Tidarfelagi.com

ባሌ እንዳመነዘረብኝ ባወቅኩ ጊዜ… (ክፍል አምስት)

“እናውራ? ማውራት አለብን!” አለኝ አምስት ለሊቶች ሳይነካካኝ አቅፎኝ ካደረ በኋላ። አምስት ጠዋቶች ከንፈሬን ሳይስመኝ ደህና ዋዪ ካለኝ በኋላ። አምስት አመሻሾች ደረቱ ላይ አቅፎ ግንባሬን ሳይስመኝ እንዴት ዋልሽ ካለኝ በኋላ….

“Finally” አልኩኝ ይህን እንዲለኝ ስጠብቅ እንደነበር በደንብ እያሳበቅኩ

“እንዴ? እንድናወራ እየጠበቅሽ ነበር? ማውራት ፈልገሽ ከነበር ለምን እናውራ አላልሽኝም?” ዝም አልኩ። እንዲህ ነኝ! ራሴን እንዴት መግለፅ እንዳለብኝ የማውቀው ከእናቴ ጋር ስሆን ብቻ ነው። እንዲህ ሲለኝ እንዲህ ብዬው በነበር የምለው ካለፈ በኋላ ነው። እንዲህ ማለት ነበረብኝ የምለው አለማለቴ መዘዝ ከመዘዘ በኋላ ነው። በተለይ ስናደድና ስከፋ ሰዎች የልባቸውን ብለውኝ ከሄዱ በኃላ ነው …. በራሴ ብስጭት እያልኩ ‘እንዲህ ባልኩ ኖሮ’ የምለው..

“ይሄ እኮ ነው ችግርሽ ምንም ሳታወሪ እንዳዳምጥሽ ትፈልጊያለሽ። ምንም ሳትጠይቂኝ መልስ ትጠብቂያለሽ። ለግምት እንኳን የራቀ ስሜት እያሳየሽኝ በልብሽ ያመቅሽውን ስሜት እንድረዳሽ ትጠብቂያለሽ።” እንዲህ ድምፁን ጮክ አድርጎ አውርቶ አያውቅም። መናደድ ይችላል ለካ! አሁንም ዝም አልኩ።

በረዥሙ ተነፈሰ እና ደግሞ በራሱ ድምፅ ማውራት ጀመረ።
“እ የምነግርሽ ነገር አለ ……” እያለ እንዴት እንደሚነግረኝ ይታሽ ጀመር።

‘አውቃለሁ’ ልለው አስባለሁ ግን አፌ አያወጣውም። ሊነግረኝ ሲጨነቅ አየዋለሁ። እንደማውቅ ልነግረው እጨነቃለሁ። በመጨረሻ ከአፉ የወጣው ሊናገር የፈለገው እንዳልሆነ በሚያስታውቅ ሁኔታ ‘ቆይ ሌላው ይቆይና …’ የሚል ለዛ ባለው ድምፅ

“ወደሽኝ ታውቂያለሽ ግን? በፍቅር? ” አለኝ።

ደነገጥኩ። ምንድነው ያስደነገጠኝ? እንለያይ ወይም ከሌላ ሴትጋ ግንኙነት አለኝ እንዲለኝ ስጠብቅ ወድጄው እንደነበር ስለጠየቀኝ? ዝም አልኩ። አሁን ግን ያለመናገር አባዜዬ ሳይሆን መልሱን ስለማላውቀው ነው። ወድጄው የማውቅበትን ጊዜ ለማስታወስ ወደኋላ ተጓዝኩ። እሩቅቅቅቅቅቅ ነው።
“ይመስለኛል!” የሚል ቃል ነው ከአፌ የወጣው።

