Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 11)

ከመኪና አደጋው ለትንሽ ተረፍን !
ከባድ መኪናው ፊት ለፊታችን ተምዘግዝጎ ሲመጣና እኔ ጩኸቴን ስለቀው ወንዴ ባለ በሌለ ሃይሉ ፍሬኑን ረገጠው … ወደፊት ተወርውሬ ስመለስ ከመኪናው ውጥቸ የተመለስኩ ነበር መሰለኝ ! መኪናችን እየተንሸራተተች ሂዳ ቀድሞን ፍሬን የያዘው ከባድ መኪና አፍንጫ ስር ቆመች …. ልክ ትልቅ ድመት አፍንጫ ስር እንደቆመች አይጥ !
በየትኛውም አደጋ ውስጥ ትንሽ ደስታ አለ …ምናልባት በህይዎት እንድንኖር አንድ እድል ስለተሰጠን ይሆናል … ደስ አለኝ በመትረፌ …ሞት እፈራለሁ አብርሽ …..እንደሞት የምፈራው ነገር የለም …. የከባድ መኪናውን ሹፌር አደነኩት … እግዚአብሔር ይስጠው ከሞት አፋፍ መለሰን ….ትንሽ ቢዘናጋ ኑሮ በቃ አለቀልን …ፊት ለፊቴ የሚታየኝ የመኪናው አፍንጫ ነበር …እስሩ ገብተናል በቃ ….ሹፌሩ እንኳን አይታየንም …. ወርጀ ባመሰግነው ደስታየ …ግን ምን ዋጋ አለው …. ሃሳቤን ሳልጨርሰው የከባድ መኪናው ሹፌር መኪናውን ወደኋላ ስቦ በወንዴ በኩል አለፈና …በመስኮት ብቅ ብሎ ‹‹ አንተ የውሻ ልጅ …አንዲት ሸርሙጣ ጋር እየተዳራህ ጣጣ ውስጥ ልትከተኝ ነው ›› ብሎ መኪናውን አስጓርቶ ተፈተለከ …. እንደው በደፈናው ወንዱን ሁሉ አትውቀሽ አትበለኝ እንጅ እንኳን እንደጎን አጥንት ማክበር የሴትን አጥንት በአፉ የሚሰብር እንደኛ ወንድ ማን አለ ??!!
እቤት ስንደርስ አፍንጫየ እየደማ እንደነበር አወኩ …የራት ልብሴ ከፊት በደም ተበክሏል … ደም አልወድም …ቢሰከ
ክርም ወንዴ አይዞሽ እንዲለኝ ፈልጊያለሁ ‹‹እንዴ›› ብየ ጮህኩ …ወንዴ ዝም አለ !! አፍንጫየን በእጀ ጠርጌ ደም የነካ መዳፌን እንዲያየው እየዘረጋሁ እንደገና ‹‹እንዴ›› አልኩ ወንዴ አየት አድርጎኝ ዝም አለ ‹‹ምን እንዴ እንዴ ትላለች ደም ብርቅ ነው እንዴ ›› የሚል ነበር ሚመስለው ….ግራ ገባኝ ወንዴኮ በየወሩ ‹‹ማንስትሬሽን›› ላይ ስሆን እንኳን የሚደነግጥ ልጅ ነበር ….
ከደሙ በላይ የሱ ቸልተኝነት አስደነገጠኝ ….ድንጋጤው ድራሹን አጥፍቶ አፉን አዘግቶት የነበረ ስካሩ እቤት ስንገባ አገርሽቶበት የባጥ የቆጡን ሲቀባጥር የከባድ መኪናውን ሹፌር አገለዋለሁ እያለ ሲፎክር ቆይቶ ልብሱን እንኳን በቅጡ ሳያወላልቅ አልጋው ላይ በቁሙ ወድቆ እንቅልፍ ወሰደው …. እንግዲህ የመጀመሪያ ቀን ያውም በተለሳለሰ ቃል ወንዴን ስለወደፊት ህይዎታችን መጠየቄ ይሄን ሁሉ መዓት ካመጣ ….አፈሩን ፈነቃቅሎ የተነሳን እውነት በራት ግብዣም በመጠጥም መልሶ ለመቅበር መሞከር እውነትን ማስቆጣት ነው … የተቆጣ እውነት ደግሞ እንኳን በትዳር መሃል የሚፈጠር ብጥብጥ ቀርቶ በአገራት መካከል ጦርነት ከመቀስቀስም አይመለስ !ነገስ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን እንጃ ….ድክም አለኝ …እኔም የራት ልብሴን ከኋላ ዚፑን ከፈትኩት ሰውነቴ ላይ እየተንሻለለ ወርዶ እግሬ ስር… ተጎዘጎዘ…. የከበበኝን ቀሚሴን ተራምጀ ወንዴ ጎን ተጋደምኩ ….
