Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 21 )

ወንዴ እቤት ሳይመጣ አስራ አምስት ቀን ….ሆነው …እጀ ላይ ያለው ብር እያለቀ ነው ….ፍሪጅ ውስጥ ምንም የለም ባዶ ሆኗል …ይሄም ሁሉ ብዙ አላስጨነቀኝም …አንድ ቀን በጧት በሬ ተንኳኳ …..ምን እንደሆንኩ እንጃ በድንጋጤ ራሴን ልስት ነበር …ወንዴ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ …ልቤ ተፈትልኮ የሚወጣ እስኪመስለኝ እየመታብኝ በሩን ከፈትኩ …. ፈፅሞ አይቸው የማላውቀው እድሜው አምሳ የሚሆን አንዳች ሚያክል ጥቁር ሰውየ ነው … ኮስተር ብሎ
‹‹ደህና አደርሽ ›› አለኝ ….በሩን ልክ እንደራሱ ቤት ገፋ አድርጎ ወደውስጥ ሲገባ ከመደንገጤ ብዛት አፍጥጨ ከማየት ውጭ ምንም ማለት አልቻልኩም ….
ሊፈራ መሰለህ ….እልፍ ብሎ ሶፋው ላይ ተቀመጠና ቀና ብሎ ተመለከተኝ …ሰውየው ፊቱ ላይ በግራ በኩል ከጆሮው ጀምሮ እስከአገጩ የተጋደመው ጠባሳ ይዘገንናል ….. ደግሞ የተቆጣ ይመስላል …..በክፉ አይኑ ነው የሚመለከተኝ ….በዚህ ድረሱልኝ ብየ እንኳን ብጩህ ‹‹ይበልሽ›› የሚሉ ጎረቤቶች ባሉበት ፎቅ ….ምን ጉድ መጣብኝ ብየ አፍጥጨ አየሁት ……እሱም ቀና ብሎ አፈጠጠብኝ …ጠባሳው ራሱ ሶስተኛ አይን ይመስላል

‹‹ምንድነው እንዲህ ያለ አጓጉል ነገር …እኔ ሰውላንተ እንደሆንኩ የሰው ብር የማልፈልግ የራሴንም ካለነገሩ የማልሰጥ ጨዋ ሰው ነኝ ›› ብሎ አንገቱ ላይ ያሰረውን ማተብ አሳየኝ …
‹‹ይቅርታ አላወኮዎትም ›› አልኩ እንደመንቀጥቀጥ እያልኩ …ግን ትንሽ ተረጋግቸ ነበር መቸም ቀድሞ ማተቡን እያሳየ የሚደፍር የሚገድል ሰው የለም ብየ …!
‹‹እሰይ እንዲህ አላውቅህም ብለሽ አሳርፊኝ ›› ብሎ የግርምት ሳቅ ሳቀ …ጥርሱ ስክክ ያለና ነጭ ነው …የሌላ የቆንጆ ሰው ጥርስ ተውሶ የመጣ ነው የሚመስለው ጥርሱን ሳይ ደግሞ ለምን እንደሆን እንጃ ደግ ሰው መሰለኝ …
‹‹ የምትኖሪበትን ቤት ባለቤት አታውቂም …ሆሆ …በይ አሁን ባለቤትሽ ካለበት ጥሪው ታልሆነም አንችው ኪራየን ስጭን …. ሳምንት ሙሉ እንዴት ኪራይ ዝም ይባላል … ስልክ ስደውል እንዴት ይዘጋብኛል ›› ብሎ አይኑን በቁጣ አጉረጠረጠ …..
