Tidarfelagi.com

ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን (1928-1998)

ጸጋዬ ገብረ መድህን (1928-1998) ባዳ ተብላ በምትታውቅ አምቦ ካተማ አካባቢ በምትገኝ ተራራማ ቦታ ተወለዱ። በአምቦ ማአረገ ሕይወት ቀኃሥ ትምህርት ቤት ከዚያም ጀነራል ዊንጌትና በአዲስ አበባ የንግድ ትምህርት ቤት በአገር ውስጥ ትምህርታችውን ከገፉ በኋላ በቺካጎ ብላክስቶን በህግ ትምህርት ተመርቀው በ1952 እንደ ወጡ በለንደን ከተማ የቴአትር ትምህርት በሮያል ኮርት ቴአትርና በፓሪስ ኮሜዲ ፍራንሴዝ ተከታትለዋል። ያኔ ተምሮ ወደአገር መመለስ ኩራት በነበረበት ዘመን ወደ ኢትዮዽያ ተመለሰው ከ1954 እስከ 1964 የቤሄራዊ ቴአትር በአርቲስቲክ ዳይሬክተርነት አገለግለዋል። ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ዲፓርትመንትን አቋቁመዋል። ሆኖም በ1960ዎቹ ደርግ አብዛኛውን የቴአትር ስራዎቻቸውን ሲያግድ እሳቸውንም ታስረው ነበር። ብላቴን ሎሬት ጸጋዬ በርካታ ግጥሞችን፥ የቴአትር ሰራዎችን የተለያዩ መጣጥፎችንና ዘፈኖችን አበርክታዋል። እንደ፡ አዉሮፓ፡ አቆጣጠር፡ በ 2002 ዓ.ም. የብላቴን ሎሬት ጸጋዬ፡ ገብረ መድህን፡ ግጥም፡ (“Proud to be African”) በአዲስ፡ በተመሰረተዉ፡ የአፍሪካ፡ አንድነት፡ መህበር፡ በሕዝብ፥ መዝሙርነት፡ ከ ብዙ ተፎካካሪዎች ልቆ ተመርጧል። በትምሕርት እየጎለመሰ ሲሄድም ደራሲነቱን ገጣሚነቱን እንዲያ ሲልም ፀሃፊ-ተውኔትነቱን በዋነኛነት በጎልማሳነት ዘመኑ ደግሞ ማህበረሰባዊ ሃያሲነት እና የአፍሪካ የሰው ዘር እና የቅብጥ ቋንቋ እና ባህል ጠቢብነትን አክሎበት እስከ እለተ ህልፈቱ ዘልቋል።

መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!
አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ፤ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ…
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

በነገራችን ላይ “ባለቅኔ ሎሬት” (Poet Laureate) የተሰኘው ማዕረግ የተገኘው ከጥንታዊት ግሪክ (በኋላም ሮማውያን) ጥበበኞችንና አሸናፊዎችን የማክበር፣ የመሾምና የመሸለም ልማድ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወይራ የባለ ቅኔዎች የበላይ ጠባቂ የሆነው የአፖሎ ቅዱስ ዛፍ ነው ተብሎ በጥንታዊ ግሪካውያን ይታመንበት ስለነበር፣ በተሸላሚዎች አናት ላይ በወይራ ዘለላ የተጐነጐነ አክሊል (Laurel Crown) ይደፋላቸው ነበር፡፡በዘመናዊው የዓለም ታሪክ፤ “የባለ ቅኔ ሎሬት” ማዕረግ ሹመት ሆኖ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ ውስጥ ሲሆን ማዕረጉም የሚሰጠው የላቀ ሥራ ላበረከተ ባለ ቅኔ ነበር፡፡ ለፀጋዬ ገብረ መድኅን በ”ባለ ቅኔ ሎሬት ማዕረግ” መጠራት ምክንያት የሆነው በዓለም አቀፍ የባለ ቅኔ ሎሬቶች ሕብረት የአለም ባለቅኔዎች ጉባኤ (United Poets Laureate International – World Congress of Poets) ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም በፊሊፒንስ ዋና ከተማ ሚኒላ ውስጥ የተመሰረተው የዚህ ዓለም አቀፍ ማህበር አላማ፤ በጥበብ (በተለይም በቅኔ) አማካይነት አለም አቀፋዊ ወንድማማችነትንና ሰላምን ማራመድ ነው፡፡ ማህበሩ በሁለት አመት አንድ ጊዜ በሚያካሂደው የአለም ባለቅኔዎች ጉባኤ ላይ ከመላው አለም የተሰባሰቡ ባለ ቅኔዎች ሥራዎቻቸውን ለጉባኤው ያቀርባሉ፤ እርስ በእርስም ስለ ቅኔ ይወያያሉ፣ ከዚህ በተጨማሪም ቅኔን የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች በጉባኤው የሚቀርቡ ሲሆን ለምርጥ ባለ ቅኔ ደግሞ የምስክር ወረቀት፣ ሜዳልያ እና የተከበረው ባለ የወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል (Golden Laurel Crown) ይበረከትለታል፡፡ ከሐምሌ 14 ቀን እስከ ሐምሌ 18 ቀን 1989 ዓ.ም በእንግሊዝ አገር፣ ባኪንግሀምሻየር ክፍለ ግዛት፣ ሀይ ዋይኮምብ ከተማ ውስጥ በተካሄደው አሥራ አምስተኛው የዓለም ባለ ቅኔዎች ጉባኤ ላይ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን “ኤዞፕ” የተሰኘውን ቅኔውን ከማሰማቱም ሌላ “Poetry Conquered Darkness and the World was Saved” በሚል ርእስ ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የዓለም ባለ ቅኔዎች አሥራ አምስተኛ ጉባኤ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን በአገሩ ቋንቋና በእንግሊዝኛም ጭምር ያበረከታቸውን ግጥሞች፣ ቅኔዎች እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን በመመርመር፤ ስራዎቹም የሰው ልጅን እኩልነት፣ ነፃነት፣ ወንድማማችነትና ፍቅር አበክረው የገለጡ መሆናቸውን ተረድቶ ባለ ቅኔ ሎሬት የሚያገኘውንና የተከበረውን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ሸልሞታል፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ይህንን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ከተሸለሙት ታዋቂ የአለም ባለ ቅኔዎች መካከል የአሜሪካው ባለ ቅኔ ሎሬት ሮበርት ትንስኪ፣ የሩስያው ኢጐር ሚኮሌሴንኮ፣ የፈረንሳዩ አሲት ቻክሮቮርቲ እና የእንግሊዙ ጆን ዋዲንግተን ፌዘር እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከተለያዩ ግጥሞች በተጨማሪ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ከ35 ተውኔት በላይ ደርሰዋል ከነዚሀም መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው

1. እሳት ወይ አበባ(ግጥምና ቅኔ)
2. የዳኒሲዩስ ዳኝነት(ተውኔት)
3. በልግ(ተውኔት)
4. የደም አዝመራ(ተውኔት)
5. እኔም እኮ ሰው ነኝ(ተውኔት)
6. የከርሞ ሰው(ተውኔት)
7. የእሾህ አክሊል(ተውኔት)
8. ክራር ሲከር(ተውኔት)
9. አስቀያሚ ልጃገረድ(ተውኔት)
10. እኝ ብዬ መጣሁ(ተውኔት)
11. ቴዎድሮስ(ተውኔት)
12. ምኒልክ(ተውኔት)
13. ጴጥሮስ ያቺን ሰአት(ተውኔት)
14. ዘርዓይ ደረስ(ተውኔት)
15. ጆሮ ገድፍ(ተውኔት)
16. ሀሁ በስድስት ወር(ተውኔት)
17. እናት ዓለም ጠኑ(ተውኔት)
18. መልእክተ ወዛደር(ተውኔት)
19. አቡጊዳ ቀይሶ(ተውኔት)
20. ጋሞ(ተውኔት)
21. ሀሁ ወይም ፐፑ(ተውኔት)
22. ቴራቲረኞች [ የምፀት ኮሜዲ፥ አልታየም ] (ተውኔት)
23. ዐፅም በየገጹ (ተውኔት)
24. ሰቆቃወ ዼጥሮስ(ተውኔት)
25. ትንሣኤ ሰንደቅ ዓላማ(ተውኔት)
26. የመቅደላ ስንብት(ተውኔት)
27. ጥላሁን ግዛው(ተውኔት)
28. ዐፅምና ፈለጉ(ተውኔት)

ጸጋዬ በ1990 ለጉበት በሽታ ሕክምና በመሻት ወደ ማንሃታን በሄዱበት ነበር ያረፉት። ፀጋዬ ከማረፉ አራት አመታት ቀደም ብሎም በዶ/ር ኄራን ሠረቀብርሃን አማካይነት በዋሽንግተን ዲሲ የፀጋዬ ግጥሞች በሲዲ ተቀርፀው ተመርቀዋል። የስንብት ዝግጅት ይሆን። ትንቢት አስቀድሞ ለነገር እንዲሉ። የማሳረጊያ ግጥሙም ይህንን ተስፋ ቢስነትን አመላካች ይሆን?

የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ሕይወት ስከረክም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም

ነፍስ ይማር !!

3 Comments

 • olivets897@gmail.com'
  ፍሬዘር commented on August 2, 2017 Reply

  እናመሰግናለን!

 • mulu getnet commented on April 5, 2019 Reply

  hulem zemen yemayshirew bale tarik sew.

 • yidinek2006@gmail.com'
  Yidnekachew commented on August 16, 2022 Reply

  ፀጋዬ ሰዎች ከሚሉለት በላይ ነዉ….

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...