በቀጣዩ ቀን አርፍደን ተነሳን ….ማታ ስለሆነው ነገር ሁሉ ሁለታችንም አንዲት ነገር ትንፍሽ አላልንም …. እዛው ሰፈር ወዳለ ሬስቶራንት ሂደን ቁርስ በላን ….እንደው ቁርስ አልኩ እንጅ ሰዓቱ ወደምሳ ሰዓት እየተቃረበ ነበር ….የወንዴ ጓደኞች ተንጋግተው ወደሬስቶራንቱ መጡ …የተለመደው ወከባ ሳቅና ጨዋታ ተጀመረ …. እነሱ ጫት እስከሚገዙ እኔና አንዲት የወንዴ ጓደኛ ‹‹ሚስት›› ወደቤት ሂደን ቤት አዘገጃጀን ….. ለምን እንደሆነ እንጃ ብቻ ውስጤን ቅፍፍ ብሎታል …ማታ የሳተኝ ሞት አመዱን አራግፎብኝ ሂዶ ነው መሰል ….ወሃ ውስጥ ተነክራ እንደወጣች ድመተፈ አስሬ ፊቴንና ፀጉሬነፈ እያርገፈገፍኩ ነቃ ለማለት እጥራለሁ,,,,,
እንደገና ቤታችን ሞቅ ሞቅ ሲል ጭሱ ወደላይ እየተነሳ የሳሎኑን አየር በመልካም መዓዛ ሲያውደው … የወንዴ ጓደኞች አብረዋቸውም የመጡ ቆነጃጅት ሳቅና መሽኮርመም ለቤቱ ሙቀት አንዳች እሳት ሲጨምር ….ይች የምናፍቃት ሰዓት እንደወትሮው አልሆን አለችኝ …. ሁሉም የእኔን እንደወትሮው አለመሆን አልታዘቡም ነበር …ወንዴን ጨምሮ ! ወንዴማ በተዓምር እንደተፈወሰ በሽተኛ ተሳስሮ የነበረ ምላሱ ተፈቶ የወሬው ፊታውራሪ ሁኖ ነበር ….እና በወሬ ውስጥ እየቀነጣጠሰ ፊቴ የሚያስቀምጥልኝ የጫት ቅጠል አለመንካቴን ያወቀው ቆይቶ ነበር …..ድንገት ዞር ሲል …ጫቱ ፊቴ ተቆልሏል ….ቀና ብሎ ፊቴን አየ ከዛም ጫቱን አየ…..
‹‹ አትቅሚም እንዴ? ›› አለኝ ….
