Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል አስር)

‹‹እንክብካቤ ሁሉ አክብሮት አይደለም ›› አለች ልእልት … ‹‹ይሄውልህ እንግዲህ አማርኛ ፊልም ላይ ድራማ ምናምን …ወይ ጸጉር ቤት ስቀመጥ የታጠበ ፀጉሬ እስኪደርቅ በአተት ኮተት ታሪካቸው የሚያደርቁኝ የፋሽን መፅሄቶች ….(በኋላ ነው አድርቅ መሆናቸው የገባኝ በፊትማ እንደውዳሴ ማሪያም ነበር የምደግማቸው ) እነዚህ የፋሽን መፅሄቶች ለሴት ያደላ በሚመስል የስጋ ወግ …..ስለስንት አይነት እንክብካቤ ነግረውኛል ….‹‹ባሌን የምወደው ስለሚንከባከበኝ ነው ›› የምትል ዘፋኝ ሞዴል ምናምን በየመፅሄቱ አትጠፋም ….. እኔም እነዚህ ሴቶች የሴቶች ቁንጮ መስለውኝ (ያው መቸስ ሰው ባዶውን መፅሄት ሽፋን ላይ ኩፍስ ብሎ የሚወጣ አይመስለኝም ነበርና) በቃ ወንዴ ስለሚንከባከበኝ ምርጥ ባል ነው ብየ ቁጭ ብየ ነበር !
አንዳንዶቹ መፅሄት ላይ የወጡ ሴቶች እዛው እኔ ፀጉሬን የምሰራበት ፀጉር ቤት እኔው ጎን ተቀምጠው የራሳቸውን ‹ኢንተርቪው› ላስረኛ ጊዜ ሲያነቡ አያቸዋለሁ ! እነሱ ጎን መቀመጤ ከዚች አገር ተመርጠን ለድሎትና ለምቾት የታደልን ወይዛዝርት አድርጌ እራሴን እንዳስብ ያደርገኝ ነበር ! ‹‹ኦ እከሊት የምትሰራበት ፀጉር ቤትኮ ነው የምሰራው›› ይሉት ተልካሻ ኩራት ! እና እነዚህ ሴቶች በነበረ ድድብና እንቅልፌ ላይ በጥሬ ፍልስፍናቸው እንቅልፍ ጨምረውልኝ ኑረዋል … እንክብካቤ ምንድነው ….ባል ለሚስቱ ቀሚስ ገዛ ተብሎ እንክብካቤ ሲባል አስበኸዋል ….አንዲት ሴት ‹‹ባሌ ስለማይደበድበኝ በጊዜ እቤቱ ስለሚገባ ይንከባከበኛል ›› የምትልበት አገር …ይታይህ አለመደብደብ እንክብካቤ ሲሆን … እንግዲህ ሚስትን መደብደብ ወንጀል ሳይሆን ‹የእንክብካቤ ጉድለት › ሊሆን አይደል …
እድገታችን ራሱ ወንድ ለሴት ልጅ ሊያደርግ የሚገባውን እንክብካቤ ከስጦታና ከሰማነው አስከፊ ትዳር የተለየ ትዳር ስላለን ብቻ ይሄንኑ ሚዛን እንድናደርገው አድርጎናል ….እውነቱ ግን የወንድ ጨዋነት ልኩ የሚታየው ሚስቱ ምንም ይሁን ምን እሱን ተከትላ መንኳተቷን አቁማ ‹‹ለምን›› ማለት የጀመረች ቀን የሚያሳየው ጨዋነት ነው …. የሚሰጠው ትክክለኛ ምላሽ ነው !! እንክብካቤ ልኩ ሚስትን አቋሟን የሚያሳምር ቀሚስ አልብሶ መጎተት ሳይሆን በራሷ እንድትቆም በሞራልም በሚችለውም ሁሉ መርዳት መቻል ላይ ነው ….
