Tidarfelagi.com

ትዳርን ከነ ብጉሩ

አንድ፡ ‹‹ወሲብ በአርባዎቹ››

ጥር የሰርግ ወር አይደለ? የትዳር መጀመሪያ…? ያንን ይዤ ትዳርን ሀ ብለው ለሚጀምሩም፣ ትንሽ ለዘለቅንበትም፣ ገና ዳር ዳር ለሚሉም ቁምነገር አይጠፋውም ብዬ ‹‹ትዳርን ከነብጉሩ›› የሚገልፁ እውነተኛ ታሪኮችን ፍለጋ ባለትዳሮችን ማነጋገር ጀምሬ ነበር።

አሁንም ከዜሮ እስከ አርባ አመታት የትዳር ልምድ ያላቸውን ባለትዳሮች እያነጋገርኩ ነው…ስለ ፍቅር፣ ስለ ጠብ፣ ስለ ልጆች፣ ስለ የእርጎ ዝምብ ዘመድ፣ ስለ መማገጥ፣ ስለ ወሲብ…እንዲያው ስለሁሉም ነገር በፍፁም ግልፅነት ብዙ ተጫውተናል… ብዙ እንጫወታለን…አንድ ቅርጽ ሰጥቼው እስካቀርብለችሁ ዛሬ ለቅምሻ 20 አመታትን በሞቀ ትዳር ከቆየ አባወራ ጋር ያደረግኩትን ጨዋታ ቅንጫቢ እነሆ….

ጌዲዮን ይባላል ስሙ….አርባዎቹ መጨረሻ፣ ሃምሳዎቹ መባቻ ላይ የሚገኝ ጎልማሳ ነው…
በደራ ጨዋታችን መሃል እንዲህ ብዬ ጠየቅኩት፤ ‹‹ለመሆኑ…ከሃያ አመት በኋላም…አንተና ሚስትህ አሁንም ፍቅር ትሰራላችሁ?››
‹‹ህእ…አታምኚኝም! እንደተጋባን…ከዚያም ልጆች ከወለድን በኋላ ራሱ በሳምንት አራት አምስቴ ሴክስ እናደርግ ነበር….አራት አምስቴ! አንዳንዴ ጠዋትና ማታ ሁሉ እናደርግ ነበር…›› አለና ፈገግ ብሎ ዝም አለ።
‹‹እሺ…አሁንስ ከሃያ አመታት በሁዋላ?›› ብዬ ጠየቅኩት..
‹‹ ያው ሁሉም ትዳር ውስጥ እድሜ ሲጨምር…ልጆች ሲኖሩ…ጊዜው ሲሄድ ሴክስ ይቀንሳል አይደል?›› ብሎ አሁንም ዝም አለ። ራሴን በመስማማት ከነቀነቅኩ ቀሪውን እንደሚነግረኝ በመገመት፣ ሃሳቡም እውነት ስለሆነ እንደዚያ አደረግሁ። ራሴን በስምምነት ነቀነቅኩ።

‹‹የእኛ ግን ትንሽ ይለያል….አሁን… አሁን እንግዲህ ሁለታችንም አርባዎቹን ላፍ አድርገን ልንጨርስ ነው… እውነቱን ንገረኝ ካልሽኝ…ዛሬ ዛሬ ሴክስ ከምናደርግ ድንጋይ ብንፈልጥ የሚሻለን ይመስለኛል…ሁለታችንም ለሴክስ የሚሆን እንጥፍጣፊ ፍላጎትም፣ ጉልበትም የለንም…ጭራሽ ትተናል….ኮምፕሊትሊ ነው ያቆምነው….ሃኪም ጋር ሁሉ ልንሄድ አስበን ነበር…የሆነ…ኮታችንን በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት ተስገብግበን ተጠቅመን የጨረስን ሁሉ ነበር የሚመስለው….ግን ድንገት አይደለም ያቆምነው…መጀመሪያ ሰሞን እንዲያው ደባል እንዳንሆን በመፍራት ይመስለኛል ተነጋግረን ቢያንስ ለአመት በአል ለአመት በአል ማድረግ ጀምረን ነበር…ከዚያ ግን በአመት ውስጥ ያሉት አመት በአሎች ራሱ በዙብን…አስቢው…ሌላውን ትተሸ ዶሮ የሚታረድበትን እንኳን ብትቆጥሪ አዲስ አመት…ገና….ፋሲካ.. ስትዩ በአመት ሶስት አራቴ ማድረግ አለብን….ደከመን…ምን እንደሆንን አናውቅም ግን ገና ስናስበው ሁሉ ትክት ይለናል….እንዋደዳለን….እንግባባለን…እንነጋገራለን…የፍቅር ችግር የለብንም…ተቃቅፈን ነው የምንተኛው…ልክ እንደ ድሮው…..›› አለና አሁንም፣ ለሶስተኛ ጊዜ በድንገት ዝም አለ…
‹‹እ…ታዲያ ምን አደረጋችሁ….በቃ አቆማችሁ አቆማችሁ?›› አልኩት።

‹‹አይ…ነግሬሻለሁ…ትዳራችን ምሳሌ የሚሆን ነው….በግልጽ ተነጋገርን እና በአንድ ሃሳብ ተስማማን…››
‹‹በምን?››
‹‹ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የማያከብረው ለእኛ ግን ተስማሚ የሆነ በአል መርጠን በዚያ ቀን ሴክስ ለማድረግ ተስማማን….››
ሆ! እነዚህ ደግሞ ልዩ ናቸው ብዬ አሰብኩና፣ ‹‹ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የማያከበረው በአል›› ሲል የቱን በአል ማለቱ ነው ብዬ በማሰብ ጉጉቴ ጨመሮ፣ በፍጥነት…
‹‹ምን በአል ነው..ማለቴ በምን በአል ቀን ነው ሴክስ የምታደርጉት?›› ብዬ ጠየቅኩት።
አላስጠበቀኝም። ፈጠን ብሎ፤
‹‹ጳጉሜ 6 ስትሆን!›› አለና ፈገግ አለ።
በሃይል ሳቅኩ።
‹‹ሳቂ አንቺ ምናለብሽ!….ትንሽ ጊዜ ስጪው አንቺም ትደርሺበታለሽ…›› አለ አብሮኝ እየሳቀ።
የበለጠ ሳቅኩ።
‹‹አንቺ እሱ ይገርምሻል….›› አለ ሳቁን ገታ አድርጎ።
‹‹ሌላም አለ?›› አልኩ እኔም መሳቅ ለማቆም እየታገልኩ
‹‹ያቺም ቀን በየአራት አመቱ ስትመጣ ከማድረጋችን በፊት ምን እንደምንል ታውቂያለሽ?››
‹‹ምን ትላላችሁ?››
‹‹ወይ ጉድ እስቲ አሁን ከምኔው አራት አመት ሞላ? ጊዜው ይከንፋል ልጄ!..››

#ትዳርንከነብጉሩ

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...