Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል! (ክፍል ሁለት)

የተጣሉ ባልና ሚስትን ለማስታረቅ ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮች መካከል አንዱ የተጣሉበትን ምክንያት ጠንቅቆ ማወቅና …የፀቡን ምክንያት ወይ ((ማካበድ)) ወይ ((ማቃለል)) ነው ….ለምሳሌ የፀቡ ምክንያት ባል ሚስቱን ‹‹ ከጎረቤቷ የሚገኝ ጎረምሳ ጋር አጓጉል ነገር ጀምራለች ›› በሚል ‹ተልካሻ ምክንያት› ጠርጥሯት ቢሆንና በዚሁ ሰበብ ቢለያዩ (ምሳሌ ነው)ለሽምግልና የተመረጠው ሰው ይህን ጉዳይ ‹‹በማካበድ›› ወይም ‹‹በማቃለል›› በጥርጣሬ የተበጠበጠውን ትዳር ወደእርቅ ለመመለስ ይችላል ….እንዴት ማለት ጥሩ ….

እንግዲህ ሽማግሌው ወደተጠረጠረችው ሚስት ይዞርና ‹‹የቱ ነው ለመሆኑ የተጠረጠረሽበት ጎረምሳ…?›› ብሎ ጎረምሳውን ቢያውቁትም ልክ እንዳላወቁት መጠየቅ…!! የፈለገ ብታውቀው የተጠረጠረችው ሚስት መልሷ ሊሆን የሚችለው ‹‹ምን አውቅለታለሁ… እሱን ጠይቁት እንጅ በህልሙ ይሁን በውኑ የሚያወራው ….. ›› ብላ እንደዳቦ ሊጥ ኩፍ ባለ የኩርፊያ ፊት ወደባሏ በአገጯ መጠቆም ነው ….

የሆነ ሁኖ ልክ የተጠረጠረውን ጎረምሳ ሽማግሌው በምልክትም ይሁን በስም ሲነገረው …. ጎረምሳውን እስከሰማይ ጥግ ማጋነን ይጠበቅበታል ….‹‹አበስኩ ገበርኩ …. እሱን ነው እንዴ ?????…… እሱማ ሰው ቀና ብሎ የማያይ….አለባበሱ ብቻ ሚኒስቴር የመሰለ ….በዛ ላይ ጨዋነቱስ ቢሆን …. እንዲህ ቀላል ቦታ የሚውል ሰው አልነበረም እኮ … ሁኔታውን ወዘናውን ሳየው ((በአመት የማያልቅ የወር ደመዎዝ)) ያለው ነው የሚመስለኝ ….አይይይ እሱጋ እንኳን እንጃ አጉል ጥርጣሬ ነው የሚመስለኝ … ምን አጥቶ የመንደሩ ሴት ሁሉ በየመጋረጃዋ ተከልላ የምታየው ሸበላ ምን አጣሁ ብሎ ከሰው ሚስት ጋር ይማግጣል ›› እያሉ ሰማይ ጥግ ድረስ መቆለል (አለ አይደል እሱጋርማ እንኳን ሄድሽ በሚመስል ድምፅ ) ….
ሚስት ከአድናቆቱ ብዛት …<<እንዴ ይሄ የሰረኩት ልጅ እንዲህ ከባድ ሰው ነው እንዴ … እኔ ግን ይህን ጅንን በፍቅሬ አንበርክኬ ያውም እግሬን ስሞ ….ሁለት ወር ከግማሽ ቀን ለምኖኝ ነው እሽ ያልኩት >>….ብላ ልታምን እስኪዳዳት …እላይ መስቀል !!(ምናልባት ሰኞ ቀን ከሰዓት ባሏ ስራ ሲሄድ ይሆናል ጎረቤቷ ቤት የገባችው ግማሹ ቀን እሱ ነው)

