Tidarfelagi.com

“አልወለድም!” (ክፍል ሁለት)

እየተደናበረች በመሮጥ ላይ ሳለች እንቅፋት መትቷት በሙሉ ሰውነቷ ው-ድ-ቅ ስትል ሁለቱም ተናወጡ፡፡ ዘፈንኑን በድንገት አቆመ፡፡
‹‹ራበኝ!›› አለች በእንቅፋት የተነደለ አውራጣት ጥፍሯን እያሻሸች፡፡ መድማት ጀምሯል፡፡
‹‹እኔም ርቦኛል…እማ›› ብሎ መለሰላት፡፡
ዝም ብላ ቁስሏን እና ረሃብዋን ስታስታምም ትንሽ ጊዜ ጠበቀና፤ ‹‹እማ…ደሃ በመሆንሽ ታሳዝኚሻለሽ…ነገር ግን ለኔ ባርነት የምታቅጂ የመርዶ ነብይ ስለሆንሽ…እማ መሞት አለብሽ!›› አላት -በሃዘን በተሸነፈ ድምፅ ፡፡
አሁንም ዝም አለች፡፡
‹ለምን ዝም ትያለሽ…?ሳልወለድ ረሃብን አታለማምጂኝ! ለልመና አትጪኝ…አልወለድም!››
ዝም፡፡
‹‹እሺ…ሞትን ከፈራሽ አንድ ምርጫ አለ›› አለ ቶሎ ብሎ ‹‹ምን?!›› አለች ዝምታዋን በፍጥነት ሰብራ
‹‹አንቺም መብትሽን ጠይቂ፤ እኔንም ከነመብቴ ውለጂኝ››
‹‹እሱን እንዴት እችላለሁ ልጄ…?.››
‹‹ካልቻልሽ እንሙት!››
‹‹አረ ባክህ ልጄ በፈጠረህ ተወኝ…! ዝም ብለህ ተወለድ… ስለ ፈጣሪህ ብለህ ዝም ብለህ ተወለድ››
‹‹ፈጣሪ ለዚህ ፈጥሮኝ ከሆነ እሱንም አልወለድም እለዋለሁ!››
‹‹አረ አንተ ልጅ እንዳታስቀስፈኝ!››
‹‹አይ እማ! አንቺ እኮ ከተቀሰፍሽ ቆየሽ….!››
‹‹አንተ ከሌሎቹ የደሃ ልጆች ማን ለየሀ?! ሌሎቹ የደሃ ልጆች መች አንወለድም አሉ?››
‹‹ተያቸው! ባርያ መሆን የሚሹ ባሪያ ይሁኑ…ባርያ የመሆን ነፃነታቸውን አልነፍጋቸውም…እኔ ግን አልሆንም!››
‹‹እና ምን አባቴ ተሻለኝ?›› አለች ሆድዋን በሁለቱም እጆችዋ ደግፋ፣ እወደቀችበት ስፍራ ያገኘችውን የሰው ቤት ግንብ ደገፍ እያለች፡፡
‹‹ለምን አትከሺኝም?!››
‹‹ምን…?ደሞ ምን አመጣህ!››
‹‹እውነት እማ! ክሰሺኝ…? ፍርድ ቤት ገትሪኝ››
‹‹ወይ ጉዴ!››
‹‹እውነቴን እኮ ነው…! ዛሬ እኮ ዳኛ የማያገኘው ለነፃነት የሚሟገት እንጂ ነፃነት ፈላጊዎችን ለመክሰስ እኮ የሀገሩ ፍርድ ቤት ሁሉ እንደ ሴተኛ አዳሪ ጭን ሃያ አራት ሰአት ክፍት ነው….ክሰሺኝ!››
‹‹ምን ብዬ? ››
‹‹ልጄ አልወለድም አለኝ ብለሽ ነዋ!››
ድካሙ፣ ጭቅጭቁ፣ ቅዠትና እውነታን አለመለየቱ፣ ረሃቡና ሌላው ሁሉ ተደራርቦ በአንድነት ቢደቁሳት ዝልፍልፍ ብላ- እጅና እግሮችዋን አወራጭታ- ቁጭ ባለችበት ተኛች፡፡

ብዙ ሳይቆይ በዚያ አኳሃን ወድቃ ያገኟት ሁለት ፖሊሶች ‹‹ውይ! ሞታለች መሰለኝ…ውይ ውይ…ደሞ ነፍሰጡር ናት…ቶሎ በል…ነፍሷ አለ…?እስቲ ቼክ አድርግ›› ተባባሉና አፋፍሰው አንዱ መንግስት ሆስፒታል ይዘዋት ሄዱ፡፡

