Tidarfelagi.com

ታስፈሩኛላችሁ

ታስፈሩኛላችሁ አለ አስኮ ጌታሁን

ታስፈሩኛላችሁ! ሳያድግ ያስረጃችሁት የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ገብታችሁ «የበለው በለው» ቅኝታችሁን ጥኡም ሙዚቃ ነው ስትሉ ታስፈሩኛላችሁ።

«ሀገር ተዘረፈ ሲባል» ሆ ብላችሁ ስትተሙ ሳይ፣ለማስጣል የመሰለኝ መትመማችሁ አብሮ ለመዝረፍ መሆኑን ሳውቅ ታስፈሩኛላችሁ።
በጥላቻ ጄሶ የታሸ የተበድለናል ለቅሶችሁ ውስጥ ያለው የታጨ አስለቃሽነት ያስፈራኛል።

«መንደሬ፣ ሀገሬ» ስትሉ ታስፈሩኛላችሁ። መንደርን እንደ ሀገር በማየት ማህደር ውስጥ ውስጥ አደገኛ አዝማሚያ እንዳለ ይገባኛል። ሀገሬ ፍቅሬ ያለ፣ ለሀገሩ ቢገድል፣ ለሀገሩ ቢሞት አይገርምም። ይሄን እያሰብኩ ታስፈሩኛላችሁ።

ክንድ የማይጠልቀው፣ምናብ የማያውቀው የዝምታችሁ ጥልቀት ያስፈራኛል። ሰው ሞተ ሲባል፣ ከእንዴት ሞተ በፊት «የማን ወገን ነው? » ብላችሁ ስትጠይቁ ታስፈሩኛላችሁ።
ከነፃነት ቀድሞ፣ ከፍትሕ ቀድሞ፣ ከተጠያቂነት ቀድሞ፣ ሸረኛ እጆች ለቸከ ቀናችሁ መጫወቻ የሰሩት በክልላችሁ ቋንቋ የሚያወራ አሻንጉሊት ይበልጥ ሲያማልላችሁ ሳይ ታስፈሩኛላችሁ።
ብቸኛ መብቴ እሱ ይመስለኛል። አያያዛችሁን መፍራት። ከስርቀተ ፀሐይ፣ እስከ ግብኣቷ
ከማለዳ ውለደት እስከ ሞቷ… የእርገጥ እርገጥ አረማመዳችሁን በስጋት መሰለል… መብቴ ነው። መብቴ ባይሆንም ፍርሃቴን መጫን መብታችሁ አይደለም።
ታስፈሩኛላችሁ!

ላለፈ ዘመን ቤተመቅደስ አቁማችሁ፣ በዘመኑ ሞኝነት የሞቱት ሰዎች ሳይበቁ ያን ዘመን የተናገረን በጠላት መዝገብ ላይ ከትባችሁ «ያንተን አይነቱን፣ ማርገፍ ነው ጥርሱን» እያላችሁ ደማችሁ ሲሞቅ ታስፈሩኛላችሁ።

ድልድይ እንስራ ሲባል እሺ ብላችሁ ወጥታችሁ በያዛችሁት አካፋ እና ዶማ ገደሉን ይበልጥ ስታሰፉት ሳይ ታስፈሩኛላችሁ። ሳትነጋገሩ ለመጠላላት መግባባታችሁ ውስጥ ያለ ጥሬ ስጋ(ዕውቀት) እየመገባችሁ ያፋፋችሁት መገፈታተር ያስፈራኛል።

በደም ፍላት እና በስሜት ሙላት የሚነፍስ ወሬያችሁን እየሰማሁ ታስፈሩኛላችሁ።
በነዚህና ባልጠቀስኳቸው ብዙ ምክንያቶች ታስፈሩኛላችሁ።

በሰው ሀገር የስደት ወለላችሁን ተሻምታችሁ እየላሳችሁ፣ ቀይ ደም ፍላት በተነከረ ትምክህት «ከክልላችን ይውጡ» እያላችሁ ስትፈሉ በጣም ታስፈርኛላችሁ። እናተን መፍራት እየደከመኝም፣ከቀድሞው የወፈረ አስፈሪ ስህተት ለመስራት አትሰንፉም። ባለመስነፋችሁ ውስጥ ሌላ የፍርሃት ሾላ ይዘንብብኛል።
ከዛስ?
«ዝም ባይ ጭምት ነው የአሰግድ ልጅ፣
ሳይወድ አስገድደው ያስወሩታል እንጂ»
ብሎ መዝጋት 🙂
8
9
10
እልፍ ጊዜ ታስፈሩኛላችሁ!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...