Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 18)

ቁጣ ነው !
ከዚህ በኋላ ያለው የልእልት ታሪክ ቁጣ ነው !!
ውብና ገራገር ፊቷ ….እንኳን ለራሷ አብሯት ለተቀመጠው ሰው ሁሉ ሰላም የሚሰጥ ልእልት … ኢያሱን ከቤቷ አባራ ለብቻዋ ከተቀመጠች በኋላ ያለው ታሪኳ በሙሉ ቁጣ ነው … ግፏን አፍኖ የኖረው የውበቷ ቀላይ ተከፍቶ ያመፀባት ፍቅር ላይ ክፉ የሚስብ የአርባ ቀን እጣ ፋንታዋ ላይ የቁጣ ዲኑን አወረደው … እርህራሄ ፣ ፍቅር ፣ ትህትና፣ ፈገግታ ፣ የዋህነት … እንደደረቀ ሳር በምድር ላይ እንደበቀለ አራሙቻ በቁጣዋ ሰደድ ተበሉ … ቁንጅናዋ ከደምና ስጋ ሳይሆን ከአስፈሪ የብረት ቅርፅ የተሰራ ያህል ድርቅ ያለና የማይናወጥ ሁኖ በፊቴ ቆመ …ታሪኩንም ዝንፍ በማይሉና እንደብረት ኳስ በጠጠሩ ቃላት እንደብረት ዘንግም ቀጥ ባለና በጠጠረ ድምፅ ያፈሰው ጀመር … ብረት የመሸከም ያህል ልቤን እየከበደው ሰማሁ ….
‹‹ኢያሱን ያባረርኩበት ቀን ማታ …ወንዴ ካለወትሮው አመሸ … አምሽቶ የማያውቀው ልጅ አመሸ …. እስከምሽቱ ሁለት ሰአት አልመጣም…ሶስት ሰዓት ሆነ አልመጣም ….. ስልኩ ላይ ሞከርኩ ተዘግቷል …. ጭንቀት ለቀቀብኝ …….እወጣለሁ እገባለሁ … ስልኩን እሞክራለሁ አራት ሰዓት ሆነ ….የመኪና ድምፅ በሰማሁ ቁጥር እወጣለሁ ….ወንዴ የለም… አምስት ሰዓት ሆነ ከምሽቱ!! ከተጋባን ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንግዲህ …. ተጨነኩ …በቃ የማደርገው ነገር ግራ ገባኝ … አንድ ነገር ሁኖ ቢሆንስ … ኢያሱ ጋር ተጋጭተው ቢሆንስ ..የማላስበው ነገር የለም … ድሮ በልጅነቴ አባባ ድንገት ሲያመሽ እናቴ በጭንቀት እየተንቆራጠጠች የምትጠብቀው ነገር ይሄው ስንት አመታት ተሻግሮ ትውልድንም ተራምዶ ዘመናዊ ነን የምንል እኛም ላይ ሴት ጠባቂ ወንድ ተጠባቂ ሁኖ ዳግም ነፍስ ዘርቶ አንሰራራ !! (ወልደሽ ቅመሽው ይሉት እርግማን ውስጥ አግበተሸ ቅመሽው የሚል ምርቃት መርገምት ሳይኖር አይቀርም)

የወደዱትን ሲያጡ ያጡትን ይቀላውጡ እንደሚሉት …ኢያሱ ጋር ደወልኩ እና ‹‹ወንዴ አመሸብኝ …ምናልባት አይተኸው ይሆን ከመሸ ›› አልኩት …አላየውም …. ሁሉም ጓደኞቹ ጋር እየደወለ እንዲጠይቅልኝ ለመንኩት ‹‹ችግር የለውም ልእልትየ አንች አትጨነቂ መልሸ እደውላለሁ ….›› አለኝ ….አየህ የኢያሱ ክፋት መገለጫው በምንም ነገር የማይናወጥ ደግነት ነው…ቀን እንደውሻ አከላፍቸ አባርሬው ምንም እንዳልተፈጠረ አብሮኝ መጨነቁን እየነገረ ያፅናናኛል ……እንዲህ አይነት ሰዎች አሉ በቃ … ደግነት የክፋታቸው አንድ አካል የሆነ … እንዲቹ እየተጨነኩ …ጠበኩ ኢያሱ አንድ ሰላሳ ደይቃ ቆይቶ ደወለና ማንኛቸውም ወንዴን ከመሸ እንዳላዩት ነገረኝ …
እሽ የት ሄደ ይባላል ?…..በመጨረሻ የማደርገው ቢቸግረኝ ለወንዴ አባት ደወልኩ ‹‹ልእልት ሰላም አመሸሽ ምነው ወንዴ ሰላም አይደለም እንዴ? ›› አሉ ድምፃቸው በድንጋጤ ይንቀጠቀጣል …..