ለሴት ልጅ የማያቋርጥ ስጦታ እየሰጡ ስጦታ ጠባቂ ተስፈኛ ማድረግ እንክብካቤ አይደለም ….እንደውም ከጡረታ እኩል ነው … ወጣት ጡረተኛ ማድረግ ….ቆንጆ ጡረተኛ ! የፍቅር ጡረተኛ ….!! ሲቆይ በብሬ ነው የማኖራት የሚል የንብረት ባለቤትነት መንፈስ ያነግሳል ! ምርጥ ወንድ በእኔ ተማመኝ የሚል አይደለም ….እኔ ባልኖርም ግራ መጋባት ባጠገብሽ እንዳያልፍ ብሎ መንገድ የሚመራ ነው …..ስንቶቹ ናቸው አባወራ ሲሞት ሜዳ ላይ ልጆቻቸውን ይዘው የወደቁ !! ወንድ ባል ወላ ፍቅረኛ እድሜ ልክ የሚኖር ብረት ምሰሶ አይደል …ሰው ነው …ወይስ ይሄም ቢሄድ ራስን ለሌላ ወንድ ጉዲፈቻ ለመስጠት ተስፋ ማድረግ ነው … ትዳር አይደለም ይሄ ጉዲፈቻ ነው ….የሚስት የፍቅረኛ ጉዲፈቻ ….!
ልክ ወንዴ ደብረዘይት የመኪና አደጋ የደረሰበት ጓደኛውን ለማየት የሄደ ቀን ዝጎ እንደቆመ ማሽን (መኪና ምናምን) …በምቾት እና ሆሆታ ታስሮ የቆመ አእምሮየ ድንገት እያቃሰተ ተነስቶ ለራሴም ልቆጣጠረው በማልችለው ፍጥነት በሃሳብ ተፈተለከ …ልክ እንደጣውላ መሰንጠቂያ ማሽን ነበር ሁሉም ነገር የሚጮህብኝ … ለምን እንዴት …የጥያቄ እና ወቀሳ መዓት እያመጣ ይቆልልብኝ ነበር …. ምንም ይሁን ማሰብ መጀመር ፈውስ ነው ….አብርሽ ሙት !! እንደውም የሴቶች ቀን የባንዲራ ቀን የፍቅር ቀን ምናምን እንደሚባለው ይች አገር ይሄ ህዝብ ‹‹የሃሳብ ቀን›› የሚል አንድ ቀን ሊሰይምለት ይገባል …ሁሉም ብቻውን ቁጭ ብሎ ፋታ ወስዶ አነሰም በዛም የሚያስብበት !! የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ማሰብ በመቻሉ ነው ይላሉ ….ምናይነት ሃሳብ ማሰብ በመቻሉ ??? የሄንኛው ቀሚስ ከዚህኛው ጫማ ጋር ማች ያደርጋል የሚል ሃሳብ ነው ከእንስሳ የሚለየን? … ይሄንኛው ቅባት ከዛንኛው የተሸለ ቆዳየን ያለሰልሳዋል ማለት ነው ከእንስሳ የሚለየን ሃሳብ …? ለራሳችን ብዙ ሳቅና የጨረባ ተስካር የሚሉት አይነት ጫጫታ በመፍጠር አለምን መርሳቱ ነው ትልቁ የአእምሯችን ፈጠራ ?
ልእልት ትክ ብላ አየችኝ …አይኖቿ ጥርት ያሉ… ምን ማለት እንደፈለገች በትክክል የገባት …በትክክልም ዓይኖቿ ነገዋን የሚመለከቱ ይመስላሉ …ኖርኩበት የምትለው ህይዎት እና አነጋገሯ አልገጥምልህ ብሎኝ አያታለሁ …. ማሰብ ከመማር እንደሚበልጥም በልእልት ገባኝ ….ሳይማሩ ማሰብ ይቻላል ተምሮም አለማሰብ ይቻላል …ትክክለኛው ትምህርት ምን ማሰብ እንዳለብን የሚያሰለጥነን ሳይሆን እንዴት ማሰብ እንዳለብን የሚመራ ብርሃን በፊታችን የሚያበራ ነው … ‹‹እንዴት›› ማለት ስንጀምር ‹‹ለምን ማለት ስንጀምር›› ቢያንስ ችግራችንን ፊት ለፊት ማየት እንጀምራለን …. እንደውም መማር ባንማርም ለምናውቀው ችግር መፍትሄ ይዞ ሲመጣ ነው …የእድገትም እንበለው የውድቀት መሳሪያ የሚሆነው …. እና ልእልት ያንን ምቾት ያንን ድሎትና ፍቅር የመሰላትን አብሮነት ….በአንድ ቀን እሷ እንደምትለው ‹‹የተረገመ ይሁን የተመረቀ ቀን›› ብቻ ‹‹ለምን ›› ብላ ጠየቀች ….