‹‹ይቅርታ አባባ …ወንዴ ከባድ የቤተሰብ ጉዳይ ገጥሞት ሂዶ ነው ….እ…ነገ ይመለሳል …ስልኩም የተዘጋው ለዛ ነው…እኔም አሁን እጀ ላይ ብር ባጋጣሚ የለም እባክዎትን ይቅርታ ያድርጉልን…. ነገ እኔ ራሴ ያሉበት አመጣለሁ …እባክዎት ስልክዎትን ይስጡኝ ›› አልኩ እንደመጣልኝ !ሰውየው አንዴ ወደላይ አንዴ ወደምንጣፉ ተመለከቱና በረዥሙ ተንፍሰው የስልክ ቁጥራቸውን ነግረውኝ ደህና ዋይም ምንም ሳይሉኝ ተነስተው ወጡ ! ታምነኛለህ አብርሽ… ቤቱ የኪራይ መሆኑንም በየወሩ እንደሚከፈልም እረስቸዋለሁ …ሰዎች የቤት ኪራይ ተቸገርን ሲሉ የማውቀውም በፊልም ድራማ ምናምን ነበር …አሁን ህዝብ እየሆንኩ ነው !! ወንዴ ስለኪራይ አንድ ቀን አውርቶኝ አያውቅም …በውጭ ለሰውየው ይከፍላቸዋል መሰል እኔጃ !

…ሰውየው ከሄደ በኋላ … ግራ ገባኝ የቤት ኪራይ ነገ እከፍለዎታለሁ ያልኩት ከየት አባቴ አምጥቸ ልከፍል ነው ….ስልኬን አንስቸ ለወንዴ ደወልኩ ስልኩ ዝግ ነው !! ….ለአባቱ ደወልኩ ዘጉብኝ !! እንዴ ወንዴ ጋር ተፋታን ማለት ነው ?….መፋታት ከምር እንደዚህ ነው ? እንዲህ የምንሰፈሰፍለት …ነፍሴን ስጋየን ማንነቴን ሁሉ ነገሬን ሰጠሁት አብሮነት መንገድ ላይ ድንገት እንዳገኙት ሰው እንኳን ‹‹ቻው ›› ሳይባባሉ በመለያት ሊያከትም ማለት ነው ? አንዲህ ድግፍ ያሉት ሰው ባዶ ቤት በጀርባ አንጋሎ ትቶ መሄድ ነው መፋታት …? ለወንዴ አባት ደወልኩ ገና በአንድ ጥሪ ስልኩን ሲያነሱት ነፍሴ መለስ አለ
‹‹አባባ ›› አልኩ በስስት ልክ አባቴ ከሞት የተመለሰ ነው የመሰለኝ ….እያለቀስኩ ወንዴ ያደረገኝን ሁሉ ልዘረግፈው ከየት እንደምጀምረው ሳስብ አባቱ ቀድመው መናገር ጀመሩ ….

‹‹አንች ልጅ ምነው …ምነው ስርአት ቢኖርሽ …ለምን በህይዎት ተረፈ ነው ? … ለምን አንድ ልጅህ በብልግናየ ተበሳጭቶ ራሱን ካላጠፋ ነው ?…ተይ እንጅ የሴት ወጉ ይኑርሽ …ለሰሚውስ ምናይነት አይናውጣነት ነው ?….ቤቱን ትቶልሽ ወጣ አይደለም …በቃ ምን ትፈልጊያለሽ ?? ብትፈልጊ የምታግዣቸው ወንዶች ጋር እንዳሻሽ ማግጭበት ….ቢያሻሽ እቃውን ሻሽጠሸ ወደምትሄጅበት ሂጅ ሁለተኛ እንዳትደውይ ነግሪያለሁ ….ውርድ ከራሴ ልጀ አንድ ነገር ቢሆን ከነቤተሰብሽ አንላቀቅም ! ደም ነው የምንቃባው!! ›› ብለው ጆሮየ ላይ ስልኩን ጠረቀሙት !!
