Tidarfelagi.com

ተአምረ መኪና

(ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ )

ወደ ረከቦት ጎዳና የሚወስደኝን አውቶብስ እየጠበቅሁ ነው። አውቶብሱ ከመድረሱ በፊት ከ’ፋኖቼ አንዱ በዚህ ካለፈ ሊፍት ይሰጠኛል ብየ ተስፋ አረግሁ። ፌርማታው፣ በጎዳና አዳሪዎች ሽንት ጨቅይቷል። እና የቆምኩበት ቦታ ለfan ሳይሆን ለጉንfan የተጋለጠ መሆኑ ገባኝ።

ዙርያ ገባውን ስመለከት፣ የሆነ የቦርጭ ወረርሽኝ በከተማው የገባ መሰለኝ፤ አልፎ ሂያጁ ሁሉ ቦርጩን በየአይነቱ እያስጎበኘኝ ያልፋል ፤ ትልቅ ቦርጭ-ትንሽ ቦርጭ- ተርዚና የምታክል ቦርጭ-ገና በንድፍ ደረጃ ያለ ቦርጭ-በጃኬት ውስጥ ያደፈጠ መካከለኛ ቦርጭ- የካቦርትና የጋቢ አፈና ያልበገረው የለየለት ቦርጭ-እንኳን በጂም ፣በዲማሚት የማይናድ ቦርጭ። ወዘተረፈ ቦርጭ።

አንዲት ዘናጭ ቶዮታ መጥታ ተፊትለፊቴ ቆመች። የመኪናይቱ መስታወት ፣ጣይ እንደነካው ጉም ገለል ሲል፣ የትየ ሰርኬ ፊት ብቅ አለ። እትየ ሰርኬ ያብሮ አደጌ የብጡል እናት ፣ብሎም የስድስትኛ ክፍል ያማርኛ መምህርቴ ናት።

ገና ስታየኝ በነገር ጠመደችኝ።

“አሁንም በግርህ ነው የምትሄደው?”

” ታድያ በደረቴ ልሂድ እትየ ሰርኬ?!”

” አጅሬ ብጡል ሶስተኛ መኪናውን በቅርቡ ገዛ ። የተባረከ ልጅ! አንተ ግን ዛሬም ሸገርን በርካሽ ጫማ ታጥናታለህ”

ሁሌም ፣የሷ ልጅ ከኔ የተሻለ ሰው መሆኑን ነግራ ልታሸማቅቀኝ ትፈልጋለች።

” እኔ በግሬ የምሄደው ለድርሰት ስራ ስለሚያመቸኝ ነው”አልኩ።

እትየ ሰርኬን ስስ ብልት አውቀዋለሁ። ( አንባቢ ሆይ !እዚጋ ‘ስስ ብልት ‘ስል ደካማ ጎን ለማለት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም ) ። እትየ ሰርኬ ስለድርሰት ሳወራ እንደምትበሽቅ አውቃለሁ። ልጇ ብጡል ስመጥር የድርሰት ሰው እንዲሆን ትፈልግ ነበር። በርግጥ ልጅ እያለን፣ ብጡል ኦክስጅን ስቦ ፣ በካርቦን ዳይኦክሳይድ ምትክ ፣ስንኝ የሚያስወጣ ፍጡር ነበር። “የከተማው ህዝብ ወደ ስቴድየም የሚጎርፈው ኳስ ለማየት ሳይሆን የብጡልን የጭፈራ ግጥም ለመስማት ነው ” ይባል ነበር ያኔ።

እዚህ ላይ፣ እትየ ሰርኬ ፣ የልጅዋን የጭፈራ ግጥም ያማርኛ ማስተማርያ አድርጋ ታቀርብልን እንደነበር ብጠቁም አጋነንክ እባል ይሆን?

“ተማሪዎች!
አይቀረደድም፣ ድፎ በጎራዴ
የበረኛው ደረት ፣ቀዳዳ ነው እንዴ?!

በሚለው የብጡል ታፈረ ግጥም ውስጥ ቤት መድፍያውን ለይታችሁ አውጡ”

ብጡል የሲያድግ የተዋጣለት የንግድ ሰው ሆነ። ቦሌ ሚካኤል ግድም ዝነኛ ምግብ ቤት ከፍቷል። እስካሁን የግጥም ችሎታው ሙሉ በሙሉ ጥሎት እንዳልጠፋ ለማሳየት፣ የምግብ ዝርዝሩን በስንኝ አሰናድቶታል።

1 ) አሪፍ የቋንጣ ፍርፍር፣
የራብዎትን ቅስም የሚሰብር
ዋጋው መቶ አምሳ ብር፤

2 ) ቆንጆ ቅቅል
አምሮትዎን ፣የሚነቅል
ብዛቱ ፣ እንደንጉስ ግብር
ዋጋው መቶ ሰባ ብር።

እያለ ይቀጥላል።

እትየ ሰርኬ ፊቷን አኮማትራ፣”ድርሰት ድርሰት እያልክ በባዶ ኪስ አትመፃደቅብኝ ። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ግጥም ሳይሆን ዳቦ ነው” ብላ ተፈላሰፈች።

“ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም!” አልኩ:

“ልክ ነህ ። ፓስታና ሩዝም መብላት አለበት”

እትየ ሰርኬ ፣ የመኪናዋን ጭስ አከናንባኝ ስትሄድ ስለመኪና ታምር ማሰብ ጀመርኩ።

2

በህይወቴ “የፊታውራሪ አሰጌን ሌጋሲ” የሚያስቀጥሉ ብዙ ወንዶች ገጥመውኛል። ይሁን እንጂ ፣ የምኡዝንና የካሳን ያክል የሴት ብልትን የሚያመልክ ሰው አይቸ አላቅም። (አንባቢ ሆይ! እዚጋ ‘ብልት ‘ የሚለውን ቃል ‘ደካማ ጎን’ ብለህ እንደማትፈታው ተስፋ አለኝ”)

ምኡዝና ካሳ ፣ በቀድም ለት፣ እልም ያለ የቦዘኔ ውድድር ውስጥ ገቡ። በውድድሩ መሰረት፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ብዙ የሴት ስልክ ቁጥር የተቀበለ ሰው አሸናፊ ይሆናል። ምኡዝ ፣ረከቦት ጎዳና ግርጌ ከሚገኘው ሲኒማ ቤት በር ላይ ይቆምና ወንድ ቀጥሮ የቀረባቸውን ፣ወይም የዘገየባቸውን ፣ደብዘዝ ያለ መልክ ያላቸውን ሴቶች ጀንጅኖ ስልክ እየተቀበለ ማከማቸት ጀመረ። በጠበሳ ጉዳይ ላይ፣ ምኡዝ ከመልክ መልክ አያበላልጥም፤ ” አስቀያሚ እይታ እንጂ አስቀያሚ ሴት የለም” ይላል። )

ያም ሆኖ፣ በውድድሩ፣ ካሳን ማሸነፍ አልቻለም።

ካሳ(ካሳ-ኖቫ) ስልክ ለመሰብሰብ የተከተለው ስልት ከምኡዝ የተለየ ነው። ካንድ ሀብታም ወዳጁ ፣በከተማው ውስጥ ብርቅ የሆነ ሬንጅሮቨር ተከራይቶ ፣ከመኪናው ጀርባ ላይ” በአነዳዴ ላይ አስተያየት ካለዎት በዚህ ቁጥር ይደውልልኝ “የሚል ፅሁፍ ለጠፈ። በመኪናው ትንሽ ከተመላለሰበት በሁዋላ ከየማእዘኑ ፣ ከሁለቱም ፆታ፣ አስተያየት ይጎርፍለት ጀመር። ካሳ፣የወንድ አስተያየት ሰጭዎችን ስልክ ቸል ብሎ የሴቶችን ቁጥር መዘገበ።

አውቶብሱ ስለመጣ ወጉን በሁዋላ እቀጥላለሁ።

በቅርቡ፣ ከቻይና በርዳታ የገባ “ዝሆን” የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ከፊት ለፍቴ መጥቶ ቆመ። ነገረ ስራው ሁሉ የተለየ ሆነብኝ። በሩን ለማግኘት አውቶብሱን ሁለት ጊዜ መዞር ነበረብኝ። ከጎማው እስከ በሩ ያለውን ርቀት ስመለከት አልቅስ አልቅስ አለኝ። መቸም ሹፌሩ ጋቢና ውስጥ የገባው በክሬን ተንጠልጥሎ መሆን አለበት።

ወደ ላይ አንጋጥጨ ስቁለጨለጭ፣ ወያላውና ሹፌሩ ጉድጏድ ውስጥ እንደወደቀ ፣ እድለቢስ ፍየል ፣ጋማየንና ጆሮየን ይዘው፣ተጋግዘው ወደ ላይ ጎተቱኝ።

“በህይወቴ እንዲህ ያለ ለተሳፋሪ የማይመች አውቶብስ ገጥሞኝን አያውቅም!” አልኩኝ፣የምመረኮዝበትን ፍለጋ ፣አየሩን እየዳበስኩ።

“ሲጀመር ለተሳፋሪ ምቾት ተብሎ የተሰራ አይደለም ጀለሴ!” አለችኝ ትኬት ቆራጯ።

” ማለት?!”

” የቻይና መንግስት ፣ለማረሚያ ቤቶች በርዳታ ያበረከተው የእስረኛ ማመላለሻ አውቶብስ ውስጥ ነው ያለኸው። በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ህዝብ እንዲያመላልስ ተመድቦ ነው”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...