Tidarfelagi.com

‹‹ባይተዋር›› (ክፍል አንድ)

( በቢኮዙሉ ‹‹ኦቨር ናይት ስትሬንጀር›› ላይ ተመስርቶ የተፃፈ)

ሰናይ እና ሜላት በስንት ጊዜያቸው ፣ ስንት ጊዜ ለምኗት፣ ስንት ጊዜ ተለማምጧት፣ ስንት ‹‹በናትሽ›› አባክኖባት፣ ስንት ‹‹የኔ ቆንጆ ስወድሽ››፣ ‹‹እስቲ አንዳንዴ እንኳን ያለልጆቹ እንደ ድሮው ወጣ ብለን እንዝናና›› አዝንቦባት እየጠጡ ሊያመሹ ቦሌ አካባቢ አንዱ በሚደነቁር ሙዚቃ እና በሲጋራ ጢስ የታፈነ ባር ቁጭ ብለዋል። እሱ ቮድካውን ይለጋል፣ እሷ ጣፋጭ ወይኗን ለኮፍ ለኮፍ ታደርጋለች።

ከተጋቡ 12 አመታቸው ነው፤ እራት በልተው እሱ አራተኛ ደብል ቮድካው ላይ ሲደርስ፣ እሷ ግን ያቺኑ አንዲት ብርጭቆ ወይን ታባብላለች። ልጆች ስላሏቸው ብዙ አያመሹም፤ እስከ እኩለሌሊት፣ እስከ ከሌሊቱ አስር ሰአት ሲጠጡና ሲደንሱ የማደር፣ የ‹‹ኦቨር ናይት ጭፈራ›› ዘመን ለእነሱ ካበቃ ቆይቷል። ድሮ ቀረ። ቢያንስ ሜላት በምልጃም ቢሆን ከሶስት ሰአት በላይ አታመሽም። ሁሌም ከስራ ወደቤት መሄድ፣ ጓደኞቿን እንኳን ቤቷ መቅጠር፣ በጊዜ በጋቢ ተጠቅልላ ቴሌቪዥን ፊት መጎለት የምትወድ አይነት ሴት ናት።

‹‹ኡፋፋ…..! ይሄ ሙዚቃ እስከዚህ ከጣራ በላይ መጮህ አለበት?ሰው እንዴት ብሎ ያወራል? ደግሞ የሲጋራው ጭስ….ምኑ ደስ እንደሚልህ አላውቅም እንዲህ አይነት ቦታ ማምሸት….በናትህ ወደቤት እንሂድ…እ? › ብላ ማማረር ከመጀመሯ፤ ፊት ለፊቷ፣ ከአንገቱ ብዙ ካልጎደለው የወይን ጠርሙሷ አጠገብ፣ ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠችው ስልኳ ጮኸ።

ሰናይ ሰአቱን አየ። ሶስት ሰአት ከሰላሳ አምስት።

(ማነው በዚህ ሰአት የሚደውልላት? ከቤት ነው? ሰራተኛቸው ናት? ልጆቹ ደህና አይደሉም?)

ስልኩን አንስታ ‹‹ሄሎ›› አለችና ሌላ ቃል ሳታወጣ ዝም ብላ አዳመጣ ዘጋችው።

ሁኔታዋ ግራ ቢያጋባውም ሰናይ ‹‹ማነው በዚህ ሰአት የሚደውልልሽ?›› ብሎ ሚስቱን የሚነዘንዝ፣ አምባጓሮ የሚያስነሳ በራሱ የማይተማመን ባል፣ ሚስቱም በዚህ ሰአት በሚደውል ‹‹ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት እና የስልክ ጥሪ›› የምትጠረጠር ሴት ስላልሆነች ምንም አላላትም።

በመሃል ከስልክ ጥሪው ጋር የማይገናኝ አንድ ሁለት አረፍተነገር ወሬ ካወሩ በኋላ አምስት ከማይሞላ ደቂቃ በኋላ ስልኳን አንስታ የሆነ ነገር ፃፈች። ቴክስት መሰለው።

አስር ደቂቃ በኋላ የሙዚቃውን ጩኸት፣ የወጣቶቹን ጫጫታ እና የሲጋራውን ሽታ መቋቋም ስላልቻለች ሰናይ ሂሳቡን ከፍሎ፣ ለአስተናጋጇ ጉርሻ ሰጥቶ፣ ጃኬቱን ደርቦ ወደቤታቸው ሄዱ።