ይህ ሰቀላና ማጋነን ሚስት ‹‹የተሳሳትኩት የማይረባ ሰው ጋር አይደለም›› ብላ ለስህተቷ እና ላሳሳታት ወይ ላሳሳተችው ጎረምሳ ክብር ለሰጠው ሽማግሌ …..በምላሹ ክብር እንድትሰጥና …ቀጥሎ የሚያቀርበውን ሃሳብ እንድትቀበል የሚያዘጋጃት አቻ የሌለው መላ ነው !! (እውነትም ከባሏ ውጭ ከሄደች ማለት ነው …ካልኬደች ምን ይቀባጥራል ልትል ወይም ግነቱ አማሏት ለመሄድ ውስዋስ ሊሆንባትም ይችላል)
መቸስ በዛሬ ጊዜ ድርጊቱ ቆሻሻ ቢሆንም እንኳን ‹‹ምን አደረገች›› ወይ ‹‹አደረገ›› ሳይሆን ‹‹ማን ጋር አደረገች›› የሚለው ነጥብ ነው በሰዎች ልቦና ውስጥ ሃፂያትን የሚያቀለውም የሚያከብደውም …..‹‹እሷ ፀዳ ፀዳ ያሉ ወንዶች ጋር ነው የምትወጣው ›› ብሎ የሚቀና ስንት ድንዙዝ አለ …..‹‹ፓ እንትና አንዲት የሃብታም ሚስት ጠበሰኮ›› ተብሎ የሚደነቅበት ዘመን ነው …

ሚስቱን ትቶ ሰራተኛው ጋ ጉድ ጉድ ያለ ወንድ ሲታማ እንኳን ‹‹ቱ እመብርሃን የመሰለች ሚስት አስቀምጦ ‹ገረድ› ጋር ጓዳ ለጓዳ ያልከስክስ አባቱ እቴ ›› እኮ ነው የሚባለው ….እንዲሁ ነው የሚባለው ! እሽ ሚስቱ እመብርሃንን ባትመስልስ ሌላ ሴት ጋር ይሂድ ግዴለም ነው ….? ይሄ ነው የብዙሃኑ ስነልቦና መቀጨጭ ምልክቱ ! ሞራል አልባ ግሳንግስ እንደኳሻኮር ፍቅር ያጠረው አካላችንን ወጥሮት ስንታይ ድሎት ይመስለናል እንጅ ቀጭጭጨናል ! ስለዚህ ሽምግልና ይችን የሰዎች ድክመት ለበጎ መጠቀምን ቢዋሳት ለተሳካ ሽምግልና ፍቱን እንደሆነች አምኛለሁ !

ይህን የተጠረጠረ የጎረቤት ጎረምሳ ማሳቀሉ ….‹‹በሚስቴ ተካድኩ›› ለሚለውም ባል ቢሆን ‹‹አልታረቅም ምናምን ብለህ እንቧ ከረዩ ትልና ሚስትህ ያረፈችበት ጎረምሳ ቀላል ሰው እንዳይመስልህ ….ካፍህ ላይ ልፎ ነው የሚጠቀልላት›› የሚል ማስፈራሪያ በመስጠት ቶሎ ሽምግልናውን ተቀብሎ ሚስቱን ወደቤት እንዲመልስ የሚያደርግ ጥበብ ነው !! ምን ጥርጥር አለው …የብዙሃኑ የአበሻ ወንዶች ፍቅራችን አንድ እግሩ ‹‹አግብቻታለሁና የትም አትሄድም›› በሚል አንካሳ የትእቢት ድጋፍ ….ሌላኛው ‹‹ቅናት ላይ›› ሶስተኛው እግርም ‹‹ሰው ምን ይለኛል›› ላይ የቆመ ነው …ምናልባትም ሶስት ጉልቻ የምንለው ይሄን ይሆናል! እዚህ ጉልቻ ላይ ተጥደን ስንገበገብ ማለቴ ነው ! …