‹‹አይ ሰላም ነን አባባ …ወንዴ እስካሁን እቤት አልመጣም ምናልባት እርስዎ ጋር መጥቶ ከሆነ ብየ ነው…. ››
‹‹ስልኩ ላይ ደወልሽ ….ጓደኞቹ ጋርስ አልደወልሽም …›› አባቱ እንስፍስፍ አሉ (መቸም የሱ ነገር አይሆንላቸውም )
‹‹ ስልኩ ዝግ ነው …አባባ ››
‹‹ልጀን ምናገኘብኝ ….የት ገባብኝ ….›› እያሉ ስልኩን ሳይዘጉት ሲያወሩ ይሰማኛል …ቻው እንኳን አላሉኝም …›› ወዲያው ኢያሱ ደወለ
‹‹ሄሎ ኢያሱ ››
‹‹ልእልትየ …ምን አዲስ ነገር አለ …?››
‹‹ምንም የለም ጨንቆኛል እባክህ !›› አልኩ ተጨንቄ ….
‹‹ልእልት መጣሁ በቃ …ወጣ ብለን እንፈልገዋለን ….አትጨናነቂ አለኝ ›› ይሻለኛል ! እቤት እየተጨነኩ ከመጎለት ቢያንስ ወንዴ ሊሄድ የሚችልባቸውን ቦታዎች ሂጀ ብፈልገው ይሻለኛል …ሰዓቱ እኩለ ሌሊት ሁኗል …የወንዴ አባት ደወሉ ….
‹‹እኔ የምልሽ ልእልት …ቀን ተጋጭታችሁ ነበር እንዴ …..››
‹‹አ….ይ …ዝም ብሎ ተራ …..ትንሽ የሆነ አለመስማማት ነበር እንጅ ይሄን ያህል እንኳን …››
‹‹ ምነው ልእልት ….ምነው ….ያለእናት ያሳደኩት አንድ ልጀ … አንችን እንደእህትም እንደእናትም አምኘ አደራ ብየ ብሰጥሽ ምነው …..›› ብለው እንባ ቀረሽ የሆነ ብሶታቸውን ወቀሳቸውን አዘነቡብኝ ! (ልቤ እየተፈረፈረ የወደቀ እስኪመስለኝ) ምናባቴ ልበል …. ስልኩን ጆሮየ ላይ ዘጉብኝ ….
ኢያሱ አፍታ ሳይቆይ ደረሰ ….ከላይ ሹራብ ደርቤ ፀጉሬን ባገኘሁት ሻሽ አሰርኩና ወጣን … አየህ አብርሽ ….አሁን ላይ ነው የገባኝ ….ኢያሱ ወንዴ ይኖርበታል ብሎ የወሰደብኝ ቦታዎች በሙሉ እንዴት ያሰቅቃሉ መሰለህ …በህይዎቴ እንዲህ አይን ቦታዎች ይኖራሉ ብየ አስቤ አላውቅም …ብዙ ጊዜ ወንዴ ጋር ተያይዘን ክለብ ወጥተናል … ተዝናንተናል …..ግን እንዲህ የሴተኛ አዳሪ እና የሰካራም መዓት የበዛባቸው ….ሽታቸው ብቻ ከበር የሚገፈትር ሲኦል የሆኑ ቦታዎች አጋጥመውኝ አያውቁም …. ኢትዮጲያ ውስጥ አልመስልሽ አለኝ
‹‹ ወንዴ እዚህ ይመጣ ነበር ?›› ከአንዱ ቤት በወጣን ቁጥር እለዋለሁ በግርምት ኢያሱን ….