ልእልት በመሃል ወጓን አቋረጠችና ቀና ብላ እያየችኝ ‹‹ደም መቃባት ምንድነው አብርሽ›› አለችኝ ….አሳዘነችኝ …
‹‹ያው እገድልሻለሁ እንጋደላለን ምናምን ማለት መሰለኝ ›› አልኳት ! ልእልት ዝም ብላ ቆየችና …የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ሰው ብንን ብላ
‹‹ ወርቅ ጥሩ ነገር ነው ›› አለችኝ አወራሯ ልክ ህፃን መሰለኝ ! ወርቅ ጥሩ መሆኑ ማን ይጠፈዋል…‹‹ አየህ በሰላሙ ቀን ወንዴ ወርቅ ልግዛልሽ ሲለኝ ሳቄ ነበር የሚመጣው …በቃ ወርቅ የትልልቅ ሰዎች ነበር የሚመስለኝ ምኑም አያምረኝም … ይሄ ቀለበቴ እንኳን ቀለበትነቱ እንጅ ወርቅነቱ ትዝ ብሎኝ አያውቅም ….ወንዴ ያኔ ቆርቆሮም ጣቴ ላይ ቢያጠልቅልኝ ለውጥ አልነበረውም …ማንኛውንም ነገር ውድም ርካሽም የሚያደርገው ነገሩ የተገኘበት ቦታና ጊዜ ነው ! እንደው ግራ እንደገባኝ ቁጭ ብየ መሸ … ማታ ወደሁለት ሰዓት ቢጨንቀኝ ስልኬን አንስቸ ለእያሱ ደወልኩ…
አብርሽ ወንድ ልጅ ቢፈልግ ዱርየ ቢፈልግ ልክስክስ ወላ አስመሳይ ይሁን … ግን በማንኛውም ባህሪው ውስጥ በትክክል ያለህበትን ሁኔታ ከተረዳ ያ ሱርየ ያ ልክስክስ ያ አስመሳይ …..ሰው ይሆነልሃል!! ምንድነው ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋለት እንደሚባለው …
ኢያሱ ስልኬን አንስቶ ‹‹ወይየ ልእልት …መቸም አታናግሪኝም ችግር ላይ ጥየሽ ጠፋሁ›› ሲለኝ ኢያሱን በዚች ቃሉ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ በላይ ወደድኩት ! ተወው ባህሪውን ወደድኩት በዛች ቅፅበት ኢያሱ አጠገቤ ቢሆን ብየ ተመኘሁ …ዝም ብየ ሰማሁት ንግግሩን ባያቋርጥ ደስታየ ….‹‹ልእልት አለሽ›› አለኝ ….
ዘለቀስኩ …በቃ አለቀስኩ ….ስቅስቅ ብየ ስልኩን ሳልዘጋው አለቀስኩ … ኢያሱ በቃ ተጨናነቀ ‹‹ምን ሁነሽ ነው …ልእልት እባክሽ ስሚኝ …ይለኛል ስልኩን ዘግቸው …በቃ ስቅስቅ ብየ አለቀስኩ …ፀጉሬን ብነጭ ደስታየ ፊቴን ብተለትለው ደስታየ ብነግርህ የማይገባህ ብስጭት …ደግሞ እዚህ ላይ (ከጡቷ ዝቅ ብሎ ያለውን ሰውነቷን ክፍል በመዳፏ ይዛ እያሳየችኝ) ሃይለኛ ህመም ለሁለት እጥፍ የሚያደርግ የሚያቃጥል ነገር …አመመኝ …በቃ ሞቴን ተመኘሁ …
ለኢያሱ ደወልኩት ‹‹ለልመና›› ነው …በቃ የቤት ኪራ ገንዘብ እንዲመፀውተኝ ነው ….ትላንት ኢያሱ እግሬ ስር ወርቅ ቢያነጥፍ ዞሬ የማላው ልጅ ነበር …አየህ የምትወደው ሰው ሲገፋህ ነው ትም ማንም እግር ስር በግንባርህ የምትደፋው … ለምን እገፋለሁ ….ለምን ለማኝ እሆናለሁ ባፈቀርኩ … እንደሰው አላማ ይኑረን እንደሰው ከጥገኝነት እንላቀቅ ባልኩ ….ለምን አብርሽ ….››
እንባዋን ጠረገች …ልእልት ከማልቀሷ ብዛት የምትሟሟ እስኪመስለኝ ….እዚች አገር ላይ በወንዶች ክህደትም ሆነ በየቤቱ በሚፈጠር ቁርሾ የሚፈሰው የሴቶች እንባ ቢጠራቀም ሌላ አባይ ሳይፈጠር አይቀርም …እስቲ የቤቷን የጓዳዋን የአመታት እንባ ትተነው … እኔ ጋር ከተዋወቅን እንኳ ልእልት ያለቀሰችባቸውን ጊዚያት ብንደማምራቸው …..

