Tidarfelagi.com

‹‹ባፍሪካ የመጀመርያው የሳቅ ትምርት ቤት››

ባለፈው፣በቤተ-መንግስት መውጫ፣ በሸራተን መውረጃ መንገድ ላይ የተሰቀለ ፖስተር አየሁ፡፡ ‹‹ባፍሪካ የመጀመርያው የሳቅ ትምርት ቤት››ይላል፡፡የዘመኑን መንፈስ ከሚያሳዩ ተቋሞች ዋናው መሆን አለበት ብየ አሰብኩ፡፡በዘመኑ ዝም ብሎ መሳቅ ከባድ ነው፡፡እንድያውም በዘመኑ ከልቡ የሚስቅ ሰው ከተገኘ እንደ ስድስት ኪሎ አንበሳ በቅጽር ከልለን ልንጎበኘውና ልናስጎበኘው ይገብባል፡፡
በረንዳ ላይ ተቀምጠህ ምሳ ስትበላ ከወገቡ በላይ ሥጋ ከወገቡ በታች የመኪና ጎማ የለበሰ ተመጽዋች ወደ ጠረጴዛህ እግር እየተንፏቀቀ ቀርቦ ልመና ይሁን ትእዛዝ ባልለየለት ድምጽ‹‹አጉርሰኝ››ሲልህ እንዴት ትስቃለህ፡፡የቤት አከራይህ ከጓሮህ ያለውን የቀለበት መ…ንገድ ከራሳቸው ኪስ አውጥተው ያስገነቡት ይመስል‹‹አካባቢውን እድገት ግምት ውስጥ በማስገባት ተዛሬ ጀምሮ በኪራዩ ላይ አንድ ሺህ ብር ጨምሬያለሁ›› ብለው ሲያረዱህ እንዴት ትስቃለህ፡፡ኮሌጅ እንዲበጥስ የሰደድከው ታናሽ ወንድምህ ለራዛ ዘመቻ የወጣ ይመስል፤ባውቶብስ ሂዶ በወሳንሳ ሲመለስ እንዴት ትስቃለህ፡፡የሳቅ ትምርትቤት መስራች አቶ በላቸው ገብቶታል፡፡ሳቅ እንደ ሂሳብ ወይም እንደ እደ ጥበብ ውጤቶች በልምምድና በጥናት ካልሆነ በቀር በዋዛ የሚገኝ አልሆነም፡፡ይህ ትምርትቤት ወደ ፊት በቢኤና በፒኤችዲ ማስመረቅ ሲጀምር ሰዎች እንደየደረጃቸው ይስቃሉ፡፡‹‹ያ ሰውየ ፍርርርስ ሲል አየከው? ከበላቸው ግርማ ትምርትቤት ማስተርሱን ስለ ሠራ እኮ ነው›› የምንልበት ቀን ሩቅ አይመስለኝም፡፡

የዘመኑን ፊልሞችን አይተሀል፡፡ሁሉም በልብህም በበብትህም ገብተው ሊያስቁህ የሚደክሙ ናቸው፡፡ባለፈው አንዱን ተከታታይ ‹‹ኮመዲ›› ለማየት ከባለንጀሮቼ ጋር ከቲቪው ፊት ለፊት ቁጭ አልሁ፡፡ተዋናዩ የሆነ መናኛ ነገር ሲናገር ወይም የሆነ አድካሚ ነገር ሲያደርግ ከጀርባ ተቀርጾ የተቀመጠ ሳቅ ይለቀቃል፡፡እኔ እቴ ወይ ፍንክች፡፡አጠገቤ የተቀመጡትማ በትከሻቸው ላይ ጋቢ በመዳፋቸው ላይ ካርታ የለም እንጂ ትኩስ የጎረቤት እዝን ላይ የተቀመጡ ነው የሚመስሉት፡፡የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀልዱን ብቻ ሳይሆን ሳቁንም ለኔ ተውልኝ ያለ ይመስላል፡፡ተከታታዩን ድራማ የሚያጅበውን ተከታታይ ሳቅ ከቢል ኮዝቢ ሾው ላይ ሳልሰማው አልቀረሁም፡፡አዘጋጆቹ import አድርገውት መሰለኝ፡፡ኮንቴነር ሙሉ ሳቅ ከመርከብ ተጭኖ ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ሲገባ ይታይህ፡፡ዘመኑ ዘመነ ትካዜ አይደል!! የሳቅ ትምርት ቤት በመክፈት ባፍሪካ የመጀመርያ የሆንነውን ያክል ‹‹የሳቅ አስመጭና አከፋፋይ ››በመክፈት የመጀመርያ ብንሆን ምን ይገርማል፡፡

ባለፈው ወደ ሾላ አቅጣጫ በግሬ ‹‹ስነካው›› የጥንቱን አጫዋች ልመንህ ታደሰን አየሁት፡፡በቀይ ሻንጣ ውስጥ ጓዙን ሸክፎ ባጠገቤ ሲሮጥ ፖሊስ የሚያባርረው የኮንትሮባንድ ሸቃይ ይመስላል፡፡ልመንህ መሆኑን ለማጣራት ዓይኔን ባይበሉባየ እሽት እሽት አድርጌ ራሱ መሆኑን ቁርጡን ሳውቅ ከንፈሬን መጠጥሁ፡፡ባንድ ወቅት የሳቅ ምንጭ የነበረው ሰውየ ዛሬ የትካዜ ምንጭ ሆኖኝ አረፈ፡፡
ሳቅ የሚባለው ነገር እንደ ክቡር ዘበኛ ብርጭቆ ወይም እንደ በርኖስ የሙዝየም እቃ ሆኖ መቅረቱ ያሳስባል፡፡ደበበ ሰይፉ ይህ ታይቶት ነው መሰል እንዲህ ገጥሞ ነበር፡፡
‹‹ይበቅል ይሆን ከዚህ ጠፍ ላይ፣ከዚህ መና ከዚህ ወና
ተስፋ ማድረግን የሚያውቅ ህልው፣ሳቅን የሚያውቅ ሰብእና
….
ይበቅል ይሆን››

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • ልሳን commented on April 11, 2017 Reply

    ይበቅል ይሆን ከዚህ ጠፍ ላይ፣ከዚህ መና ከዚህ ወና
    ተስፋ ማድረግን የሚያውቅ ህልው፣ሳቅን የሚያውቅ ሰብእና፡፡ አይመስለኝም አርቴፊሻል ሳቅ በዝቷል ሳቁ እንሳቅ ሳይሆን ስቆ የሚያናድድ ሳቅ በዝቷል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...