Tidarfelagi.com

ቡቡ ዘተበሃለ ስንዝሮ (ከ “የስንብት ቀለማት” የተወሰደ)

ተረት ተራች ነኝ፡፡ ድሮ ድሮ እንደ እኔ አይነቱ ተራች፣ ጉዳይ ቀማሚ ፣ የታሪክ ጉድፍ ነቃሽ ‹ሐዳሚ› ይባል ነበር፡፡ በጥንት አፍ እንግዲህ ሐዳሚ ነኝ፡፡ ህይወት ተወሳስባ፣ ተተረማምሳና ተሸፋፍና ልታልፍ ስትል ለአፍታ ጆሮዎ ስር አቆማትና በአንደበቴ (በልሳነ ጥንት፣ በልሳነ ድንጋይ ዘመን ቀባጢሶ) በአጭር ምሳሌና ተረት አሰማምሬ ግልጥ አደርጋታለሁ፡፡ ባይግለጠለጥም በአጥፍተን እንጥፋ አሉባልታ የመለገ ጆሮዎችዎ ውስጥ ወጌን እንደ ኩክ አጣብቄ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፡፡

ከፍጡራን ሁሉ በመረጥኳቸው ውሾች ምሳሌ ለሰው ልጆችና ለውሾች ተረቴን መንገር ነው (የሚሰማኝ ጆሮና ልቦና ሳገኝ)፡፡ ለዚህም ስራዬ እንዲቀለኝ ከ120 በላይ ቋንቋዎችን መናገር እችላለሁ፡፡ ይሄው በቶታነ እምልላችኋለሁ፡፡ ቶታነ ይሙት፡፡ ‹ቶታነ› ማነው? በሉኝ፡፡ ቶታነ ያው የማጂ ልጅ ነው፡፡ ቶታነ አንዱ አምላኬ ነው፡፡ አዋቂና አብራሪ፡፡
የወጣልኝ ስሜ እንደ እናንተ እንደ እናንተ ‹‹ስንዝሮ›› ይባላል፡፡ ሲጀመር ‹‹መንኮብያ›› ነበር የምባለው፡፡ ‹‹መንኮ››– ሲያጥር፡፡ የበለጠ ሲያጣጥር — መንኪ፡፡ እናቴ ገነቴ ስታቆላምጠኝ ያው (ሰው ባይሰማም) ‹‹መንኪዬ›› ትለኝ ነበር፡፡ ነፍሷን ትማር፣ ነፍሷ በፋሌክ(1) ትቀመጥ (በእርግማናችሁም ይሁን በምርቃታችሁ እንዳትደርሱበት፡፡ ምናችሁንም አልፈልግምና)፡፡ ይሄው ገና ሲጀመር ነገር ነገር ያለኝ፣ ነገር ቢያጋጥመኝ ነው እኮ ወገኖቼ፡፡ ወጋችሁ ይፍረስና፡፡

እናቴ ገነቴ የምትባል ልዕልት ነበረች፡፡ ይሄን አታውቁም፡፡ በተረት ብልጣብልጦች ሸፈንፈን አድርገው ‹የስንዝሮ እናት አንዲት የተቸገረች ባሏ የሞተባት ሴትዮ ነበረች› ብለው አሏችሁ በቃ አመናችሁ፡፡ ግድ የለም በነተቡ አእምሮዎች አላሾፍም፡፡ መቼም ሰው ባለው ነው፡፡ እንደናንተ ባይበዛም ደደብነት አላጣም፡፡
የተወለድኩት በዋይዝ ከተማ ነው፡፡ ይሄን አታውቁም፡፡ ምክኒያቱም እንድታውቁ አይፈለግም፡፡ ለመሆኑ ዋይዝ የተባለ መዲና ነበር? አዎ፡፡ በአጭሩ ከአክሱም ቀድሞ ከላሊበላ ቀድሞ ዋይዝ ነበረች፡፡ ጥያቄው ብዙ የተደበቀ ታሪክ ስለሚጎለጉል በማናናቅ ተራች ነን ባዮች ‹ስንዝሮ በአንዲት ትንሽ መንደር ተወለደ› ይሉአችሁዋል፡፡ አሁንም በሰው የአእምሮ ዝግመት አልፈርድም፡፡ እኔም አንዳንዴ አላጣም፡፡ የዘሬ እኔንም ያንዘረዝረኛል፡፡ እናቴ ሶስት እህቶችና ሶስት ወንድሞች ነበሯት፡፡ አጼ ኢትዮጲስ ወይም ኤልካኖ የሚባለው አጎቴ ነበር፡፡ ይሄ ይሄም አልተነገራችሁም፡፡ ያልነገሯችሁ ብቸኛ ወፍ ዘራሽ ሊያደርጉኝ ስለፈለጉ ነው፡፡ ይኼም ምንም አይደለም፡፡ ተረታቸውን እየሰማና እያነበበ ያመነው ኡሪና ሽማግሌ ብዙው ወፍ ዘራሽ ዲቃላ ነው፡፡ አልፈርድም፡፡ እኔም በሆነ ስልት ዲቃላ ነኝ፡፡