‹‹እና አብርሽ….. የዛን ቀን እዛች ሶፋ ላይ ተኮርምቸ ….የነገ እጣ ፋንታየ ምንድነው ብየ አሰብኩ … ሚሊየኖች ላባቸውን ጠብ አድርገው እንደልፋታቸው ሳይደሰቱ በሚኖሩባት አገር …. ሚሊየኖች እንደኔው ከደሃ ቤተሰብ ተፈጥረው ግን ከእኔ በላይ በስራ ፈግተው ቁራሽ ዳቦ እያጡ በርሃብ በሚጠራሞቱባት አገር ….. የፈሰሰ ውሃ የማላቀና እኔ በህይዎት ዘመኔ አንዲት ነገር ሰርቸ የማላውቅ እኔ እንዲህ የተቀማጠለ ህይዎት ለመኖር የታደልኩት በምን ምክንያት ነው አልኩ …ቆንጆ ሴት ስለሆንኩ ብቻ ? በቃ ? አእምሮየ የመጣልሽን እድል አትግፊ አርፈሽ በድሎት ኑሪ ይለኛል …ለማንም አስቤ አይደለም አገር ህዝብ ለሚባለው ነገር የምቆረቆር ሁኘም አይደለም ….ግን ዛሬ ለዚህ ምቾት የዳረገኘን እድልም በለው አጋጣሚ ነገ ከተሰቀልኩበት ማማ አውርዶ ችግር ላይ እንዳይፈጠፍጠኝ አስተማማኝ ነገር ለመፍጠር እየቃተትኩ ነበር ….››
በቀጣዩ ቀን ወንዴ ከደብረ ዘይት መጣ ….ጓደኞቹ ሁሉ ከነሳቃቸው ከነጫዋታቸው … ከነጫታቸው ….ከነቆንጆ ሴት ጓደኞቻቸው ቤታችንን ሞሉት ….ነብሴ ትላንት ሙሉ ቀን በብቸኝነት ስትላቅጥበት የነበው ሃሳብ ያ ሁሉ ፍልስፍና ላስታውስህ ብለው ከየት ይምጣ ….በቃ ወንዴን እጠይቀዋለሁ ያልኩት ሃሳብ ሁሉ ድራሹ ጠፋብኝ …. ምሳ ይበላ ሲባል እና ካ ከዚህጉርሻ ታጠቁ እጆች ወደኔ ሲወነጨፉ (ሁልጊዜም ወንዶችም ይሁን ሴቶች መሃል ስገኝ እንክብካቤው ወደኔ ያደላል መሃል እሆናለው በቃ ትኩረቱ እኔ ላይ ይሆናል…ትንሽ ኩራት ሳይጭርብኝ አልቀረም ይሄ ነገር ) ….ቡና ይፈላ ሲባል ….ጫት ሲቀራርብ ….ቤቱ በእጣን ጭስ ተሞልቶ ጨዋታና ሳቃቸው የማይጠገብ ጓደኞቻችን ግራ ቀኝ ጥርስ የማያስከድን ጨዋታቸውን ሲያዘንቡት …ደግሞም በዛ ህልም በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ወንዴ አስር ጊዜ በፈገግታ ሲመለከተኝ በስሱ አይኖቹ እየተመለከተኝ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው የጫት ቅጠሎቹን እየቀነጣጠሰ ሲሰጠኝ …..ጫቱ ራሱም ውስጤ ስራውን ሲሰራ እንኳን ለነገ ለቀጣይ ሽ አመታት በምድር ብኖር ችግር እንዲች ብሎ የማይነካኝ ዘላለም ልእልት ሁኘ በፍቅር ነግሸ የምኖር መስሎ ተሰማኝ !!