‹‹አልቅምም!! ›› አልኩ ……ከአፌ የወጣው ቃል አስደሰተኝ ….ዝም ብሎ የሆነ መጥፎ ነገር ‹‹አላደርግም›› ስትል የሚሰማህ ኩራት አለ አይደል እንደዛ ተሰማኝ …እናም ደገምኩት ‹‹አልቅምም ›› ይሄ ቃል ወንዴን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እንደተለየ አዋጅ አስገርሟቸው ‹‹ምነው …በሰላም ነው ሊ ….ችግር አለ እንዴ ›› ….እያሉ በጥያቄ አዋከቡኝ ….እንደውም እያሱ የሚባለው የወንዴ ጓደኛ (ነገር ማካበድ የሚወድ ሽቅርቅር… እባብ ባህሪ ያለው ) በሪሞቱ ከትልቁ ሲዲ ቴፕ የሚንቆረቆረውን ሙዚቃ እየቀነሰ …(የፈረደበት ቦብማርሊ …ፀበኛ ፖለቲከኞችነ አስታረቀ ቅብርጥስ ቦብ ይሉልኛል ደግሞ…ሲሉ አየሰሙ መጀመሪያ ቦብ ስላስታረቃቸው ፖለቲከኞች ከመደስኮር ከራሳቸው በታረቁ )
እና ይሄ እያሱ ሙዚቃውን ቀነሰና በዛ ጋጋኖ ድምፁ (ሲያወራ ጆሮው አፉ ስር ቢሆንም ይጮሃል) ‹‹አመመሽ እንዴ ወይስ ይሄ ሰውየሽ በሆነ ነገር አበሳጨሽ ›› ብሎ ወደወንዴ በአገጩ ጠቆመና አረንጓዴ ቅጠል የተጨቀጨቀበት ሙቀጫ የሚመስል አፉን ከፍቶ ሃሃሃሃሃ እያለ ሳቀ …..ምንም አያስቅም ….ሁልጊዜ ችግሮችን ወደወንዴ መግፋት … ወንዴ የሚናገራቸውን ነገሮች በእኔ ፊት በማጣጣል በእኔ አይን ግርማ ሞገስ እንዲኖረው እንደሚጥር ገና ድሮ አውቃለሁ !
ተንኮለኛ እንደሆነ አውቃለሁ ….ደግሞ አስተያየቱን አልወደውም …..ሁልጊዜም እሱ ፊት ለፊት መቀመጥ አልፈልግም …. ልክ ወዳጅ መስሎ …‹‹ለ ልእልት ጫት ስጣት እንጅ ብሎ ወንዴን ይገስፀዋል ›› አባባሉ ውስጥ ከወንዴ የበለጠ አስብልሻለሁ የሚል መርዘኛ መልእክት አለ … አውቃለሁ!! ምንስ ከ12ኛ ክፍል ባቋርጥ የሴት ደመነፍሴ እንዲች አይነቷን መብለጥለጥ ከህይዎት ዩኒቨርስቲ በመዓረግ ተመርቃባታለች !
ማን እንቋመጠብኝ …ማን ምራቁን እንደሚውጥብኝ ጠንቅቄ አውቅ ዘንድ የመጣሁበት መንገድ ይሄንኑ ነው ሲሞላኝ የኖረው ….አእምሮየ ውስጥ ሂሳብ የለ ቪዚክስ ማን አየኝ ማን አሽኮረመመኝ በሚል ከንቱነት ነው እድሜየን የፈጀሁት ! ባይጠቅምም የሄምእውቀት ነው ! …..ይሄንንም ልጅ አይኑ የጤና እንዳልሆነ አውቃለሁ …እጠነቀቀዋለሁ ! ይሄን እያሱን ! ለምን እንደሆነ እንጃ ሁሉም እሱ ሲያወራ በአክብሮት ይሰሙታል ….እውቀቱ ግን አዲስ የመጡ ስልኮችን ጎርጉሮ ፈረንጅ የፈጠረውን ‹አፕ› እራሱ የሰራው ያህል ጥቅሙን አጠቃቀሙን አጋኖ ከማውራት አታልፍም …ይሄም ታላቅ ጥበበኛ ሁኖ ይታይ ዘንድ ሰው በሌለበት የጫት ጉባኤ ትልቅ ሰው ተደርጎ እንደታሰብ አደረገው …ነፍሴ ግን ትንቀዋለች ….አንድ ቀን ቃል አውጥቶ ተናግሮኝ አያውቅም ግን ይሸክክኛል …. እውቀት የለኝ ጥላቻየን ተንትኘ በዚህ ምክንያት ጠላሁት አልል ….ግን የእውቀት ማነስ ቀልብህን እንድታምን ያደርገሃል !! ቀልቤ አልወደደውም !!
