Tidarfelagi.com

አለመታደል ነው (ክፍል አምስት)

“ልክ አይሆንም። እኔና አንተ ከዚህ ቀደም ከነበረን የዘለለ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም።” አለችኝ ……

“ቅድም ‘ከአዕምሮ ይልቅ ልብ ይማርከኛል‘ አልሺኝ አይደል?”

” እም… ” የምቀጥለውን ለመስማት እየሰገገች

“ሲገባኝ ሌላ ፍቺው ከስሌት ይልቅ ለስሜት ቅርብ ነኝ ማለትሽ መሰለኝ። …… ልክና ስህተቱን በስሌት ልቀምርልሽ አልችልም። …… ባንቺ ፍቅር ከመውደቅ በላይ ልክ የሆነ ስሜት ተሰምቶኝ እንደማያውቅ ግን ላረጋግጥልሽ።… ” አልኳት አሁንም ምን ያህል እንተረዳችኝ ባይገባኝም…

“ምናልባት እስክጋደምልህ ይሆናል። … የተወጠረ ሽፍደትህን እስክታረግብ… ” ከአፏ የሚወጣው ቃልም ድምፀትም የሷ አይመስልም… ጥርሷን እያፏጨች ነው የተናገረችው……

በመጀመሪያ ደነገጥኩ። …… ስምሪት እንዲህ ስትናገር ሰምቼ አላውቅም። በመቀጠል ተናደድኩ። በፍፁም እየተረዳችኝ አልነበረም። በመሰለስ ግን ስለዚህች ሴት የማላውቀው ብዙ ነገር መኖሩን ማሰብ ጀመርኩ።

ስደነግጥ
ለኔ ሳይሆን ለእርሷ ማንነት የማይመጥናት የመሰሉኝን ቃላቶች በማውራቷ አይኖቼን ጎልጎዬ አፈጠጥኩባት።

ስናደድ
“እየገባሁሽ አይደለም። ስለሴክስ እያወራሁ አይደለም። …… እዚህ ጋር(ልቤን በእጄ ደግፌ) ስለሚሰማኝ ስሜት ነው እየነገርኩሽ የነበረው… …” አልኳት በአፏ አልመለሰችልኝም። ፊቷ ግን ስልችት አሳየኝ።

ማሰብ ስጀምር
“ማነው?” አልኳት

“ማን?” መለሰችልኝ

“እንዲህ Abuse ያደረገሽ?”

በረዥሙ ተንፍሳ ፀጥ አለች።

“ድብቅ ነሽ።” አልኳት

“ድብቅ እንኳን አይደለሁም።” መለሰችልኝ

“እኔ የማልነግርሽ ክስተትም ስሜትም ኖሮኝ አያውቅም። ስላንቺ አንዲትም ነገር አውርተሽ አታውቂም።”

“ጠይቀኸኝ አታውቅም። ለራሴ ውድ ቦታ አለኝ። ……ዋጋ የሌለኝ ሰውጋ ራሴን የምጥል ርካሽ አይደለሁም።” ያለችው በትክክል ገብቶኝ እንደሆነ እርግጠኛ አልነበርኩም።

“አቤት? ዋጋ ባልሰጥሽ ኖሮ ስለራሴስ አወራሽ ነበር?”

“ዋጋ ስለሰጠኸኝ ሳይሆን… … ዋጋ ስለሰጠሁህ ነው ያወራኸኝ። … ከሴቶችህ ብዙዎቹ ስለራሳቸው ነግረውሃል። አንተ ግን ስለራስህ ለአንዳቸውም ነግረህ አታውቅም። ለምን ይመስልሃል? ልትሰማቸው እንጂ ሊሰሙህ ጊዚያቸውንም ልባቸውንም አልሰጡህም።” ከተናገረችው ሁሉ የገባኝ(ቃል በቃል ባትለውም) ‘ልቤን ሰጥቼሃለሁ‘ ያለችው ነው።

” አሁን ልሰማሽ ዝግጁ ነኝ። … ንገሪኝ… ”

