Tidarfelagi.com

ባሌ እንዳመነዘረብኝ ባወቅኩ ጊዜ እጅጉን ደስ አለኝ!! (ክፍል አንድ)

“ቦታችን በተለመደው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። አፈቅርሃለሁ!” የሚል መልዕክት ነው እንዲህ ያስቦረቀኝ!!

እሱ ጏዳ ቁርስ እያበሰለ የሚያማስለው የመጥበሻ ድምፅ ይሰማኛል። ስልኩ መልእክት ሲቀበል ድምፅ አሰማ ያለወትሮዬ እጅ ጥሎኝ ስልኩን አነሳሁት።

አንደኛ የራሳቸው ቦታ አላቸው! እኔና እሱ የኛ የምንለው ቦታ ኖሮን አያውቅም!! ከቤታችን ውጪ
ሁለተኛ የተለመደ ሰዓት አላቸው። እኔና እሱ ለምንም የተለመደም የተመደበም ሰዓት የለንም። የልደት ቀኖቻችንን እንኳን እረስተነው አልፎ … ‘ለካ ትላንት ነበር’ የምንባባልበት ጊዜ አለ።
ሶስተኛና ዋነኛው ታፈቅረዋለች።
ይሄ ሲሰላ ቀመሩ እሱም ከኔ በላይ ያፈቅራታል ማለት ነው!
ደስ ሲል …..

“ምን ተገኘ?” ይለኛል አስሬ የሰራልኝን ቁርስ እያጎረሰኝ
“ምነው?”
“በጣም ደስ ብሎሻል! ይሄን ፈገግታ ካየሁት የማላስታውሰውን ያህል የጊዜ ርዝመት ያህል ዘመን ሆኖ ነበርኮ!” አለኝ የተለመደ የተመጠነ ፈገግታውን እየፈገገ… ዝም አልኩ

እያመነዘርክብኝ እንደሆነ ሳውቅ ነው ደስ ያለኝ! ይባላል? አይባልማ!!
.
.
.
ሊወጣ ይለባብስ ጀመር።
“እሱን ሸሚዝ ቀይረው። ቅዳሜ አይደል? ፈካ ያለ ነገር ልበስ.. ቆይ እኔ ልምረጥልህ!” ብዬው ቄንጠኛ ሸሚዝ እፈልግ ጀመር … ተዝረክርኮ ሄዶ የባሌ አፍቃሪ ፍቅሯ እንዲቀንስ አልፈልግማ! ተውቦ ነው መሄድ ያለበት!!

አንዴ ፀጉሩን አንዴ ጫማውን … ደሞ ኮሌታውን ሳስተካክልለት ግራ ተጋብቶ ያየኛል።
“ዛሬ በጣም ጥሩ ሙድ ላይ ነሽ!” ብሎኝ ከንፈሬን ስሞኝ ወጣ!!

ልፀልይ ሁሉ ቃጣኝ። ግን እንዲህ ያለው ፀሎት ለእግዜር ነው ለሰይጣን የሚቀርበው?
“በምንዝርናው እንዲፀና አድርግልኝ! ደግሞ ደጋግሞ እንዲያመነዝር እርዳው!! ”
እንዲህ ያለው ድርጊት አምላክን አይመለከትም! ለዲያቢሎስ የትብብር ውይም የድጋፍ ጥያቄ ላቅርብ? ያው እኔ ባልጠይቀውም ወጥሮ ማስመንዘር መደበኛ ስራው ነው ብዬ ነው።

የአስር ዓመት ትዳሬ ነውኮ….. የመጀመሪያው ትሁን? እንዳገባ ታውቅ ይሆን? ሄዶ ሲስማት የኔን ከንፈር ልቅላቂ እንደምትስም ታውቅ ይሆን? እቤቱ ሲገባ የሚያስኮንን አፍቃሪ መሆኑን ታውቅ ይሆን? ዛሬም ከ10 ዓመት በኃላ እያጎረሰኝ እንደምበላ ታውቅ ይሆን? ወይስ እሷምጋ ዝንፍ የማይል አስኮናኝ አፍቃሪ ይሆን?

“ውሎህ እንዴት ነበር?”
“ፍቅሬ ለ2 ሰዓት ብቻ ነውኮ የተለያየነው?” አለኝ ከሷጋ እንደመጣ
“እኮ ቢሆንስ ”
” እሺ ቆንጆ ነበር!” አለኝ መገረም ሳይለየው

ተጣልተው ይሆን? ተጨቃጭቀው? ለምንድነው የተለየ ፊት የማያሳየው? ምን አይነቷ ናት? ለሁለት ሰዓት እያገኘችው እንዲስቅ ማድረግ ያቅታታል? ወይስ እሷም እንደኔ መፈቀር ደከማት?

ባጠገቡ ሳልፍ መቀመጫዬን ደለቅ አደረገኝ!! እህህህ በቀን ሁለት እሙሙ አይሰለቸውም? ወይስ እሷ አትሰጠውም? እሷ እንደእኔ ሚስት ስላልሆነች ግዴታ የለባትም ይሆን? ወይም እንደኔ በገዛ ሀጢያቷ ስላልታሰረች ካልመሰላት ታፆመዋለች?

እኔ ሳገባው ቄሱ በመከራውም በደስታውም … በድህነቱም በሀብቱም … ብለው ያስማሉኝ እንጂ መሳቢያው ውስጥ እንደሚያስቀምጠው ገንዘብ በፈለገ ጊዜ እየከፈተ የሚዘግነው ንብረት እንዲሆን እሙሙዬን ማስያዜን አላስታውስም! (መሀላው የማላውቀው ውስጠ ወይራ ይኖረው ይሆን? ታዲያ የሚስትነት ግዴታዬ እንደሆነ የማስበው ማን ምን ብሎኝ ነው? ዛሬ ይለፈኝ ካልኩት የበደልኩት የሚመስለኝ በየትኛው ህግ ነው?

አንድ ቀን …. ርቆ እንደህልም በሚታወሰኝ አንድ ቀን በሰራሁት በደል …. ራሴን በእዳ አስይዣለሁ!!
“ሁለተኛ ቂጤን እንዳትነካኝ!” አልኩት ኮስተር ብዬ
“እንዴ? ለምን?”
“የራሴው ቂጥ አይደል?”
“አዎ”
“እንደገና ደግሞ የራሴው ሰውነት ላይ አይደል ያለው? ራሴው አይደል የተሸከምኩት?”
“እንዴ ፍቅር ምን ሆነሻል?”
“ሌላ ደግሞ አንዳንድ አንዳንድ ጊዜ ተሸከምልኝ ብዬ አላስቸገርኩህም አይደል? ደሞም ቂጤን በማጣፍት የሚመለስ የተበደርኩት ብድርም የለብኝምኣ?”
“ምንድነው ጉዱ?”
“በነዚህ ከተስማማን በገዛ ቂጤ የማዘው እራሴው ነኝ! ደስ ባለህ ሰዓት እጅህን እየላክ በጥፊ እንድታላጋው አልፈቅድም!! አበቃሁ!!” ብዬው ማሳረጊያ የተለመደ ፈገግታ ፈገግ ብዬ ሄድኩ።

ክፍል ሁለት  

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...