እና ((ጫት አልቅምም)) ማለቴ የቤቱን ሰው ሁሉ ሲያስደነግጠው እያሱ በዚች ንፋስ እንኳን በማታሳልፍ ቀዳዳ…. በትንሹ በተከፈተች የመኪና መስተዋት በኩል እንደምትነፍስ ስለታም ንፋስ እየነፈሰ ወደልቤ ለመግባት ጥራዝ ነጠቅ እውቀቱን መሰላል ሊያደርጋት ሞከረ ‹‹ ሴቶችኮ ስስ ፍጥረቶች ናቸው….ትንሽ ነገር ካሳዘናቸው ስሜታቸው እንደመስተዋት እንከሽ ነው በቃ …ለምሳሌ ልእልት…. ›› በቃ እንደመንገድ የረዘመ ወጉን ይተረትረው ጀመረ …ደግሞ ለክፋቱ ሁሉም እራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰሙታል ….በኋላ ስሰማ ድግሪ አለው አሉ ….እውር ቤት አንድ አይና ብርቅ ነው ! እና ይሄ ድግሪ ቅጥ አጣ እንዴ …ሰው እንዴት ድግሪውን እንደማርገብገቢያ ….የነገር እሳት ለማቀጣጣያነት ይጠቀምበታል ….. ነገር ሸቶታል ኢያሱ በእኔና በወንዴ መሃል ሽብልቅ ሁኖ ሊሰነጥቀን እግሩን እያስገባ ነው ….!የኔም የደመነፍስ አፍንጫ ውሻ ያስንንል ከየትና የት ነው ከክፋት የምትሸተኝ !
ልእልት እያወራችኝ ከንፈሯን ነከሰች … ይሄ እያሱ ያረጋት ነገር ይኖር ይሆን እንዴ ብየ አሰብኩ …. ምን አስቸኮለኝ ልሰማው ….
‹‹ ከዛን ቀን ጀምሮ ….ጫት የሚባል ነገር በአፌ ሳይዞር ሳምንት ሞላኝ … የወንዴ ጓደኞች እኔ ላይ የተፈጠረው ስሜት አልተመቻቸውም አንድ በአንድ እያሉ ከቤት መቅረት ጀመሩ ቤታችን እየቀዘቀዘ መጣ ….ወንዴ እኔና ይሄ እባብ እያሱ ብቻ ቀረን …. ወንዴ ጓደኞች ሌላ ቤት መቃም እንደጀመሩ ወንዴ አንድ ምሽት አዝኖ ነገረኝ ‹‹ሊ ጓደኞቸን እያስቀየምሻቸው ነው …እቤታችን ሲመጡ ፊት መንሳት የለብንም ›› አለኝ
‹‹ምንድነው ፊት የነሳኋቸው ››
‹‹አይ አልቅምም ስትይ ደበራቸው›› ይታይህ አብርሽ … አንግዲህ እንግዳ ተቀባይነታችን የሚጨበጨብለት ራሳችንን ገድለን ከመጣ ከሄደው ጋር ስንመሳሰል ነው (እንደውም ‹ተመሳሰይና…እኛን ምሰያ› የሚሉት ፈሊጥ ሁሉ አላቸው) ይሄው እንግዲህ ያ በሰው ተሞልቶ የሚውል ቤት በመጨረሻ ኦና ሆነ … ሳቁ ከሰመ ….ወንዴ አንድ ሁለት ቀን ብቻውን ጫት ይዞ መጥቶ ሊቅም ሞከረ ምኑም ምኑም አልጣመውም …ደግሞ ሊያስቀይመኝም አልፈለገም … የሚገርምህ እንደዛ ቁጭ ብየ ሶስት አራት ጊዜ አፈላ የነበረው ቡና ለአንዴውም ሰለቸኝ …. ወንዴ ጋር ማውራት ነበር የምፈልገው ስለነገ ማውራት ….ምን እንስራ ምን እናድርግ ….ወንዴ ደግሞ ይሄ ወሬየ አንገሸገሸው ……
እንደውም አንድ ቀን ጫት ልግዛ ብሎ እንደወጣ ደወለልኝና ጓደኞቹ ጋር እንደሚቆይ ነገረኝ …. ባሌን ጨምሮ ያ የጫት ጉባኤ ብቻየን ጎልቶኝ ሄደ ….ከዛች ቀን በኋላ ከሰዓት ብቻየን መዋል ጀመርኩ ወንዴን ለምን ትተኸኝ ትሄዳለህ ማለት አልፈለኩም … የሆነ መለመን መስሎ ተሰማኝ … ማለማመጥ መስሎ ተሰማኝ … ሄደ መጣ ማለቴ አልነበረም ግን በሴት ልብ ውስጥ ብቻ ያለ ማንም ሊረዳው የማይችል የክብር መለኪያ አለ … ማንንም ብንወድ እንኳን ልብሱን ጎትተን አትሂድብን ማለት አንችልም …የክብር መስመር አለ …ልብሱን ሳይሆን ነብሱን ጨምድደን ለመያዝ ነው ጥረታችን …. ችግሩ ያው የብዙሃኑ ወንድ ነብስ ደግሞ መያዝ አትወድም !!