“አሁን ሰዓት ሄዷል። ወደ ቢሮ እንመለስ!” አለች በዓይኗ አስተናጋጅ እየፈለገች
…………
…………

ፍቅር የብዙ ነገር ቁልፍ መሆኑ ገባኝ። አለምን የምናይበት መነፅር ፣ ራሳችንን የምናይበትም ጭምር … አስቤ ስለማላውቃቸው ብዙ ነገሮች ማሰብ ጀመርኩ። …… ከመለዮዬ ውጪ ምን ስለመልበስ አስቤ የማላውቀው ሰው ራሴን ልብሶች ስሸምት አገኘሁት። ……

“ያንተ ተክለ ሰውነት ልብስ ያስጌጣል እንጂ አንተን ልብሱ አያስጌጥህም። ለምትለብሰው መጠንቀቅ አይጠበቅብህም።” ብላኛለች ስምሪት ከመለዮዬ ሌላ ለብሼ ያየችኝ የመጀመሪያ ቀን

“ለምን እራቁቴን አታዪኝም?”

“አትባልግ እንግዲህ!”

……
በሌላ ቀን ለአንዲትም ቀን አስቤው የማላውቀውን ራሴን ቤተክርስቲያን ስፀልይ አገኘሁት… …( በእርግጥ ከፀሎት ይልቅ ለንግግር የቀረበ ነገር ነበር)

ፍቅር የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው…… የሁሉንም የህይወት ጥጎች ማጠንጠን ጀመርኩ። …… እስካሁን አንድ የሆነ ቦታ ላይ… … የሆነ እድሜዬ ላይ ቆሜ የነበር አይነት ስሜት ነበር የሚሰማኝ። …… ገና አሁን በስምሪት ፍቅር መኖርን የጀመርኩ……

በገፋችኝ መጠን ወደርሷ የሚስበኝ ፍቅሯ ልቤን ከብዶት ይጎትተኝ ጀመረ። ቀናቶች የንስር ክንፍ አውጥተው ይበራሉ……እሷ በቻለችው መጠን ትሸሸኛለች…… እኔ ደግሞ ከምችለው በላይ ወደርሷ እወነጨፋለሁ።

የምንገናኝባቸውን እና ልናወራ የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች ትዘጋቸዋለች። ……

“ከነገ ጀምሮ እረፍት ወጣለሁ።” አለችኝ የሆነ ቀን የቀኑ ስራ ማብቂያ ሰዓት ላይ እየወጣን

“ለምን? ሽሽት ነው?” አልኳት

“የምን ሽሽት? ማረፍ ፈልጌ ነው።” አለችኝ አይኖቼን እየሸሸች…… ቆምኩኝ። ቆመች። …… አየኋት። አቀረቀረች። …… የጡቶችዋ ጫፎች ደረቴን እስኪነኩት ተጠጋኋት። አልሸሸችኝም። …… ምንም እንቅስቃሴ አላደረገችም። … ወደ ጆሮዋ ከንፈሮቼን አስጠግቼ

” ታውቂያለሽ? ሁሌም አንድ እርምጃ ወደፊት የማያራምደን የ‘ባይሳካስ?‘ ፍርሃት ነው።…… እመኚኝ!! …… እመኚኝና ልብሽን ስጪኝ… … አንድ ነገር ቃል እገባልሻለሁ። ልብሽን አልሰብርም!!” አልኳት አይኗን ገርበብ አድርጋ ነበር የሰማችኝ ከመግለጧ በፊት አየኋት… … አይኔ ከንፈሯ ላይ ቀረ። …… ውጤቱን ማሰብ አልፈለግኩም። ወይም ምንም ቢሆን ግድ አልነበረኝም። …… ከንፈሮቿን ሳምኳቸው። …… ለምን ያህል ሰከንድ እንደሆነ ባላውቅም መልሳ ስማኛለች። እጇ በወገቤ ዙሪያ አልፏል። …… ይሄን ያሰብኩት ድንገት አቁማ ገፍታኝ ስትቆም ነው እንጂ ስትስመኝ ከጥፍጥናዋ ውጪ ማወቅ የቻልኩት ነገር አልነበረም።

“ኪሩ? ምንድነው የምታደርገው?” ጮኸችብኝ…… ፈገግ አልኩ…… ልቧን ስትሰማው ስማኛለች። መንገድ ላይ መሆናችን እንኳን አላሳሰባትም ነበር። አዕምሮዋን ስትሰማው ነው የገፋችኝ። …… ባትነግረኝም የማትክደው ስሜት አላት። …… ፈገግታዬ አበሳጫት። ተናደደች።

“ኪሩ ሁለተኛ እንዲህ ብታደርግ እንጣላለን። የምሬን ነው!!” አለች ድርጊቴ እንዳናደዳት ለመግለፅ እየጣረች

“እሺ። ከዛሬ በኋላ ራስሽ ካልጠየቅሽኝ አላደርገውም።”

“ማለት?”

