Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል ስምንት )

የኔ ነገር …ምንድናት ቀበሮ ትሁን ጥንቸል(ለካ ጢንቸል ስጋ አትበላም) ብቻ የሆነች <ጅል> እንስሳ ናት አሉ…. ከዝሆን ኋላ ኋላ እየተከተለች ሙሉ ቀን ዋለች እንደሚባለው ሆነ ….ምንትሱ ሲወዛወዝ ይወድቃል ብላኮ ነው ….እኔም እንደዛች እንስሳ ነው የሆንኩት ….የልእልትን ትረካ ልቤ ተንጠልጥሎ እየሰማሁ ካሁን ካሁን ለዛ ወፈፌ ባሏ ያላት ፍቅር በትረካዋ ሲወዛወዝ ከልቧ ተነቅሎ ይወድቅና እኔም እፎይ እላለሁ ብየ ….እሷ እናትየ…. አውርታ አውርታ በየመሃሉ ‹‹ወንዴን ግን ስወደውኮ›› ትለኛለች …..ይች ልጅ ባሏ በቢለዋ የጀመረውን ራእይ በቅናት ለማስቀጠል የተላከች እስኪመስለኝ ….ቆዳየን በሚሰነጥቅ ጥልቅ ስሜት ባሏን እንደምትወደው ትነግረኛለች ……
አንዲት ሚስት የተጣላችውን ባሏን ለምን ወደደች አይደለም የእኔ ቅሬታ ….ግን ቢያንስ በነብስ የምንፈላለግ ሰዎች መሃል ስለአንድ ሰው መለዓክነት ማውራት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው …?? ምንስ ልእልትን ቀልቤ ቢወዳት …ምንስ ቁንጅናዋ አፍ ቢያስከፍት ስለት መዞ በጭካኔ ሊገድለኝ የሞከረን ሰው ሩህሩህ ነው ብሎ ሃሳቤን ያስቀይረኝ ዘንድ የሷ ቃል ምን ተአምር አለው ….??.በእርግጥ ሴቶች ስላለፈ ሂወታቸው ማውራት እንደሚወዱ በትንሹም ቢሆን ካሳለፍኩት ተረድቻለሁ ….አንዳንዴማ ሴትን ከወንድ የጎን አጥንት ሳይሆን ከታሪክ ጎድን የፈጠራት እስኪመስለኝ ስለትላንት ማውራት በፍቅር የሚወዱ ሴቶች አጋጥመውኛል ….ልእልትም ትላንትን እንዲህ ቦርቀቅ አድርጋ ትሰልቀው ይዛለች …..ችግሩ ገፀ ባህሪዋ ቀድሞ እኔ ውስጥ ስለጠቆረ ታሪኩም ታሪክ ሳይሆን የጥላሸት ብናኝ ሁኖብኝ ልቤን እያጨፈገገው ተቸገርኩ !

ድንገት ግን ልእልት ….. እንደሃምሌ ሰማይ ፊቷ ጠቋቆረ ….አይኖቿ ከትዝታ ሰገባቸው ተመዘው ወጡ ….እናም መራር ታሪኳን በምሬት ትዘረግፈው ገባች … ‹‹ወንዴ ውሻ ነው›› አለች (እንዲህ ደግ ደጉን ማውራት ነዋ ልእልቴ) ግን እያመረረች ስትሄድ ‹‹ጉዳዩ ምንም ይሁን ስለፍቅር ማውራት ይሻላል አልኩ …ያንን ያህል ጥላቻዋን ስናፍቀው እንዳልቆየሁ ! ልእልት ግን በሚንተገተግ ቁጣዋ ትረካዋን ቀጠለች (እንደው እኒህ ቆንጆ ሴቶች ላይ የሚያስጠላው ነገር ምን ይሆን …? ቁጣ ራሱ እሷ ፊት ላይ ዘንጦ ነው የሚቆጣው)
<<…የእኔና የወንዴ ፍቅር እንዲህ የሚያሳብድ ነበር….. በኋላ ሳስበው ግን (መቸም በኋላ ነው ሁሉን ነገር የምናስበው ) የወንዴ ፍቅር በለስላሳ ስፖንጅ የተጠቀለለ የብረት ዱላ ነገር ነበር ….ወንዴ በዚያ ብትር ሲመታኝ ህመሙ አይሰማኝም ነበር ….በደሉ አይቆረቆረኝም ነበር ….ግን እድሜ ስፖንጁን እየበላው አብሮ መቆየት ድልዳሉን እያሳሳው …ትክክለኛው ዱላ ፈጦ መውጣት ጀመረ … የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ እስከአጥንቴ ዘልቀው ይሰሙኝ ጀመር….
