Tidarfelagi.com

ባይተዋሩ ግመል

አንዳንድ ድምጻውያን አዲስ አልበም ሊያወጡ ሲሉ ነጠላ ዜማቸውን ቀደም ብለው እንደሚለቁት፣ከአዲሱ ‹ያልተቀበልናቸው› ከተሰኘው መጽሐፌ ከአንዱ ወግ ቀንጭቤ ጀባ ልላችሁ ወደድኩ። 

ባይተዋሩ ግመል

(….)
ግመሉ የተገለለ ነው – ከወንዙ ተነጥሎ፣ ከወገኑ ተለይቶ፣ ለተሻለ ኑሮ፣ ወይም ለተሻለ የመንፈስ ፀጥታ፣ ወይም ለተሻለ ዕውቀት ባህር ማዶ እንደተሻገረ ባይተዋር ኢትዮጵያዊ፣ መልኩ ከመልካቸው አንድ እንዳልሆነ፣ በጥቁርነቱ መዘባበት እንደደረሰበት፣ በዘር መድልዎ ኅሊናው እንደተመታና ሞራሉ እንደተነካ ጥቁር አፍሪቃዊ…

ባይተዋሩን ግመል አይቼዋለሁ፤ ባየሁት ጊዜ እኔም እዚህ ምናመጣው? ብዬ ደንግጫለሁ።ትዝ ይለኛል፣ ከአመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ግመል ስመለከት፣ ምቾት አልተሰማኝም ነበር። እየቆየሁ ስሄድ፣ ግመል በአፋር፣ ሶማሌና በሌሎች በረሃማ አካባቢ ለኖሩ ሰዎች የሚውለውን ውለታ ሳውቅ ከበሬታዬን ቸርኩት። እየቆየሁ ስሄድ፣ እንደ በረኸኞቹ ወተቱን ጠጣሁ፤ ስጋውንም በላሁ። ሳይከብደኝ።

አንድ የሰባት ቤት ጉራጌ ነዋሪ፣ ግመልን ማየት የሚችለው፣ ያብሬት ሸህ ወደተባለ ቦታ (ቸሃ ወረዳ) የሄደ እንደሆነ ብቻ ነው። እዚያም ቢኬድ ግመል እንደልብ አይደለም። ቦታው ቁርዓን የሚቀራበት፣ መንዙማ የሚንቆረቆርበት፣ ምርቃንና ርግማን የሚጎርፍበት፣ የአላህ፣ የነቢዩ መሃመድና የሌሎች ሙስሊም ቅዱሳን ሱሃቢዎችና ወሊዮች ስም በአክብሮት የሚጠራበት ነው።ከየአቅጣጫው – ከወሎ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ፣ ከየትም ቦታ ያሉ-አማኞች ይመጣሉ። ክብረ በዓሉ ሲከበር ደግሞ ሩቅም ያሉት ቅርብም ያሉት፣ እንግዳ ማስተናገጃ ይሆን ዘንድ በሬ፣ ፍየል፣ በግ፣ ጊደርና ግመል ይዘው ይመጣሉ። እንስሶቹ ተልዕኳቸው አንድ ነው – መታረድ። ቁርጡም፣ ጥብሱም፣ ቅቅሉም፣ ክትፎውም በሽበሽ ነው። ይህ ለጥቂት ቀናት የሚቆይ ፌሽታ ነው – ዓመታዊ ፌስቲቫል። ለስጦታ ከሚመጡ እንስሶች፣ ቅቤ፣ ቡና፣ ማርና ጫት ቀንሶ፣ ቆርሶና መጥኖ ወደ ጓዳው የሚያስገባ የእምነቱ ተከታይ የለም። ስለቱ የሰመረለት፣ ፀሎቱ የተደመጠለት፣ አኪሩ የዞረለት፣ ቀኑ ቀና የሆነለት፣ የመከራ ደመና የተገፈፈለትና እርሻው የሰመረለት ተሰባስቦ ለፈጣሪው ይሰግዳል፤ ይፀልያል፤ ያመሰግናል…

እዚህ በዓመት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ግመል አለ። ግመሉን እንደልብ የሚያዩትም ታዳሚዎች ናቸው፣ግመሎቹ ባለፉባቸው መንገዶች የሚኖሩ የጥቂት ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ኗሪዎችም ጭምር። ሌሎቹ የት ብለው? በምን ተገናኝተው?