ይሄ የሆነው አርብ እለት ነበር።

የዛኑ እለት ማታ ቤት ደርሰው፣ ልብስ ቀይረው አልጋቸው ውስጥ ሲገቡ ሚስቱ በዚያ ሰአት የተደወለላትን ስልክ አንስታ ከሄሎ በስተቀር አንዲት ቃል ሳትናገር መዝጋቷ ሆድ ሆዱን እየበላው ነበር።

በነጋታው ቅዳሜ ጠዋት፣ ሁሌም እንደሚያደርገው ሳሎን፣ ላፕቶፑ ላይ አፍጥጦ ከሳምንት የተረፈ ስራ ሲሰራ ፒጃማዋን እንደለበሰች፣ ጠዋት የጠበሰችውን እንቁላል እንቁላል እየሸተተች አጠገቡ መጣችና

‹‹ሰናይዬ፣ ይሄ ስልክ ዜንደሩ አልሰራም ብሎ አስቸገረኝ…እስቲ እይና አስተካክልልኝ›› ብላ ስልኳን አቀበለችው። ሜላት የቴክኖሎጂ ነገር የማይሆንላት፣ ለትንሹም ለትልቁም የእሱን እርዳታ የምትጠይቅ አይነት ሚስት ናት። ሪሞት ኮንትሮል በትክክል አነጣጥራ ቲቪ መክፈት ሲያቅታት ቢሮ ደውላ ‹‹እምቢ አለኝ…ምን ላድርግ›› የምትል አይነት ሚስት። ‹‹ባትሪው ላልቶ ይሆናል…እስቲ ክፈቺውና ነካ ነካ አድርገሽ እንደገና ሞክሪው›› ሲላት ‹‹ውይ…አንተ ደግሞ…በቃ ስትመጣ አያለሁ›› ብላ የምትዘጋ አይነት ሚስት።

ስልኳን ሰጠችውና ወደ በረንዳ ወጥታ ቀድማ ካዘጋጀችው ባልዲ እየቀዳች አትክልቶቿን ውሃ ማጠጣት ጀመረች።

በራሱም በሚስቱም የማይተማመን ባል ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሞ አርብ ማታ፣ ለአራት ሃያ አምስት ጉዳይ ላይ ለሚስቱ የደወለው ማን እንደሆን ለማጣራት ስልኩን ይበረብር ነበር። ሰናይ ግን እንዲህ ያለ ባል ለመሆን ዝግጁ አልነበረም። እሱ፣ ሚስቱን የሚያፈቅርና የሚያምን፣ በሶስት ልጆች የፀና ጠንካራና ደስተኛ ትዳር ያለው ሰው ነው። አእምሮው የተረጋጋ፣ መንፈሱ ያረፈ አባወራ ነው።

አይደለም እንዴ?

ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ የስልክ ጥሪዎች ታሪክ የሚጠራቀምበት ቦታ ገብቶ አርብ ማታ የደወለውን ሰው ወይ ቁጥር መፈለግ ያዘ።

አርብ፣ ከምሽቱ 3፡35 ደቂቃ- ‹‹ኤ›› በሚል ስም የተመዘገበ የማያውቀው ቁጥር፣

ጥሪው የቆየበት ጊዜ፡ አምስት ሰከንዶች።

እምምምም…..!

ጣቶቹን አፍጥኖ ወደ መልእክት ሳጥኗ ገባ። በዚያው ምሽት፣ ከእሱ ጋር ተቀምጣ፣ ለ ‹‹ኤ›› የፃፈችውን መልእክት አየ። ‹‹ ሃይ፣ ፓርቲ ነኝ…ጫጫታ ስለሆነ አይሰማም። እደውልልሃለሁ›› ይላል።

ፓርቲ ነኝ?

ወደ ላይ ሄደና ከዚያ በፊት የፃፈችለትን ማየት ጀመረ። ሃሙስ እለት ማታ የፃፈችውን ‹‹ሃሃሃ…ይገርማል…ትዝታው ሊገልህ ነዋ! ›› የሚል አገኘ።

ትዝታው? የምን ትዝታ?

