Tidarfelagi.com

‹‹ቦግ – እልም›› 

ቅድም ባንክ ሄጄ ነው። የሚመለከተኝን ቅፅ ሞልቼ ከደብተሬ ጋር ወረፋ አስያዝኩና ሊሞላ አንድ ሰው በቀረው አንዱ አግዳሚ ላይ ተቀመጥኩ። ከመቀመጤ መብራት ሄደች።

‹‹ኤዲያ! ምን ጉድ ነው …አሁንማ ባሰባቸው….›› አሉ አጠገቤ የተቀመጡት ሰውዬ። ሙሉ ልብስ ካለ ከረቫት የለበሱ፣ ባርኔጣ ያጠለቁ ስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የምገምታቸው ግርማ ሞገሳም ሰውዬ ናቸው።

እንኳን ከሰሞኑ ብሶበት በደህናውም ጊዜ ማንም ኢትዮጵያዊ መብራት ሃይልን የማውገዝ አጋጣሚን ሊያባክን አይገባምና ቀበል አድርጌ፣ ‹‹እውነት ነው…የሰሞኑማ ባሰ! ምን እንደነካቸው እንጃ!›› ብዬ ንጭንጭ አዋጣሁ።

በድጋፌ የተደሰቱ መስለው በደንብ ዞር ብለው ትኩር ብለው አዩኝና ድምጻቸውን ከቅድሙ ለመቀነስ ሳይሞክሩ ፣ ‹‹ሳቦታጅ እኮ ነው…! ሳቦታጅ!›› አሉኝ።

የማድመጥ ፍላጎቴም ሳቄም አንድ ላይ መጣና መልሼ እያየኋቸው ‹፣እንዴት…የምን ሳቦታጅ?›› አልኩኝ።

ከዚህ በኋላ አስር ለሚጠጋ ደቂቃ የተፈጠረው ውይይት አይደለም። ውይይት ስላልነበረ ራሴን እየነቀነቅኩ፣ አፌን ከፍቼ እሰማቸው እንደነበር ብቻ ልንገራችሁና በሰላ ምላሳቸው፣ በተባ አንደበታቸው ያተቱልኝን እንደወረደ እንካችሁ!

‹‹አየሽ ልጄ…የዛሬ ልጆች ቂላቂል ናችሁ…ከናንተ ያለፈ ነገር መች ትሰሙና መች ታዩና…ይሄማ የለየለት ሳቦታጅ እኮ ነው…እግዜር በቃል ኪዳን ምድሩ ተአምሩን ሊሰራ ጊዜው ቢደርስ…የቃል ኪዳን ልጃችንን በስንት ለቅሶ እና ዋይታ ቢልክልን… ይኸው ጥቅሙ የተነካው አድመኛ አላንቀሳቅስ አለው….ልፋቱን ሁሉ የእምቧይ ካብ…ድካሙን ሁሉ ረብ የለሽ ለማድረግ ቀን ከሌት አልተኙለትም…
የኔ ልጅ…አላወቁም እንጂ እሱ እኮ ከላይ የተላከ ነው…አንዲያጠፋ እንጂ እንዲጠፋ አልተመረጠ…ቢሆንም መች ተኙለት….በፍቅር ኑ…እንስማማ ሃገር እናሳድግ ቢል መች ተዉት! ማገዙ ቢቀር መች ይሁንልህ ያውልህ አሉት….
ምድረ ተባይ….! ተባይ ናቸው መቼስ….ያሳዝነኛል…ስንቱን ይቻለው…ይህን ሲደፍን ሌላ ቀዳዳ…አንዱን ሲለው አንዱን…ባተሌ ሊያደርጉት እኮ ነው ሃሳባቸው…ግን አይሳካላቸውም ልጄ…ለምን በይኛ! አዎ…ለምን ማለት ጥሩ…ከላይ ነዋ የመጣው! በፀሎት ነዋ የወረደው….
…..ባታነቢ ጫፍ ጫፉን ሳትሰሚ አትቀሪም መቼም.የዛሬ ልጆች አታነቡም እንጂ ትንቢቱ እኮ መቶ አመት አልፎታል….እሱ ሲመጣ እልቂቱ ሁሉ በርዶ ብልፅግና ይመጣል…ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የሚደርስባት የለም ይላል እኮ…ጃፓንን እናስከነዳለን…አሜሪካንማ ከየት አባቷ ደርሳብን! ማተብ የለሽም….ክርስትያን ነሽ ልጄ? …. የተፃፈ ነው የምነግርሽ…ምን ቢውተረተሩ የእሱ ቃል ዝንፍ አይል እንግዲህ! አለቀኑ መች ሰጠንና….

እኔማ ትላንት ያለው ነው ደስ ያለኝ…. ቆፍጠን አለና፣….‹‹አዝዣለሁ›› አለ…ልብ በይ! እጠይቃለሁ እንዲህ እንዲያ አላለም…አ-ዝ-ዣ-ለ-ሁ….አለ …መለማመጡን ተወ! እንዲያ ነው እንጂ! …
…አየሽ እኛ ፍቅር አይወድልንም እኮ…የአፍሪካ ህዝብ በአንዱ እጅ ጨብጦሽ ባንዱ ድንጋይ ይስላል…ብቻ አሁንም መጠንቀቅ አለበት…ተስፋ አየን ሲሉ ጨለማ ሊጨምሩን አይደል….ተባይ ናቸው እነዚህ….ደሞ። ግሮሰሪ ምን ብለው ይነተርኩኛል …እንዲህ ካለማ ክፉ ሊሆን ነው! ዞሮ ዞሮ እሱስ መች ዲሞክራት ሆነ ምንትስ….

….አይ ወግ እቴ! ራሳቸው…ለመስደብና ለመክሰስ ካልሆነ አፋቸው የማይከፈት ሰዎች አንድ ቀን ተዉ በቃ…እርምጃ እወስዳለሁ ቢል ክፉ አድርገውት ቁጭ! ታዲያ ዘለእለም እሹሩሩ ሲል ሊኖር ነው እንደ እናት ልጅ…? ምነው…! ትእግስት ሲበዛ ፍርሃት ይመስላል…አሁንም ግን መmንቀቅ ይበጃል። ንቁ ሊሆን ይገባል…እሱ አንድ ነገር ቢሆን ይህች ሃገር እንጦሮጦስ ነው የምትገባው….ደግሞ ይሄ ላይ ላይ ማየቱን ትቶ ታች ያለውን ሴል መምታት አለበት…አዎ…ይሄ በየቀበሌው ተሰግሰግስጎ ሰላም የሚነሳውን…እሱን ነው መምታት…ይሄ መብራቱም የነሱ ስራ እኮ ነው…ውሃ እንኳን እሱ ከመጣ በሽ ነው….ብቻ ቶሎ ብሎ እነሱን ማጥፋት ነው ልጄ…ቆፍጠን ማለት…አሳ ነባሪ ጥርስ መሃል ሆኖ ፍቅር የለም…ሳያጠፉት ሴሉን ነው መምታት….ብቻ ግን ኢትዮጵያ ምንም አትሆንም የቃል ኪዳን ሃገር ነች…እሱም የቃል ኪዳን ልጇ ነው….››

ጨለማው አብቅቶ መብራቱ መጣ።

ተሰናበትኳቸውና ወደ መስኮቱ ስሄድ ጭንቅላቴ ከብዶኝ እንደ መንገዳገድ አደረገኝ።

በሕይወቴ በሃገሬ ጉዳይ በአንዲት ቅፅበት እንዲህ ፈርቼም፣ በተስፋ ተሞልቼም አላውቅም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...