ይኼ ግመል፣ ከአፋር ወይም ከሶማሌ ክልል የመጣ ይመስለኛል። አጎቴ ተክሌ ናጂ የሰማውን እንደነገረኝ፣ ይሄ ግመል ሊታረድ ሲል፣ እንደ ሌሎቹ አንገቱን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ፣ መስዋዕት ለመሆን እንደ መዘጋጀት፣ አሻፈረኝ አለ። የሚያሳዝን፣ ነፍስን የሚያላውስ፣ ረዘም ያለ ድምጽ አሰማ። ልኑርበት አለ። አራጆቹን ተማፀነ። ተሞከረ፤ በእምቢታው ፀና። ጭራሽ አመለጠ። ሊይዙት የሚሞክሩትን ካልነከስኩ አለ። ይህን ያስተዋሉ አንድ አባት፣ ‹ተዉት በቃ፤ ይሄኛው ግመል የተለየ ነው፤ ራሱን ነፃ አውጥቷል!› አሉ። ግመሉ ነፃ ሆነ። ተለቀቀ። የተሴረበትን አውቋልና፣ ካራ በአንገቱ ሥር እንዳያልፍ አድርጓልና፣ በአንድ አባት አማላጅነት ነፍሱን ከሞት አትርፏልና፣ ሃሳባቸውን ቀይረው አዘናግተው የሚያርዱት ይመስል፣ ከመሃላቸው በፍጥነት ተለየ። ማን ይከተለው?! ተከታዮችም ተመልሶ መምጣቱ፣ ወደመጣበት መዝለቁ አይቀርም በሚል ተስፋ፣ ወደኋላ አፈገፈጉ።

ግመሉ ግን ሄደ፤ የበረሃው ንጉሥ፣ የአካባቢው ጌታ፣ አለ ፍጥረቱ ወደ ደጋማ አካባቢ ‹ከፍ› አለ። ከፍም ወደ በረዶ።

ልክ እንደ አንድ የፖለቲካ ስደተኛ ሆነ። ከወገኑ መንጋ ተገነጠለ። ሕይወቱን ለማትረፍ፣ ከክፉ አሟሟት ለመዳን ብሎ፣ በማያውቃቸው ማኅበረሰቦች መሀል ተገኘ። ከአዳኞቹ፣ ከገዳዮቹና ከአራጆቹ አምልጦ። የተሻለ ነገር ይገጥመኛል በሚል ተስፋ፣ የ13 ወራት ፀጋ መሆኗን ከተነገረላት አገር፣ እንደ ዳቦ የሚበላ፣ እንደ ከረሜላ የሚኮረሸም አየር አላት ተብሎ ከሚነገርላት የትውልድ አገሩ ወጣ።እንደ አንድ ስደተኛ ፖለቲከኛ ሆነ – ግመሉ።

ያኔ፣ አያቴ ማለትም የእናቴ እናት አርፈው ስለነበረ፣ ቀብረን በተመለስን ጊዜ ነው- ግመሉን ያየሁት። በጉመር ወረዳ። ጉመር፣ ሰባት ቤት ጉራጌ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ ናት። ዝምተኛ እና ርጋታን የተላበሰች ወረዳ ናት። ትበርዳለች። ነዋሪዎቿ ልክ እንደ አንኮበር ሰው፣ በጉም መሀል ጋቢ ተከናንበው፣ ሹራብና ካፖርታ ደርበው ነው – የእርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑት፣ልቅሶ የሚደራረሱት። የነዋሪዎቹ የሞቀ ፈገግታና ልባዊ አቀባበል ባይታከልበት፣ ጉመር እንግዳ የሚሰነብትባት ወረዳ አይደለችም።