አንገቱን ደፍቶ ዝም አለ። መሬት መሬቱን እያየሁ እንባው መሬቱ ላይ ጠብ ሲል አየሁት። ለማረጋገጥ ቀና አልኩ። በአስር አመት ውስጥ እህቱ የሞተች ጊዜ ካልሆነ ሲያለቅስ አይቼው አላውቅም። ዘልዬ ላቅፈው ፈልግያለሁ። እንባው መሬቱ ላይ ከመድረሱ በፊት በጣቶቼ ከጉንጩ ላይ ልጠርግለት። አታልቅስ ብዬ ልለምነውም እፈልጋለሁ። ከአፌ አይወጣልኝም። አስለቃሽዋ ራሴ ሆኜ ማባበል ትርጉም የሚሰጥ ነገርም አልመስል አለኝ። ለሰራሁትም ላልሰራሁትም ሀጢያት ይቅርታ ጠይቄው ለቅሶውን ላስቆመው እመኛለሁ። ውስጤ ሲታመስብኝ ይታወቀኛል።

“ስራ አልቆ መጥተህ እስክትወስደኝ በናፍቆት የምታመም የሚመስለኝ ጊዜ ነበር፣ ስትስመኝ ከመሳሳቴ መቼም የማልጠግብህ የሚመስለኝ ጊዜ ነበረ፣ ልታገባኝ ሽማግሌ የላክህ ቀን በዓለም ላይ የደስታ መጨረሻው ያ መስሎኝ ነበር፣ መጀመሪያ ቢሮዬ መጥተህ ያየሁህ ቀን ልቤ በአፌ የምትወጣ መስሎኝ ነበር፣ እራት ልጋብዝሽ ያልከኝ ቀን ምን ብለብስ ልትወደኝ እንደምትችል ስለብስ ሳወልቅ……. ተቀብቼ የማላውቀውን ሊፒስቲክና ኩል ስቀባ አንድ ሰአት ነበር የፈጀብኝ፣ የሰርጋችን ቀን ማታ መቼም ከእቅፍህ እራሴን እንደማላርቅ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፣ ከልክ በላይ ስታቀብጠኝ በምድር እንደእኔ እድለኛ ሴት እንዳልተፈጠረች ያሰብኩባቸው ጊዜያት ብዙ ነበሩ፣ ይሄ ሁሉ ፍቅር ከነበረ አዎ አፍቅሬህ አውቅ ነበር። ግን እውነተኛ ፍቅር ቢሆን ያልቅብኝ ነበር? ፍቅር ያልቃል?”

ራሴን ሳብራራ አገኘሁት። አውርቼ ስጨርስ ፈገግ እያለ እንደሆነ አየሁት። ከተናገርኩት ምኑ ነው ደስ የሚያሰኘው? ድንገት ተስፈንጥሮ አቀፈኝ። ግንባሬን ፀጉሬን አንገቴን እየሳመ
“ፍቅር አያልቅም! በጥላቻ ወይ በቂም ግን ይሸፈናል። ” እያለኝ ደስ መሰኘቱን ቀጠለ።

ግራ ገባኝ። ምንድነው እየሆነ ያለው? አትሳቅ ተብሎ ሳቁን ለመቆጣጠር እንደሚታገል ሰው ያላለቀ ፈገግታ ፈገግ እያለ ተነስቶ መንጎራደድ ጀመረ።

ዓይኖቼን አብሬ ከማንቀዥቀዥ ያለፈ ማድረግ የቻልኩት የለም።

“ጠይቂኝ እስኪ? ምንድነው እንዲህ የሚያስፈጥዝህ በይኝ? ለዛሬ እንኳን ደስታዬን ሙሉ አድርጊው! ለሚሰማኝ ስሜት ግድ አላት ልበል?” አለኝ
እያለ ያለው እንደገባኝ እርግጠኛ አይደለሁም። የቅድሙ እንባውን ከማይ ደስታውን ሙሉ የሚያደርገው የኔ መጠየቅ ከሆነ ሺህ ጊዜ ብጠይቀው ግድ አልነበረኝም።

“ምንድነው ደስ ያሰኘህ?”