አስተዳደጋችን ያመጣብን ጠንቅ ሳይሆን አይቀርም ! ፍቅር እኮ ዋና ምሰሶ የሆነበት ትዳር ትንሽ ነው … አሮጌ ሰፈር ውስጥ ያለ አሮጌ ቤት …አይታችሁ ታውቁ የለ ?? ጣራው ላይ ቆርቆሮው በነፋስ እንዳይነሳ ድንጋይ…ዝናብ እንዳያስገባ ላስቲክ የተደረተበት ጥግንግን ….ልክ እንደዛ ነው አንዳንዱ ትዳር … የጥንዶቹ የአብሮነት ጣራ በፍቅር ሚስማር ሳይሆን …የጎረቤት ይሉኝታ… ልጅ ወልዶ የመለያየት ይሉኝታ …የዘመድ አዝማድ ድጋፍ ማስፈራሪያ ምናምን ….ብንፋታ ንብረታችን ይበታተናል ….የሚሉ ከድንጋይ የከበደ ምክያት ተሸክሞ የቆመ ነገር ነው ! …… ላንቦጫቦጭነው አብሮነት እንደቅመም ነው በተን የምናደረገው ፍቅርን !

እንግዲህ ይሄን የሽምግልና ‹‹የማናናቅና የማሳቀል›› መላ ድፍን ሌሊት ‹‹ተመራምሬ›› ያገኘሁት ራሴ ነኝ !! መቸም የኛ ሰው አንዱን ነጭ ፈጠረው ካልተባለ በስተቀር የስነልቦና ይሁን የፍልስፍና ጉዳይ አይዋጥለትም ! ተዋጠም አልተዋጠም ግን ((እጅግ ውብ)) የሆነችውን ጎረቤቴን ((እጅግ አሰልች)) ከሆነ ባሏ ጋር ለማስታረቅ ከተመረጥኩባት ደቂቃ ጀምሮ ይህን ጉዳይ ስመረምር ቆይቸ የደረስኩበት መደምደሚያ ይሄው ነው !! የተጠረጠረችበትን ወንድ ማጋነን ! ከእግዜር ዝቅ አድርጎ ሰማይ ላይ በደመና ማቀፊያ እሽሩሩ ማለት …..ማንሳፈፍ ! ባል ከዚህ ክፉ ባላጋራ ሲሸሽ ሽማግሌው ሃሳብ ላይ ያርፋል !
አዎ ሽምግልና ቀላል ነገር አይደለም …እየተፈላለጉ የተራራቁ ሰዎችን በየፊናቸው ጨምድዶ የያዛቸውን እልህ እና ትእቢት አስጥሎ (ሁለቱም አሸናፊነት እንዲሰማቸው በማድረግ) ወደእርቅ የማምጣት ጥበብ ነው …በትዳር መካከል የሚደረግ ሽምግልና ቀላል ነገር አይደለም …በተጣሉ ባልና ሚስት መካከል አርጅቶ ሙቶ የተቀበረ ፍቅርን በጥበብና በብልህነት መቆፈሪያ የለበሰውን አፈር በመቆፈር የደረቀውን የፍቅር ውሃ እንደገና በየልባቸው ውስጥ እንዲመነጭ የማድረግ ጥበብ ነው …እውነተኛ ሽምግልናን የሞራል የሃይማኖት እና የሰበዓዊነት ዋጋ ብቻ ሊገዛው የሚችል ውድ ነገር ነው !!
ሲጀመር ሽማግሌ መሆን የሚችል ሰው ራሱን የገዛ የሌሎች ህመም የሚያመው የሌሎች መዋደድ የሚያስደስተው ሰው መሆን ይኖርበታል ….አዎ! ምቀኛ ሽማግሌ መሆን አይችልም …..ተንኮለኛ ሰው ሽማግሌ ሊሆን አይችልም …ተጠራጣሪ ሰው ሽማግሌ ሊሆን አይችልም ….ማንም ከመሬት ተነስቶ ሽማግሌ ሊሆን አይችልም ….ሽምግልና ንፁህ ልቦናን ይፈልጋል ……አሁን ዋናው ጥያቄ ይሄ ነው …(((የዚች ውብ ጎረቤቴና የዚህ ጅል ባሏ መታረቅ ለሽምግልና የተመረጥኩ እኔን ያስደስተኛል ወይ ???))))….በሚገባ !! ለምን ትዳራቸው መፍረሱ አሳዝኖኝ ነው ?….በጭራሽ ! እናስ ምንድነው? ….