አስደሳቹ ነገር በነዋሪዎቹ ድምጽ ውስጥ ጩኸት የለም፤ መቅበጥበጥ የለም፤ መቸኮል የለም።ወረዳዋ የምትነቃው፣ የምትነቃቃው እንደ ግመሉ አመጣጥ ድንገት የተለየ ፍጥረት፣የተለየ ክስተት በመካከላቸው የተገኘ እንደሆነ ነው።ግመሉ፣ ከዕለታት አንድ ቀን፣ በመንገዳቸው ሲጓዝ አዩት። ያዩት ሰዎች መጀመሪያ አንዳች አውሬ፣ ከጅብ የባሰ ሃይል ያለው በልቶ የማይጠረቃ ፍጥረት መሰላቸው።ልጆቻቸውንና ከብቶቻቸውን ሰበሰቡ።ይህ ፍጥረት ሊተናኮላቸው ካሰበ፣ እንዴት አደብ ማስገዛት እንዳለባቸውም መከሩ። እናም ጠበቁት። ቢያዩት ማንንም አይጎዳም። መንደር የሚያውክ ድምጽ አይወጣውም።

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ፣ ወደ ገበያ በመሄድ ላይ የነበረ አንድ ሙስሊም ሰው፣ የፍጥረቱን ስም ነገራቸው። ግመል። ግመል በማኅበረሰቡ ዕውቅና ስላልተሰጠው በጉራጊኛ ቋንቋ ሌላ ስም የለውም። አልወጣለትም። ሥጋው እንደሚበላ፣ ወተቱም እንደሚጠጣ የተነገራቸውን ነገር ማመን ከበዳቸው። የአህያን ሥጋ የመብላት ያህል ቀፈፋቸው።

ግመሉን ቀርበው አዩት።ጅላጅል መስሎ ታያቸው። ገልጃጃ። እናም፣ በመጀመሪያዎቹ ሰሞናት፣ ያየው ላላየው እየጠቆመ፣ ትልቁም ትንሹም፣ ወንዝ አቋርጦ፣ ተራራ አሳብሮ፣ ቀጠሮ ይዞ ሊያርግ ነው የተባለ ይመስል ይጎበኘው ገባ።የጉመር ነዋሪዎች ግመሉን ባዩ ጊዜ ልብ ብለው ባላዩት በፈረሶቻቸው ውበት ተደመሙ።

ግመሉ፣ ባህር ማዶ ሄዶ፣ በጥቁረቱ ተመልካችን እንደሳበና የልጆችን ቀልብ እንደሰረቀ ስደተኛ፣ ጎብኚው በዛ። አንዳንድ ነጮች፣ ጥቁር ሰው ሲያገኙ፣ ‹ከዕውቀታችን፣ ከጉልበታችንና ከአቅማችን ዝቅ ያለ፣ ግን ያለ እኛ እርዳታ መቆም የማይችል!› ብለው እንደሚንከባከቡት ሁሉ፣ ነዋሪዎችም ይህንን ግመል ይንከባከቡት ጀምረው ነበር – ዳቦና ቆጮ እያጎረሱ። በኋላ ግን ግመሉን፣ ምንም ላይጠቀሙበት ቀላቢ ሆነው መገኘታቸው ቅብጠትና ግብዝነት መስሎ ታያቸው።በገዛ ወገኖቹ እንዳልተፈለገ፣ እንደትቢያ እንደተቆጠረ፣ ዓመሉን ከዓመላቸው ጋር ማረቅ እንዳልቻለ ዓይነት ሰው ሆነባቸው።

ያ ማለት ግን፣ ይህ የበረሃ መርከብ፣ በጓሯቸው ሲሽሎከሎክ፣ በዛፎቻቸው መሃል ሲንፈላሰስ፣ በመንገዶቻቸው ሲመላለስ የሚያሳዝን ነገር ሲደርስበት አላዩም፤ አያዩም ማለቴ አይደለም። ኧረ እንደምን አያዝኑለት? ግመሉን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሴት ተርቦ አይተውት ያውቃሉ! ግመሉ ወሲብ በመሻት ብዛት ነፍሱ ስትቃትት ያዩ ጎበዛዝት እንዴት መቃተቱን ያብርዱለት?! ሴት ግመል ከየት ያምጡለት?

