Tidarfelagi.com

ባሌ እንዳመነዘረብኝ ባወቅኩ ጊዜ (ክፍል ሰባት)

“አልቻልኩም። …. አልቻልኩም!” ሁለት እጆችዋን ጨብጣ ደረቴን እየደበደበች ታለቅሳለች። ጉንጮቿ እና ከንፈርዋ ይንቀጠቀጣሉ። አንጀት የራቀው ሆድዋ ይርበተበታል።

እየደጋገምኩ “እሺ” ከማለት ውጪ የምለው አጣሁ። ድብደባዋን ስታበቃ ንፁህ ያልሆነው መሬት ላይ በነጭ ሱሪዋ ተቀመጠች።

“ላናግርህ እፈልጋለሁ” ብላ ሱቋ ጠርታኝ ነው ሱቁን ዘግታ በእንባዋ እየቀጣችኝ ያለችው።

ከመምጣቴ በፊት ወይም ከጠዋት ጀምሮ አልያም ያለፈውን ቀናት በሙሉ እያለቀሰች እንደነበር አብጦ ለመከፈት የቸገረው አይኗ ያሳብቅባታል። ቅጣት ነው!! ፈጣሪስ ቢቀጣኝ ከዚህ በላይ በምን ቢቀጣኝ ነው ከዚህ የባሰ ህመም የሚያመኝ?

“እመነኝ እየወቅስኩህ አይደለም። እረዳሃለሁኮ …. መደበቂያ ስትፈልግ …. የምትተነፍስበት ባጣህ ጊዜ አገኘኸኝ ….ጉድለቴን ስታውቀው ስላሳዘንኩህ ያፅናናኸኝ መስሎህ ፍቅርህ ውስጥ ደበቅከኝ። በትዳርህ ተስፋ ስትቆርጥ ልብህን የምታዘው መስሎህ ነው እወድሻለሁ ያልከኝ። ….እኔ ነኝ እንጂ ከንቱዋ እሷን እንደምታፈቅራት እያወራኸኝ ለሷ ባለህ ፍቅር ውስጥ ዘፍቄ የተዘፈዘፍኩ።” አለችኝ በየመሃሉ ሳግ እያቋረጣት

ይሄ ነገሯ ነው እሷ ውስጥ እንድጠለል ያደረገኝ። ራሴን እንዳልወቅስ የምታደርገኝ ነገርዋ …… ራሴን ይቅር እንድለው የምታደርገኝ …… ነገርዋ ራሴን እንድወደው የምታደርገኝ ነገሯ ……. ሰብሬያት እንኳን እኔ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ ከማድረግ ራሷን ትኮንናለች ከዚህ በላይ ቅጣት ካለ ንገሩኝ?

አንዳንድ ሰዎች አንድ ሺህ ነገር አውርተሃቸው አንድ ሺውንም ይሰሙሃል። የቱንም ግን ላይረዱህ ይችላሉ። እሷ ሁለት ቃል አውርቼ ያላወራሁትንም 200 ቃል ደምራ ትረዳኛለች። ያ ነው እሷጋ ያስከንፈኝ የነበረው። የሆንኩትን ልነግራት ስጀምር እንዴት እንደሆነ በማይገባኝ ሁኔታ እኔ እንደተሰማኝ …እንደዛው አድርጋ …. ትጨርስልኛለች። እሷም እዛው ስቃይ ላይ እንደነበረች …….. የታመምኩትን እንደታመመች … የተናደድኩትን ተናዳው እንደነበር …….. ልክ እንደዛው …….. ጥፋቴን እንኳን አጥፍታው የነበር እስኪመስለኝ እኔ እንደሚሰማኝ አድርጋ ትገልጽልኛለች።

ለምን ለሚስቴ መውለድ እንደማልችል እንደደበቅኳት ስትጠይቀኝ። ሌላ ሰው ሲሰማው ውሃ የማያነሳ ራስ ወዳድ ምክንያቴን ሳስረዳት
“አንዳንዴ የምትወደውን የማጣት ፍርሃት ምክንያታዊ እንዳትሆን ያደርግሃል። አሁንህን ለማዳን ነገህን ታበላሻለህ!” ነበር ያለችኝ።

“እረዳሃለሁ እሺ … ትወዳታለህ!! …እኔንም ትወደኛለህ። ….እሷ ሳትወድህም ትወዳታለህ! የተናደድክባት ጊዜም ትወዳታለህ። የበቃህ የመሰለህ ጊዜም ትወዳታለህ። ….. እኔ እንድጎዳብህ እንደማትፈልግም አውቃለሁኮ” ደግሞ አቁማ ድምፅ አውጥታ ታለቅሳለች።

“እኔስ ባሌንም ዛሬም ድረስ እወደው የለ ከዛ ደግሞ አንተንም ወደድኩህ አይደለ? አልፈርድብህም እሺ! ልብህ እሷጋ ነው። አንተ አታዝበትም።”
ይኸው ከራሴ ጋር እንኳን እንዴት ነው ሁለት ሰው መውደድ የቻልኩት እያልኩ የምጣላበትን ሀቅ እኔን ሆና ታብራራልኛለች።