‹‹አዎ ልእልትየ ! እና የሁልጊዜ ንትርካችን ምን ሆነና …ተው ስርዓት ያለው ቦታ ዋል ….አንተ ባለትዳር ነህ …. አንተስ የራስህ ጉዳይ ልጅቱ ላይ የማይሆን እዳ እንዳታመጣባት ስለው በቃ እኔን እንደጥላት ሆነ የሚያየኝ ›› እያለ ከመጀመሪያው የባሰ ቦታ ይወስደኛል … (በኋላ ቆይቶ ሲገባኝ ግን ኢያሱ ያንን ያደረገው ሆነ ብሎ ለወንዴ ያለኝ አመለካከት ዝቅ እንዲል ለማድረግ ነው …..ደግሞም በሰዓቱ ብቸኛ ሃሳቤ ወንዴን ማግኘት ይሁን እንጅ ….የእውነትም ወንዴ ይሄድባቸዋል የተባለባቸውን ቦታዎች ካየሁ በኋላ …ውስጤ የሆነ ነገር ደፍርሶ ነበር ››
እንዲቹ ጉራንጉር ለጉራንጉር ኢያሱ ጋር ስዞር አምሽቸ …. ድንገት ስልኬ ጠራ ….ወንዴ ነው …ማመን አልቻልኩም ….
‹‹ወንዴ….የት ነህ ምን አድርጌህ ነው ወንዴ …››
‹‹የት ነህ …? የ….ት ነህ …..?ሃሃሃሃ አንች ራስሽ ቤቱን ቆልፈሽው የት ነሽ? ….የቀኑ አልበቃ ብሎሽ ተከትለሽው ሄድሽ …?? ››
አየህ አብርሽ ከተናገረው ነገር ይልቅ ያስደነገጠኝ ይሆናል ብየ በውኔም በህልሜም አስቤው የማላውቀው ነገር ወንዴ ስክር ብሎ … እግዚአቤርየ ! ድራማ ላይ ፊክሽን ላይ እንደሚታየው… ፊልም ላይ እንደምናየው … ምናምን ….ወንዴ በእኔ ተናዶ ሰክሮ !! ውይ ጉዴ ! ….ለካስ ነጋችንን ነው ፊልም እያልን ስናይ የኖርነው ….ኢያሱን ኩንትራት ታክሲ አስይዞ እንዲልከኝ ነገርኩት …..ደግሞ ወንዴ እሱ ጋር አይቶኝ ልብሱን እንዳይጥል ብየ …

‹‹ኖኖ ቆይ …ጓደኛየ አለ ያደርስሻል ›› ብሎ የሆነ ልጅ ጋር ደወለ ….ልጁ ያለበት ወስዶኝ በዛንኛው መኪና … ወደቤት ሄድኩኝ ….ልክ ከመኪና ስወርድ እና ወደላይ ስመለከት በራችን ላይ …. ሰው ተሰብስቧል …..በዚህ በሌሊት ነጫጭ ጋቢያቸውን ለብሰው ሃዘን ቤት ነው ያስመሰሉት …አብርሽ ራሴን እንዳልስት እየፀለየኩ ያንን ደረጃ በምን ፍጥነት እንደወጣሁት …አላውቅም … ወንዴ ደረጃው ላይ ተቀምጦ አፉ ሁሉ እየተያያዘ ይለፈልፋል … አባቱ በሩ እጎኑ ተቀምጠው እንደታመመ ሰው አቅፈው ያባብሉታል ….እማማ ቁንጥሬ ….ምን የቀረ ጎረቤት አለ ….ደረጃውን ወሮ ቁሟል ….‹‹ ወንዴ ›› አልኩ ….የከበቡትን ሰዎች አልፌ ፊቱ ቁጢጥ እያልኩ ….አብርሽ መዳፉን ፊቴ ላይ እንደዚህ አሳርፎ ወደኋላየ ቢገፋኝ ከዛ ከፎቅ ልምዘገዘግ እግዚአብሄር ነው ያወጣኝ … ከኋላየ ማን እንደሆነ እንጃ ደግፎ አዳነኝ …..