ግመል ወሲብ ባሰኘው ጊዜ፣ ከቁመቱ ግዝፈት የተነሳ ብልቱን ወደ ሴቷ ግመል ብልት ማስገባት፣ ማረሻ በመርፌ ቀዳዳ የማሽሎክን ያህል ስለሚከብደው፣ ብልቶቻቸውን በማገናኘት የምትተባበረው ሴት ልጅ ናት አሉ። ወሲብ ሊፈጽም ሲል፣ ወንድ ልጅ ሊተባበረው ከተጠጋ፣ ወይም ምን እያደረገ እንደሆነ ተጠግቶ ካየበት፣ ወንዱን ልጅ አሳድዶ ይነክሰዋል፤ጫንቃውን ይነክሰዋል ይላሉ – ባህርይውን የሚያውቁ። አሁን ግን፣ አጠገቡ ሴት ግመል ስለሌለች፣ማንም አጠገቡ ቢቆም፣ ማንም የነቃ የተነቃቃ አካሉን ቢያይበት ግድ ያለው አይመስልም። እናም የሞቀ ስሜቱን ለማብረድ ሲል፣ግመሉ ራሱን በራሱ ማርካት ጀመረ፤ የታፈነ የታመቀ እሳተ ገሞራዊ ስሜቱን ለማስከን፣ ወደ አንዲት ጉብታ ተጠጋ፤ ጉብታዋን እንደ ሴት ግመል ቆጥሮም ወጣባት።ወጣቶቹ ግመሉ ሕይወት የሌላትን ጉብታ ለመገናኘት ሲታትር ሲያዩ ልባቸው እንደምን አይነካ? መንፈሳቸው እንደምን አይታወክ?! እንዴትስ ተሰዳጅነትና ባይተዋርነት አይሰማቸው?!

የጉመር ሰዎች እንደነገሩኝ፣ ግመሉ አሣዳሪ የለውም። ጠባቂ አልተመደበለትም። ማንም ተነስቶ ግመሉ የእኔ ነው ቢል፣ ከንብረቶቼ እንደ አንዱ ይቆጠርልኝ ቢል፣ ሩቅ ገበያ ወስጄ እሸጠዋለሁ ቢል፣ እህል እጭንበታለሁ፤ እቃ ከቦታ ወደ ቦታ አመላልስበታለሁ ቢል ከልካይ የለውም። ተቆጪ የለውም። ግን ነዋሪው ይህን አድርጎ ቢገኝ፣ሌሎች ሰፈርተኞቹ እንደ ሥራ ፈት መዘባበቻ ይሆናል እንጂ አበጀህ የሚለው የለም። ይልቁንስ፣ ግመሉ በመካከላቸው መመላለስ ከጀመረ በኋላ፣ ቀውላላውን፣ ጅላጅሉንና ቀርፋፋውን ለመገሰጽ ሲፈልጉ፡ የግመሉን ስም በስድባቸውና በተግሳጻቸው መሃል ያስገቡታል – ይሄ ደግሞ እንደ ግመል ነው፤ ሮጦ አያመልጥም፤ አካሄድ አያምርበትም እየተባለ… አስጠሊታም ቅርፀ ቢስ ነው እየተባለ….

