Tidarfelagi.com

ባለ ከረሜላው ሰውዬ

ቢሮ ሆኜ ከስራ ፋታ ሳገኝ ማረፊያዬ ዩ ቲዩብ ነው።

የድሮ ዘፈን እየጎረጎርኩ አዳምጣለሁ። ዛሬ ጠዋት የ80ዎቹ እና 90ዎቹን አር ኤንድ ቢ ሙዚቃዎች እየሰማሁ ሳለ የልጅነት አእምሮዬ ላይ ተነቅሶ ከቀረ አንድ ዘፈን ጋር ተገናኘን።

ርእሱ ‹‹ካንዲ ሊከር›› ዘፋኙ ማርቪን ሴስ ይባላል።

ገና ማዳመጥ ከመጀመሬ በትዝታ ተሽቀንጥሬ ሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ላይ አረፍኩ።

ዘመኑ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ ከሰአት ዝግጅት ብቸኛ መዝናኛ የነበረበት ነበር። አብሶ የ11 ሰአቱ ድራማ። አብሶ የነሐይሉ ፀጋዬ ድራማዎች ትዝ ይሏችኋል? እነዚያ በቲና ተርነር ሙዚቃ መግቢያ የምንሰማቸው ድራማዎች። ቲና ‹‹አህህህህ…..›› ብላ የምትከፍታቸው ድራማዎች? ትዝ አሏችሁ? እንደዚያ ስትል ድራማዎቹ ከእሷ አፍ ውስጥ እ…..ፍ…..ብለው የሚወጡ ይመስለኝ ነበር። ‹‹ፕራይቬት ዳንሰር›› የሚባለው ዝነኛ ዘፈኗ ከእኛ ድራማዎች ሴራ እና መቼት ጋር ምንም ግኑኝነት እንደሌለው ለመረዳት ሃያ አመት ፈጅቶብኛል።

እሱን ተዉትና ያ ዝግጅት የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎችን በብቸኝነት ከምናደምጥባቸው ጥቂት ዝግጅቶች አንዱም ነበር። በተደጋጋሚ ከሚጫወቱት ሙዚቃዎች ደግሞ አንዱ የማን ነበር? የዚህ ማርቪን ሴስ የተባለ ሴሰኛ ሰውዬ ‹‹ካንዲ ሊከር›› ዘፈን።

ሴሰኛው ማርቪን፣
‹‹ቤይቢ – ሌትሚ ሊክ ዩ አፕ- ሌት ሚ ሊክ ዩ ዳውን፣
አይ ዋነ ቢ ዩር ካንዲ ሊከር ገርል…›› ብሎ ይጀምርና እየባሰበት ይሄዳል።

በዘመን ሂደት ውስጥ የዚህ አንድ ሙዚቃ መረዳቴ ከእድሜዬ ጋር መለዋወጡ ዛሬ ላይ ያስቀኛል። ሁለት አስርት አመታት በፈጀው የማዳመጥ ሂደቴ ‹‹ካንዲ ሊከር›› ይገባኝ የነበረው እንደሚከተለው ነው።

ከ10-11 አመት ‹- ‹ባለ ከረሜላው ሰውዬ››

የአስር እና አስራ አንድ አመት ልጅ ሳለሁ ከዚህ ዘፈን የሚሰማኝና የማውቀው ብቸኛ የእንግሊዝኛ ቃል ‹‹ካንዲ›› ነበር። እሱንም የነገረኝ ሩሲያ ተምሮ የመጣው አጎቴ ነው። ስለዚህ ዘፈኑን ተደጋግሞ በሰማሁት ቁጥር ሁሌም የሚመስለኝ ስለ ባለከረሜላ ሰውዬ የተዘፈነ ነበር። የሆነ ብዙ ከረሜላዎች ያሉት፣ እየዞረ ከረሜላ የሚሸጥ ሰውዬ ይታየኝ ነበር። በጊዜው የማውቃቸውን የከረሜላ አይነቶች…ጉንፋን ከረሜላ፣ ደስታ ከረሜላ እና ዱላው ከረሜላ (ቀይ ሆኖ ባለ ነጭ ሰረዝ) ተሸክሞ የሚዞር ሰውዬ።

ይሄው ነው።

13-14 አመት- ‹‹ከኋላ የሚያለከልከው የምን ውሻ ነው?››

አደግ ስል ከዘፋኙ ጀርባ የማለክለክ ድምፅ እና ሌሎች ቃላትን መስማት ጀመርኩ። ምስጋና ለተማሪ ዲክሽነሪዬ በዚህ ጊዜ የ‹‹ሊክ››ን ትርጉም ደርሼባት ነበር።:

ልብ በሉ። ‹‹ካንዲን›› ቀድሜ ይዣለሁ። አሁን ደግሞ ‹‹መላስ›› ን ተረድቻለሁ። ስለዚህ ከባለከረሜላው ሰውዬ ይልቅ የሚላስ ወይ የሚመጠጥ ከረሜላ ላይ የተመሰረተ ዘፈን መሆኑ ወገግ ብሎልኝ ነበር።፡ ሚስጥሩ ያልተፈታልኝ ነገር ቢኖር ግን ከኋላ ሲያለከልክ የምሰማው ውሻ ነው? ከረሜላ እና ውሻ ምን አገናኛቸው?

‹‹ሌት ሚ ሊክ ዮ አፕ- ሌትሚ ሊክ ዩ ዳውን፣
ተርን – ቤይቢ ሌትሚ ሊክ ዩ ኦል አራውንድ
ኦህ…ሌት ሚ ሊክ ዩ አፕ…

ላይክ ዩር ላቨር ሹድ….››

ዘፋኙ ከፊት ‹‹አሃሃሃሃሃ›› ሲል ከኋላው የሚያለከልክ ውሻ ይሰማኛል። ፈረንጅ አገር ከረሜላ በሊታ ውሻ አለ?

ከ16-20 ‹‹ይሄ ስድ አደግ! እነዚህ አግድም አደጎች!››

‹‹አይ ዋነ ሊክ ዩ ኢን ዘ ሞርኒንግ፣
ኤንድ ኢፍ ዛት ኢዝ ኦራይት ቤይቢ- አይ ዊል ሊክ ዩ ኢን ዘ ኢቭኒንግ።

ኤንድ ኢፍ ዩ ሪሊ ላይክ ዘ ዌይ አይ አም ሊኪንግ ዩ ገርል – አይ ዊል ሊክ ዩ ሌት አት ናይት…

አይ ጀስት ዋና ቢ …ኤት ደይስ ኤ ዊክ…
ዩር ካንዲ ሊከር ገርል››

በ16 አመቴ…

እድሜ ለጎበዝ የእንግሊዝኛ መምህሬ (ያስተማረኝን እንግሊዝኛ ለዚህ ማዋሌን ቢያውቅ ደረቱን እየደቃ ‹‹ዋይ ለኔ ዋይ ለኔ›› ይል ነበር) ግጥሙን በደረቁ ስረዳው ብዥታዬን ለማጥራት (ሃሃ) የመጀመሪያ የወንድ ጓደኛዬን ስለ ዘፈኑ አወራሁት።

በእንግሊዝኛም በሕይወት ክህሎትም ከኔ ቀድሞ ሙክክ ያለው ቦይፍሬንዴ (የመሃል መርካቶ ልጅ ነበር) የዘፈኑን ጭብጥ ለነገ ሳይል ፍርጥርጥ አድርጎ ነገረኝ።

‹‹ወይኔ ይሄ ስድ አደግ! ወይኔ እነዚህ ከኋላ እንደ ውሻ የሚሰራቸው ሴቶች…ምን አይነት አግድም አደጎች ናቸው!›› ብዬ እምቡር እምቡር አልኩ።

ከድንጋጤዬና እና እድሜዬን ከቀደመ የአልጋ ላይ ጨዋታ እውቀቴ ሳገግም ግን ያሰብኩት አንድ ነገር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዝግጅት ሰዎችስ ይሄን ሙዚቃ ለአመታት ሲያጫውቱት እንደኔው ቀስ በቀስ እየተረዱት አድገው ነው ወይስ በፍፁም ግዴለሽነት!? አርታኢዎቹስ? ከእጅ አይሻል ዶማ ሆነው ነው?

ለማንኛውም ከአመታት በኋላ የእኛዋ ማርቪን ሴስ የሆነችውን ትእግስትን አውቄ ‹‹ቱቱዬ››ን እስክሰማ ድረስ በዘፈን እንደዚያ ተሸማቅቄ፣ እንደዚያም ደንግጬ አላውቅ!

የዛሬ ልጆችስ በአይናቸውም በጆሯቸውም በገፍ የሚገባውን የዘመኑን ‹‹ሊክ ዩ አፕ›› ሙዚቃና ፊልሞች እንዴት ሆነው እያስተናገዱ ይሆን?

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...