በእርቅም ይሁን በፍርድ ቤት ትዛዝ …..ብቻ ያችን ውብ ልጅ እዚህ ሰፈሬ ያውም እዚህ ብሎኬ ላይ እንደገና የማየት ከፍ ያለ ጉጉት ስላደረብኝ ነዋ!!(ለምን ይዋሻል …ውሸት በልብ ይዞ ሽምግልናማ ነውር ነው) ላያት እፈልጋለሁ …. ‹‹እንዴዴዴዴዴ ….የሰው ሚስት ለምን ታያለህ ›› …የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል … ጥሩ ጥያቄ ነው! ….ግን ለምን የሰው ሚስት ለማየት እንደጓጓሁ እንጃልኝ !! (መሞቻየም ሁና እንደሁ እንጃ)
እንግዲህ ሁለተኛው የሽምግልና መንገድ ማናናቅ ነው …. ማናናቅ ለሽምግልና እንዴት ጠቃሚ ነገር መሰላችሁ … አሁን ከላይ ባነሳነው የእነዚህ ሁለት ጎረቤቶቸ ጉዳይ ላይ እንኳን ብናየው ማናናቅ ወደእርቅ እንደሚመልሳቸው አትጠራጠሩ ….! ባሏ ሚስቲቱን (ያችን ቆንጆ ሚስት …ያችን የማለዳ ኮከብ የመሰሉ አይኖች ያሏት ሚስት) ‹‹አለሌ ናት›› ብሎ ዘልፏታል ….እና የት አለለች ?ለምን አለለች ከማንስ ጋር ? ተብሎ ቢጠየቅ አንዱን የጠረጠረውን ወንድ ስም ማንሳቱ አይቀርም …አሁን እንግዲህ ማናናቅን ተግባራዊ ማድረግ ነው
‹‹ ፕስስስ ….ስጋ ቁጠር ቢሉት አሉ ጣንፊያ አንድ አለ ….አሁን ማን ይሙት አንተን የመሰለ እናት የሆነ ባል ትታ እዚህ በኤሌክትሪክ ምድጃ ሲቀቀል መብራት እንደጠፋበት ፓስታ የተሸማቀቀ ሳይበስልም ሳይጠርርም(ጥሬ ሳይሆን) የቆመ ‹መሃል ሰፋሪ› ጋር ትሄዳለች ብለህ ታስባለህ … ? ተው ተው ! ተጣላን ብለህማ እንዲህ ያረባ ቦታ አትጣላት …ምንስ ቢሆን አንተን የመሰልክ ሸበላ ክንድ አቅፋ ያደረች ሴት እኮ ናት !! ነውር ነው ….አይባልም! …በል ለሌላ ሰው ይሄን ወሬ ብለህ እንዳታወራ ኧረ በመድሃኒያለ……..ም›› ብሎ ባልየውን ሰማይ ጥግ ….ተጠርጣሪውን አምዘግዝጎ ካፈር መደባለቅ !
በቃ ባል ልቡ ሙልት ይላል !! ድሮም ቀናተኛ ባል ስለሚስቱ ሌላ ወንድ ጋር መሄድ ሲያወራ ….እንዲያስተባብሉለት እንጅ ‹‹አዎ ልክነው ሚስትህ አንተን ትታ ሌላ ወንድ ጋር አልላለች ››ብለው ቁስሉን እንዲያባብሱበት አይደለምና…. ለመታረቅ ልቡ ቧ ብሎ ነው የሚከፈተው ! ሚስቱ ሌላ ወንድ ጋር መሄዷን ባይኑ በብረቱ ቢያይም እኮ ነው …መሸነፍን አይወድማ ! ቆፍጣናው አበሻ !