አብጀለት ነበር ስልህ አብርሽ ….እይውልህ ልክ 12ኛ ክፍል ስገባ ትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜየ የምሄድበት ቦታ ሆነ ….ጭራሽ ተማሪዎቹም መምህራኑም አስጠሉኝ …. ልቤ ወንዴ ጋር ነው ….ስንት መዝናኛዎችን ባየሁበት አይኔ ….እዛ የጠመኔና ጥቁር ሰሌዳ ትግል የፈጠረው አቧራ የሞላው ክፍል ውስጥ …ተጎልቶ መዋል መወፈፍ መሰለኝ ….. ተማሪ ነሽ አስተማሪ አነሰብኝ ….ተምረን ስራ ይዘን ደመዎዝ ምናምን ሲባል ….እኔ ምኞቱን ቀድሜ ደርሸበት ወደትምህርት ቤት የተመለስኩ መሰለኝ ….(መቸስ አገራችን ላይ ተምሮ ሮኬት ለማምጠቅ ከሚያስብው ተማሪ ይልቅ ያችኑ የወር ደመወዙን ተቀብሎ ዶኬውን ግፋ ቢልም የፈረደበትን ጥሬ ስጋ የሚያልመው ይበዛል)
እና ለየትኛው ተአምር ነው የምማረው …እየው የትምህርት ጡንቻ ሲልፈሰፈስ መማር ኑሮን መቀየሪያ መሳሪያ ሳይሆን በራሱ ኑሮ ይሆናል …እንደመነገድ …እንደመዝፈን…. እንደመደለል ….መማር ገንዘብ ማግኛ አንድ የስራ ዘርፍ ይሆናል …..ያኔ ነው ራእይ ገንዘብ የሚሆነው ….በቃ ተምረህም አምጣው ሰርቀህ …. አመንዝረህም አግኘው ሎተሪ ደርሶህ ብር ማግኘት ከቻልክ መማር እድሜ መፍጀት መስሎ ይሰመሃል ! ምን ይሰራልሃል …የውስኪ ብርጭቆ አያያዝ ለማሳመር ሀ ሁ ምን ቤት ነው ….ጥሬ ስጋ ለመቁረጥ ኤቢሲዲ ሚጥሚጣ ነው ዳጣ …….እንዲህ ነው ትምህርት ግርማ መጎሱ የሚገፈፈው …..
እናቴና እህቴ ጋር ወንዴን አስተዋወኩት ወደዱት (ባይወዱት ነበር የሚገርመኝ) …አባቴ ከሞተ ቆይቷል….በእርግጠኝነት የምነግርህ አባቴ ቢኖር ወንዴን አይወደውም ነበር …. እንግዲህ በምድር ላይ ያሉኝ ዘመዶች እነዚሁ ሁለቱ ናቸው …. ወንዴን ወደዱት … ወንዴ እቤት መጥቶ እንደእቃ አንጠልጥሎኝ ሲሄድ እናቴ የምትናገረው አንድ ቃል ብቻ ነው ‹‹አታምሹ››…(አይ አለማምሸት እቴ ) ወደቤት አልመለስም በዛው እናድራለን ….ማታ ደውየ ለእህቴ እነግራታለሁ (ለእናቴ ደፍሬ ወንድ ጋር ላድር ነው ማለት መቸስ ይከብዳል ….የኛ ነገር ማድረጉ አይከብደንም እንጅ መናገሩ ላይ አጉል ጨዋ ካልሆንን የምንለው ነገር አለ )
የሴት ልጅ ትልቁ ድክመት መልኳንም መፈቀሯንም ዘላለማዊ አድርጋ ማየቷ ነው …. ያ ደስታችን ዘላለማዊ መስሎኝ …ያችኑ የፊደል ቆጣሪ ሁሉ ተስፋ (ደመዎዝ) ተቋድሸ ይችን ጤዛ ህይዎቴን እንኳን በራሴ እንዳቅሜ እንዳልመራት እንደቅንጡ አይነስውር ያለችኝን አንዲት ብትር አሽቀንጥሬ ጣልኳት ….ትምህርቴን ! ምናለ ትምህርቴን በወጉ ባቋርጠው ….ምንስ ቢሆን አስራ አንድ አመት ተንገታግቸበታለሁ …. ውድቀትንም ታሪካዊ ማድረግ አንድ ነገር ነው …. ሰበብም ጥሩኮ ነው …..ውድቀትን ሰበብ ማስደገፍም ቢያንስ ወሬ ለማሳመር እንኳን ይረዳል …..አብርሽ ሙት …..እስቲ አሁን ምንም ሳትሆን መጥተህ የሆስፒታል አልጋ ላይ ብትተኛ ለጠያቂስ ምን ይባላል …..በቃ ትምህርቴን ያለምክንያት ከመሬት ተነስቸ ተውኩት …..መተዌ አይደለም የሚገርመኝ ተውኩበት መንገድ ……ከሞቱ አሟሟቱ ነው ምናምን የሚባል ተረት አለ …….