ግመሉ ባይተዋር ነው። ለሰው ብቻ ሳይሆን፣ ለእንስሳሶቹ ብቻ ሳይሆን፣ ለአየር ጸባዩ ብቻ ሳይሆን፣ ለዛፎቹም ባይተዋር ነው።

አንዳንዴ፣ግመሉ፣ልክ እንደ ‹ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ልዑል›፣ አሁን እየኖረ ያለው ሕይወት የመረረው የሚደርስበት መገለልና መድልዎ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ረዥም ድባቴ የተጫነው ይመስላል። ግዙፍ የሆነ ዝምታ ይከናነባል። ፊቱ አለቅጥ ይረዝማል። እግሮቹ አጠገቡ ካሉ ዛፎች በላይ ይረዝማል። አንገቱ ይንዘላዘላል። ሁሉም ነገር እንደቸከው፣ እንደታከተው ዓይነት…‹ዘመዶቹ› እንደናፈቁት ዓይነት… የወጣበት ማኅበረሰብ ጠረን፣ ቋንቋና አኗኗር እንደናፈቀው ዓይነት… የበረሃው ግለት፣ ሸክም እንደናፈቀው ዓይነት…

(…)

እየናፈቀው የማይመስለኝ ነገር ቢኖር አንድ ዛፍ አለ።ስለዚህ ዛፍ የነገሩኝ፣ አፋር፣ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያስተምሩ የነበሩ ወዳጆቼና የአካባቢው ተወላጆች ናቸው።ይህ ዛፍ፣ ለሰዉም፣ ለከብቱም መርዝ ነው። ዛፉ አንዴ ከቧጨረህ የመዳን ተስፋህ የመነመነ ነው። ቂም ይይዛል፤ ካልገደለህ፣ ካላመነመነህ፣ ከሰው ተራ ካላስወጣህ አይተውህም። በአፋር ምድር ይህ ዛፍ መብቀል የጀመረው በጃንሆይ ዘመን ነው ይባላል።

ችግሩ አለመጥቀሙ አይደለም። አጠገቡ ካሉ ከሌሎች የዛፍ ዝርያዎች መኖ ይሰርቃል፤ ሌጣቸውን አስቀርቶ፣ ስፍራቸውን አስለቅቆ፣ ያላቸውን አሟጥጦ ይወስድባቸዋል። ዛፉ ባለበት ሌሎች አይኖሩም።ዘረኛ ነው። ወገኑን ተራዳኢ ነው።ኪራይ ሰብሳቢም ነው። ዛፉ ለምንም ነገር አይጠቅምም፤ አንዴ ከተተከለበት ቦታ ለመንቀል ጊዜ ይፈጃል። በቀላሉ፣ የመሰሎቹን ቁጥር የማብዛትና ግዛቱን የማስፋፋት ችሎታ አለው። አርብቶ አደሮቹ ለብዙ ጊዜያት ያህል፣ ይህን ለግመሎቻቸው ሳይቀር ሳንካ የሆነባቸውን አረም ለመንቀል ግረዋል። ግን አልሆነላቸውም።እነሱ ተስፋ የሚያደርጉባት አንዲት ሀረግ አለች። ይህቺን ሀረግ ዛፉ አጠገብ ይተክሏታል።ሀረጓ፣ዕድሜዋን ለማሰንበት ስትል፣ ዛፉ ላይ ትጠመጠማለች፤ ቁመቷን ታስረዝማለች፤ ዛፉ ደግሞ ከሰውነቱ ከግንዱ የተጣበቀችውን ሀረግ ለማስወገድ አቅም የለውም። ሁለቱም ተያይዘው ይወድማሉ፤ ይጠፋሉ። ወፍ ዘራሹን የወያኔ ዛፍ፣ መድረሻ ጥግ ያሳጣዋል እየተባለ፣ ሀረጉን የሚጠጉ አካላት መምጣታቸው፣ ግመሎቹ ሳይቀሩ ሰምተው፣ ዝምታ የዋጠው ፊታቸው ፈገግታ መፈንጠቅ የጀመረ ይመስላል።

ይኼ፣ በጉመር ወረዳ ብቅ ያለው ግመልም፣ በሕይወቱ ሲሆን ማየት የሚፈልገው አንዳች ነገር ይህ ዛፍ ሲደመሰስ ማየት ይመስለኛል። ያ ካልሆነ፣ ይሄ ስደተኛ ግመል፣እንኳንም አመለጥኩ፤ እንኳንም ዛፉን ትቼ መጣሁ፤ እንኳንም…የሚለው ነገር ከዚህ ዛፍ ሌላ፣ ሌላ ምን ሊኖር ይችላል ብዬ አስባለሁ!