‹‹አብርሽ ››አለችኝ ድንገት
‹‹ወይየ ልእልት›› አልኩ (በለውውውው ‹ወይየ› ያች ነገረኛ እህቴ በአካባቢው አለመኖሯ እንጅ ይች ቃል ታሪካዊ ሁና በተመዘገበች ነበር በህይወቴ ማንንም ‹‹ወይየ›› ብየ አላውቅም ….እንኳን ወይየ …ወይ እራሱ የሆነ ማግኔት መንፈስ ያለው ቃል እኮ ነው ….አቤት አለሁልሽ ምን ልታዘዝ ስለጠራሽኝ ደስ ብሎኛል የፈለግሽውን ጠይቂኝ …ወዘተ የሚል ‹እንስፍስፍ› ቃል ነውኮ ወይየ !! ….መንገድ ላይ ድንገት መንገድ ጠፍቶብን ልንተይቃት አንዷን ልጅ …ይቅርታ የኔ እህት ስንላት ‹‹ወይየ ›› ብትለን የሆነ የሚነዝር ስሜት አለውኮ ….ኧረ ስለወይየ እናውራ ካልን ስንት ጉድ አለ አስማተኛ ቃል ነው ….እና ልእልት ‹አብርሽ› ስትለኝ ‹ወይየ› አልኳት )
‹‹መቸም ጫት ቅመህ ታውቃለህ !!›› አለችኝ ጥያቄ ሳይሆን ‹‹እና ጫት መቃምን እንደምታውቀው ›› ብላ ወሬዋን ለመቀጠል እንደመንደርደሪያ ነበር ጣል ያደረገችው
‹‹አይ አላውቅም ›› ስላት ቀጥ ብላ በግርምት ተመለከተችኝ ….አልገረመኝም ….ብዙ ጓደኞቸ ጫት ቅሜ አላውቅም ስል ልክ ‹‹ከተወለድኩ ጀምሮ ውሃ ጠጥቸ አላውቅም ወይም ምግብ በልቸ አላውቅም ›› ያልኩ ያህል በግርምት ይመለከቱኛል ግርምቱ ውስጥ ብዙ አለማመንና ግማሽ አታካብድ ባክህ የምን ማካበድ ነው ›› የሚል ወቀሳ ቢጤም አለበት …እና የልእልት ግርምት አልገረመኝም
‹‹ማለት …?›› አለችኝ
‹‹ምን ማለት ….?›› አልኳት ግራ ገብቶኝ
‹‹ጫት ምንም ቅመህ አታውቅም ወይስ አቁመህ ነው ?››
‹‹አይ ጫት ቀምሸ አላውቅም ›› አልኳት …(እሷ በመቃሟ ወቀሳ እንዳይመስልብኝ መቃምም አለመቃምም ያን ያህል የሚካበድ ጉዳይ እንዳልሆነ ለመግለፅ ቀለል ለማድረግ በሚሞክር ድምፅ ›› ልእልት የግንባሯን ቆዳ ወደላይሰብሰብ አድርጋ መገረሟን ገለጸችና ….
‹‹እንግዲያውስ የምልህ ሁሉ አይገባህም ›› አለችኝ ….
‹‹ለምን አይገባኝም በደንብ ይገባኛል እንጅ ›› አልኳት በዚች ስበብ ታሪኳን እንዳታቋርጠው ፈርቸ
ዝም ብላ ወደኮርኒሱ ስትመለከት ቆየችና ‹‹ ጫት ስትቅም …. የጫት ስም ሲነሳ ጫቱ አይደለም ትዝ የሚልህ … ስሜቱ ነው ….የሆነ የሚያንሰፈስፍ ስሜት አለው … ለምሳሌ ሁልጊዜ የወንዴ ጓደኞች ሲመጡ ምሳ ስንበላ ቀጥሎ ጫት እንደምንቅም ቡና እንደሚፈላ ሳስብ የሚሰማኝ ጉጉት ….የሆነ አፌ ምራቅ ሁሉ ይሞላል …የሆነ የሚያጣድፍ ነገር ውስጥህን ይሞለዋል … እንዴት ልበልህ በጣም የምታፈቅራት ልጅ ቀጥርሃት ልትመጣ ቤትህን ስታዘገጃጅ ነገር ….እንደዛ አይነት ስሜት አለው ….በቃ ምሳ በልተን ቦታ ቦታችንን ይዘን…. ጫቱ የተጠቀለለበት ጋዜጣ ሲከፋፈት የሚያሰማው ድምፅ ጆሮየ ላይ እንደውብ ሙዚቃ ነበር የሚናፍቀኝ … የመጀመሪያዋ የጫት ጉርሻ አፌ ውስጥ ስትጨመቅ መራር ግን አእምሮ ላይ የሆነ ንዝረት የሚፈጥር ጭማቂው በጉሮሮየ ሲወርድ ዝናብ እንደናፈቀው መሬት የሚረሰርስ አንዳች ነገር አለ …ያኔ ሁሉንም ነገር በፍቅር ነው የማየው …በዛች ቅፅበት ቀጥሎ ላለችው የጫት ጉርሻ አገር ሽጭልን ቢሉኝም ጆሮዋን ነበር የምላት ››
አባባሏ አሳቀኝ …ከልቤ አሳቀኝ በዛ ላይ ቆንጆ ፊቷ ላይ እንደወሬው ስሜት የሚፍለቀለቀውና እዝን የሚለው ስሜቷ የሆነ የማይጠገብ ናፍቆት ይጭራል (እኔማ እንኳን ዘንቦብሽ አሉ …እንደልእልት አባባል ጫት እንደተባለው አይነት ስሜት ካለው ለእኔ በዚህ ሰአት ልእልት ጫት ነው የሆነችብኝ … ቀጣይ የወሬ ጉርሻዋን ለመስማት አገር ሽጥልን ቢሉኝ ….ከመረብ መልስ ….ጆሮዋን ነበር ይችን ጦቢያን!! ….ለብር ተሸራርፋ ከምታልቅ ለፍቅር ብትሸጥ ለሷም ሳያዋጣት ይቀራል ?ቢበዛ ለሴት ብሎ አገሩን ሸጠ ተብ ብወቀስ ነው …እራሷ ጦቢያስ ‹‹አንች በሉኝ›› ያለችው ሴትነትን መርጣ አይደል!!)