ወንዴን ዝም አልኩት ….በአይኔ ብቸኝነቴን ነገርኩት … እንዳላየ ወደጓደኞቹ ሮጠ …ጧት በሞፈር ተሰቅስቆ የማይነሳው ልጅ እንደወፍ ጧት መነሳት ጀመረ …. አብርሽ ወንዴ ቷት ሲነሳ በእሱ ቦታ የሚገባው ነፋስ እንዴት አጥንቴን እንደሚሰነጣጥረው …..ጧት ሲያቅፍ ደስ ይለኝ ነበር … ጧት አልጋችን ውስጥ ሁነን የሚረባም የማይረባም ነገር በጎርናና የጧት ድምፅ ሲነግረኝ ደስታየ ልክ አልነበረውም ….እንዲህ እንደድንች ልጣጭ ብርድልብሱን ከላያችን ላይ ገሽልጦ ጥሎ መሮጥ ከየት እንዳመጣው እያሰብኩ እስካሁንም እገረማለሁ …..አንድ ቀን ተየኩት ‹‹ወንዴ ለምንድነው ቷት የምትነሳው››
‹‹አባባን ማገዝ አለብኝ ›› አለኝ ‹‹ስራ ጀምሪያለሁ ›› የእኔ ጥያቄ ከትክክለኛ ስሜቴ ይልቅ መናቅን እንዳሳደረበት ገባኝ …ስራ ለመለወጥ እንጅ ለእልህ አይሰራ ! አንድ ቀን ታዲያ እኔም አብሬህ እሄዳለሁ አልኩት ! ‹‹ከፈለግሽ›› አለኝ ….ተያይዘን ወደአባቱ ሱቅ ሄድን …. ወከባ …ስሚንቶ ይጫናል ይወርዳል …ብረት ይጫላል ይወርዳል ….ጣውላው …ብቻ ሁሉም ነገር ሩጫ ነው …..ወንዴ ሰራተኞቹ መሃል ቁሞ ‹‹እንዲህ አድርጉት እንጅ እንደዛ አድርግ አንተ ምን ቁመህ ታየኛለህ ›› እያለ ያመናጭቃቸዋል …ያው ለእኔ ስራ እንደሚችል በአባቱ ንብረት ማዘዝ እንደሚችል ማሳየቱ ነው ….ሚስኪን ወንዴ …..
አባቱ እኳን እንደሱ አይዋከቡም… ሽክ ብለው በረንዳቸው ላይ ተቀምጠው ….ቡናቸውን እየጠጡ ያፏጫሉ… እኔን ሲያዩኝ ከመቀመጫቸው ተነስተው ደረታቸው ላይ ልጥፍ አድርገው አቀፉኝና …. አብሯቸው ለነበረ አንድ ሰውየ አስተዋወቁኝ ….‹‹የወንድየ ሚስት ናት ….›› አሉት ሰውየው በአድናቆት እያየኝ …‹‹እንደአወስትራሊያ ሞራሌ ቀጥ ያለች ውብ ከየት አገኛት ባክህ ›› ሁለቱም ሃሃሃሃሃሃ ብለው ሳቁ ….አወስትራሊያስ መቸም አወስትራሊያ ነው ‹‹ሞራሌ›› ምንድነው እያልኩ ዝም አልኩ ….