አንድ ቀን ከትምህርት ቤት እንደወጣሁ ወንዴ ጋር እራት በልተን በዛው አብረን አደርን ….ያው ትክ ብሎ ካየኝም ተከትየው መንጎድ ነው መቸስ በፍቅር ስም እንደለማዳ ውሻ መከተል ….ጧት (አብረን ስናድር ቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ከሆነ ጧታችን አራት ሰዓት ወይ አምስት ሰዓት ነበር ) ያን ቀን ግን ትምህርት ስለነበር …በጧት ‹‹ወንዴ ውይ ረፈደብኝ ›› ብየ ልነሳ ስል አይኑን እንኳን አልገለጠም በጎረነነ የጧት ድምፅ ‹‹ አቦ አርፈሽ ተኝ ››› ብሎ አቀፈኝ …አይገርምህም አብርሽ….. እቅፉ ውስጥ ገብቸ ለሽ …ምን ለሽ…. መሟሟት በለው …. በኋላ የሚሆነው ሁሉ ሁኖ የውሻሸት ልክ እሱ ብቻውን አስገድዶ በር ላይ ወታደር አቁሞ እጅና እግሬን አስሮ ያስቀረኝ ይመስል … ከትምህርት ቤት አስቀረኸኝ ብየ ተነጫነጭኩ …አለ አይደል ‹‹ መቅረቴን በሆነ መንገድ እንዲባርከውና ለራሴም ከትምህርት ቤት መቅረቴ ልክ ነበር ለካ እንድል ››
‹‹ልእልትየ ….ይሄን ትምህርት ምናምን ተይው በቃ!! ተጋብተን አሪፍ ቤት ተከራይተን እንኑር አለኝ ›› ልቤ ለሁለት ስንጥቅ ያለች ነው የመሰለኝ …ወንዴን አየሁት ከምሩ ነው ….
‹‹እውነትህን ነው ? ››
‹‹አባቴ ይሙት ›› በአባቱ ከማለ አይዋሽም …..አባቱም በወንዴ ከማሉ አይዋሹም ….(አንድ አይነቶች) በቃ ትምህርቴን !! የሚገርምህ ዩኒፎርሜን እንኳን ያደርንበት ሆቴል እንደተውኩት ያስታወስኩት በቅርቡ ነው (ማሰብ ስጀምር) ተውኩት በቃ ! ከዛን ቀን ጀምሮ ትምህርት ቤቱን ዙሬ አላየሁትም ! ታዲያ የማቋረጥ ሳይሆን የሆነ የመመረቅ ስሜት ነበር የሚሰማኝ ይሄ በሜዳሊያ ምናምን መመረቅ እንደሚሉት ….. እውነቴን ነው አብርሽ አንዳንዴ ከስንት እንዳቋረጥኩ ሁሉ ትዝ የሚለኝ አስቤ ነው …
ወንዴ ጋር ቤት ተከራየን (ለነገሩ ከዛም በፊት ነበረው መሰል…. ተከራየሁ ብሎ በውድ እቃ የተሞላ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ሲያስገባኝ ግራ ቀኙን አላየሁም እንደእቃ ገብቸ ተጎለትኩ) ከመሬት ተነስቸ የተከበረች የቤት እመቤት የመሆን መንፈስ ከበበኝ ! ጧት ተነስቸ ፒጃማየን እንደለበስኩ ቁርስ ለመስራት ጉድ ጉድ ስል ‹‹አስር አመት በትዳር የኖረች ሚስት አስንቃለሁ›› በገዛ ህይዎት ላይ ድራማ መስራት !ልክ ፊልም ላይ እንዳየሁት ነበር ትዳርን ያገኘሁት ! ወንዴ ከውጭ ሲመጣ ከንፈሩን ስሜ መቀበል …ዘንጠን ወጥተን እራት መገባበዝ …እና ሰዎች የሚፋቱት ደደብ ስለሆኑ ነው ብየ ያሰብኩት ስንት ቀን መሰለህ ….
