Tidarfelagi.com

ንባበ ህሊና ወከባቢ

ያለሁበት መኪና(ተስፈኛ አንባቢዎች <ያለሁበት ባቡር> ብለው ማንበብ ይችላሉ) ያለቅጥ ይበራል፡፡ ይሄን ሹፌር፣ ‘ስምህን ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ይጥራው!’ ብሎ የረገመው አለ? እላለሁ በውስጤ፡፡ `ኸረ ባክህ ቀስ በል` ይላሉ ካጠገቤ የተቀመጡት ሴቶች፡፡ በመስታዎት ውስጥ ውጭውን ማስተዋል ጀመርኩ፡፡
………… በቀኙ የአስፓልት ዳር፣ መንገድ ስቶ ቦይ ውስት የተገለበጠ ተሳቢ!……. ይሄኔ ሹፌሩ ከቤቱ ሲወጣ “በቀኝህ አውለኝ“ ብሎ ይሆናል የወጣው፡፡ ያው ፈጣሪውም ፀሎቱን ሰምቶ፣ በቀኙ አዋላው፡፡ ግልፅነት የጎደለው ፀሎት ጣጣው ብዙ ነው…ሃሃሃ ….እግዜር ግን የልባችንን መሻት እያወቀ፣ ለምን በፀሎት `ቢዚ` ሊያደርገን እንደሚፈልግ ግራ ይገባኛል፡፡ የምንፈልገውን ካወቀ አርፎ አይሰጠንም? የምን……… (ተዉት ግድ የለም)

ሹፌሩ ግን ለምን እንደሚጣደፍ ያውቀዋል? ሕዝቡ እራሱ ለምን እንደሚጣደፍ ያውቀዋል? ምን ለማግኘት ነው? ምን ለማትረፍ? አዲስ አበባ ነው፣ ሰማይ ቤት ውሰደኝ ብዬ የተሳፈርኩት? …… ትኩረቴን ወደተከፈተው ሬድዮ አደረኩ፡፡ <….. እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሕዝብ የተለየ እና የሚያምር ባህል ያለን ህዝቦች ነን፡፡…..ሁሌም ኢትዮጵያዊ በመሆኔ እንድኮራ ያደርገኛል……ልልል…..ላላላ….> ትላለች አንዷ፡፡ ደከመችኝ፡፡

….ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ……..ምንድን ናት ኢትዮጵያ? ኢትዮጵያዊ ከመሆን ሰው መሆን አይቀድምም? የብዙዎች የኢትዮጵያዊነት ትርጉም በአፍጢሙ የሚተከለው፣ ሰው ከመሆን ስለሚያስቀድሙት ነው፡፡ ቆይ ግን ገጣሚው “ሰው ነው ሀገር ማለት“ ሲል፣ የትኞቹን ሰዎች ማለቱ ነው፡፡ ወንጀለኞቹን? ሙሰኞቹን? ሀብታሞቹን? ወይስ ድሆቹን? ሁሉም? እሺ ሁሉም እንበል፤ ሙሰኞች ኬኒያም አሉ፣ ድሆች ሶማሊያም አሉ፣ ወንጀለኞች አሜሪካም አሉ፡፡ ሀብታሞችም የትም አሉ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ከኬንያ በምን ትለያለች? ከሶማሊያ በምን ትለያለች( ሀገር ሰው ከሆነ ማለቴ ነው) …ሀገር ማለት ሰው ከሆነ፣ የኛን ህዝብ ቻይና ወስደን፣ ቻይናን ኢትዮጵያ ማለት እንችላለን? አሊያም የቻይናን ሕዝብ እዚህ አምጥተን፣ ቻይኖቹን ኢትዮጵያውያን ማለት እንችላለን?