የወንዴ አባት ጎረምሳ ነገረ ናቸው እንደእድሚያቸው አይደሉም …የባጥ ቆጡን ሲያወሩኝ ቆይተው ምሳ ጋብዘውን ወንዴ እቤት አድርሶኝ ወደጓደኞቹ ተፈተለከ !! በቃ ብቻየን መዋልን ለመድኩት !! የማልዋሽህ እንኳን ወንዴ ጓደኞቹ ሁሉ እንደልእልት የሚያቀማጥሉብኝ ጊዜ ይናፍቀኛል …..አንዳንዴ የመስኮቴን መጋረጃ ከፍቸ ታች መንገዱ ላይ ወጣቶች ተያይዘው ሲሄዱ እያየሁ እንባየ ይመጣል …ሰው እወዳለሁ ….ብቻየን የሆንኩባቸው ጊዚያት ትንሽ ናቸው ….ሰው ብቻውን ሲሆን ምን እንደሚያደርግ አላውቅም …. (ይሄ ይሆን ሰው ብቻውን መሆኑ ጥሩ አይደለም ነው ምናምን የሚባለው) እተኛለሁ እነሳለሁ ….ይበለኝ በሰላም አገር አጉል ቅብጠቴ ነው እንደሰባራ ቅል ያስወረወረኝ እላለሁ ….መገፋት ይመስለኛል ….የአገሩን ህግ ጥሶ ደጁ እንዳትደርሱ እንደተባለ ወንጀለኛ የተገለልኩ ይመስለኛል …..በቃ እንዲቹ ቁጭ ብዲግ ስል እውላለሁ ወንዴ ጓደኞቹ ጋር ውሎ ይመጣል ….‹‹ሃይ ብለውሻል›› ይለኝ ነበር መጀመሪያ አካባቢ ሲቆይ እሱም ራሱ ሲገባ ሃይ ማለቱን ተወው !!
ቢጨንቀኝ እህቴን ቀን ቀን እንድታዋውለኝ እጠራት ጀመር …ከዩኒቨርስቲ ታማ አቋርጣ መጥታ እቤት ነበረች …(መቸስ ዞረን ባናያቸውም ለችግራችን ያው ቤተሰብ ነው) ወንዴን ፈራሁት ፊቱን እያቀጨመ ያችን ርእስ እንደገና እንዳላነሳት አደረገኝ ….መሸሽ ነበር መፍትሄው አብርሽ ….እንደውም አንድ ቀን … ማታ ወንዴ ጋር ራት እየበላን (ምንም ፀባዩ ቢቀየርም ቢሞት ራት ውጭ አይበላም ) አለ አይደል ለወንድ መንበርከክ ልክ ባይሆንም ይሄንኛውኮ ባሌ ነው ብየ …እስቲ ነገር ላብርድ አልኩና …. ‹‹ወንዴ እኔ ላስቀይምህ ፈልጌ አይደለም ስለወደፊት ኑሯችን ያነሳሁት ….›› አልኩት ….ዝም ብሎ ይበላል አበላሉ የእልህ ነበር የሚመስለው ቀን እህቴ በጥታ የሰራችው ወጥ …. ዝም ሲለኝ ቀጠልኩ
‹‹አንተም እኔን ከመሸሽ ቢያንስ የተሰማህን ነገር በግልፅ ብትነግረኝ …..›› ብየ ሳልጨርሰው እጁ ላይ የያዘውን ጉርሻ ሰሃኑ ላይ አስቀምጦት ….ተነሳ ….እጁን አወናጭፎ በሰለቸ ድምፅ ‹‹ ንዝንዝሽ ሰለቸኝ …. ምን ጎደለብሽ ልብስ ነው …መዝናናት ነው …. ከማንም ሴት በላይ ድልቅቅ ብለሽ ትኖሪያለሽ …ላንች ስል ከጓደኞቸ ልለያይ ….ምንድነው….ቀን ንዝንሽን ሽሽት ቤት እንደሌለው ሰው ማንም ቤት እውላለሁ ማታ ደግሞ የት ልሂድልሽ ›› ብሎኝ እጁን ታጥቦ ወደምኝታ ቤት ሄደ! እጁን ሲያወናጭፍ ፊቴ ላይ አንዲት የወይ ቅንጣት አረፈችብኝ ….ረዥም ሰዓት የተቀመጥኩበት ሳልነቃነቅ ቆየሁ ! በታሪክ ወንዴ ደፍሮ እንዲህ ገልምጦኝም ተናግሮኝም አያውቅም !!