እናቴን ስፈራ ስቸር ወንዴ ጋር ልንጋባ ማሰባችንን ነገርኳት ‹‹በሞትኩት እኔስ እንደዘመኑ ልጆች መስሎኝ ነበር ለካስ ቁም ነገረኛ ኑሯል›› አለችኝ ….እህቴ ገና ድሮ ስለቬሎ ማውራት ጀምራ ነበር … በቃ !ወንዴ ለአባቱ ሲነግራቸው አጠገቡ ነበርኩ ትዝ ይለኛል እዛ ሲሚንቶ መሸጫ ሱቃቸው ውስጥ አብረን ሂደን (ከዛም በፊት አስተዋውቆ ወደውኝ ነበር ….እንደውም አንዳንዴ ወንዴ ጋር ስንሄድ እኔን ወደኋላ ያስቀሩና ‹‹የሻይ›› ብለው የሻይ ንግድ ብጀምር ወረት የሚሆን ብር ይሰጡኛል …. ወንዴ ጋር አመድ እናደርገዋለን !) ታዲያ ልንጋባ እንዳሰብን ሲነግራቸው ብዙ ብር እየቆጠሩ ነበር …መቁጠራቸውን ቆም አድርገው ሁለታችንንም በግርምት ተመለከቱንና …..‹‹ ልእልት ይሄ ልጅ የሚያወራው እውነቱን ነው ?? ›› ብለው ጠየቁኝ …. ወንዴ ክንድ ላይ እንደተጣበኩ እራሴን ከፍ ዝቅ አድርጌ አረጋገጥኩላቸው …..
‹‹ሂዱ እስቲ ሻይ ቡና በሉና ተመለሱ ›› ብለው እጃቸው ላይ የገባውን ብር አፍሰው ሰጡን ›› ትንሽ ተረባብሸው ነበር …..ከሱቅ ስንወጣ አባቱ ሲያፏጩ ነበር ….. ቆይቸ ይሄን የሚያፏጩትን ዜማ የት ነው የማውቀው ስል ….የሆነ ዘፋኝ ስለትዳር የዘፈነው ነው ….
‹‹ማየት መልካም ሁሉን እይው
ግን በትዳር ቀልዱን ተይው ….. ይችን ራሷን ነው ሲያፏጩ የነበሩት …..
የሆነ ሁኖ ተጋባን ….ሰርጉ ለእኔ ድካም ነበር … ወደዛ ቬሎየን ወርውሬ ወንዴ ጋር ብቻችንን የሆነ ቦታ መሆን ነበር ያማረኝ …..እስካሁን እንደህልም የሰርጉ ጭፈራ ይታየኛል …..ጓደኞቸ ሲያብዱ (ምን አሳበዳቸው) ጭፈራቸው ራሱ ዛር ነበር የሚመስለው …. ከዛም በኋላ ስንትና ስንት ወር ሙሉ የወንዴ ዘመዶች ስጦታ እየያዙ እቤታችን እየመጡ ከረሙ …..ብቻችንን መሆን እስኪናፍቀን …..!!ከተጋባን በኋላ ….. አባቱ እራሳቸው ግቢ ውስጥ እንድንኖር ፈልገው ነበር …እኔም ወንዴም ግን ወጣ ማለት ፈለግን …. ወደሲኤም ሲ ቤት አሰራላችኋሁ አሉን ያሰሩ አያሰሩ እንጃ …..ሰውየው ባህሪያቸው ምንም የሚያዝ የሚጨበጥ አይደለም ! ለነገሩ እኛም አብረን እንሁን እንጅ ቤት ይሁን በረት ግድ አይሰጠንም ያኔ ….. እዚህ ኮንዶሚኒየም መጥተን መኖር ጀመርን ….እኔ ሰፈሩን ወድጀው ነበር ….ወንዴም ተመችቶታል ….እንደቀልድ ሶስት አመት አለፈን …..