“እነዚህን ቃላት ካንቺ አፍ ለመስማት ስንት ቀናት መናፈቄን ታውቂያለሽ? ፈጣሪዬን ለምኜው እንደማውቅ ታውቂያለሽ? ካንቺ አፍ የተሰማሽን ስሜት የሚገልፅ ቃል ፈልቅቆ ከማውጣት ……. ”

አልጨረሰውም ቃል ጠፋው።

“ለምን አትጠይቀኝም ነበር? ዛሬ እንደጠየቅከኝ?ለምን …”

“ለመልሱ ዝግጁ አልነበርኩም ነበር።” አለ ችኩል ብሎ!! ቀጥሎ
“ሁሌም እወድሻለሁ ስልሽ ‘እኔም’ ነበር መልስሽ። የዛሬ አራት ዓመት ህዳር 7 ጠዋት እወድሻለሁ ስልሽ ‘እኔም’ ማለቱ ሲያስምጥሽ አየሁ። እያስጨነቅኩሽ እንደሆነ ስለገባኝ እወድሻለሁ ማለቱንም ተውኩት።”

ምን ልበለው ዝም አልኩ። ተቀምጦ ዝም አለ። እናቱ የሚወደውን ነገር ልትገዛለት ወጥታ መመለሷ እርቆበት በደስታና በጉጉት እንደሚቅበጠበጥ ህፃን እያደረገው ተቀመጠ።

“እኔኮ ግን ባትነግረኝም እንደምትወደኝ አውቃለሁ።” ብዬ ያሰብኩት ነው ያመለጠኝና ቃል ሆኖ የተናገርኩት
“(ፈገግ እንደማለት ብሎ) ቃሌን የሚተካልሽ ነገር አጊንተሽ አይደለም? መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ስጦታ የገዛሽልኝ? የዛሬ ሰባት ዓመት የልደቴ ቀን….”
(ሰባት ዓመት ሙሉ ሲዘንጥ የሚያደርገውን ሰዓት እያሳየኝ። እሱ ባለፈው ወር ጫማ ገዝቶልኝ ነበር።)

“መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ፈልገሽ የሳምሽኝ? መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ባንቺ ተነሳሽነት ፍቅር የሰራ…..” ቃሉን ሁላ ሳይጨርስ ተቀበልኩት

“ያስጠላኛል።” ዛሬ ምን ሆኜ ነው የማስበው የሚያመልጠኝ?

መጀመሪያ ደነገጠ። ከዛ ከት ብሎ ሳቀ። ከሶፋው ተነስቶ እግሬ ስር ቁጢጥ ብሎ …. እጆቹን እግሬ ላይ አድርጎ ወደ ላይ እያየኝ እየተንፈቀፈቀ ሳቀ…. ቡፍ ይላል እያረፈ….
“ምንም የሚያስቅ ነገርኮ አልተናገርኩም።”
“(ጭራሽ ከት ብሎ እየሳቀ) እንደሱ አድርገኝ ….. አዎ እሱጋ በለው ….. ብለሽኝ የነበረበት ዘመን እንደነበረ ትዝ ብሎኝ ነው።” ብሎኝ መንፈቅፈቁን ቀጠለ

“የቱጋ መቼ እንዳስጠላኝ አላውቅም።” አልኩት እንደማፈር እያደረገኝ
“ለኔ ያለሽ ስሜት የቀነሰብሽ ቀን” አለኝ ኮስተር ብሎ ቀጠል አድርጎ “ለምን በግልፅ አልነገርሽኝም? እያስጠላኝ ነው ማድረግ አልፈልግም ለምን አላልሽኝም?”

“ባሌ አይደለህ? ሴክስ ማድረግ አልፈልግም ይባላል?”
“ባልሽ መሆኔኮ አንቺን የማስደሰት ሀላፊነትም አብሮ ይሰጠኛል። abuse እያደረግኩሽ እንድደሰት መብት አይሰጠኝም።” አለኝ። ምንጣፉ ላይ በቂጡ ተቀመጠና እንደመተከዝ እያለ….