በእነዚህ ዋና ዋና መረጃዎች ብቻ እኔ ስንዝሮ ከታሪክ ተሳድጄ ወደ ተረት አለም እንድገባ ሆነ፡፡ ከዚህ በሁዋላ እውነትን ብናገርም በውሸት ሞረድ ሲልም የነበረው የወገኖቼ አንጎል እውነቱን ቆንጥጦ የሚይዝበት ልቡ ስለጠፋ የሚያዳምጠኝ ጆሮ አልነበረም፡፡ ትክክለኛውን ታሪክ የመንገር ልፋቴ ካለመኖር ወደ መኖር እንደመምጣት ነው፡፡ ከሞትኩበት ብራና ተነስቼ የዘመኑ ወረቀት ውስጥ መግባት ልክ መሰለኝ፡፡ የሰው ልጅ የአኗኗር መላ ከወርቅ ወደ ብር፣ ከብር ወደ ነሐስ፣ ከዛ ወደ መዳብ፣ ከዛ ወደ ብረት፣ ከዛ ወደ ተራ ድንጋይ እንደወረደው እንዲሁ እኔም ያልታደልኩ ከብራና በተራ የፈስ ግለት አመድ ወደሚሆን ወረቀት መጣሁ፡፡ ስልጣኔም ይሁን ግለሰብ መቼም ያው ባለው ነው፡፡
እናቴ ሳሉታ፣ ቲካና ሎዛ የሚባሉ ከእሷ የሚወዳደሩ ቆነጃጅት እህቶች ነበሯት፡፡ ሁሉም ቆንጆ ከመሆናቸው የተነሳ ህዝብ የፍቅር አምላክ አድርጓቸው ነበር፡፡ ከወላጅ እናቴ በተቀር እህቶቿ በመልካቸው የታበዩ ነበሩ፡፡ እንደውም እናቴ መልኳ ብቻ ሳይሆን ላቧ በሽተኛ የሚፈውስ ርሄ ነበር ይባላል፡፡ እሷን ሲያዩ ከራስ ምታት የተፈወሱ፣ ከቁርጠት የተላቀቁ፣ ከስርቅታ የዳኑ፣ እያነከሱ መጥተው እየዘለሉ የሄዱ፣ ድምጻቸው የተዘጋ እየሸለሉ ቤታቸው የተመለሱ ሺህዎች ነበሩ፡፡ በአይኖቼ ስላላየሁ እነዚህን ሆነዋል ብዬ አፌን ሞልቼ መማል አልችልም፡፡

እህትማማቾቹ በየወሩ ተያይዘው በግዮን ወንዝ ዳርቻ በናፓታ ለአማልክቶቻቸው ለመጸለይ ሲሄዱ የሚያርፉበት ያማረ አቱት(2) (የተገለለ) ቤተመንግስት አሰርተው ነበር፡፡ አንድ ቀን እዛ በሚዝናኑበትና በሚጸልዩበት እለት እናቴ ገነቴ ሎጋ ውብ አሳ አጥማጅ አይታ በምስ ተያዘች፡፡ ዛሬ ዛሬ ፎንቃ የምትሉት(3)፡፡ ይሄ ከተራ ሰው ጋር መንፏቀቅ፣ መመሳሰስና መሞላፈጥ ለልዕልቶች ያልተፈቀደ ስርአት ነበር፡፡ ምንም ያልጎደለባት አንዲት እንደ አምላክ የምትቆጠር ውብ የነገስታት ዘር፣ ብዙ የጎደለበትን አሳ አጥማጅ ማፍቀር አልነበረባትም፡፡

