Tidarfelagi.com

ነፍስ ይማር!!

በፍቅር ሰበብ; ሴት ስለሚገድሉ ወንዶች የሚወጡ ዜናዎችን እንሰማለን፡፡ በወጣትነታቸው የተቀጠፉ ጽጌሬዳዎች ያሳዝናሉ፡፡
ነፍስ ይማር!!

በፍቅር ሰበብ መግደል በተለይ የወንዶች ችግር ይመስለኛል ፡፡ ሴቶች በወደዱት ሰው መገፋትን በእንባቸው ያጥቡታል፡፡ ለወንድ ግን ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም፡፡
ለብዙ ወንዶች ከሴት ጋር የሚደረግ ግኑኝነት የፍቅር ጉዳይ ብቻ ኣይደለም፤ የክብር ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ኣንድ ሴት ፈልገው እምቢ ስትላቸው ሰማይ እንደ ብረት ቁና የሚደፋባቸው ወንዶች ጥቂት ኣይደሉም፡፡ ኣልፈልግህም መባል ተንቄ ነው የሚል ስሜት ያሳድራል፡፡ ሰው መገፋቱን ለብቻው ይዞ እንዳያስታምም ማህበረሰብ ኣስተያየት ከባድ ቀንበር ሆኖ ይወድቅበታል፡፡ ” ጠይቋት ጥምብ ርኩሱን ኣውጥታ ”ኣባረረችው የሚል ሽሙጥ ኣርፈህ እንድተኛ ኣያደርግም፡፡ ኣብዛኛው ያለም ህብረተሰብ ኣሸናፊውን የሚቀድስ ተሸናፊውን የሚያራክስ ነው፡፡ እኛም“ የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” ብለን ዘግተነዋል ፡፡ ኣንድ ሰው እምቢ ያለችውን ሴት ሲቀጥፍ ብቻውን ኣይደለም፡፡ ሽንፈትን የሚያጋንን ማህበረሰብም ኣባላትም የሆንነው እኛም በስውር ተባብረነዋል፡፡

ኣፍቅራችሁ የተገፋችሁ ወንዶች መገፋታችሁን በጸጋ የምትቀበሉበት ጽናቱን ይስጣችሁ፡፡“ንቃኝ ነው፡፡” ከማለት“ እኔ ምርጫዋ ስላልሆንኩ ነው፡፡ እኔን የምትፈልገኝ ሴት ደግሞ የሆነ ቦታ ኣለች ፤የሆነ ጊዜ ላይ ትመጣለች” ብሎ ማሰብን ተለማመዱ፡፡ በርግጥ ሰዎች በተቆጡበት ወቅት በቀልን እንጅ ጠቃሚ ምክር የሚያስታውስ ልቦና እንደሌላቸው ይገባኛል፤ እንዲያው ቢቸግረኝ ነው፡፡

የዛሬ ኣበባዎች የነገ ሰለባዎች ሴቶች ሆይ ! ልባችሁ ያልፈቀደውን ሰው በይሉኝታ ወይም ለእናት ኣገራችሁ ስትሉ የማቀፍ ግዴታ የለባችሁም፡፡ ለእናት ኣገራችሁ ስል ኣንድ የሰነበተ ወግ ትዝ ኣለኝ፡፡ በመንጌ ጊዜ ኣንዲት ቆንጆ ሴተኛ ኣዳሪ ነበረች፡፡ የኣፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በተደረገ ጊዜ ካፍሪካ ኣምባገነኖች ኣንዱ ከጀላት፡፡ ይህን ያወቁ የመንጌ ቦዲጋርዶች መኖርያዋ ድረስ መጥተው “የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ስለወደዱሽ ተኝላቸው ” ብለው ኣባበሏት፡፡ እሷም እሺ ብላ የፕሬዚዳንቱን ወቀጣ ጥርሷን ነክሳ ስትቀበል ኣደረችና ማለዳ እያነከሰች ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ በማግስቱ ምሽት እንደገና ልኡካኑ መጥተው ሊወስዷት ሲያግባቧት“ ኧረ ምን በወጣኝ !! ትናንትም ለእናት ኣገሬ ስል ነው የተረዳሁ ”በማለት መለሰች፡፡(” የተረዳሁ“ የሚለው ቃል የዋናው ቃል ምትክ ሆኖ ገብቷል፡፡ )

እና ቆነጃጅት ለእናት ኣገራችሁ ሲባልም ቢሆን የማትፈልጉት ወንድን እሺ የማለት ግዴታ የለባችሁም፡፡ ግን በተቻላችሁ መጠን ኣለመፈለጋችሁን በተለሳለሰና በተሽሞነሞነ ቃል ለመግለጽ ሞክሩ፡፡“ እኔ ደግሞ የሚገጥመኝ ሙጀሊያም ሙጀሊያሙ ነው ”ኣይነት መልክት ያለው ፊት ላለማሳየት ተጠንቀቁ፡፡ በለሰለሰ ቃል የተገለጸ እምቢታ ከእሽታ ልተናነሰ በጎ ስሜት ይፈጥራል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለን ሴት ተማሪዎችን ኣስቁመን ባንድ እጃችን በላብ ያደፈ ደብተራችንን፤ በሌላ እጃችን የተፈቃሪዋን እጅ ጨብጠን “ ኣበባው ግሮሰሪ ገብተን ብንጫወት ምን ይመስልሻል?” ስንል የሚመለስልን መልስ ኣይረሳኝም፡፡“ ይቅርታ ! እኔ ኣላማ ኣለኝ፤ በእህትና በወንድምነት ከሆነ ግን ችግር የለውም” ይሉን ነበር፡፡ በጊዜው ኣላማ የሚለው ቃል ትልቅ ክብደት ያለው ቃል ነበር፡፡ ህብረተሰብን ከመሃይምናትና ከኋላቀርነት የማውጣት ኣላማ፤የኣገር ኣንድነት ኣላማ ምናምን የሚባሉ ግዙፍ ቃሎች ጋር የተያያዘ ነበር፡፡እና ከልጅቷ ኣላማ ጋር ሲነጻጸር የኛ ሽፍደት ኢምንት ሆኖ ይታየናል፡፡ በዚያ ላይ፤ ያችን በመሰለች ልጅ በወንድምነት መታጨታችን ያጽናናል፡፡ እናም በመጣንበት እግራችን በሰላም እንመለሳለን፡፡

ከላይ ያስቀመጥኳቸው የግጭት መፍቻ ሀሳቦች ከችግሩ ትልቅነት ኣንጻር ኣቅመቢስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ በተረፈ “ ኣይድረስ” ማለት ነው፡፡

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...