ሀኪሙ በቀኝ እጁ የእናቴን ሆድ ያለርህራሄ ጫን ጫን ሲያደርጋት ከሰመመኔ ነቃሁ፡፡ የሚሰራው ነገር ምን አይነት ህመም ውስጥ እንደከተተኝ ያወቀ አይመስለኝም፡፡ እኔን ሃኪም ያድረገኝ! መሃይም ነገር ነው፡፡ ቢያቆም ብዬ ጣቶቹን በእርግጫ ለመስበር ትንንሽ እግሮቼን አወናጨፍኩ፡፡ ግን የጎዳሁት መሃይሙን ሃኪም ሳይሆን ምስኪን እናቴን ነበር፡፡

ብዙ ሳይቆይ ‹‹ራጅ ትነሳ!›› ሲል ሰማሁት፡፡ ራጁ አይኔ ላይ ቦግ ሲልብኝ ‹‹አረ በህግ! አይኔን እንዳታጠፉት!›› ብዬ ጮህኩ፡፡ የሰማኝ አልነበረም፡፡
‹‹እሷም ልጁም አደጋ ላይ ናቸው፡፡ በአስቸኳይ በኦፕሬሽን መውለድ አለባት!›› ሲል ስሰማው እሪ አልኩ፡፡ ‹‹እረፉ! እንዳታወጡኝ…! እንዳታወጡኝ! በህግ አምላክ! እኔ መወለድ አልፈልግም!›› ብዬ ብጮህም ጩሐቴ የአውሎንፋስ ውስጥ ሹክሹክታ ሆኖ ቀረ፡፡

ጮሄ ሳይወጣልኝ ከባድ የመደንዘዝ ስሜት በመላ አካሌ ተሰራጨ፡፡ እኔም እማዬም በድን የሆንን መሰለኝ፡፡ በዚህ ቅፅበት በሞት ነፃ የወጣን መስሎኝ መደሰት ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አፍታ ሳይቆይ የቅድሙ እጅ ከደሃ እናቴ ምቹ ዋሻ ፈልቅቆ አወጣኝ፡፡ ‹‹ያልቆረጠ ከግቡ አይደርስም›› ብዬ የቁርጥ ሰአት ጩሐቴን እና እሪታዬን ቀጠልኩ፡፡ መወለዴን እንደምቃወም ለማሳየት አምርሬ አለቀስኩ፡፡ የማያባራ ለቅሶዬን ሲሰሙ ካሁን ካሁን ይሄ ልጅ መወለድን አልፈለገም ወደሚለው መደምደሚያ ይደርሱና ወይ እናቴ ማህፀን ይመልሱኛል ወይ ይገሉኛል ብዬ ስጠብቅ በአናቴ ዘቅዝቀው ‹‹ጎሽ…አለቀሰ! ጤነኛ ልጅ ነው ማለት ነው›› እያሉ ሲደሰቱ ሰማሁ፡፡ ፍፁም ግራ ሆነብኝ፡፡ ማልቀሴ እንዴት ጤና መሆኔን ነገራቸው…?የዚህ መከረኛ አለም ህግ ይሄ ነው?
እዩት ደግሞ ይሄን መሃይም ሃኪም! ከእግዜር በሚመጣጠን ስልጣን እና ድፍረት ከእናቴ ማህፅን መንጭቆ ሲያወጣኝ ልብስና ምግብ፣ ቤትና አልጋ ያዘጋጀልኝ ይመስል በሙሉ ጥርሱ ይገለፍጣል! ጥርሱ ይርገፍና!
አንስተው እኔን የሚካል አልጋ ጋር ሲወስዱኝ በአየር መንገድ ላይ ሆኜ የተቀደደ የእናቴን ሆድ እንደ ብትን ጨርቅ ሲሰፉት ሳይ በሆዴ ምግብ ቢኖር ሊያስመልሰኝ ይችል ነበር፡፡ ደሃዋ እናቴ- <<ይቅርብሽ ሙቺ…ይቅርብሽ እንሙት>> እያልኳት…የነገ ከዛሬ ይሻላል አጉል ተስፋዋ ሽልማት ይሄ ነበር፡፡ በድህነቷ ላይ ቀዳዳ ሆድ ሰጣት!
አልጋዬ ላይ ሆኜ አካባቢዬን ለመልመድ በመትጋት ላይ ሳለሁ መሃይሙ ሃኪም ከአንዲት ነርስ ጋር ወደኔ መጣ፡፡
‹‹እም…ቢያንስ እስከ ስድስት ወር የእናቱን ጡት መጥባት አለበት… ንገሪያት!›› አላት፡፡
‹‹እምቢ! የእናቴን ጡት አልጠባም!››አልኩ ድምፄን ከፍ አድርጌ፡፡
ራሴን በለስላሳ እጆችዋ ትደባብስ የነበረችው ነርስ እጇ ላይ እሳት እንደተነሳ ሁሉ እያርገበገበችው ጩሐትዋን ለቀቀችው፡፡
ሃኪሙ ደንዝዞ ያየኛል፡፡
መጮህ ያላቆመችው ነርስ ‹‹ወይኔ ዶ/ር ተክላብ! ለካ እውነት ነው…በየሱስ ስም…!ምን ተአምር ነው…›› እየተስገበገበች ማውራት ጀመረች
‹‹ምንድነው እውነቱ?›› አላት እኔን ማየቱን ሳያቆም፡፡ ድንዛዜው አልለቀቀውም፡፡
‹እናቱ…እናቱ…እናትየው…››
‹‹አትንተባተቢ ምንድነው..አይዞሽ…›› አላት ቀና አለና ትከሻዋን አቀፍ አድርጎ
‹‹ልጄ ያወራል…ያወራል ስትለን ስንስቅባት ነበር…ጌታ ሆይ!››
በሚቀጥሉት ሰአታት ውስጥ ሆስፒታል ውስጥ ያሉት ሀኪሞች፣ ነርሶች፣ ማደንዘዣ ወጊዎች፣ ቀጠሮ ያዢዎች፣ ወረፋ ሻጮች…በአጠቃላይ የከተማው ህዝብ እየተመላላሰ ያየኝ ይመስለኛል፡፡
እተኛለሁ፡፡ እነቃለሁ፡፡ ስተኛም ስነቃም ብዙ ሰዎች ከበውና አጅበውኝ አገኛለሁ፡፡
አመሻሽ ላይ አስገድዶ ያስወለደኝ ሃኪም በተረጋጋ መንፈስ ወደኔ ተጠጋና፤
‹‹እኔ ምልህ…ምን ነበር ያልከው ቅድም…ከግርግሩ በፊት?›› አለኝ
‹‹የእናቴን ጡት አልጠባም!›. ፈጠን ብዬ መለስኩ
ፊቱ ‹‹ወይኔ ጉዴ..እውነት ነው…›› ይላል፡፡
‹‹እህም…ለምን…ለምን ነው ማትጠባው?…››
‹‹እናቴ ሳምባ ነቀርሳ አለባት፡፡ጡት ልጥባ ብዬ ትንፋሽዋን ስምግ ሳምባ ነቀርሳ ብምግስ! በግድ አሰወልዳችሁኝ ደግሞ በበሸታ ልታሰቃዩኝ ነው?!››
ሀኪሜ ሚዛኑን እንደመሳት ብሎ ከተንገዳገደ በኋላ በፍጥነት ጥሎኝ ሄደ፡፡