እና ይሄን ይሄን በቁም ነገር አሰላስየ ሽምግልናየን ለመጀመር ወደልጅቱ ልደውልና ልቀጥራት መሸት እስኪል መጠበቅ ጀመርኩ ( የምትገኘው በእህቷ ስልክ ስለሆነና እህቷ ወደቤት የምትገባው ወደምሽቱ ሁለት ሰዓት ስለሆነ…. በዛ ሰዓት ደውልላት ብሎኝ ነበር ባሏ ‹‹ወንድየ አንበሳው›› !! ሁለት ሰዓት ሲሆን ስልኬን አነሳሁና የተሰጠኝን ቁጥር ከወረቀት ላይ አይቸ ልደውል ካልኩ በኋላ አንድ ነገር ትዝ አለኝ …ስሟን አላውቀውም !! ወይ ጉድ…. ስሟን እንኳን ሳላውቅ ነው ይሄ ሁሉ ከመንገድ የረዘመ ሃሳብና ሃተታ ….ኤዲያ !ለነገሩ ሁሉም ቆንጆ ሴቶች ስማቸው ‹‹ቆንጆ›› ስለሆነ ነው መሰል ስለስማቸው የምናስበው ቆይተን ነው ! ለነገሩ በህይዎት ቅኔ ውስጥ ስም ወርቅም ይሁን ቆርቆሮ ማንነትን መሸፈኛ ሰም ነው! ስም እንደውም ሰምና ወርቅ ከሚበለው ነገር የመጣ ሳይሆን አይቀርም ! …..

ወቸ ጉድ ምንድነው ግን እንዲህ የባጥ የቆጡን የሚያስለፈልፈኝ …አንድ ችግርማ አለ ! ሸቶኛል ግዴላችሁም የሆነ ጣፋጭ ችግርማ ሽቅብ የቤቴን ደረጃ ሲወጣ እየተሰማኝ ነው !! (እዚህ ብሎክ ላይ አብርሃም የሚባለው ልጅ የተከራው ቤት የትኛው ነው እያለ) (እኔ ነኝ ችግርየ ና ግባ …የምል አይነት እተሰማኝ ነው …ሆሆ ‹‹ተው ልቤ ተው ልቤ ገደል ትገባለህ ›› አለ ዘፋኙ)