‹‹ እንግዲህ እንደዛ እንስፍስፍ ብየ የምጀምረው ጫት ….ጨዋታው እየሞቀ ….ምርቃናው(ቃሉ ያጠላኛል) ከፍ እያለ ይሄድና ….መልሶ ስሜቱ ወደመቀዛቀዝ ሲወርድ …..አንዱ የወንዴ ጓደኛ ….የሆነች ጉዳይ እንዳለችው ገልፆ ሲወጣ …ሌላው ሲቀጥል …ያ ሁሉ ጫት ወድሞ የጫት ገረባ ፊታችን ሲከመር ….የቅድሙ ፍክት ያለ ንጣታቸው ተፍቶ የአተላ ቅሪት የተደፈደፈባቸው የቡና ሲኒዎች ፊታችን ተደርድረው አንዳንዶቹም ምንጣፉ ላይ ተከንብለው ….ሳይ …ማጨሻው እሳቱ ከስሞ ከነአመዱ ሲያንቀላፋ ….ሆድ ይብሰኛል ….የሆነ (((እቃቃው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ))) አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ … እና ያንን ደስታ ያንን ስሜት ለማምጣት የነገውን የመቃሚያ ጊዜ በናፍቆት እጠብቃለሁ ….ነገም ያው ነው ….ከነገወዲያም እንደዛው … ያጫት ህይዎት በቃ ያች ከመጀመሪያ ጉርሻ እስከመጨረሻዋ ግረባ ያለችው ጊዜ ናት ›› ከዛ ግን የሚተርፍህ የተወዛገበ አእምሮ ብዙ ጊዜም የሌሊቱን ግማሽ በሚያስጠላ የሙቀት ስሜትና እንቅልፍ ማጣት እዚሀና እዛ በሚዛብር ያልተጨበጠ ሃሳብ መባዘን ነው ››

የዛን ቀንም …ልክ ቂምሃው ሲያበቃ ….ወንዴ ጓደኞች አንድ ሁለት እያሉ ሲሰናበቱን … እኔና ወንዴ ብቻችንን ስንቀር …ባለፈው ቀን ሲያስጨንቀኝ የነበረው ሃሳብ ሁሉ ኬት መጣ ሳልለው ተንጋግቶ መጣልሃ ….ወንዴን ዝም ብየ አየሁት ….ሌላ ነገር የፈለኩ መስሎት በእጁ ያዘውን የጫት እንጨት ወርውሩ እጆቹ ጡቶቸ ላይ አረፉ ….ሌላ ሰው የነካ ይመስል ምንም አልተሰማኝ ዝም ብየ ሳየው እሱም ግራ ገባው መሰል ‹‹ ሊ ›› አል ሲጠራኝ ‹‹ሊ›› እያለ ነው ….እንግዲህ ልእልት ሲቀናጣ መሆኑ ነው እኔም ሊ ሲለኝ ደስ ይለኛል …በዚች ፊደል ስንት ቀን ዘራፍ ብሎ የተነሳ ልቤን ውሃ እየቸለሰ አቀዝቅዞታል …
‹‹ሰላም ነሽ የኔ ማር ›› አለኝ
‹‹ወንዴ …ትላንት ሳስብ ነበር ….››
‹‹ምን የሚያሳስብ ነገር መጣ ልጆቹ ናቸው … ስራው ነው …ወይስ እግሬ ወጣ ሲል ጠብቀው በሌለሁበት መጥተው አገሪቱን ምሪልን ካላንች ተስፋ የላትም አሉሽ.. ›› ብሎ እየሳቀ አቀፈኝ ….ቀስ ብየ ከእቅፉ ወጣሁና ነገሬን ከምን እንደምጀምር ግራ ገብቶኝ አየሁት …ወይኔ ባልቃምኩ ኑሮ ….አልኩ…..!! አንዱን አስቤ አንዱን ቅዥብርብር አለብኝ ….እስቲ አሁን ከየት ልጀምረው ……ብየ ግራ ገባኝ ….ባወጣ ያውጣው ብየ አፌ ላይ ከመጣልኝ ዘነኮርኩት ደግነቱ የሴት ምላስ በራሱ አእምሮ ነገር ነው ነገሮችን ያደራጃቸዋል …..