ኢትዮጵያ የምትባል ነገር የለችም! ፈጠራ ናት፡፡ አባቶች ህሊናችን ላይ የሳሏት ስዕል ናት፡፡ ተጨባጭ ያልሆነች…. አልኩ ለራሴ፡፡ ሰው ለምን በዜግነት ተከፋፍሎ ይኖራል? እንግሊዝ ጣሊያን፣ ሱዳን፣ ቅብርጥሴ….. ሁሉስ ሰው ሰራሽ አይደሉምን? ብዙዎች እራሳቸውን ቡድን ውስጥ ካልከተቱ ህልውና ያላቸው አይመስላቸው፡፡ ወላይታ ነኝ፣ትግሬ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣አማራ ነኝ፣…… እንትን ነኝ…..ነኝ…. ይላሉ፡፡ ከ`እኔነት` ስፋት ይልቅ፣ የ`እኛነት` ጥበት ይማርካቸዋል፡፡ ሰው ከመሆን ውበት በልጦ፣ ቡድን የመሆን ፉንጋነት ያነሆልላቸዋል፡፡ ….. ሰው መሆኑን ከመቀበሉ በፊት፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል፣ እሱ መናፍቅ ነው፡፡….. ኢትዮጵያዊ ከመሆኔ በፊት ሰው ነበርኩ፤ ኢትዮጵያዊ ከሆንኩ በኋላም ሰው ነኝ፤ ሰው ከሆንኩ በኋላም ሰው ነኝ፡፡ የአንድ ብሔር አካል ከመሆን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በስንት ጣዕሙ( ብዙ አራት ነጥብ)
*
*
ሹፌሩ `መጨረሻው!` ሲል ከሃሳቤ ባነንኩ፡፡ ወረድኩ፡፡ ሕዝቡ ይጣደፋል፡፡ ምን ሆኗል? የወያሎች፣ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች፣ የሊስትሮዎች ጩኸት….ጥድፊያውን ያባባሰው ይመስላል፡፡ ከመኪኖች የሚወጣው ጭስ፣ አዲስአበባን ትልቅ ኩሽና አስመስሏታል፡፡…… ወሩን ሳስበው ፆም ነው፡፡ፆም ስለሆነ፣ አንድ ሆቴል ገብቼ ቅቅል በላሁ፡፡ …..ቅቅል የበላሁት ስላማረኝ ብቻ አይደለም የበላሁት፣ ፆም ስለሆነም ነው፡፡ ብዙዎች ከሚያደርጉት በተቃራኒ ማድረግ ደስ ስለሚለኝ ነው፡፡

ለነገሩ እውነቱን እናውራ ከተባለ፣ ቅቅል አልበላሁም፡፡ በዚህ ቅቅል ኑሮ፣ ቅቅል መብላት እራስን መቀቀል ነው ብዬ ስላመንኩ ትቼዋለሁ፡፡ ግን ቃሉ `…. ያየ በልቡም የተመኘ እንዳመነዘረ ነው` ስለሚል፣ እኔም `በልቤ ስለተመኘሁ፣ በሃሳቤም ስለበላሁ` እንደበላሁ ነው የሚቆጠረው፡፡ ከሆቴሉ ስወጣ( መጀመሪያዉኑስ ግን መች ገባሁ? ሃሃ) ያ ቅድም ሲጣደፍ የነበረው ህዝብ አሁንም ይጣደፋል፡፡ ተፍ…ተፍ…ተፍ…….ደፍ……ደፍ….ደፍ……ክው….ክው….ክው….ጡል… ጡል…. ጡል….

ለምን እንደሚጣደፍ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ መጣደፍ ልማድ ሆኗል፡፡ በዕውቀቱ “ሲመላለስ እንጂ ሲደርስ አይታይም“ ያለው እውነቱን ነው፡፡ የሆነ ከፍታ ላይ ወጥቼ፣ `ህዝቤ ሆይ ተረጋጋ!` ማለት አሰኘኝ፤ `ምን ያጣድፍሀል? ደና ህዝብ አልነበርክ እንዴ? መሮጥ ብቻ እኮ የህይወት ግብ አይደለም፤ የምትሮጥለትን ነገር ማወቅ አለብህ፡፡ ዝም ብለህ ሲሮጡ አይተህ፣ ባለመድከው እሩጫ፣ በአፍ-ጢምህ ልትተከል ነው? ኸረ ተው የድሮ አንተነትህ ይሻልሀል…` ልለው አማረኝ፡፡ “ ይሄ ሕዝብ በዚህ ሰዓት እግር እንጂ፣ ጆሮ የለውም“ ብዬ ስላመንኩ ተውኩት፡፡

…. የምር ግን ይሄ ህዝብ አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብን የሚያማክር ሳያካተሪስት ይኖር ይሆን? ቢኖርስ ሕዝብ እንዴት ተደርጎ ይመከራል፡፡ ህፃን ልጅ አይደለ፣ ጉልበትህ ላይ አስቀምጠህ፣ ፀጉሩን እየደባበስክ አትመክረው፡፡ትልቅ ሰው አይደል፣ `እስቲ እዛች ወንበር ላይ ቁጭ በል` ብለን አንመክረው፡፡ ወይ ሕዝብ!

ብዙዎቹ ጥድፍ ጥድፍ ሲሉ ይቆዩና፣ ደክሟቸው ይሁን ትንሽ አረፍ ብሎ ለመጣደፍ እንጃ… ባቅራቢያቸው ካለ ካፌ ገብተው ቁጭ ይላሉ፡፡ አይናቸው ውስጥ ግን ያልተረጋጋ ጥድፊያ አለ…. ተነሱ እንጣደፍ እያለ የሚጎተጉት! ቁጭ ቢሉም አላረፉም፡፡ ደሞ፣ ማኪያቶ፣ ቡና፣ ኮካ…. ነገር ነው የሚያዙት…. ይበልጥ ለመጣደፍ ይመስል፡፡ እሷን ጠጥተው ተነስተው ቱር ይላሉ፡፡ …… ኸረ ተው አንተ ሕዝብ!