አየህ ስልኩን ከዘጋሁት በኋላ አንድ ሰአት እንኳን ቆየሁ አይመስለኝም በሬ ተንኳኳ …ቀጥ ብየ ሂጀ ከፈትኩት … አየህ ብዙ ሰዎች የተገፋች ሴት ጨካኝ ናት ደፋር ናት ይላሉ …አይደለችም የሴት ልጅ ህይዎት ውስጥ ፍርሃት ውበቷ አንድ አካል ነው … አንዲት ሴት ፍርሃት የሚባል ነገሯን ሁሉ ጣጥላ ላንኳኳ ሁሉ በሯን ያውም በጨለማ ከከፈተች …የሚመጣው ሞት ቀድሞ ውስጧ ከተቀመተው ተስፋ መቁረጥ በታች ሁኗል ማለት ነው ! ከፈትኩት በሩን ….ኢያሱ ነው …. ምን ኢያሱ ነው ይሄ መለአክ ነው እንጅ ….

እንባየ አስጨንቆት ሲከንፍ የሚደርስ ሰው ….ምኑ ላይ ነው አስመሳይነቱ …ለምኑ ነው ስፈራ የኖርኩት ለሴትነቴ ?….ምንድነው ሴትነት …የማንም ደደብ እንጀራና ጫት ደመዎዝ እየከፈለ እንደከፈን ድሪቶ እያለበሰ እንዳሻው ሲያደርገው የኖረ ሴትነት ምኑ ብርቅ ሁኖ ነው ይሄን ያህል ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ?… አንዱ ተንሰፍስፎ ያገኘው እስኪሰለቸው የተጫወተበት ስጋየ …ሲሰለቸው ባዶ ቤት እንደተቀደደ ምንጣፍ ረግጦ ትቶት የወጣው ስጋ …. ….ሌላ ምን አለኝ ?…እንኳን ስጋየ ነፍሴም እግዚአብሔር ወሰዳት ሰይጣን ዋጋ ምታወጣ አልነበረችም ለኔ …ማንም ሰው የሆነ ቀን ቁሞ የሚሄድ ምንም የሚሆንበት ጊዜ አለ …. በዛች ቅፅበት ኢያሱ በቆምኩበት ፒጃማየን ቢያወልቀው ተው አልለውም ነበር … ብዙ የዋህ ወንዶች አንዲትን ቆንጆ ሴት በዚህ ሰዓት ሲያገኟት ለእነሱ ትልቅ እድል …ትልቅ የማሳመን ችሎታ …ትልቅ አማላይነት ተፈላጊነት ምናምን ይመስላቸዋል …ግን ሁሉም አይደለም …ማንኛዋም ሴት የሆነ ጊዜ በሆነ ምክንያት ከፊቷ የቆመው ሰው ይሁን ግድ ግድ የማይሰጥባት ጊዜ አለ !! ልክ አጋጣሚ የገደላትን ሴት ሬሳ እንደመጎተት በለው !
