Tidarfelagi.com

‹‹ብንሄድ ብንሄድ- አንደርስም ገና ነው››

ቴዲ አፍሮ ‹‹ቀና በል›› የሚለውን ሙዚቃውን በለቀቀ ማግስት ለስራ ጉዳይ ጎረቤት ሃገር ተላክሁ።
ከአየር ማረፊያው ወደ ሆቴሌ የሚወስደኝ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ብዙዎችን ያላቀሰውን ሙዚቃ በጥሞና ለማዳመጥ የጆሮ ማዳመጫዬን ከስልኬ አገናኘሁ።
ልክ ቴዲ ‹‹አርማሽ ይውለብለብ ከደጄ-ልቤ ናፍቆሻል ወዳጄ›› ብሎ መዝፈን ሲጀመር ‹‹ቪንሰንት›› ነኝ ብሎ የተዋወቀኝ ትሁት ሹፌርም መኪናውን ማንቀሳቀስ ጀመረ።

ብዙ አልቆየም፤ ቪንሰንት በሙስና በተበላው የከተማዋ ጎዳና ላይ ሰውነቴን እየናጠ ሲወስደኝ፣ ቴዲ ደግሞ ስለት ባላቸው ግጥሞቹ እና አንጀት በሚቦረቡር ዜማው ሁለንተናዬን በስሜት ያናውጠው ጀመር።
ይሄ ሰውዬ …ስንኝ በሰንኝ ላይ እየደረበ፣ ዜማን ከዜማ እየቀጣጠለ…
አዲሱን ከአሮጌው፣ ዘንድሮን ከድሮ እያደባለቀ….
በአንድ ጊዜ ቁስሌ ላይ ጨውም የሚነሰንሰው፣ እንጨትም የሚሰደው እንዴት ነው?
በተመሳሳይ ጊዜ እያከመ የሚያሳምመኝስ በምን ያለ ምተሃት ነው?
በተስፋ የረሰረሱ ስንኞችን በሙሾ ዜማ አድርጎ የሚሰጠኝስ ምን በሚሉት ስሌት ነው?
እውነቴን ነው። ሁለመናዬ ሲታወክ፣ ብዥም ዥውም ሲልብኝ ተሰምቶኛል።
ቪንሰንት ከስግብግብ ሹፌሮች ጋር እየተሸቀዳደመ መኪናዋን አፈር ድሜ ያስበላታል።
ቴዲ የማልጠግባት ሃገሬን ስም እያነሳ ሆዴን ያንቦጫቡጫል።
ጉድ የፈላው ግን
‹፣እኛስ ከመንገድ ላይ- ጠፍተን መች አወቅነው
ብንሄድ ብንሄድ አንደርስም ገና ነው›› ባለ ሰአት ነው።
ልክ እንደዚያ ሲል….
ለአመታት እንዳትወጣ ብዬ ግድብ ያበጀሁለት የሚመስል እምባዬ የማላውቀውን ግምብ አፍርሶ….ከየት መጣ ሳልለው በአንድ ጊዜ ፈንድቶ ፊቴን ሲያጥበኝ፣ ያለ ይሉኝታ ጮህ ብዬ መንሰቀስቅ ጀመርኩ።
ሃገሩን ረስቼዋለሁ።
መንገዱን ረስቼዋለሁ።
መኪናውን ረስቼዋለሁ።
ቪንሰንትን ረስቼዋለሁ።

መኪናው በድንገት ሲቆምና ልጁ ዞሮ ‹‹እንዴ….ምን ሆነሽ ነው?›› ሲል ነው ከቀልቤ የተመለስኩት።
ዳሩ ቀልብ ገዛሁ እንጂ፤ ማንባት ማቆም ግን አልቻልኩም።
ለዘመናት የገነባሁት የእምባዬ ቅጥር የፈረሰ፣ አይኖቼ በእምባ ብዛት ደክመው ካልጠፉ ለዘልአለም የማለቅስ እመስል ነበር።
‹‹ምን ሆነሽ ነው?›› አለ ቪንሰንት እንደገና። ‹‹ምኗን ጉድ ነው የጫንኩት ዛሬ ደግሞ›› እንደማለት።
ምን ልበለው?
ሃገሬ ታማ ፈውስ ርቋት ነው? ለቁስሏ መድሃኒት አጥታ ጣር ይዟት ነው?
በዘፈን ወጌሻ እያመመኝ ታሽቼ ነው? በዜማው ያለባበስኩትን አውጥቶ ዘርግፎብኝ ነው?
ወይስ፣ በቀላሉ….ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ነው?
ምን ልበለው?
‹‹የግል ጉዳይ ነው። ይቅርታ ካስደነገጥኩህ›› አልኩት።
ያላመነ በሚመስል ሁኔታ መንዳቱን ቀጠለ ። ዝም ብሎ የሚወርደውን እምባዬን በአንገት ልብሴ እያባበስኩ ሙዚቃዬን ልቀጥል ስከጅል ግን፤
ቪንሰንት ‹‹ኢትዮጵያዊ ነሽ አይደል?›› አለኝ።
በደህና ጊዜ ቢሆን እንዴት አወቅህ…ምናምን የሚል የወሬ ቱባ እየተረተርኩ መንገዱን ለመጨረስ እተጋ ነበር።
‹‹የዶርዜ ጥበብ የአንገት ልብሴን አይተህ ነው? የላልይበላ መስቀሌን ተመልክተህ ነው? ሃይለስላሴን ስለምታውቅ ነው ?…ሃይሌ ገብረስላሴን ስለምታደንቅ ነው….? አይነ-ውሃዬ ነው?›› እያልኩ።
አሁን ግን ከቴዲ ምት የተረፈኝን ጉልበት ሰብሰብኩና ‹‹አዎ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ብቻ አልኩት››
‹‹ኦ…ኢትዮጵያ ሲቪል ዋር አለ አይደል…ሲ ኤን ኤን ላይ……?›› ብሎ ረጅም ወሬ ሊያወራኝ ሲጀምር ግን ከቪንሰንት ጋር በዚህ ሰአት፣ በዚህ ጉዳይ ለማውራት እንደማልፈልግ ስላወቅኩ በጨዋ ደንብ
‹‹ይቅርታ…የሆነ ነገር እየሰማሁ ነው…በኋላ እናወራለን›› ብዬ ወደ ቴዲ ተመለስኩ።

ግን….የቪንሰንትን አፍ ለጉሜ የቴዲን ልክፈት እንጂ….
እንዴት አወቅሽ አትበሉኝ እንጂ…በዚያች እኔ የምሆነው በጠፋኝ ቅፅበት…
ሃገሬ ትልቅ ድንኳን ፣ ቴዲ ደግሞ ሙሾ አውራጅ ሆኖ… ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ…በየዓለም ጥጉ እዬዬ የተባለ ይመስለኛል…
ለብዙ ኢትዮጵያውያን ፀሃይ ወጥታ ጨለማ ፣ መስኮት ተከፍቶ የመታፈን ስሜት የነበረ ይመስለኛል።
በዚያች ቅፅበት…በዚያች አፍታ… የጋራ ቁስላችን በሚመዘምዝ መድሃኒት እያመመን የታከመ ይመስለኛል……

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • Yeshiwas commented on October 28, 2022 Reply

    የምትፅፊው ሁሉ የሚያስተምር ሀሳብ ነው ቀጥይበት።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...