‹‹ለወንድየ አንበሳው›› ደወልኩ ….
‹‹ሄሎ›› አለኝ …ድምፁ የተቆጣ ይመስላል …ከኋላው የጠርሙዝ ካካታና የሰዎች ጫጫታ ይሰማል …አጅሬው መጠጥ ቤት ነው ማለት ነው …
‹‹ሄሎ ወንድየ አብርሃም ነኝ …ሰላም አመሸህ ››
‹‹ደህና›› ባጭሩ ቆጣ ብሎ መለሰልኝ ! ሆሆ
‹‹ ለባለቤትህ ልደውልላት ብየኮ ስሟን ለካ አላውቀውም ››
‹‹ ወንዴ አንበሳው ውሃ በላሽ….›› ብሎ ፎከረና ….‹‹ስማ ጭራሽ ደውለህ የሚስትህን ስም ንገረኝ ትላለህ ….ጎረቤት አክብሬ ነፍስህን ባተርፋት ጭራሽ ለኔው ደውለህ የሚስቴን ስም …. ወይኔ ወንዴ አ…..›› ከሽ ! በብስጭት የመጠጥ ጠርሙዙን ሳይሰብረው አልቀረም …..
ግዴላችሁም ይሄ ልጅ ጨረቃ ሲወጣ የሚነሳበት አጋንንት አለ …ጧት ሰላም አልነበር እንዴ ??….ግራ ገባኝ! ደውልና አስታርቀኝ ብሎ ስልኳን ሰጥቶ ምናባቱ ነው እንዲህ የሚያስፎገራው … እኔም ቱግ አልኩ ….በውስጤ ግን ‹‹ እስቲ ብስጭቱም ናፍቆቱም ይሆናል›› ብየ ታገስኩ ! ( እንደራስ ነው መፍረድ ….እኔስ ብሆን …ያችን የመሰለች ልጅ ትታኝ ብትሄድ እንኳን ጠርሙዝ ጨረቃን አውርጀ አላንኮታኩታትም?? …የሚሰበር ነገር ሁሉ አልሰብርም እንዴ …ከቤቴ ኮተቤ ሰፈሯ ድረስ ሩጨ ሪከርድ ጭምር አልሰብርም እንዴ ??…..ቢቆጣ እውነት አለው ! ) እና ላረጋጋው ሞከርኩ!
‹‹ወንዴ ኧረ ተረጋጋ ….እኔ የደወልኩት የባለቤትህን ስም ሳላውቀው ብደውልላት ….›› አቋረጠኝ
‹‹ተው እንጅ ….እና ስሟን ሳታውቅ ነው ሚስቴን የበ ….›› እግዚኦኦኦኦ!! አፈረጠው ብልግናውን !!ስድ!!ምናለ አማርኛውን ለስለስ ቢያደርገው …ምናለ ‹‹ስሟን እንኳን ሳታውቅ ነው ሚስቴ ጋር አንሶላ የተጋፈፋችሁት›› ቢል …እሽ ይሄን ባይችል እንኳን …ምናለበት‹‹ስሟን እንኳን ሳታውቅ ነው ….ሚስቴ ጋር አለምህን የቀጨኸው ›› ቢለኝ ….ምናለ ? ስልኩን በብስጭት ጆሮው ላይ ዘግቸ በግርምትና ግራ በመጋባት ቁጭ አልኩ ….‹‹ሆሆ ሚስቴን ….›› ወይ ብልግና እናተ ! እኔስ እሽ ይሁን …ይሄን ብልግናውን ብትሰማ ያች ቆንጆ ሚስቱ ምን ትላለች …..ሽምግልና ውሃ በላት !

**** ****** ******

ልክ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ በግርምት ከተቀመጥኩበት ንቅንቅ ሳልል የቤቴ በር በሃይል ተንኳኳና በድንጋጤ አስደነበረኝ ….ምን ተንኳኳ ብየ አለሰልሰዋለሁ ተንጓጓ እንጅ ! ጓ ጓ ጓ …..
‹‹ማነው ›› አልኩ ድምፄን ጎርነን አድርጌ ( ድምፅ በማጎርነን ጠላት ቢመለስ ኑሮ ጥሊያን ያንን ሁሉ ፉከራና ሽለላ ንቆ ድንበራችን ላይ ድርሽ ባላለ ነበር ወንድነት በድምፅ አይደለም ከድምፁ በኋላ በለው ክንድም እንጅ)
‹ወንድየ ነኝ ›› አለ ከኔም በጎረነነ ድምፅ …..አሁን ነው የወንድ ልኩ እንግዲህ !! ‹‹ ዘራፍ ›› ለማለትም ‹‹እውይ እድሌ›› ለማለትም ግራ እንደገባኝ በሩ ከበፊቱ ጠንከር ባለ ጉሸማ ተንጓጓ ….(አሜሪካ መኖር ጥቅሙ ለዚህ ጊዜ ነበር 911 ደወል ይደረጋል… እዚህ …ወይ ደውየ ‹‹ብሎክ አስራ ስምንት ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል›› ካላልኩ በስተቀር ፡)ነጋሪት ቢጎሰምም ፖሊስ ከነገ ወዲያ ነው የሚደርሰው) ለነገሩ እንጅ እኔ አብርሃም ይሄን ሰካራም ፈርቸ ነው ለፖሊስ ምደውለው ? ወንድ አያውቅም !