እናንተ ድሮ የታደላችሁ ዛሬ ያልታደላችሁ ወገኖቼ ሆይ! ስሙኝ፡፡
እናቴ ገነቴ ከአሳ አጥማጅ ጋር ፍቅር እንደያዛት ለሶስቱ እህቶቿ መንገር ፈርታ ሰበብ እየፈጠረች፣ እየተደበቀች ወደ ግዮን ዳርቻ ትሄድ ነበር፡፡ ያልለመዱት አይነት መመላለስ ስታበዛባቸው ሳሉታ፣ ቲካና ሎዛ (በተለይ ሎዛ እማማን አትወዳትም ነበር፡፡ ምነ ቢሉ ሎዛ ከራራ፣ ወግ አጥባቂ ነበረች፡፡ በሚስጥር ቅጽል ‹ሎዛ አረንዛ› ነበር የምትባለው በቤተ መንግስት) ምን አግኝታ ይሆን? ብለው ሰላይ እየላኩ ይከታተሉዋት ጀመር፡፡ ብዙ ሳይቆይ ከወደደችውና ከወደዳት አሳ አጥማጅ ጋር ወንዝ ዳር በፍቅር ስትጫወት መዋልዋን ደረሱበት፡፡ በአንድ የተረገመ ቀንም የምታደርገውን በአይናቸው መመስከር ቻሉ፡፡ ከመዝናኛቸው አቱት ወደ ቤተመንግስት ከተመለሱ በሁዋላ ያጋጠማቸውን ሁሉ ለአባቷና ለንጉሳውያን ቤተሰቦች ነገሩ፡፡ እማማ የምታደርገው ግንኙነት ትክክል እንዳልሆነና በፍጥነት ማቆም እንደሚገባት እልፍኝ ተጠርታ ትእዛዝ ተሰጣት፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን ተመርምራ ድንገት ካረገዘች ሽሉ በመድሃኒት ወጥቶ እንዲገደል፣ ካተቻለም ቀን ተጠብቆ ሲወለድ ወንዝ እንዲጣል ተመከረ፡፡ ይሄንንም መልዕክት ሁሉም እንዲሰማው ጠቢባን በተገኙበት አዛውንት ልብ እንዲሉ፣ ሹማምንት እንዲታዘቡ በእልፍኝ ተነገረ፡፡ እናቴ ገነቴ በዚህ ጨካኝ ውሳኔአቸው ተበሳጭታ ንጉሦች ባሉበት አውድ በቁጣ ከተቀመጠችበት ተነስታ እየተንጎራደች (እናቴ አይደለች)፤
‹‹ለመሆኑ ምን ያገባችሁዋል? ከማልወደው የመኩዋንንት ዘር ከምወልድ ከምወደው አሳ አጥማጅ ስንዝር የሚያህል ልጅ ብወልድ ይሻለኛል›› አለቻቸው አሉ፡፡ ለንጉሡ የሚያዳሉ ሰገሎችና ሟርተኞች እንደ አፍሽ ይሁንልሽ አሉዋት፡፡ ይሄ በእነሱ እርግማን ነበር፡፡ እናም ስንዝሮነቴ በዛች አፍታ ታቀደ፡፡