እጀ ላይ የያዛኳትን ጉርሻ ወደሰሃኑ መለስኩ …የወንዴ ተዘጋጅታ የተቀመጠች ጉርሻ በዛ የኔ በዚህ ቁመው እየሞተ ላለው መከባበራችን መታሰቢያ የቆሙ ሃውልቶች መሰሉ ….እንደጥያ ትክል ድንጋዮች ጉርሻወቻችን በየፊታችን ሰሃኖቻችን ላይ ቆሙ …. አላዘንኩም እንደውም ከየት መጣ ሳልለው …. እልህ አይሉት ቁጣ ከተቀመጥኩበት አስፈንጥሮ አስነሳኝ … እንዳበደ ውሻ ባሌ ፈርቶ የሚሸሸኝ ልእልት ሁኛለሁ ለካ ….የተለጎመ አፌን በግድ ከፍቶ ካልተናገርሽ የሚለኝ ባሌ …ቃሌን አፉን ከፍቶ ከነጓደኞቹ በጉጉት ለሚሰማኝ ወንዴ ‹‹ንዝንዜ የሚሰለች መንቻካ ሚስት›› ሁኘበታለሁ ለካ …..ከእግር እስከራሴ የሆነ ስሜት ወረረኝ …ወደመኝታ ቤት ሂጀ በሩን በርግጀው ገባሁ …. ወንዴ ተከናንቦ የተኛውን የአልጋ ልብስ ከነብርድልብስ እና አንሶላው ጓፍፌ መሬት ላይ ጣልኩት …..
ወንዴ (((በሌሊት ልብስ))) ሁኖ በግርምት አፈጠጠብኝ …. ((((( ደግሞ ከመቸ ወዲህ ነው የሌሊት ልብስ ለብሶ መተኛት የጀመረው … ))))) ደሜ ፈላ ….ይሄ ቀላል ነገር ይመስላል አይደል …..አይደለም …..!! መጀመሪያ ቀን አብረን ካደርንባት ቀን ጀመሮ እኔ ጋር ሲያድር ወንዴ ራቁቱን ነበር የሚተኛው …. ከተጋባንም በኋላ ቢሆን ከቀለበቱ ውጭ መለመላውን ነው የማውቀው ….እኔም እንደዛው …እንግዲህ ይሄ ምንድነው ….ሰውነቴ እንዳይነካው የልብስ ቅጥር ዙሪያውን ማቆሙ አይደል …በፍቅረኞች መሃል ቃል የማይገልፃቸው ግን ከመንፈስ የሳሱ ስንት ድርጊቶች ስንት ልማዶች አሉ ….ከቃል በላይ ከድብደባ በላይ እነዛን ነገሮች በሚወዱት ላይ ሲቀየሩ ማየት ያበግናል ያቃጥላል !!
ተቃጠልኩ …መነጋገር ሳይሆን ወንዴን በጥርሴ መዘልዘል በጥፍሬ ሰውነቱን ማረስ አማረኝ … እኔም ከዛ በፊት እንደዛ አይነት ልጅ መሆኔን አላውቅም ነበር ….ለካስ በውስጣችን ለክፉ ቀን የተቀመጠ ክፉ እኔነት አለ …አሁን ልእልት አይደለሁም ….አሁን እንባ የሚቀድመኝ ልእልት አይደለሁም … አሁን በወንዴ አይኖች በወንዴ ቃሎች በወንዴ እጆች ዳሰሳ እንደቅቤ እጁ ላይ የምቀልጥ ልእልት አይደለሁም ….አሁን ልውደቅልሽ ልነጠፍልሽ የሚለኝ ባሌ በዓይኑም በአንደበቱም ያቀለለኝ …ያልተማርኩ ሃብት የሌለኝ ተስፋ የሌለኝ ልእልት የምባል ምንም ነኝ ….አሁን በሃያል ጥላቻ ክንድ ከሳሎን ወደዚህ ወደናቀኝ ወንድ የተወረወርኩ ድንጋይ ነኝ …..እንኳን ትላንት ጉልበቴ ስር ተንበርክኮ ሲያለቅስ የነበረ ወንድ ….ሰይጣንም በምትወደው ወንድ የተናቀች ሴት ፊት እግር ጥሎት ቢቆም….. ጅራቱን ሸጉጦ ነው እግሬ አውጭኝ የሚለው …. ወደፊት ተራመድኩ ወደአልጋው ….

በአልጋው ትክክል (ክፍል 12)

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...