‹‹ የሴት ልጅ ሴት ያሳደገሽ …. ›› አለኝ ወንዴ ….በቁሜ በረዶ ነው የሆንኩት ….. ጎረቤቱ የወንዴን ፀያፍ ስድብ እየሰማ ተው ሊለው መሰለህ … ‹‹በቃ አይዞህ አሁን ግባ ›› እያሉ ያባብሉታል …አባትየው ዞረው እንኳን አላዩኝም …. በሌሊት ልብስ ላይ ካፖርት ደርበው ነው የመጡት …እንግዲህ ወንዴ ሲመጣ ያግኙት ወይ ከሆነ ቦታ ያግኙት እግዜር ይወቅ ….
‹‹ሃሃ አያችኋት አይደል …ቀን ሌላ ወንድ ጋር …አሁን ደግሞ ሌላ ወንድ ›› አለ ያመጣኝ መኪና ቁሞ ወደነበረበት እያሳያቸው …..‹‹ጧት አንድ ማታ አንድ አለ ሃኪም ….ሃሃሃሃሃ ›› ብሎ ሳቀ ወንዴ ጥንብዝ ብሎ ሰክሯል …እንዳለ አካባቢው መተጥ መጠጥ (ምኑን ቢተጣው ነው በእግዚአብሔር) በተቀመጠበት እየተወዛወዘ እና መዳፉን ጨብጦ ልቡን እንደከበሮ እየደቃ ….
‹‹ አንች ….እኔን …እኔን ወንዴን ንቀሽ ሌላ ወንድ ጋር …ያውም በራሴ ቤት … አባቴ የኔ አባት (አባቱን በሁለት እጆቾ ራሳቸውን ይዞ ወደራሱ ሳበና ግንባራቸውን ሳማቸው) …አባቴ አንደላቆ ባኖረሽ … የራሴ ጓደኛ ጋር …ድሮም መንገድ ላይ የተገኘች ሴት ….መንገደኛ ናት ….እናትሽ ….ትበ.. የአባት ክብር የት ይገባሻል …
‹‹ወንዴዋ ተው የኔ ጌታ ….ግባና አረፍ በል ….እዚህ በብስጭት ልብህ ጦሽ ቢል ሁሉም ደስታው ነው የናቴ ልጅ ተኳኩሎ አዳሜ እግሩን እያነሳ ነው የሚሄደው …አባትህ ናቸው በሃዘን የሚሞቱብህ ››እያሉ ያባብሉታል …ይች ሴት እንዴት እንዳስጠሉኝ እንዴት እንደቀፈፉኝ !
‹‹ትክክል!! ትክክል ነዎት እማማ …..(አገሳው ) ቁንጥርየ ልክ ነዎት !! …. ምድረ ሸርሙ. የሸርሙ. ልጅ … እኔ ድፍት ብል ደስተዋ ነው … እኔ ምን አሳጣኋት …..እማማ ቁንጥሬ እርሰዎ ጥሩ ሴትዮ ነዎት … እናቴ ነዎት ….መካሪየ ነዎት ….ሁሉንም ያውቃሉ ….እኔ ለዚች ውሻ (ተነስቶ ወደኔ ሊመጣ ሲል ከግራ ከቀኝ ያዙት) አይታ የማታውቀውን ልብስ አላለበስኳትም እንዴ ? …….አላለበስኳትም ወይ … እዚህ ቤት ስትመጣ …አያውቋትም ርስዎ … እማማ ቁንጥሬ …. ?››
‹‹ወንዴዋ ሁሉንም እናውቃለን ….ግባና አረፍ በል አባትህንኮ ብርድ ላይ አስቀምጠህ አሰቃየሃቸው …›› ያባብሉታል አባትየው እንገቱን አቅፈው ዝም ብለው ተክዘዋል ….ልክ ልጃቸው ተሰምቶ የማያውቅ በደል የተበደለ ዓይነት ፊታቸው ላይ የነበረው ሃዘንና ቁጣ ብታየው አብርሽ ያሳቅቃል !