ዝም ብየ አየሁት ኢያሱን …. በር ላይ ፊት ለፊት ስገተርበት ግራ ገብቶት ነው መሰል አንገቱን አስግጎ ወደውስጥ ተመለከተ ….ሰው አለ እንዴ ብሎ …. በሩ እንደተከፈተ ትቸው ወደቤት ገባሁና በቁሜ ሶፋው ላይ ተወዘፍኩበት ….ኢያሱ ቀስ እያለ ተከትሎኝ …ገብቶ በእጅና እጁ ትከሻየን ይዞ በጭንቀት አየኝ …. አብርሽ ኢያሱን የዛን ቀን ብታው እንዴት እንደሚያሳዝንህ ያ ረዥም ቁመቱ እጥፍጥፍ ብሎ ምንጣፍ ላይ ከፊቴ ተንበርክኮ ሲያባብለኝ … ኢያሱ ድሮ ማን እንደነበር ለምን እንደጠላሁት ሁሉ ጠፋኝ …ራስህን ከጠላህ የጠላሃቸውን ሁሉ ትረሳቸዋለህ … !!
‹‹ ወንዴ ትቶኝ ሄደ ምንም አላደረኩትም …ወንዴን እወደዋለሁ ….አባቱ ሰደቡኝ ›› አልኩት ….
‹‹ተያቸው እነሱን ልእልት አሁን አንች ተረጋጊ …›› አለኝ …ድምፁ ውስጥ እንዴት ደስ የሚል ወንድነት አለ … የሆነ ማንም ቢሄድ ቢመጣም እኔ አለሁልሽ የሚል ድምፅ ! ቀጥ ብየ አየሁት ኢያሱ አዲስ ሰው ሆነብኝ …ታምነኛለህ አብርሽ አይኖቹ እንባ ኳትረው ነበር !!
‹‹ማን ኢያሱ ?›› አልኳት ተገርሜ
‹‹ገረመህ አይደለ ….እኔም ልክ እንዳሁኑ እንዳንተ ነው የገረመኝ ….›› አለችና …ፈገግ እንደማለት ብላ …‹‹ግን ከምር ኢያሱ ሊያለቅስ ምንም አልቀረውም …. የሆነውን ሁሉ ነገርኩት ቤት አከራዩ ሰውየ መምጣቱንም ነገርኩት ››
‹‹ በቃ አታልቅሽ … እኔ በጧት እመጣና አብረን ሰውየው ቤት እንሄዳለን …ከዚህ በኋላ አትጨናነቂም …የስድስት ወር ኪራዩን ወርውረንለት እንመጣለን …እሽ ልእልትየ ›› ይሄን ሁሉ ሲለኝ ፊቴ ተንበርክኮ አይን አይኔን እየኝ ነው …
‹‹ አሁን ተነሽና ወተት ጠጭ …በቃ ነቃ ብለሽ አሪፍ እንቅልፍ …›› ብሎኝ ተነስቶ ወደፍሪጁ ሂዶ ከፈተው …ወተት እንደምወድ ያውቃል … ፍሪጁ ባዶ ነው ….ኢያሱ ደነገጠ የፍሪጁን በር እንደያዘ በግርምት ወደኔ ዙሮ … ተመለከተኝ ›› ምንም ሳይናገር ፈሪጁን ዘግቶ ወጥቶ ሄደ ….ፊቱ ላይ የነበረውን ሃዘን ብታይ አብርሽ ኢያሱ አይመስልህም …. ቆይቶ ሲመለስ ፌስታል ሙሉ የታሸገ ወተት ዳቦ ….‹‹ቴክ አዌ›› ፒዛ ›› ተሸክሞ መጣ … ዝም ብየ አየዋለሁ … ኪችን ገብቶ ብርጭቆ አወጣ ወተት ቀዳ …ፒዛውን የሆነ ሰሃን ላይ አወጣና ፊቴ መጥቶ ተቀመጠ …ብርጭቆውን አቀበለኝ …ወተቱን እና ፒዛውን ሳይ ርሃቤ ክፉኛ ተቀሰቀሰ …ሙሉ ቀን ምንም እንዳልቀመስኩ ትዝ አለኝ !ዝም ብየ መብላት ጀመርኩ ….ኢያሱ አምሽቶ ሌላ ሌላ ወሬ አውርቶኝ …እንደውም ያኔ ምን እንዳለኝ እንጃ እንጅ አስቆኛል ሁሉ ! ሊሄድ ሲል ስንት እንደሆነ ያላወኩት የተጠቀለለ ብር ‹‹ለማንኛውም›› ብሎ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦልኝ ወጣ !!ሲሄድ አልሳመኝም …ለምን እንደሆነ እንጃ ቶሎ መውጣት ፈልጎ ነበር አሳዝነው ይሆናል እኔጃ !!