“ልነግርሽ የሚገባ ነገር አለ!” አለኝ
“አውቃለሁ!” አልኩት። ግራ ገባው። እንዴት እንዳወቅኩ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሬ ነገርኩት።
“እንዴት አልጠየቅሽኝም? እንዴት አስቻለሽ?”
“አንተ ስንት ዘመን ሁሉ አስችሎህ ዝም ብለኸኝ የለ?”

“እንደዛ ነው የምታስቢው? ምናለ በይሆናል ራስሽን ከምትቀጪ ብትጠይቂኝና የሚሰማኝን ብታውቂው? እኔኮ በዓይኔ ነው ያየሁሽ። የምጠይቅሽ ጥያቄ አልነበረኝም። ራስሽን ይቅር ያላልሽው አንቺ ነሽ። እኔ ገና ድሮ ይቅር ብዬሽ አልፌዋለሁ።”

“ምን ያህል ጊዜያችሁ ነው?”

“ካወቅኳት?” በጭንቅላቴ ንቅናቄ ‘አዎ’ አልኩት

“ከተዋወቅን ስድስት ወር ገደማ። …….ስለፍቅር ማውራት ከጀመርን አንድ ወር …….ከሳምኳት ሁለት ሳምንት …….” ከዛስ የሚለውን አይኔን አፍጥጬ እጠብቀዋለሁ።

“አድርገን አናውቅም። ታምኚኛለሽ?”

‘አዎን’ አልኩት በጭንቅላቴ ንቅናቄ። ….. ዝም ተባባልን!! ….. ወርጄ አጠገቡ ተቀመጥኩ። …. ምን እያሰበ እንደሆነ ልጠይቀው እፈልጋለሁ። ግን ከአፌ አይወጣልኝም። አቅፎ ትከሻው ላይ አስደገፈኝ። ዝም ተባብለን ብዙ ከቆየን በኃላ … …. አቅጣጫውን ቀይሮ ከፊቴ ተቀመጠ። በጣቶቹ አገጬን ደግፎ ቀና አድርጎኝ አይኖቹን አይኖቼ ውስጥ ዘፍዝፎ

“ፍቅሬ እኔ ስላበድኩልሽ ያላንቺ ፍላጎት የራሴ አድርጌ ላቆይሽ እንደማልችል አውቃለሁ። ምንድነው የምትፈልጊው? መለያየት ከሆነ የምትፈልጊው am ready now. ቢከብደኝም ልለቅሽ ዝግጁ ነኝ!! ምንድነው የምትፈልጊው? እንደገና መሞከር ነው የምትፈልጊው? Am ready … አሁን ግን እኔን ወይም ቤተሰብሽን ሳይሆን ራስሽን ሰምተሽ ራስሽ ወስኚ .. …. የፈለግሽውን ጊዜ ያህል ውሰጂ የሚያስቸኩለኝ ጉዳይ የለብኝም።” አለኝ

“እሷስ?” (ኤጭ ዛሬ ምንድነው ችግሬ የማስበውን የማወራው?)
“(ሳቅ አለ) እሷ ስላንቺ ታውቃለች ጣጣዬን እስክጨርስ ላለመገናኘት ተስማምተናል።”
“ለመወሰን ብዙ ጊዜ ቢፈጅብኝስ?”
“10 ዓመት ጠብቄሽ የለ? እጠብቅሻለሁ።” አለኝ። ከጀርባዬ መጥቶ እግሮቹ መሃከል አድርጎኝ ካቀፈኝ በኃላ “ያ የሚያስጠላሽንም ነገር አናደርግም (ድክም ብሎ እየሳቀ) ሆ ሰው ፍሰሃ ያስጠላዋል? (ቡፍ ካለ በኃላ) ራስሽ ፈልገሽ ያውም ‘እባክህ ፍቅሬ’ ካላልሽኝ አናደርግም” ብሎኝ እጁን በቱታዬ ስር ሰዶ ወገቤን አቀፈኝ።

ይሄ ሰውዬ ዛሬውኑ እባክህ ሊያስብለኝ ነው እንዴ?

ክፍል ስድስት

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...