Tidarfelagi.com

ታሪክን የሗሊት!

ከእለታት አንድ ቀን፤ የሺዋ ሃያላን፤ ጭንቅ እማይችለውን ፤ሁሌም take it easy የሚለውን ፤ልጅ ኢያሱን በካልቾ ብለው ፤ከስልጣን ካባረሩ በሗላ የምኒልክን ልጅ ዘውዲቱን ዙፋን ላይ ዱቅ አደረጏት ! ተፈሪ መኮንን የተባለውን ጎረምሳ መስፍን ደግሞ “አልጋወራሽ” ና “እንደራሴ” የሚል ማእረግ ሸልመው፤ ወረፋ እንዲጠብቅ አደረጉት፤ አይዞህ ቀስ ብለህ ትደርስበታለህ ብለው ትከሻውን መታ መታ አድርገው አረጋጉት:: ተፈሪ ዘውዲቱ እስክትሞትለት ሊታገስ አልቻለም፤ ተቅበጠበጠ! በመንግስቱ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ሆነ፤ ብዙ ሳይቆይ በንግስቲቱ እና በአልጋወራሹ መካከል የስልጣን ፉክክር ተጀመረ! መንግስት በዜድና በተፌ መሀል ተከፈለች፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደፈረደበት በሁለቱ ጉልቤዎች ብጥብጥ የሚመጣውን መዘዝ በስጋት እየጠበቀ ተቀመጠ::

ዜድ እንደ እቴጌ ጣይቱ ብልጥ አልነበረችም፤በርግጥ የምኒልክ ዘመዶች እና አርበኛዎች ከጎኑዋ ነበሩ፤በዚያ ላይ የምኒልክ ቀጥተኛ ወራሽ ነኝ ፤ሰፊው ህዝብም ከኔ ጋር ነው ብላ ተዘናግታለች፤

ተፌ በበኩሉ ቀጥተኛ ወራሽ አይደለም፤ ጉድለቱን ያውቀዋል!! ስለዚህ እንቅልፉን ሰውቶ ጉልበት በመሰብሰብ ተጠመደ፤ ካባቱ የወረሰውን ሀብት በመጠቀም የዘውዲቱን ወራሾች ማስኮብለል ጀመረ፤የንግስቲቱን ብዙ አሽከሮች ሰላይ አድርጎ መለመላቸው፤ ወጣቶችን አብዛኛው ሰራዊት ከጎኑ ማሰለፍ ጀመረ፤

አልፎ አልፎ የዘውዲቱ አሸከሮች ተፈሪን ዋጋውን ለመስጠት መሞከራቸው አልቀረም ፤ ተፌ ሙከራቸውን በተደጋጋሚ አከሸፈ፤ ብዙ ሳይቆይ ተፈሪ የበላይ ሆኖ ወጣ! የዘውዲቱን ቅንጥብጣቢ ስልጣኖች ሳይቀር ቀማት፡፡

” ስልጣን፤(power ) በዙርያው ያለውን ካልጠቀለለ በቀር አርፎ አይቀመጥም” ይላል የአልቦ- መንግስቱ ሊቅ ሩዶልፍ ሮከር፤ የተፈሪ የፈረስ ስም ጠቅል መሆኑ አለምክንያት አይደለም!

ቀሰ በቀስ የዘውዲቱ ስልጣን የይስሙላ ሆነ! ደግሶ ከማብላት እና ቤተክስያን ከመሳም ውጭ የረባ ሞገስ ያለው ተግባር የምታከናውንበት አቅም አጣች! ምንም አይነት የመንግስት ስልጣን የሌለው ርእሰ መንግስት ሆና ተቀመጠች፤ ይህንን የታዘበው የይድነቃቸው ተሰማ አባት አዝማሪ ተሰማ እሸቴ በልቡ እየሳቀ ፤የሚከተለውን ነጠላ ዜማ ለቀቀ!

“አዳራሽ ቁጭ ብላ፤ስታበላ ጮማ ስታጠጣ ጠጅ
ስእል ትመስላለች የምኒልክ ልጅ”

the morale of the story

ስል እንጂ ስእል አትሁን!

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...