የወንዴ ጓደኞች ከሰዓት ውሏቸው እኛ ቤት ነበር ….ሁልጊዜ በሰው እንደተከበብን ነን ….ቀን ጓደኞቹ ጫት ይዘው ይመጣሉ ….እኔም ‹ምናለበት› ሲሉኝ ‹ አታስደብሪና እናተን ብለን መጥተን› ሲሉኝ …..እንዳልለይ አንድ ሁለት ስል የለየልኝ ቃሚ ሁኘ ቁጭ አልኩ ….አብረን ምሳ እንበላለን ….በየሄድንበት አስተናጋጆች ያውቁናል …..ጫት ይገዛል እንቅማለን ….ፊልም እናያለን …ወደማታ ወጥተን አብረን ራት መብላት መጠጣት ሁሉ ጀመርን … ሲደጋገም ህይዎታችን ይሄው ሆነ … ተመሳሳይ ፕሮግም ነበር በየቀኑ ….ሁሉም የወንዴ ጓደኞች የሃብታም ልጆች ናቸው ….በየቀኑ አዲስ ሰው ይዘው ይመጣሉ …ሴቶችም ወንዶችም ….እኔ ራሱ ይናፍቁኛል ….ወሬው ሳቁ …ምን ልበልህ ሰው መልመድ ክፉ ነው …..
ከቤት ባልወጣም በእነሱ በኩል ከተማው ውስጥ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ልክ በቦታው ያለሁ ያህል ሁኘ አውቀዋለሁ ….ደግሞ እቤት ስለምውል ነው መሰል …አማረብኝ ….ፊቴ ጥርት አለ …በቃ ተስማማኝ ….በምድር ላይ እንደኔ ደስተኛ ሴት ያለች አይመስለኝም ነበር ….አንዳንዴ …እንዲሁ በረንዳ ላይ ቁሜ ከስራ የሚመጡ ሴቶችን ስመለከት በዛ ጠራራ ፀሃይ ከልተው ከልተው የሚሉ ሴቶችን ሳይ ‹‹እንዴት እድለኛ ልጅ ነኝ›› እያልኩ እታበያለሁ …በወንዴ ጓደኞች ታጅቤ ወጣ ባልኩ ቁጥር እውነትም የልእልትነት ስሜት ነበር የሚሰማኝ ….በእኛ ነገረ ስራ የማይቀና አልነበረም ….አንዴ እቤታችን የመጣ ወይም የመጣች ሴት በቃ በግሩፑ ፍቅር ከመውደቅ አትድንም ….አስደሳች ጊዜ ነበር የምናሳልፈው …
ጉዱ የመጣው አንድ ቀን ነው ታዲያ ….ይሄ አእምሯችን አብርሽ …›› አለች በውብ አመልካች ጣቷ ከጆሮዋ ከፍ ብሎ ያለ ጭንቅላቷን እየነካችና ጣቷን እንደቡለን መፍቻ ግራ ቀኝ እያሽከረከረች ….‹‹ ….ይሄ አእምሯችን እንደተቀበረ ፈንጅ እኮ ነው …የፈለገ ምቾት ውስጥ ብትቀብረው …ብር ውስጥ ብትቀብረው ….ግርግር እና አጀብ ውስጥ ብተሸጉጠው ….አንድ ቀን የእውነት እግር የረገጠው ቀን መፈንዳቱ አይቀርም …. በቃ ምን እየሰራህ ነው ይለሃል ….ይሄውልህ ወንዴ ጋር ያሻንን በልተን ጠጥተን የፈለግንበት ቦታ ሂደን ….እየኖርንን ነው ….ምንም ነገር ቸግሮን አያውቅም …..ልብስ ብትል …አገር ያስለቀቀ ነው…. ያ ባለፈው ያየኸው መዘዘኛ ሻንጣ ካለኝ ልብስ እንደው ለጊዜው የምለብሰው ብየ እንዲሁ ቆንጠር ያደረኩት ነው (የሻንጣውን ክብደት አስታውሸ አባባሏ ገረመኝ ….ያንን የሚያህል ሻንጣ ሙሉ ልብስ ‹ቆንጠር› ) …..እና አንዲት ቀን አኮ ናት …..