ጓጓጓጓጓጓጓጓጓ …..አሁንስ በእግሩ ነው መሰል ያንኳኳው !! እንግዲህ የመጣው ይምጣ ብየ ወደበሩ ሄድኩና
‹‹ማነው ›› አልኩ ….ሃሃሃ ….ቅድም ማን እንደሆነ ነግሮኝ ነበር እኮ ….አይ ፈርቸ እንኳን አይደለም…. ((በስህተት ሰላማዊ ሰው ላይ ጥቃት እንዳልፈፅም ብየ ነው)) እነአሜሪካ በኢራቅ በአፍጋኒስታን ….የአየር ድብደባቸው የሚተቸው ለምንድነው? ….እነኢስራኤል የሚወቀሱት ለምንድነው? …በቅርቡ እንኳን ራሽያ የአየር ጥቃቷ ሲወገዝ የነበረው ለምንድነው ?…..‹‹ሰላማዊ ሰው ላይ ጥቃት እያደረሳችሁ ነው›› በሚል አይደል?!! ….ከነሱ መማር አለብኝ …ዜና መስማትማ ሁሉም ይሰማል ዋናው ነገር ከዜና መማሩ ነው !! ተምረን ለአለም ሰላም የራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርብናል !!
ጠላቴን አፈር ከድሜ ከማስበላቴ በፊት …ከዚህ ፎቅ ላይ አምዘግዝጌ እዛ ታች ያለ ብሎኬት ላይ ከመፈጥፈጤ በፊት …በጥቃቴ የማይጎዳ ሰላማዊ ሰው በሬ ላይ አለመኖሩን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለብኝ !! አዋ…. ‹‹ወንዴ አንበሳው››ን ቁልቁል ስወረውረው ባሏ አምሽቶባት ውጭ ቁማ የምትጠብቅ ሚስኪን ሰላማዊ ሴት ላይ ቢያርፍስ … !! ሰውስ ባትሆን ….የምሽት ጉርሱን የሚለቃቅም ውሻስ ቢሆን ካለእዳው ለምን ይሙት ????…..
ደግሞ በሬን ያንኳኳው ሌላ ጎረቤት ቢሆንስ … ሰው ለስንት ነገር ጎረቤቱ ጋር ይሄዳል …ሰዓት ሊጠይቅ የመጣ ጎረቤት ሊሆን ይችላል …የዛሬ ሁለት ወር አሞኝ ነበር ምናልባት ያኔ ያልተመቸው ጎረቤት ሲመቸው መሻሌን ለመጠየቅ ብርቱካን ቢጤ ጠልጠል አድርጎ መጥቶም ሊሆን ይችላል …እና ለማረጋገጥ እንጅ ፈርቸ አይደለም !! ለምን እፈራለሁ ‹‹ወንዴ አንበሳው ›› እንዳይገድለኝ ? ቲሽ ! …ልሙታ ! እንኳን ((ያችን ለመሰለች ውብ ልጅ)) ሰው ላረባ ነገርስ ተፋልሞ ይሞት የለ እንዴ ….ኧረ ለልማት ተቆፍሮ ክፍቱን በተተወ ጉድጓድ ውስጥም ገብቶ መሞትም አለ …አንድ ፈላስፋ ‹‹የምትሞትለት ነገር ከሌለህ የምትኖርለት ምክንያት የለህም ›› አለ ነው የተባለው ? ይበል ምናለበት እሱ… እንደኔ በሩ በጨለማ አልተንኳኳ …..
እከፍተዋለሁ በሩን ….ችግር የለም ! ይብላኝለት ‹‹ለወንዴ አንበሳው›› መለዓክ የመሰለች ሚስቱን ትቶ በመለዓከ ሞት ጥቁር አክናፍ ታንቆ ወደሲኦል ለሚምዘገዘገው ….እኔማ ከዚህ ምድር ምን ሊቀርብኝ ….ማቄ ነው ጨርቄ …..ዘራፍ !! እከፍተዋለሁ!!

በአልጋው ትክክል! (ክፍል ሦስት)

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...