አሁንም በአባባሏ ሳኩ ….ደግሞ እውነት አላት ..ሴቶች ተበሳጭተው እንኳን እንደእኛ እንደወንዶች አይዘነኩሩም ….የፈለገ ቢያወሩ ቢጮሁ ምላሳቸው አእምሮ ነገር ነው ውሉን አይስትም !ደግሞ የተናገሯትም አይረሱም ነጥብ አይረሱም !! ልእልት ለወንዴ ኬት ጀምራ ምን ብላ እንደነገረችው ማየቱ በራሱ ይሄን ነገር ያረጋግጣል ….
‹‹ትላንት ጓደኛህ የመኪና አደጋ ሲደርስበት ደነገጥኩ …. በጣም ፈራሁ ….ይሄ ነገር አንተ ላይ ቢሆን ኑሮስ ብየ ፈራሁ ወንዴ ….››አለችው ወንዴ የመፈቀር ሃሳብ ልቡን አስከፈተውና ቀጥሎ የምትነግረውን ሁሉ ለመስማት ሰፍ አለ …..ልእልት እንዲህ ብላ ወጓን ቀጠለችልኝ ‹‹ይሄን እየነገርኩት ሳላስበው እንባየ ተዘረገፈ …. ወንዴ ድንገት በተዘረገፈ እንባየ ደንግጦ ጥብቅ አድርጎ አቀፈኝና ….ምንም ያለሰብኩትን ዝባዝንኬ ያወራ ጀመር ….
‹ሊ የጓደኛየን አደጋ እኔ ጋ ምን ያገናኘዋል ….…ጓደኛችንኮ ያው ሲነዳ ተሸውዶ ነው ….ፍሬን ያዝኩ ብሎ ነዳጅ ሰጠውና … ፊት ለፊት የሚመጣ ሌላ መኪና ጋር …ተላተመ ….አየሽ እንዲህ አይነት አደጋ ሲያጋጠም መሪ ላይ መጫዎት አለብሽ …..መኪናሽ ድንገት ወደፊት ሊወረወር ይችላል ….በተለይ ማኑዋል ከሆነ መኪናው …..›› በቃ ወንዴ ማለት ይሄ ነው ….እስቲ አሁን ጓደኛህ እንዴት አደጋ ደረሰበት አልኩ? ወጣኝ ?….ነዳጅ ይርገጥ ፍሬን ይርገጥ እኔ ምን ቤት ነኝ ?….ዋናው ጥያቄ ‹‹አንተን ባጣ ምን እሆናለሁ ? ነው ….ሰው የሚሞተው ፍሬን ረግጣለሁ ብሎ ነዳጅ ስለሰጠ ብቻ አይደለም መቸስ ….ትንታም በተቀመጥክበት ሊያስቀርህ ይችላል …. ከሞት በኋላስ ነው ..የኔ ጭንቀት ….ሟችማ ያው ወይ ገነት ወይ ሲኦል ይገባል እንደሚባለው ….ቀሪው ነው እንጅ በተለይ እንደኔ ሟች ላይ ተለጥፋ ቅንጡ ህይዎት የለመደች ከንቱ ነገር ነው እንጅ … አሳሳቢው !