ባለስልጣኖቹና መኳንንቱ እናቴ ልማድ ስላፈረሰች፣ ከዚህም አልፋ ስለተተበየች ከውሳኔውና ከምክሩ ሌላ ወደ ግዮን ዳር እንዳትሄድ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲደረግ እሷ ሳትሰማ መከሩ፡፡ እንዲህ አይነት ጨካኝ ውሳኔ ቢያስተላልፉም እሷን ከፍቅረኛዋ አሳ አጥማጅ ሊለያዩ አልቻሉም፡፡ እህቶቿ ሳሉታ፣ ቲካና ሎዛ ከደም የለሽ ሰው ወልዳ የማይሆን ወራሽ ነጋሲ እንዳታመጣ ለመጨረሻ ሊያስቆምዋት አቀዱ፡፡ በዘመኑ በጥንቆላ ስራቸው ለንጉሱ ያደሩትን ሁለት የኖባ ሰገሎች አሳ ወደሚያሰግርበት ግዮን ወንዝ ዳር ሰደው የእናቴን ወዳጅ ጉብል በድግምታቸው ሰውነቱን ወደ አሸዋ ለወጡት፡፡ (አፈር ይሁን አሸዋ የትኛው እንደሆነ በትክክል እንጃ)
ወሩ መስከረም ነበር፡፡ አደይ አበባ በአገሩ በቅሎ ምድር የማር ባህር መስላለች (እማማ እንዳብራራችልኝ)፡፡ ቀለም በቀለም የሆኑ ቢራቢሮዎች ሰማዩን ጥላና አበባ አስመስለውታል፡፡ ወፉ አገሩን በዜማ ሞልቶታል፡፡ ንቡ ጣፋጩን ሚስጥር አዝሎ በየስፍራው ይንዛዛል፡፡ የሚያማምሩ ባለቀለም እባቦች በየጉራንጉሩ ያፉዋጫሉ፡፡ እንስሳት ይቦርቃሉ፡፡ ከብቶች ይፎልላሉ፡፡ እናቴ በለመደችው ሰአት ከወዳጅዋ ጋር የሚገናኙበት ቦታ ስትሄድ በቀጠሮው ሳይመጣ ቀረ፡፡ ዘመዶቿና ዘመዶቹ አስፈራርተው ከእሷ እንዳሸሹት ጠረጠረች፡፡ በሃዘን ተቆራምዳ ዛፍ ስር ተቀምጣ ስትተክዝ ባላገሮች መጥተው ሰገሎች ያደረጉትን ነገር በዝርዝር ነገሯት፡፡ በዚህ አዝና እሱ የሞተበት አሸዋ ላይ ተኝታ እንዲህ ብላ አለቀሰች ይባላል፤

አበባዬ ሆይ ለምለም
አበባዬ ሆይ
ለምለም
ሶስቱ እህቶቼ
ለምለም
ቁሙ በተራ
ለምለም
ባልንጀሮቼ
እዩኝ በተራ
ለምለም
አሸዋ አቅልጬ
ለምለም
ቤት እስክሰራ
ለምለም
እንኩዋን ቤትና
ለምለም
የለኝም አጥር
ለምለም
ግዮን አድራለሁ
ለምለም
ጠጠር ስቆጥር

ዘፈንና ደስታ በሚንቦገቦግበት በአዲሱ ዘመን ስታለቅስ ሳለ ሃዘኗ ያስጨነቃቸው የምድር አምላክ መሃርምና የሰማይ አምላክ ዋቃ ከዚያ በፊት ያላደረጉትን አደረጉ፡፡ እሷ ደለሉ ላይ እየተንከባለለች ስታለቅስ አሸዋውና ደለሉ እድ ፍጡር ተነቃነቀና ገላዋን ሸፈነው፡፡ በዛን አፍታ እኔ ተጸነስኩ፡፡ ይሄንን ያደረገው የወንዙ የግዮን አምላክ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ገነቴም መፀነሷን ስታውቅ ልጄ በጠላቶቹ እንዳይገኝና እንዳይገደል ከአይናቸው የተሰወረ ትንሽ ይሆናል አለች፡፡ በሰገሎቹ ከተነገረው እርግማን ብሶ አውራ ጣት ማከሌ በእናቴ ምኞት ስር ያዘ”

………………………………..
(1)በሰማያት መጨረሻ
(2)’የተገለለ
(3)በዚያ ዘመን ቋንቁዋ አመሰ
ሳት ይባላል፡፡ መሰሰች፤ በፍቅር ተያዘች፡፡ ምስ፤ ፍቅር፡፡ ምሴ፤ ፍቅሬ፡፡ ተማመሱ፤ ተፋቀሩ (ዛሬ ዛሬ ‹ፎንቃ› የሚባለው)

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...