Tidarfelagi.com

ባሌ እንዳመነዘረብኝ ባወቅኩ ጊዜ… (ክፍል ሦስት)

“ልጅ ልሰጥሽ ስለማልችል ትተይኛለሽ?” አለኝ
“ስንጋባም መውለድ እንደማትችል ታውቅ ነበር?”
“አዎ ”
“ለምን አልነገርከኝም?”
“እንዳላጣሽ ፈርቼ። ብነግርሽ ኖሮ ታገቢኝ ነበር?”
“ምርጫ አልሰጠኸኝምኮ! ከልጄና ከፍቅርህ እንድመርጥ ምርጫ አልሰጠኸኝም! ራስህን ራስህ መረጥክልኝ!! ”
“እኔ ብሆን ልጅ አልሰጠሽኝም ብዬ አልተውሽም! ይሄን የሚሻገር ፍቅር አለኝ። ”
(ከዚህ በላይ የሚሆን ፍቅር ከሌለሽ ተይኝ የሚል መልእክት ነው ያለው።)

የዛን ቀን ባሌ የሆነ መገኘቱ ከልቤ ላይ ግምስ ሲል ታወቀኝ። ግን ምንም አላልኩም። እንዴት እንደሆነም ለራሴ መግለፅ ይከብደኛል። በቃ ግምስ ብሎ ተናደብኝ። ፈልጌው ነው? የሆነ ሴትነቴን አታሎ የቀማኝ መሰለኝ። ግን ዝም አልኩ።

በሆነ መንገድ ራሴን እንድወቅስ ማድረግ ይችልበታል!! ቆይ መውለድ ትችላለህ ወይስ አትችልም? ተብሎ ይጠየቅ ነበር? እንደማይችል ሲያውቅ ሊያሳውቀኝ ይገባ የነበረው እርሱ አልነበር? ግን በቃ ይችልበታል። ማጣራት ነበረብኝ ብዬ ራሴን ወቀስኩ። ዝም አልኩ።
‘እናት ልታደርገኝ ስለማትችል በቃኸኝ!’ይባላል? አይባልም! መሃን ስለሆነ ፈታችው ሲባል ጆሮ ላይ ጭው ይላል አይደል? ዝም አልኩ!

ለአመታት ዝም አልኩ። ስራ ይሸኘኛል። ከስራ ይመልሰኛል። ቁርስ ያበስልልኛል። ምሳ አበስላለሁ። እራት ያበስላል። እሱ ምንም ዝንፍ ያለ ነገር የለውም። ደከመኝ ያልኩ ቀን እግሬን አጥቦ አሽቶ ያስተኛኛል። ሲለው እንደሰርግ ቀኔ ተሸክሞ ወደአልጋ ይወስደኛል። ሞከርኩ። የተጋባን ሰሞን ይሰማኝ እንደነበረው ሲነካኝ ደስ የሚለኝን ፣ ሲስመኝ አልጋው የሚያምረኝን እሳት ላመጣው ታገልኩ። አቃተኝ!

ምንም ሳያወራ እራሴን እንድወቅስ ማድረግ ይችልበት የለ? እሱ እንዲህ ጥሩ እየሆነልኝ እኔ ለምን እንደሱ መሆን አቃተኝ እያልኩ ራሴን ረገምኩ። ፍቅሬ ስላለቀ ራሴን ወቀስኩ።

ፍቅር መስራት ፍቅር መስራት መሆኑ ቀርቶ ስራ መስራት ሆነብኝ። በአፌ እንቢ እንዳልለው የምሰራው ስራ አለኝ በሚል ሰበብ እሱ እንቅልፍ እስኪወስደው እየጠበቅኩ መተኛት ሆነ ልምዴ። ማምለጥ ያቃተኝ ቀን እሱ ላቡ ጠብ እስኪል ሲለፋ እንባዬን እንዳያይ እታገላለሁ። (አንዳንዴ የኔ ባል ብቻ ነው የገነት በር ይመስል የማህፀን በር ላይ እንዲህ የሚተጋው? የሚል ሀሳብ ይመጣልኛል። ተፈጥሮ እንኳን እንዴት አይነግረውም? ደርቆ እያታገለው በምራቁ እያራሰ የሚጋጋጠው የዘለዓለም ህይወት ሊያተርፍበት ነው ወይስ የስጋ ደስታ?)

እንደደነዘዝኩ ብዙ ዓመት ዓመትን ደረበ።
በትዳር ብዙ የቆየች አብራኝ የምትስራ ሴትን “እሱ ነገር እንዴት እየሄደልሽ ነው?” ብሎ መጠየቅ ያምረኝና ስንቴ ከአፌ እመልሰዋለሁ።

ከብዙ እንዲህ ያለ ቀናት በኋላ አለቃዬ ሊያማልለኝ ጀመረ። የሆነ እለት እጄን ሲነካኝ ባሌ ድሮ ሲነካኝ የሚሰማኝ እሳት ተሰማኝ። ባልሰማ አለፍኩት። ግን ሰምቼዋለሁ! ወላ ፈገግ ብያለሁ ለራሴ ‘ለካ የሆነ ነገር ጎድሎኝ አይደለም።’ አልኩ። ጭራሽ ይሄ ነገር ከመሽኛነት ውጪ ለራሴ ጥቅም ላላውለው ነው ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበራ!! ባለግኩ!

ከቅሌቴ በኋላም እሱ ዝንፍ ያለ ነገር የለውም። ሳይናገር ራሴን እንድወቅስ ማድረግ ይችልበት የለ? ዝምታው “አየሽ ብትሄጂብኝም ስለማፈቅርሽ እንዳጣሽ አልፈልግም” የሚል መልእክት አለው።

ዛሬ ልፋቱ ይቅርብኝ ያልኩ ቀን ያለ ምንም ቃል “ምነው ለኔ ሲሆን ነው? ለማንም ጠረጴዛ ላይ አንጋለሽው አልነበር?” የሚል መልእክት ያስተላልፍልኛል። እንዴት ነው ግን ሳያወራ መልእክቱ የሚደርሰኝ? እናቴ ቤት ሄድኩ።

የሆነውን እና የሚሰማኝን ሁሉ ለእናቴ ነገርኳት። ከሁሉም አብልጣ የሰማችኝ ከአለቃዬ ጋር መባለጌን ነው። ዘገነንኳት።
“ይሄን ጉድሽን ለራስሽ እንኳን ደግመሽ እንዳትናገሪ! በይ ሂጂና ይቅርታ ጠይቂው! እንዴት ያለው እግዚአብሄር የባረከው ነው? ከነዚህ በደልሽ ልቀበልሽ ማለቱ? ደሞ ካንቺም ብሶ ቤትሽን ለቀሽ ትወጫለሽ?” አለችኝ። እሱ ይቅርታ እስክጠይቀው አልጠበቀም። እናቴ ቤት ድረስ መጣ። ምንም እንዳልተፈጠረ ስሞኝ ይዞኝ ተመለሰ።

ስንኖር …..ስንኖር ብዙ ስንኖር ነው የስልኩን መልእክት ያገኘሁት።
የሆነ ስርየት የሆነልኝ የመሰለኝ። እነሆ ሀጥያቴ በሀጥያቱ ታጠበ ……

ክፍል አራት

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...