“እኔ ግን መጠበቅ አልችልም! አንተ እሷን ጠብቃት። የጥበቃህ መጨረሻ ምንም ቢሆን እባክህ ስወድህ ተመልሰህ እኔጋ አትምጣ! እኔ አሁን የሚሰማኝ ህመም እንዲያምህ አልመኝልህም ስለዚህ ትዳርህ ይስመርልህ። ባይሆንም ግን አትምጣ።”

መሬቱ ላይ ከነሱፌ አጠገቧ ተዘፈዘፍኩ። ላቅፋት እጄን ስዘረጋ ጥቅልል ብላ ውስጤ ተሸጎጠች። እናቱ ከገረፈችው በኋላ መልሳ ስታባብለው እንደሚብስበት ህፃን ህቅ ብላ አለቀሰች። ቁጥሩን ለማላውቀው ያህል ጊዜ ደጋግሜ ይቅርታ አልኳት። ይቅርታ ባልኳት ቁጥር ህቅታዋ ከአንጀቷ ድረስ እየተሳበ ህቅ እያለች ታለቅሳለች።

“አታስብ እሺ ምንም አልሆንም። አሁን አባዬ ነቅቶ የለ? ህይወት ሁሉንም አትሰጥም አይደል? …. አልረሳህም ግን እተውሃለሁ።”

እንዴት ነው እንባዋ ሸሚዜን እያጠበው ፈገግ የምትለው? እያለቀሰች የምትስቀው? እየታመመች ደህና እንደሆነች የምትሆነው?

“ሂድ በቃ!” አለችኝ ከእቅፌ ወጥታ …. ልነሳ ስል ደግሞ ያዝ አድርጋኝ …
“ቆይ ትንሽ ደቂቃ ልይህ.. ” ጉንጬን አገጬን አንገቴን ፀጉሬን ስትነካካኝ ቆይታ
“እሺ በቃ ሂድ ….” አለችኝ ድክም ባለ ድምፅ

እየተንፏቀቅኩ ተነስቼ በሩጋ ከደረስኩ በኋላ ዞሬ አየኋት መሬቱ ላይ ኩርምት ብላ ጉልበቶቿን አቅፉ ሳያት ራሴን ጠላሁት። ምንድነው ያደረግኩት? ምንድነው ያደረግኩት? እንዴት ክፉ ነኝ?

እቤት ደርሼ መኪናውን ካቆምኩ ቆየሁ ግን አልወረድኩም። የሆነ ቦታ መጥፋት አሰኘኝ። ብቻዬን የምሆንበት ቦታ!! ባዶ ሆንኩ …..ባዶ …. ፀፀት ብቻ የሞላበት ባዶ ጭንቅላት ….. ህመም የበዛበት ባዶ ልብ !

ወደኃላ ተመልሼ ህይወቴን ማረም ብችል ከየት ነው የምጀምረው? ስህተቱ ይበዛል …. ባለትዳር ሆኜ ሌላ ሴት ስቀርብ? አይደለም ከዛ በፊት ሚስቴ እንድትጠላኝ ያደረጋት ውሸቴን …. እሱም አይደለም። ለውሸቴ ሰበብ የሆነችኝ እውነቱን ስነግራት የተወችኝ የድሮ ፍቅረኛዬን? …. እሷም ጋር አይደለም …. ለመካንነት ሰበብ የሆነኝ የሞተር ሳይክል አደጋ…. ይሄን ሁላ ባጠፋው … እኔ አልሆንማ!! ….

ስቆይባት በሩን ከፍታ ብቅ ስትል አየኋት። እግሬን እየጎተትኩ ወርጄ ወደቤት ገባሁ።

“ምነው ደህና አይደለህም?”
“ደህና ነኝ” ካልኳት በኋላ መልሼ “ደህና አይደለሁም!” አልኳት እየተቆጣሁ እንደሆነ እየታወቀኝ።

“ምን ድረስ ነው ግን የምወድሽ? እንዴት አድርጌ ወድጄሽ ነው በህይወቴ ውስጥ አንቺ እስካለሽበት የሌላ ንፁህ ሰው ህይወት ማመሳቀል እንኳን ቢሆን ሁለቴ ሳላስብ የማደርገው?”

ያልኳት አልገባትም ዝም አለችኝ። አልፋኝ ሄዳ ተቀመጠች። እሷን ምን አድርጊኝ ብዬ ነው የምቆጣት? ዝም ተባብለን ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ
መቼም እለዋለሁ ብዬ የማላስበው ነገር የአፌን በር ለቆ ሲወጣ ራሴን ሰማሁት።

“ለተወሰነ ጊዜ ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ!” የተገረመች መሰለች።

“ሁለታችንም ብቻችንን ጊዜ ያስፈልገናል።”

 

ጨርሰናል!!

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...