የነወንዴ ጓደኛ የመኪና አደጋ ደረሰበት ተብሎ ወንዴ ከነጓደኞቹ እዚህ ደብረ ዘይት ሂደው ብቻየን ነበርኩ ….ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻየን እቤት የዋልኩበት ቀን ነው …..በቃ ብቻየን ቁጭ ብየ የማደርገው ነገር ጠፍቶኝ አንዴ ፊልም እከፍታለሁ አንዴ በረንዳ ላይ ወጥቸ እቆማለሁ …. በቃ ቤቱ ሊበላኝ አልቅሽ አልቅሽ አላኝ
እና ግራ ቢገባኝ ቤት ገብቸ ሶፋ ላይ ኩርምት ብየ ተቀመጥኩ … ደግሞ ደጋግሞ ያዛጋኛል …ያን ሁሉ ጊዜ ያላሰብኩት የጥያቄ ናዳ ወረደብኝ ….አእምሮየ ብቻየን ሲያገኘኝ ቤተክርስቲያን እንደገባች ውሻ ከዛ ከዚህ ያዋክበኝ ጀመረ …ደግሞ ሁሉም ጥያቄ መልስ የሌለው !!እሽ ከዚህ በኋላ ኑሮየ ምንድን ነው ብየ አሰብኩ ….መልስ የለም!! ….እሽ ዛሬ አደጋ የደረሰበት ወንዴ ቢሆን ኑሮ ቀጥሎ የማደርገው ነገር ምንድን ነበር አልኩ ….መልስ የለም !!…..ሌላው ይቅር እጀ ላይ እንኳን ያለው ብር ስንት ነው ?…አልኩ እዛ ጠረንጴዛው ላይ ከተቀመጠ ትንሽ ብር ውጭ ምንም አልነበረኝም …(አንድ ሽ ብር እንኳን መሙላቷን እንጃ)
ከሆነስ ሆነና ወንዴ ስራው ምንድነው? ብየ አሰብኩ ….አይገርምህም ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ የባሌ ስራ ምን እንደሆነ አላውቅም ….ከምር አላውቅም(ማን ያምናል ይሄንን) …በቃ ይሄዳል ይመጣል ብር ሁልጊዜ እጁ ላይ አለ ….አባቱ ናቸው የሚሰጡት ! ወንዴ እንዲች ብሎ አንዲት ስራ አይሰራም ሰርቶም አያውቅም …. ግራ ገባኝ ….ልክ ከእንቅልፍ እንደመባነን ባነንኩ …አንዳንዴ መቸስ ከራሳችን ጋር መፋጠጥ ጥሩ ነው …. ይሄ ግርግር ስንቱን ጉድ እውነት አድበስብሶ ቀብሮታል መሰለህ ይሄው ያንተ ቁስል እንኳን የሚጠዘጥዝህ ብቻህን ስትሆን አይደል (እውነት ነው በተለይ ልእልት ሳትኖር)
ልእልት አሁንም በሆነው ነገር ሁሉ ተደምማ ታወራኛለች ተደምሜ እሰማለሁ …..….
‹‹ አሰብኩ በቃ አእምሮየ ሊፈነዳ …..እንደው ሌላው ሁሉ ይቅር ወንዴ ሌላ ሴት ወዶ በቃኝ ቢለኝ ምንድነው የኔ መጨረሻ ….ትምህርቴን አቋርጫለሁ ቤተሰቦቸ ያው ለራሳቸው አይነሱ እንጅ እንደገና ወደነሱ መሄድ ሞት ነው ….ምቾት ብየ የተደገፍኩት ነገር ሁሉ የንቧይ ካብ ሁኖ ታየኝ …..ነብሴ ውስጥ የስጋት ሻማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለኮሰ ….ሻማው ሲለኮስ ግር ግር ጨለማ ውጧቸው የሌሉ የመሰሉ ግን በነብሴ ውስጥ የታጨቁ በርካታ ጉዳዮች አቧራቸውን እያራገፉ እፊቴ መጋረጣቸውን አየሁ! የማልሸሻቸው ሃቆች !!
