Tidarfelagi.com

ታሪክን የሁዋሊት

በዘመነ የጁ በ1837 ዓም ግብፆች በገዳሪፍ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ገብተው ነበር፤ በጊዜው የደምቢያ ገዥ በነበሩት ደጃዝማች ክንፉ የተመራ የኢትዮጵያ ጦር ወራሪዎችን በመደምሰስ ድል ተቀዳጅቱዋል ፤ እንጦኒዮስ ደአባዲ የተባለ መንገደኛ መዝግቦ ያስቀመጠው የጥንት ግጥም ስለጦርነቱ የሚከተለውን ይተርካል፤

‘የረጀባ ተዝካር አወጣነ ብያ
አምስት መቶ ታርዶ ቱርክና ሻግያ
የመዩ ጎራዴ ጥቁር የነበረ
እየቀላ ሄደ ቱርክ እየመሰለ‘

“ረጀባ “ ከመጋቢት አስራሁለት እስከ ሚያዝያ አስራ ሁለት ያለውን ጊዜ የሚወክል የአረብኛ አቆጣጠር መሆኑን ሊቁ ብርሃኑ አበበ ነግረውናል! ጦርነቱ የተደረገው በሚያዝያ ወር ውስጥ እንደሆነ ይገመታል፤ ስንኙ እንደሚተርከው በጦርነቱ ውስጥ አምስት መቶ የግብፅ እና የሱዳን ወታደሮች ተደምስሰዋል፤ ወይም በገጣሚ/ዋ አገላለፅ ለተዝካር ማውጫ እንደቀረበ ፍሪዳ ታርዱዋል ! የቀድሞ አበሻ በመልክ ቀላ ያሉትን አረቦችን በደፈናው “ቱርክ “ብሎ ይጠራል ! ጥቁር ሱዳኖች ደግሞ” ሻግያ “ በሚል ስያሜ ይጠሩ ነበር ፤ ጎጃሞች በአፄ ዮሀንስ አራተኛ ዘመነ መንግስት ደርቡሽን ለመግጠም በዘመቱ ጊዜ “ያንን ሻግያ እንደ ዱባ እየወጋን ጊጤ መጫወቻ እናደርገዋለን” ብለው እንደፎከሩ አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ መዝግበውታል፤ (ጊጤ=dartboard )

“መዩ” (መይሳው ሲቆላመጥ) የደጃዝማች ክንፉ የፈረስ ስም ነው፤ እየቀላ ሄደ የሚለውን ህብረቃል ሰሙን “ቀይ እየሆነ “ ማለት ሲሆን ፤ወርቁን ለታከለ ኡማ ትቸለታለሁ፤
ለማንኛውም በመቶ ሰማንያ አራት አመት በሁዋላ አያቶች የገጠማቸው ፈተና ተደቅኖብናል፤ ድልና ሰላም ከኛ ጋር ይሁኑ !

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...