ኢያሱ በቀጣዩ ቀን መጣና ….ማታ እንዳለው ሰውየው ጋር ደውለን ሰፈራቸው ሄድን …የስድስት ወር ኪራይ ስንሰጣቸው ማመን አልቻሉም ያ ማታ ያስፈሩኝ ሰውየ ከነዘር ማንዘሬ መርቀው ሸኙን ….!! ስንመለስ ምሳ ሰአት እስከሚደርስ ኢያሱ እንዲሁ ሲያዞረኝ ዋለ …ደስ አለኝ ከተማው አዲስ እስኪሆንብኝ ….ምሳ ሰአት ሲደርስ የሆነ አይቸው የማላውቀው ቤት ወስዶ ምሳ ጋበዘኝ …ታምነኛለህ አብርሽ ሃዘኔን ሁሉ ረሳሁት ! ምሳ በልተን እንደወጣን ኢያሱ ዝም ብሎ ወደሆነ ሰፈር የዞኝ ሄደ የት ነው የለ ምን የለ ዝም ብየ የሚወስድብኝን ማየት ብቻ … አንድ ትልቅ ግቢ ያለው ቤት ስንደርስ …ገባንና …የሚገርም ቪላ ውስጥ እየመራ አስገባኝ … ሰራተኛ ብቻ ነች ያለችው … አስተዋወቀን
‹‹ወ/ሮ ልእልት ትባላለች ጓደኛየ ባለቤት ነች ….ቡናሽ አሪፍ እንደሆነ ሰምታ ነው የመጣቸው›› አላት … አነጋገሩ ሁኔታው የሆነ ዝም ብሎ ቤተሰብ የሚያደርግህ አይነት ነው …ልጅቱ መምጣቴ ደስ ብሏታል ከምኔው እንዳቀራረበችው እንጃ ቤቱን በእጣን ጭስ ሞላችው …. ቡናው ፈላ …
‹‹ይሄን ይመስላል ቤታችን ልእልት›› አለኝ እያሱ ፊት ለፊቴ ተቀምጦ የሶፋውን ትራስ እንደአሻንጉሊት አቅፎ እያየኝ …
‹‹ያምራል ›› አልኩት ከልቤ ነበር …..

‹‹ አባትና እናቴ ተያይዘው ኤሮፕ ሂደዋል… ታላቅ እህታችን ወልዳ ምንድን ነው የሚባለውን… ሊያደርጉ›› አለ …ሰራተኛዋ ፈጠን ብለው ‹‹ሊያርሱ›› አለች …ተሳሳቅን ! ኢያሱ ረጋ ያለ ልጅ ሆነብኝ ….ያ የማውቀው ኢያሱ የት ሄደ እስከምል ….
በዚች ቅፅበት ስልኬ ጮኸ …ከቦርሳየ አውጥቸ ሳየው ማመን አልቻልኩም ….ማ መ ን .አልቻልኩም አብርሽ ….. ማን ቢሆን ጥሩ ነው ….ወንዴ!!

በአልጋው ትክክል (ክፍል 22 )

2 Comments

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...