ከዚያ በፊት ኤ የፃፈውን አየ።

‹‹ስሚ ቆንጅዬ…ባለፈው ሳምንት ቀኑን ሙሉ ታምር የሰራንበትን ራሱን ክፍል መልሰው አይሰጡኝም? አይገርምም?›› ይላል።

ይሄን ጊዜ ሰናይ ሁለመናው ከእንጨት እንደተሰራ ሁሉ ይደርቃል።

ከአፉ ምራቅ ይጠፋል።

አይኑ ይደፈርሳል።

ሚዛኑ ይዛባል።

ልቡ ልክ ባልሆነ ዘዬ ይመታል።

ጣቶቹ መንቀጥቀጥ ይጀምራሉ።

ሁሉም ጸጉሮቹ መቆም ይጀምራሉ።

ወደ ላይ ይለዋል።

ሽንቱ ይወጥረዋል።

መሬት ላይ ተዘርሮ ቁና ቁና መተንፈስን ይመኛል።

ግን በሚንቀጠቀጡ ጣቶቹ ወደ ላይ ይገልጣል። የኤ እና የታማኝ ሚስቱን የቃላት ድሪያዎች ለደቂቃዎች ያነባል።

አንዱ መልእክት ወደሌላው እየመራው፣ አንዱ አንዱን አንብብ እያለው የሚያንፈራፍር የሆድ ህመም እስኪይዘው ድረስ ብዙ ጉድ አየ፣ ብዙ ጉድ አነበበ። ማለቂያ የሌለው የብልግና መልእክት ክምር ውስጥ ራሱን አገኘ።

ማንበብ ማቆም ይፈልጋል። ግን ያቅተዋል።

በእያንዳንዱ መልእክት የሚስቱ ስብእና ይሸራረፍበታል።

በእያንዳንዱ ‹‹ሃይ ፍቅሬ›› ቤቱ ይፈራርስበታል።

በእያንዳንዱ ‹‹እኔም ናፍቀኸኛል›› አለሙ ይጠብበታል።

ግን ማንበብ ማቆም ያቅተዋል።

ባገኙት መድረክ ሁሉ ይባልጋሉ፣ ይሞላፈጣሉ፣ ይጨማለቃሉ። ዋትስአፕ፣ ቫይበር፣ ቴሌግራም። ….ሃያ ባልሞላ ደቂቃ ውስጥ የ12 አመት ትዳሩ አፈር ድሜ ጋጠ። የሚያፈቅራት ሚሰቱ፣ በሃያ ደቂቃ እድሜ፣ የሶስት ልጆቹ እናት የቡና ቤት ሴት፣ ጎዳና ላይ ቆማ ገበያ የምትጠብቅ ሴት አዳሪ ሆነች። በሃያ ደቂቃ እድሜ ሕይወቱ አይሆኑ ሆነ።

የደስታ ኑሮው አፈር ለበሰ።

ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ጢምበራው እንደዞረ ሰው ጭ….ው…እንዳለበት፣ እንደተወዛገበ፣ አለሙ እንደጠበበ፣ ሁለንተናው እንደተበጠበጠ፣ ሶስት ልጆቹ ጠባቡ ግቢ ውስጥ ሲጫወቱ ይሰማዋል። ሜላት…ይህች የማያውቃት፣ ባይተዋር ሴት አትክልቶቿ አጠገብ በርጩማ ላይ ተቀምጣ ስታያቸው ይታየዋል። የረፋድ ፀሃይ በረጅሙ መስኮት በኩል ወደቤት ገብታለች።

ምንድነው የሚያደርገው?

ቀጥታ ወደ ኩሽና ሄዶ ከቢላዎች መሃል ትልቁን ቢላ መርጦ እየተምዘገዘገ አጠገቧ ደርሶ አትክልቶቿ ፊት እንደ አትክልት ይከትፋታል?

የኔ አንጀት እንዲህ ነው የተበጠሰው ብሎ በቢላው አንጀቷን በጥሶ ያሳያታል?

ልጆቿ /ልጆቻቸው ፊት ይገድላታል?

አያደርገውም።

ፊትለፊቱ የተቀመጠውን ትልቅ መስኮት የሚያህል ቴሌቪዥን (ያ ሁሌ እንደ ጨዋ ሴት በጊዜ ቤቷ ተሰብስባ፣ ተጎልታ የምታየውን) ይከሰክሰዋል?

ልብሷን ሁሉ እያወጣ ፀያፍ ስድብ እየተሳደበ…‹‹አንቺ ሸርሙጣ›› ምናምን እያለ በረንዳ ላይ ይወረውረዋል?

እንደ ቆሰለ አውሬ ያጓራል?

እንዳበደ ውሻ ይጮሃል?

(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...