Tidarfelagi.com

…ቸል ያደርገኛል

‹‹ከጠዋት እስከማታ እለፋለሁ፡፡ የምለፋውም በቸልታ፡፡ ነገሥታቶቹ ምቹ ላይ ይተኛሉ፡፡ የሚንቀጠቀጥ ማለፊያ እንጀራ ሰሀኖቻቸው ላይ ዘርግተው የእኔ የደንባራው ነገር ገርሟቸው በሳቅ ይፈርሳሉ፡፡ በንቀት የመጣ አለመግባባት እንጂ ሌላ ምንድን ነው?
ይሄ ቸል ያደርገኝ ነበር፡፡

ቀኑን ሙሉ በቆዳ ቦት የታሰሩትን እግሮቼን ማታ ላይ አወላልቄ ሳያቸው ያበጡና የቀረኑ ናቸው፡፡
ይሄም ቸል ያደርገኛል፡፡

ስለእኔ ስለደሃው እያወሩ በቅቅል ባሕር ላይ፣ በበሬ ጎድን ጀርባ ውስጥ የክትፎ ዓሳ ያጠምዳሉ፡፡ እኔ እህቴ ጫልቱ ቤት ነጭ ሽንኩርቱ ያልሞተ ሽሮ በቅራሪ አምጌ አድራለሁ፡፡ (ምነ? ብል ስንት ሺሕ ሕዝብ በድርቅ ተጎድቶ ይሉኛል፡፡ ደሃ ብትሞት ደሃ ትቁሰል እንደማለት)
ይሄም ቸል ያደርገኛል፡፡

እኔ መማሪያ መጽሀፍ ሳይኖረኝ እነሱ ልጆቻቸውን አውግዙት እያሉ ወደሚያጣሉን ምዕራብ ሀገር ይልካሉ፡፡
ይሄም ቸል ያደርገኛል፡፡

ከጉቦኛ ትራፊኮች እላከፋለሁ፡፡ ሳይገባኝ ሁሉም ጉቦ እንደሚወድ፡፡
ይሄም በልግም ይመታኛል፡፡ ግድ የለሽ ያደርገኛል፡፡

እያንዳንዱን ዜጋ እንደመሪዬ ልጠብቀው እፈልጋለሁ፡፡ እሱ ግን ይንቀኛል፡፡ ሐሳቤን ሲሰማ ‹‹የጠገበ ወታደር›› ይለኛል . . . .
ይሄም ቸል ያያርገኛል፡፡

ያጠፋ ሳስቀጣ ያጠፋው ይጠላኛል፡ ‹ወንድሜ ከስህተትህ ተማር› ስለው ይገላምጠኛል፡፡
ይሄም ቸል ያደርገኛል፡፡

‹‹እህቴ ሆይ በእሱ በኩል አትሂጂ መኪና ሲታጠፍ ትገጪያለሽ›› ስላት ‹‹የማነው ዝተት›› ትለኛለች፡፡ መኪናው ይላተማታል፡፡ እያነከሰች ተነስታ ‹‹ያ ነጀሳ ፖሊስ ነጅሶኝ ነው›› ትላለች፡፡
ይሄም ያስከፋኛል፡፡ ቸልም እላለሁ፡፡ ሁሉም እላለሁ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡

‹‹አውቶብሱ ውስጥ ቀስ ብላችሁ ግቡ›› እላለሁ፡፡ ‹‹ወሮበላ አለ›› እላቸዋሁ፡፡ ‹‹ከየት የመጣ ነው፣ ምጥ ለናቷ አስተማረች›› ይሉኛል፡፡ ከዚያ ይዘረፋሉ፡፡
ይሄም ያሳዝነኛል፡፡ ይሄም ቸል ያደርገኛል፡፡

ወሮበሎችም ይጠምዱኛል፡፡ እነሱም ያማሩ ወሮበሎች በየመንገዱ ቆመው ወደ እኔ እየጠቆሙ ‹‹እሱ ህዝብ ደህንነት ነው›› ይሉኛል፡፡
ይሄ ያስከፋኛል፡፡
የወሮበሎቹ ጠላት ነኝ የሚለው ሰላማዊው ሰውም ያምናቸዋል፡፡
ይሄ ቸል ያደርገኛል፡፡

ለህዝብ ስልክ አስር ሳንቲም ያወጡና ሳጥኑ ሲውጥባቸው ውዱን ማሺን ይደበድቡታል፡፡ ‹‹ኧረ ተዉ›› ስላቸው ‹‹የማን ነዝናዛ ነው›› ይሉኛል፡፡ ይሰበራል፡፡ ሌላው ዜጋ መጥቶ ይሞክርና አልሰራ ሲለው ‹‹የማይረባ ስልክ አስቀምጠው በዘበዙን›› ይላል፡፡ ‹‹ከአንተ ቀድማ እህትህ እዚህ ነበረች›› ስለው ያልገባቸው ዐይኖቹን በቁጣ ያገላብጣል፡፡
በዚህም አዝናለሁ፡፡ ሃኬትም በደም ስሬ ይሰርግብኛል፡፡