ለዚህ ሕዝብ፣ ሁሉ ነገር ጥድፊያ ሆኗል፡፡ ወሬው እንኳን ጥድፊያ ነው፡፡ ፌዴሬሽንን…ፌዴሬሽን…. ቤቲ ቤቲ….ግብፅ…. ግብፅ… ሹመት …ሹመት…. ሽረት… ሽረት…. ሁሉ ነገር ጥድፊያ ነው( ጥድፊያ እንጂ፣ ጥልቀት የለም)…. “ሴቶች እራቁታቸውን ይሂዱ አትከልክሏቸው“ የተባለ ይመስል፣ ብዙዎቹ ራቁታቸውን ናቸው፡፡ ብዙ ከርፋፋ ወንዶች፣ ከርፋፋ ልብስ ለብሰው፣ በተቻለቸው አቅም፣ ከጥድፊው እኩል ለመጣደፍ ይሞክራሉ፡፡
…. ከፊት ለፊቴ ረዥም የታክሲ ሰልፍ አለ፡፡ ከታክሲው ሰልፍ ዳር የሚጮህ ሰባኪ!… እንዲህ ይላል፤ “…ጆሮ ያለህ ስማ…. አዳኛችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ፣ `መምጫዬ ቀርባለች እና ንስሃ ግባ ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል!….“ … ሳቅኩ፡፡ `ጥሪውን ያስተላልፋል` የምትለዋ ቃል የምር አሳቀችኝ፡፡….. እንደሰባኪው አባባል፣ የክርስቶስ መምጫ በቅርብ ነው፡፡ ያ ማለት፣ የእኛ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስም ተጣድፏል፡፡ ነው? የተጣደፈው ሕዝብ አካል፣ የሆነው `የተጣደፈው ሰባኪ` ነው፣ አጣድፎ ሊያመጣው የሚሞክረው፡፡

ሰባኪው ቀጥሏል፡፡ “ የንስሃ ጊዜዬ ቀርባለችና….. ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል!“ …ሰዉ ሰባኪውን የሚያዳምጠው አይመስልም፡፡ ሁሉም የውስጡን ጥድፊያ የሚያዳምጥ ይመስላል፡፡ ግን የክርስቶስን መምጣት የሚያስንቅ ምን የሚያጣድፍ ነገር ተገኘ፡፡ እውነት በሰባኪው በኩል ጥሪ አስተላልፎ ከሆነስ( እሱ እንደው የተናቁትን ነው የሚመርጠው)…. ለንሰሃም የባከነ ሰዓት ጭማሪ ይኖረዋል ብሎ ተስፋ አድርጎ ይሆን? ….አይ እግዜር ግን! እራሱ ፁሙ፣ ፀልዩ ብሎ፣ ቢዚ ሲያደርገን ከርሞ፣ አሁን ደግሞ፣ በድንገት ልመጣ ነው……..! ….ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዝም ብዬ ቆምኩ- በጥድፊያው መሃል፡፡ …….. ሰዓቴን አየሁ፡፡ እቺን ይወዳል! ወደ ታክሲ መያዣዬ ተጣደፍኩ(ሃሃሃ ሕዝቡ ተጋባብኝ ወይስ አጋባብኝ)… ታክሲዬን ይዤ ወደ ሰፈሬ፡፡ …. እቤቴ ገባሁ፡፡

ስገባ፣ እህቴ `Z` ነው `X` የምትባል አረብ ሀገር ያለች ጓደኛዋ የላከችላትን ደብዳቤ ቁጭ ብላ ታነባለች፡፡ እህቴ፣ `አታነብም!` ተብላ እንዳትታማ የሚያደርጋት አንድ ነገር ቢኖር፣ እቺ ጓደኛዋ ደብዳቤ ስትልክላት ማንበቧ ነው፡፡ ልብሴን ቀያይሬ ወደ አልጋዬ አመራሁ፡፡

“እራት ላቅርብ“ አለች እህቴ፡፡

“ በላሁ“ አልኳት፡፡

“ የት?! “
“ ሆቴል“

“ምን በላህ?“

“ ቅቅል!“ ሃሃሃ…….. ዝም አለች፡፡ ዝም አልኩ፡፡

ከጎረቤት የአከራዮቼ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ትዳር ውሸት! ጥድፊያ ውሸት! ሕዝብ ውሸት! ቡድን ውሸት!…. ውሸት ውሸት! ሁሉም ውሸት! አልኩ ለራሴ፡፡ ጥቅልል ብዬ ተኛሁ፡፡ ከአንድ እንቅልፍ በኋላ፣ ሕዝቡን ሆኜ እነቃለሁ፡፡ ከአንድ እምቅልፍ በኋላ ጥድፊያውን፣ እውሸቱን፣ የቡድን አስተሳሰቡን፣ ፈሊጡን እቀላቀላለሁ!…… ሽፍንፍን! ለጥ!!!! ……. አውቄ ተኛሁ፤ ሲቀሰቅሱኝ ላለመስማት……

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...