ጫቱ ነው መሰል ከዛ በኋላ ያሰብኩትን ልክ ባሰብኩበት መንገድ አንበለበልኩለት ለወንዴ …. ምንደነው የነገ እጣ ፋንታየ አልኩት ….አንተም ስራ የለህ እኔም አልሰራም እስከመቸ በቤተሰብ ሃብት ተማምነን በወጣትነታችን እየተጦርን እንኖራልን አልኩት …. አንተ አንድ ነገር ብትሆን የእኔ እጣ ፋንታ ምንድነው …አልኩት (ለራሷነው ለካ የተጨነቀችው ብሎ ይታዘበኛል ሳልል …ይታዘባ!! ያወራሁት እውነት ነው…. አዎ ለራሴ እያሰብኩ ነው…. እና ከሆነ በኋላ ማነው ለኔ የሚያስብ) ….በቃ ከዚች ቀን ጀምሮ የራሳችን ነገር የምንተማመንብት የማንም ጥገኛ ሳንሆን እንደባልና ሚስት በራሳችን የምናዝበት ስራም ይሁን ሃብት ሊኖረን ይገባል …አልኩት እፎይይ !!
ወንዴ በግርምት አየኝ ፊቱ ሳቅም ግርምትም የተቀላቀለበት ግራ የገባው ፊት ነበር እና ….ሳይስቅም ሳይኮሳተርም እንዲህ አለኝ
‹‹ሊ …ዛሬ ከምር መርቅነሻል …..እስቲ ወጣ ብለን እንመለስ …..እንደውም ዛሬ አሪፍ ራት እለቅብሻለሁ ››
አየህ አብርሽ … እንደዛ ሙሉ ቀን ከበረንዳ ሶፋ እየዘለልኩ የተጨነኩበት ጉዳይ ባጭሩ ‹‹ምርቃና ›› የሚል ስም ተለጠፈበት እና አረፈው …..እዛው ላይ ነገ ጫት እንደማልቅም ወሰንኩ ….አዎ ሳልቅም እነግረዋለሁ ….እውነትን ማስደግፊያ ሰበብ ሲያጣለት ያኔ ምን እንደሚለኝ አያለሁ … ለማንኛውም ነገሮችን ከጅምሩ ላለማክረር ብየ …የራት ግብዣውን ተቀበልኩ …..ሆዴ በአሩስቶ እና ዋይን ቢሞላም …. አእምሮየ አንዴ ከጨመደደው ሃቅ ዘወር አላለም ….ማሰብ ጀምሪያለኋ …በቃ ጥያቄየ ‹ነጋችንስ› ነው ……..
ወንዴ እንደልማዱ የዛን ቀን ደጋግሞ ጠጣ … ሞቅ አለው ….በቃህ ብለውም አልሰማኝም …ሰከረ ….ሰክሮ ደግሞ ወደመኪናው …..አእምሮየ ታዲያ ይችን ሰበብ ለቀም አደረገና ንትርኩን ቀጠለ ‹‹ አየሽ እንግዲህ ይሄ ባልሽ በዚች ምሽት ፍሬን የረገጠ መስሎት ነዳጅ መስጫውን ቢረግጥ ቀጥሎ ህይወታችሁ ምን ሊሆን ይችላል??›› እያለ …. ሁለታችንም ካለቅን ትርፉ ለሳጅን ማንትስ የጧት ዜና መሆን ነው …ችግር የለውም ….ወንዴ አንድ ነገር ቢሆንና እኔ ብተርፍስ ?….ለዜናም ለወሬም የማይመች ነገር ነው ….እንግዲህ ፈጣሪ ይጠብቀን ብየ ወደመኪናው ገባሁ …. ወንዴ እየነዳ ያወራኛል
‹‹የኔ ልእልት …ሬስቶራንቱ ውስጥ ያለው ወንድ ሁሉ እንደውሻ በውበትሽ ልጋጉ እተዝረበረበኮ ነው የሚያይሽ …..አንች ግን የኔ ሚስት ነሽ የሰማኒያ ሚስቴ …. እኔ እያለሁልሽ ስለኑሮ ጭንቀት አሰብሽ….?ወይኔ ወንዴ አንበሳው …. ብፈልግ የኮንዶሚኒየሙን ብሎክ ሙሉውን በስምሽ እገዛልሻለሁ …. ነዋሪውን ሁሉ እያስወጣሁ እያባረርኩ እቃቸውን ምን እቃ ነው ኮተታቸውን ….ቅራቅንቧቸውን ….ሙቀጫ ነሽ ብረት ምጣድ …ማቡኪያ ነሽ መክተፊ …..ቲቪ ነሽ ላፕቶብ ….አሽቀንጥሬ ሳበቃ የኔን ልእልት ድፍን ብሎኩ ላይ ማኖር እችላለሁ …..የአባቴ ንብረት ማለት የኔ የራሴ ነው …. በአንድ የስልክ ጥሪ እንደፈለኩ የማዝበት !