በየሰፈሩ እየዞርኩ ጠላ እንድጠጣ ይፈልጋሉ፡፡ እምቢ እላለሁ፡፡ ከሱሶች እርቃለሁ፡፡ በዚህ ያኮርፉኛል፡፡ በዚህ ይስቁብኛል፡፡ በሚያምሩ ጥርሶቻቸው ይስቁብኛል፡፡
ቸልታ ይነፍስብኛል፡፡ እትትትት፣ እትትትት እላለሁ፡፡
‹‹አትጃጃል›› ይሉኛል፡፡ ‹‹ምኔ ተጃጃለ?›› ስላቸው ‹‹ለምን እንደሰው አትሆንም?›› ይሉኛል፡፡ ‹‹ድራፍት ሰው ያደርጋል›› ይሉኛል፡፡ የድራፍት አረፋ እያደነቁ ያወራሉ፡፡ ‹‹ካገኘኸው ሰው ተጋበዝ የሚጋብዝ ተገኝቶ ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹ አይሆንም ኧረ አይሆንም›› እላለሁ፡፡ ‹‹ቀሽም ነህ›› ይሉኛል፡፡ ቢራ፡ ክትፎ የሰው ምግብ ነው ይሉና ከወንጀለኛ ይዳራሉ፡፡ ‹‹ የምን ሰው?›› እላለሁ፡፡ በዚህም ይስቃሉ፡፡
በዚህ ቅር ይለኛል፡፡ በዚህም ቸልታ ይጠናወተኛል፡፡

ወደ እኔ እየጠቆሙ እየሳቁ ‹‹ ምነው ከስራው ቸለለ?›› ይሉኛል፡፡ ‹‹እዩት ያን ሃኬተኛ›› ይሉና በኮሚኒስቶች ሊመሰገኑ ይለምናሉ፡፡ እኔም ማርያምን ለመከላከያ አስቀድሜ ከጠዋት እስከማታ እለግማለሁ፡፡ ሁሉም ታዲያ ሁሉን ይተቻል፡፡ ሌላውን ይተቻል፡፡ ‹‹ዐይኖቻችን ውስጥ ስንት ስልክ እንጨቶች አሉ? የሰው ሰናፍጭ ስናሳድድ›› ስላቸው አንጀታቸውን ይዘው በሳቅ … ለሁለት ታጥፈው በሳቅ ይፈርሳሉ፡፡

ይሄ ሁሉ ይጠረቃቀምና ከነፋስ መውጫ የተሳፈርኩበት አውቶቡስ ምነው ቢገለበጥ ኖሮ እላለሁ፡፡ ምናለበት የአውቶቡሱ ሹፌር ዐይኖቹን ጋርዶት በሆነ ዓባይ የሆነ ዴዴሳ ይዞኝ ቢወርድ፡፡ ያቺ ልቤ ውስጥ የቀረችው በሰው ልጅ ላይ ያለችኝ ትንሽ እምነት እንደ በረዶ ኩይሳ ስትቀልጥ እሰማታለሁ፡፡ ብቻዬን ሆኜ እምነት የሌለው ለመሆን ትንሽ እንደቀረኝ ሲገባኝ ሰውነቴ በፍርሃት ይንቀጠቀጣል፡፡

ከዚያም እነሱው መልሰው ይላሉ….. ‹‹እንዴት ነው ትንኙ ሁሉ ብልጥ በሆነባት በዚህች መሬት አንዲት ጠብታ ጣዝማ መስራት የከበደን….. ››
ቢቸግረኝ የሚሰማኝ ወዳጅ ባጣ ወሎዬው የት ሔደ?….. አልኩ፡፡

የማይሞቱ እስስቶች ሜዳችንን ሸፍነው እንደ ትራክተር ይንገላወዳሉ፡፡ መሬትዋ በቆሻሻ ወፍራለች፡፡ ጠባሳችን ሁለመናችንን ሸፍኖታል፡፡ ማሩ የደረቀ ቀፎ ውስጥ ተቀምጠን ክንፋችንን ተበላልተን በጉንድሻችን የምናቃስት….. በዝገት የኮራን….. ታሪክ እንደንብ፣ የየቀኑ ሕይወት ግን ዝንብ ያደረገን…. ታሪክ ታላቅ…. ዛሬ ዛሬ ግን ቆለጣችን (በግራ እጄ አቅፌዋለሁ፡፡ እንዳይጠፋ ወይ እንዳልጥለው) ላይ የተመታን…….. ››

ግራጫ ቃጭሎች

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...