አይደለም ስል ከዛ ደግሞ ኤዶም ራሷን ስትስት አንጠልጥለህ በመኪናህ ስትወስዳት ተከተልኩህ። ያረፍክበትን ሆቴል አይቼ ተመለስኩ። ዛሬ ኤዶምን ህክምና ቦታ ላደርስ ስል እየተከተልከኝ እንደሆነ ገባኝ። እንዳላወቀ ሆኜ ቀድሜህ ሆቴልህ መጣሁ…as simple as that…” ለካ ስሜታዊ ሆኜ የለቅሶው እለት ራሴን ሰው አይን ውስጥ ከትቻለሁ። ተፀፀትኩ። ቀጥላም “ማቲዬ ኤዶምን የት ነው የምታውቃት?ለምንድነው የምትከታተላት?” ብላ ጠየቀችኝ። ጉድ ፈላ ይቺ ልጅ ነገሬን ልትገለባብጠው ትችላለች። ቀለል አድርጌ “ሰላምን ነው የማውቃት ኤዶምን አንዴ አይቻት ደስ ብላኝ በምን ልተዋወቃት ብዬ ዛሬ ነገ ስል ሰላም አረፈች። ይኸው የምወዳት ልጅ እንዳትጎዳ በሩቁም ቢሆን አይኗን አይቼ እመለሳለሁ” ተከዝ ብዬ መለስኩላት። “እንኳንም እኔ ላይ ጣለህ አስተዋውቃችኋለሁ።”አለችኝ ፈገግ ብላ። “ቆይ ገና ነው እኔ አጥንቻት የሚሆን ነገር ከመሰለኝ ነው የምተዋወቃት አንቺ አትድከሚ።ይልቁንስ አገባሽ?”አልኳት ወሬ ለማስቀየር።
ክፍል 11
ያነሳሁባት ጥያቄ ፊቷን አጨለመው።እንባዋ ድቅን ብሎ “አግብቼ ነበር ሞተብኝ” አለችኝ ባንዴ ድምጿ ተሰብሮ። ደነገጥኩ።ራሴን ይሄን ጥያቄ በማንሳቴ ረገምኩት። እንባዋን እንዳላይባት ፊቷን አዞረች። ስፈራ ስቸር እጇን ይዤ “አዝናለሁ የኔ እመቤት አይዞሽ” አልኳት። “እሱ ከሞተ በኋላ ነገር አለሙ ሲያስጠላኝ የአራት አመት ልጄን ይዤ አገሬ ገባሁ።አሁን አድጋልኛለች። ስራዬም ለምዶልኛል” የቀላው ፊቷ መለስ እያለ ነው። አሳዘነችኝ። ፍቅር አይበርክትልሽ የተባለች መሰለችኝ። አንዳንዶች እንዲህ ተረግመናል…እኔ ገጠር በልጅነቷ ወልዳኝ ጥላኝ ከተማ በተሰደደች እናት ናፍቆት ተሰቃይቼ በልጅ አቅሜ ልፈልጋት ብሄድ ገፍታ ወደማልቋቋመው እሳት ተጣልኩ…ኤዶም እህቴ በወንድሟ የበቀል ፍርድ እናቷን ገና ከማህፀን እንደወጣች ተነጠቀች…ዘመኗ እንደተኮላሸ ሰላሳ አመት ኖረች…ቅድስት በጦርነት ደም ከገበሩ ህዝቦች አንድ ራሷ ተርፋ በጉዲፈቻ ከሄደችበት ሀገር ጠማማው እድሏ ተከትሏት ኖሮ ፍቅሯን በጠዋቱ ተነጠቀች።ሲያስጠላ…
“ቅድስቴ አይዞሽ እሺ?…ለመሆኑ እዚህ ምንድነው የምትሰሪው?”ጥያቄዬ ሀዘኗን እንዳያባብሰው ተጠንቅቄ። “መድሀኒት አስመጣለሁ”አለችኝ ባጭሩ።” አንተስ ምን እየሰራህ ነው?ትዳር?ህይወት?” አይኔን ታየኝ ጀመር። “ይኸው ላለፉት ሀያ አመታት የማእድን ሽያጭና ገበያ አጥኚ ሆኜ እየሰራሁ ነው።አላገባሁም አልወለድኩም። የሚገርምሽ አገሬ ላይ ብሆን ይሄኔ የሰባት ልጆች አባት ሆኜ ነበር” ስላት በሳቅ ሞተች። የኑሮ ሩጫው ለጋብቻ ብዙም የማያጣድፈው የአውሮፓ ህይወት ከሞላ ጎደል ሽሙጡን እንድትረዳ አግዟታል። ከእህቴ ጎን መሆኗን አልጠላሁትም። የሰውን ልጅ እድሜ የሚያሳጥረው አንዱ በቀላል ሻይ ቡና ሀሳቡን የሚያካፍለው አጥቶ በብቸኝነት መቀጣት ነው። ቅድስት እንደስሟ ለእህቴ የተቀደሰ ጅማሬ የምትሰጥ እንደምትሆን አመንኩ።ለኔ ደግሞ ፈጣሪ የፀፀት ዘመኔን በእህቴ ሞት እንዳልቋጨው ወደህይወቷ እንድገባ የተሰራች ድልድይ ሆና ታየችኝ።

“አሁን ለሀገርህ አብቅቶሀል እልል ብዬ እድርሀለሁ። ይገርምሀል ማቲዬ እኔ ህይወትን መኖር የጀመርኩት ሟቹ ባለቤቴ ህይወቴ ውስጥ ከገባ በኋላ ነበር። በልጅነቴ ጭንቅላቴ ውስጥ ተቀብሮ የነበረው የፈንጂና የጩኸት ድምፅ እሱ ሲያቅፈኝ ለዘላለም በንኖ ሄደ።…”
ታድላ! እኔንና ኤዶምን የዘለለን ፈውስ ለዚህች ሴት ወገግታውንም ቢሆን አሳይቷታል።እያወራችኝ እያለ አስተናጋጁ መጣና”ይቅርታ እናት መኪናሽ መንገድ ዘግቶ ነበር ታንቀሳቅሺልን?” ሲል ጠየቃት። “ማቲዬ አንዴ መጣሁ” ብላኝ ተነስታ ወጣች። እኔም ወደስልኬ አቀረቀርኩ። ብዙም ሳይቆይ በሁለት ተኩስ አካባቢው ተናወጠ።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...