ወንዴ ሲመጣ በስርዓት ስለወደፊት ህይወታችን መነጋገር እንዳለብን ወሰንኩ እናም …. ማዛጋቱ ሲበዛብኝ እየፈራሁ እዛው ሰፈራችን ያለች ጫት ቤት ሂጀ ጫት ገዝቸ ተመለስኩ …. እንግዲህ ይታይህ ስንት አመት ሳመነዝከው የኖርኩትን ጫት ዋጋ እንኳን ገና ዛሬ መስማቴ ነው ….የገባኝ አንድ ነገር …. ብቻየን ሁኘ ጫቱን ስመለከተው ሳቄ መጣ …ይሄንን ነው ስበላ የኖርኩት ብየ አገላብጨ አየሁት አዲስ እንደተወለደ ህፃን ሁሉ ነገር እንግዳ ሆነብኝ …. በፍቅርም ይሁን በቤተሰብ ወይም በዝምድና አለኝታ የሚመስሉን ሰዎች እንደመቃብር አፈር ተጭነው ከአለም አለያይተውን እንደኖሩ የሚገባን ልክ እነሱ ሲነጠሉን በራሳችን አንድ እርምጃ እንኳን ለመራመድ ሁሉ ነገር ጨለማ ሲሆንብን ነው …. ደግሞ አንዳንዴ የምንደገፋቸው ሰዎች እንኳን እኛን አስደግፈው ሊቆዩ ራሳቸውም ምን ተደግፈው እንደቆሙ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው ….እስቲ አሁን ወንዴ አባቱ ባይኖሩ በዚች ምድር ምን ሰርቶ ምን ሁኖ ነበር የሚኖረው ….
እኔስ ወንዴ ባይኖር ምን ሁኘ ምን ሰርቸ ነበር የምኖረው …. ማን ማንን ነው የተደገፈው ….ይሄስ ድግፍግፍ ጥግንግን ህይዎት እንዴት ነው ራስን ችሎ ወደመቆም የሚቀየረው ….ወንዴ ይምጣልኝ ….ጓደኛ አልፈልግም ሰው አልፈልግም ….ፊልም አልፈልግም …ብር አልፈልግም ….ጫት….አልፈልግም …..መዝናናት አልፈልግም ….መሳሳም መተሸሸት አብሮ መተኛትም አልፈልግም …ሆዴ ማሬ እያሉ መንቆለጳጰስ አልፈልግም !!
ምፈልገው ….ነገየን ነው … ቢያሻው ጠንቋይ ቤት ሂዶ ይጠይቅ …ከፈለገ እንደመንግስት መስሪያ ቤት ራእይ ምናምን ብሎ በሩ ላይ ፅፎ ይለጥፍ አያገባኝም …. ብቻ ወንዴ አንዲነግረኝ እፈልጋለሁ ….የነገ እጣ ፋንታችን ምን እንደሚሆን እንዲነግረኝ እፈልጋለሁ ….‹‹መቸም አባባ እስከሚሞት ጠብቀን ሃብቱን መውረስና የሱን ንግድ መቀጠል ካለኝ ገርሞኝ አላባራም !›› ብቻ ወንዴ ይምጣ ….ደግሞ ልቤ ተጨነቀ ሲመለሱ መንገድ ላይ የሆነ ነገር ቢገጥማቸውስ ብየ …. ‹‹እግዚአብሔርየ ›› ብየ አይኔን ወደላይ ወደኮርኒሱ አነሳሁ …‹‹ውይ ልእልት ዛሬስ ከምን አስታወሽኝ…. በስንት ዘመንሽ›› ያለኝ ነው የመሰለኝ እግዚአብሔር …..

በአልጋው ትክክል (ክፍል ዘጠኝ)

 

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...