Tidarfelagi.com

ተሰቅለን ነበር…ወረድን!

ሳምን፣በእድሜው ማምሻው መቋሚያ ይዞ፣ቅድመ ግብዓተ መሬቱን እንደሚማጠን ሰው አልነበርኩም። ቀንበጥ እድሜያችን ገፅ ላይ የተፃፈው እየሱስ ብቻ ነበር።ጌታ ሆይ ብሎ ጀምሮ፣ጌታ ሆይ ብሎ የሚቋጭ (እንዲያውም አይቋጭም ነበር)…የሚዘልቅ!
,,,
መቁረቢያ እድሜው ሲደርስ፣ «የእግርህ መርገጫ የሆነችው ምድር ላይ ስትመጣ፣እኔ ላይ እርገጥ» ብሎ እንደሚንጋለል የሰፈሬ አዛውንት አልነበርኩም። ሁሉ የገባኝ የመሰለኝ በልጅነቴ ነበር። ከሰኞ እስከ ሰኞ ሰታሪ የቤተክሲያን ደንበኛ ነበርኩ!
,,,
እያንዳንዱ ድርጊቴ ውስጥ ፈጣሪን ያለማስቀየም ጥንቃቄ ያደፈጠበት ጊዜ ነበር። የውብ ሴት ኋላ ማየት፣ከመንፈሳዊ ህይወት ወደ ኋላ መቅረት መቅረት መስሎኝ ነበር።ክብር የማይገባቸው ታላላቆቼን ጭምር ለማክበር ተፍጨርጭሬያለሁ፣ እሱን ለማስደሰት።
,,,,
ተሰቀለልህ ሲሉኝ ድምፄ እስኪዝል ዘምሬያለሁ። መዳፌ እስኪግል አጨብጭቤያለሁ። እግሬ እስኪደክም( መቀመጥ መንፈሳዊ ድክመት መስሎኝ) ቆሜ አስቀድሻለሁ። በዚህ ሁሉ አልረካም ነበር። ትንሿ መንፈሳዊ ማፈንገጥ፣ከፈጣሪ እንዳቀያየመኝ አስባለሁ። መሳት፣መሳሳት ሰዋዊ ሁነት መሆኑን እዘነጋለሁ። ሰው ማለት ለኔ፣ የሃጢያት ወንዝ አቋርጦት የሚያልፍ ካናል ነበር። እኔም ለራሴ እንደዛው ነበርኩ። በምህረቱ ያልጠፋን፣በበደላችን የከፋን ሆኖ ይሰማኛል።
,,,
የእግዜር ቤተመቅደስ ነህ ብለውኝ፣ የገዛ እራሴ ላይ እግዜር የሾመው ጥበቃ ነበርኩ። ፀሎቴ ሁሉ፣ «እንደ ምህረትህ እንጂ፣እንደ በደሌ አትይብኝ»በሚል ሃረግ የተዘመዘመ ነበር። አስር በጎ ስራዬ፣ሩብ በማትሞላ ሃጢያቴ የሚፈረካከስ ይመስለኝ ነበር። ከዛ በቀደመው ጊዜ ደግሞ፣ክርስቶስ ራሱ ኦርቶዶክስ ይመስለኝ ነበር።
አቻዎቼ ከሚቋምጡለት «አዲስ ፊልም ቤት»ይልቅ ሰንበት ትምህርትቤት ይማርከኝ ነበር። ያልገባኝን ጥቅስ እና መዝሙር ሳንቸለችል ነበር። ነበር የሚለው ቃል ደስ ይላል 🙂
,,,,,
ቆይቶ፣ሳላየው መንፈሱ የሚቀጣኝ ጌታ፣ «ኳስ ስትጫወቱ አቧሯ አቦነናችሁ» ብሎ ለሰዓታት በቁጭ ብድግ፣ በፑሽ አፕ… ከሚቀጣን ደረጄ ተመሳሰለብኝ።ደረጄ፣ከውትድርና የተመለሰ የሰፈራችን ሰው ነው፤ውትድርናው ግን መለስ ያላለለት። ሰፈሩ «የታባታቸው በላቸው»ብሎ የተስማማለት ኢምንት ያህዌ 🙂
!
አሜን እንጂ፣ለምን አያውቀኝም ነበር።ዓለምን በዝሙት ምክንያት ያጠፋ ጌታ፣ሎጥ ከልጆቹ ሲወልድ(ሲወልዱ) ዝም ብሎ ይመለከት ነበር ሲሉኝ፣ዝም ብዬ ተቀብያለሁ።የድሮ እባብ ያወራ ነበር ሲሉኝ፣አምኛለሁ። ጥርጣሬ ነክቶኝ ሲያልፍ፣ «የሚፈትነኝን ሴጣን አብርልኝ»ስል ተንበርክኬ ማልጃለሁ።እግዜር እረኛዬ መሆኑን እንጥሌ እስኪነድ ዘምሬያለሁ። ሲገባኝ፣
«እግዜር እረኛ ነው፣ብለው ሲናገሩ፣
በግ ነህ፣ነው ሚስጥሩ» ብያለሁ። ይቅር ይበለኝ 🙂
,,,,,
ኤቲስትነት እንደ ሮም ነው።በአንድ ቀን አይገነባም፣ገንብተው ሲገቡበት ግን ዓለም ነው።እርግጥ ገብቶ የሚቃዥ አይጠፋም።እኛን የሆነን ይሁነው 😉 ዛሬ፣ ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት መልካም መሆን እንደሚችል ይገባኛል። we are good without God እንዳሉት አበው። የሰው መሆንን ገደብ እረዳለሁ።ያ በፊት አይገባኝም ነበር። ቅድስናው ላይ ባንኖረበትም፣አድማስ ግንባሬን እስኪገጨኝ ድረስ ከክፋት እሸሻለሁ።
,,,
ቀደም እድሜዬን የሞላው፣ መዳፍ ዛሬ የመጨበጡ መቁት እንኳ የለም። ዘለላ ጭንቀት የለብንም። እነሆ ለዘላለሙ፣አሜን!
ለሁላችሁም መልካም ስቅለት።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...