እናቴ ተመርምራ መጨረሻዋ እስኪታወቅ በሃኪሙ ትእዛዝ ‹‹ለተአምረኛው ልጅ ›› እየተባለ የተለያየ አይነት ወተት በሚያምር ጡጦ እየመጣልኝ ለሁለት ቀናት በምቹ አልጋዬ ላይ ከረምኩ፡፡

በተወለድኩ በሶስተኛው ቀን ግን ለወትሮው በሌሊት በጡጦ ተሳፍሮ የሚመጣልኝ ወተት እስኪረፍድ አልመጣም፡፡ ሽንት ጨርቄም ክፉኛ ያቃጥለኝ ጀመር፡:
ሰዎቹ ሁሉ የት ሄዱ?
እነዛ እኔ ልግባለት እኔ ልግባለት እያሉ የሚሻሙብኝ ነርሶች ዛሬ የት ገቡ?
ረሃብ ሊደፋኝ ደረሰ፡፡
ሽንቴና ምናምንቴዬ ለራሴ ከረፋኝ፡፡
የረሱኝ እንዲያስታውሱኝ በለመድኩት ዘዬ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡
ለሰአታት አለቀስኩ፡፡
ማንም አልመጣም፡፡ በራሴ ለቅሶ ደክሜ ዝም እንዳልኩ ግን ያለሁበት ክፍል አጠገብ ካለው መተላለፊያ ላይ የቆሙ የማላያቸው ሁለት ሴቶች እንዲህ ሲያወሩ ሰማሁ፡፡
‹‹ይሄ ምስኪን የደሃ ልጅ ላንቃው እስኪደማ ይጮሃል…›› አለች አንደኛዋ
‹‹ተአምረኛው ልጅ ነው አይደል! የት ሄደው ነው ጥለውት የጠፉት?›. ሌላኛዋ
‹‹የቴዲ አፍሮ ሚስት ዛሬ እዚህ ሆስፒታል ወልዳለች አሉ…የሱን ልጅ ለማየት ሁሉም ወረፋ ላይ ናቸው…›› የመጀመሪያዋ መለሰች፡፡
የህፃን ደሜ ፈላ፡፡

 

(ይቀጥላል)

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

2 Comments

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...