እዚህ፣ ያ ዛፍ እግር አብቅሎ አያሳድደውም። አይቧጭረውም።መተላለፊያ መንገድ አያሳጣውም። ይህ መሆኑ ግን ደስታውን ምሉዕ አላደረገለትም። ብቻውን ነው። አጠገቡ ያሉት አህዮች፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስለዚያ ዛፍ በሚገባቸው ቋንቋ ቢነግራቸው አያምኑት ይሆናል። ለእነዚህ ጥድ፣ ባህር ዛፍና ቀርከሃ እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ዛፍ የለባቸውም። ለነሱ ዛፍ መጠለያ፣ መሸሸጊያ፣ የአሳዳሪዎቻቸው መከታ እንጂ ለስደትና ለምሬት የሚዳርግ አይደለም። ክፋቱን ለማመን የሚያስችል የሕይወት ልምድ የላቸውም። በዛፉ አልተፈተኑም። አበቃቀላቸው፣ አተካከላቸውና አስተዳደራቸው ለየቅል ነው።

ግመሉ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ስደተኛ ነው። አብዮታዊ እርምጃ እንዳይወሰድበት ብሎ፣ በአሸባሪነት እንዳይወነጀል ብሎ የገዛ ነፍሱን ከሞት እንደታደገ ባይተዋር።ቋንቋውን በማያውቁ፣ሣቁን በማይካፈሉ፣ ተረቡን በማይረዱና ሕመሙን በማይታመሙ ሰዎች መሃል እንደተገኘ እንግዳ… በማያውቃቸው ተራሮች፣ የስልጣኔ ማማዎች፣ በአሜሪካ፣በአውሮፓ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሌሎች አገራትና አህጉራት ወንዞች መሃል፣ ሰው እንደተራበ።

አጎቴ እንዳጫወተኝ፣ ግመሉ አሁን አሁን አካሉ ገዝፏል፤ እንደተመቸው ዲያስፖራ የደለበ አካል ይዟል። ተመልሶ ወደ በረሃማ ስፍራ የመቀላቀል ፍላጎት ያለው አይመስልም። ማኅበረሰቡ፣ ከእንስሶቹ፣ ከጋማ ከብቶቹ እንደ አንዱ አድርጎ ሊቆጥረው እንዳልፈቀደ ቢያውቅም፣ መናቁ፣ የሌለ ያህል መቆጠሩ፣ ቅርፀ ቢስ መስሎ መታየቱን የለመደው ይመስላል።

ወደ ጎጆ ቤታቸው ገብቶ በጋጣቸው እንዲያድር እድሉን ባይሰጡትም፣ ከወንዛቸው እንዳይጠጣ አላገዱትም። ብቻውን የሚጠጣው ውሃ፣ የአንድ አባወራ ከብቶች ሊያጠግብ እንደሚችል እያወቁ እንኳ፣ ከወንዛቸው እንዳይጎነጭ እገዳ አላበጁበትም። ያልተገባ ነገር አልጫኑበትም። መንገላታት አላደረሱበትም። ‹አራጆቹ› ወደሚገኙበት ቦታ አልሰደዱትም። ድንገት ከዐይናቸው ቢሰወር፣ ምን አግኝቶት ይሆን ብለው ልባቸውን ትካዜ ውስጥ ባይከቱም፣ ግመሉ ለልጆቻቸው መደሰቻና ጨዋታ መፍጠሪያ መሆኑን በማየታቸው አልጨቆኑትም።

ግን ይኖራል።ባይተዋሩ ግመል ኑሮውን ይቀጥላል-ተሰዳጁን፣ የተገፋውን፣ ነፍሱን ከሞት፣ ሥጋውን ከእንግልት ያተረፈውን የፖለቲከኛውን ሰው ሕይወት እንደወከለ።እንደተመሰለ…

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...