“‘ኪሩቤል ሳመኝ‘ ብለሽ አፍ አውጥተሽ ካልጠየቅሽኝ አልስምሽም።” አልኳት።

“ወገኛ! ኪሩ እኔ አንተ እንደምታውቃቸው አይነት ሴቶች አይደለሁም።” አለች መንገድ እየጀመረች

“አውቃለሁ!! ከነሱ የሚለይሽ ነገር ባይኖር ከነሱ የተለየ ስሜት አትሰጪኝም ነበር።” መለስኩላት እርምጃዬን ከርሷ ጋር እያመጣጠንኩ

“ለምን እኔን? ለምን? ደግሞስ ለምን አሁን? አንተ ማንም ሴት የምትደነግጥልህ ወንድ ነህ!”

“ማንም ሴት ደንግጣልኝ ይሆናል። ካንቺ ውጪ ያስደነገጠችኝ ሴት የለችም። ለውጡ እንዴት አይታይሽም?” አልኳት……

ተለይታኝ ሄደች። …… በልቤ ተሸክሚያት ወደ ሱሴ ሄድኩ።……

ጥያቄው መሸነፍህ አይደለም። መዋጋትህ እንጂ…… ምክንያቱም ሳትታገል ሁሌም ውጤቱ የተዋቀ ነው። ተሸናፊ ነህ። በትግልህ ውስጥ ውጤቱ ከሁለት አንዱ ነው። ማሸነፍ ወይ መሸነፍ!! ጥያቄው መዋጋትህም ብቻም ላይሆን ይችላል። የተዋጋህለት አላማ እንጂ …… እሷ ናት… … ምንንም ባልፍላት የሚገባት… …
………
………
………

ናፍቆቷን መታገስ ከምችለው በላይ ነበረ። ስልኳ እረፍት ከወጣችበት ቀን ጀምሮ ዝግ ነው። …… ጭንቅላቴ የሚፈነዳ መሰለኝ። …… እቤቷ ላለመሄድ ከቁጥር በላይ ለሆነ ጊዜ አመነታሁኝ…… በስምንተኛው ቀን እሷን ሳላያት ባድር ትንፋሼ ቆሞ የማድር መሰለኝ። …… ከስራ ወጥቼ እቤቷ ሄድኩ። ………… በሩን ስትከፍትልኝ ምን እንደምላት፣ ምን ለብሳ እንደማገኛት፣ ስታየኝ ምን እንደሚሰማት… … እያሰብኩ በሩን በስሱ ቆረቆርኩ። …… ደገምኩት። …… ጨዋታ አቋርጦ እንደከፈተልኝ የሚያስታውቅ ሰው ያላለቀ ሳቁን እየቀጠለ በሩን ከፈተልኝ። ……

“አቤት?” አለኝ

ሰምቼዋለሁ ዝም አልኩ። …… ደገመልኝ። ዝምታዬን ደገምኩለት… … ስምሪት ከጀርባው ብቅ አለች።…… ምንም አይነት የፊት ሜክአፕ ስትጠቀም አይቻት አላውቅም። …… ተቀባብታ ሌላ ሴት መስላለች። …… ከከንፈሯ ውጪ ያልደመቀ የለም። …… ለፓንትነት የቀረበ ቁምጣ እና ለጡት ማስያዣነት የቀረበ ሹራብ ለብሳለች። …… ፀጉሯ ቢመሳቀልም ተለቋል። …… እሱን አየሁት… … በሲሊፐር ነው…… እንግድነት አይታይበትም…… የከንፈሩ ጠርዝ ላይ የከንፈር ቀለም አስተዋልኩ……

አለመታደል ነው (ክፍል ስድስት)

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...