ልእልትየ የኔ ውብ ….ዶክተር መሆን አቅቶኝ ነው? እንኳን እኔ ያ ሃብታሙ ዶክተር ሁኗል (ሃብታሙ የአባቱ ተላላኪ የነበረ ልጅ ነበር ተምሮ ዶክተር የሆነ …ይቆጨዋል … ….ዶክተር የሆነው ስለተማረ ሳይሆን ለአባቱ ስለተላላከ ይመስለዋል መሰል …ምሳሌው ሁሌ እሱ ነው ) …….ኢንጅነር መሆንስ ያቅተኛል ? ልእልቴ የኔ የውበት ጥግ … አይደለም ልእልትየ …..ግን በቃ ምን አደከመኝ … ሁሉም ድካም ለብር ነው ብር ደግሞ አለ አለና…. ከመኪናው ኪስ ውስጥ አንድ እስር ብር አውጥቶ ታፋየ ላይ አስቀመጠው…. ወደመኪናው ኪስ መለስኩት ! ‹‹ ….ልእልትየ የኔ ውብ … ምንድነው የምትፈልጊው…. መኪና ….ቤት …ቤትኮ ….ቤት …ቆይ እንደውም አባባ ቤት ጀምሮልን አልነበር ምን ደረሰ ልደውልለት ቆይ …..› ብሎ ስልኩን ለማውጣት ይታገላል እየነዳኮ ነው
‹‹ወንዴ ስርዓት ….ከመሸ ደውለህ ልታስደነግጣቸው ነው …እኩለ ሌሊትኮ ነው ›› ብየ ስልኩን ከእጁ ላይ ቀማሁት …
‹‹ …ለካ እኩለ ለሊት ነው ….የኔ ፀሃይ አንችን የመሰልሽ የምታበሪ ልጅ ጎኔ ተቀምጠሸ ….እኩለ ቀን መሰለኝኮ ሃሃሃሃ …..ታበሪያለሽኮ የኔ ልእልት …አሁን እኔ የመኪናውን የፊት መብራት ባጠፋው….መብራት ሃይልም የመንገዱን መብራት ሁሉ ቢያጠፋፋው …. ከአንች አይኖች በሚወጣው ብርሃን ብቻ እስከሱዳን ድንበር መንዳት እችላለሁ …ይሄው ካላመንሽ …..› ብሎ መሃል መንገድ ላይ ያውም እንደዛ እየፈጠነ የመኪናውን የፊት መብራት ድርግም አደረገው ….እንኳን እስከሱዳን አምስት ሜትርም ከፊታችን ያለው መንገድ አይታይም ነበር የመንገድ ዳር መብራቱም ሲጀመር አልነበረም …. ጨለማ …ድቅድቅ ያለ ጨለማ …..አእምሮየ ታዲያ ይችን አጋጣሚ ተጠቅሞ …..‹‹አየሽ ነገሽ እንደዚህ ነው ….ጨለማ ምንም የማይታይበት ……ልክ እንደዚህ እንደመኪና ዝም ብለሽ ነው የምትጓዥው ….ትጋጫለሽ ….የመኪናው ቆርቆሮ እንደሚጨራመተው ይሄ ምቾት ያሳበደው ውበትና ኑሮሽ ይጨራመታል …እንደመኪናው መስተዋት ተስፋሽ ይንኮታኮታል ….አትጠገኝም !! ›› ይለኛል …..ማሰብ ጀምሪያለኋ….
‹‹ወንዴ መብራቱን አብራው ….ፕሊስ አብራው ›› እያልኩ ስጮህ
ፊት ለፊት አንድ ከባድ መኪና ጡሩንባውን እያንባረቀ…. አጭርና እረዥም መብራቱን እያበራብን ወደእኛ ሲምዘገዘግ ወንዴ ወደኔ ዙሮ አላየውም ….
‹‹ቁርጡ ቀን መጣልሽ ›› ብሎኝ አእምሮየ ትቶኝ ጠፋ ….መደንዘዝ በለው ……

በአልጋው ትክክል (ክፍል 11)

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...