‹‹እ…ኮ …እዚህ ሰፈር ….እዚህ…እዚህ ፎቅ …. እዚህ ቤት ስትመጣ ይች ውሻ …(በእጁ ወደእኔ እየጠቆመ) ያንን እንደደረቀ ቅጠል የሚንኮሻኮሽ የትምርት ቤት ካሽ መሪ ዩኒፎርም ለብሳ ስትመጣ … በተራመደች ቁጥር ሲንኮሻኮሽ እ…..ዛ ብሎክ አስር ድረስ እየተሰማ ….ስትመጣ ….እማማ ቁንጥሬ አይተዋት የለ? ….ዘበኞቹ አይተዋት የለ ?…..እኮ እኔ አባቴ ላቡን ጠብ አድር…..ጎ ስሚንቶ አቡንኖ ጣውላ ሽጦ አባቴ …..(ድንገት እየተንገዳገደ ተነስቶ አባቱ እግር ላይ ተደፋና እግራቸውን ሊስም ሲል ጎትተው አነስተው አስቀመጡት )
‹‹ይቅር በለኝ አባቴ … ሰው ይሆናል ብለህ ለእኔ ስትደክም ….እኔ .ብርህን ለአንዲት ሸርሙ. በተንኩት ….ይሄው … የእኔ አባት ሲሚንቶ ሻጭ ስለሆነ ጣውላ ሻጭ ስለሆነ …ሚስማር ሻጭ ስለሆነ …ስድስት ቁጥር ሚስማር ሽጦ ሰባት ቁጥር ቢስማር ሽጦ …አስር ቁጥር ቢስማር ሽጦ ….ኩርንችት ሚስባር ሽጦ …ሰው ስላደረጋት እኔን ልጁን ንቃ ….ኢያሱ ጋር …የሪል ስቴት ባለቤት ልጅ ጋር …..ወይኔ ወንዴ አንበሳው (ግንባሩን በመዳፉ ገቸው) ….. የኢያሱ አባትኮ ሌባ ነው … እንደኔ አባት ሰርቶ ላቡን ጠብ አድርጎ አይደለም ሃብቱን ያገኘው … እኔን በሌባ ልጅ ቀየረችኝ ….. !! እማማ ቁንጥሬ ….የሌባ ልጅ ሰው ሁኖ ትዳር ተትቶ ይኬድለታል ….? ራሴ ቤት እራሴ ፍራሽ ላይ ተቃቅፈው …
‹‹ኧረ ወንዴ በእግዚአብሔር ›› አልኩ መለፋደዱን መቋቋም ቢያቅተኝ …
‹‹አንች ውሻ ልጅ ….ዝም በይ ….›› ብሎ ያንን አንዳች የሚያክል ውድ ስልኩን ወርውሮ ታፋየ ላይ መታኝ ….ስልኩ እኔ ላይ አርፎ ደረጃው ላይ ወደቀና ብትንትኑ ወጣ …ግማሹ ከፎቁ ላይ ወደታች ወደቀ …..
‹‹ምነካሽ አንች ዝም በይ እንጅ ደግሞ አማረብኝ ብለሽ ትናገሪያለሽ … ›› ብለውኝ እርፍ አባትየው …
‹‹ በግዚአቤር …..በግዚአቤር ….ሃሃሃሃሃሃሃሃ ባይኔ በብረቱ በዚህ (ሁለት አይኑን በእጆቹ በልጥጦ ለጎረቤቶቹ እያሳየ ) በዚህ ነው ያየኋት …. አንችንንም እሱንም ልክ ማስገባት አቅቶኝ ነው ? አይደለም !! …ጨዋ አባት ስላሳደገኝ (አሁንም የአባቱን ግንባር እንደህፃን ልጅ ጎትቶ ሳመና) ጨዋ አባት ስላሳደገኝ ……ትቻችሁ ወጣሁ ….ለምን …ሴት ሞልቷላ …እንኳን እንዳንች አይነት ችጋራም መሃይም የሴት ልጅ …ቀርቶ ከተማውን የተማሩ ቆንጆ የሃብታም ልጆች ፈሰውበታል ሴት ሞልቷል …..አይደል እንዴ እማማ ቁንጥርየ ….?
‹‹ሞልቷል የኔ ጌታ ኧረ ሞልቷል ሴት እንጅ ከተማውን ያስለቀቀ አሁን ተነስና ግባ …››አሉት ያች ነገረኛ ባልቴት ….
‹‹እኮ ….በቃ አሁን ወደቤት !!… ነገ እንደሰራተኛ …ልብስሽን በፌስታል ይዘሽ ከዚህ ቤት ውልቅ …እዛ ሂደሽ ብትፈልጊ ለዛ ሪል ስቴታም ሌባ የሌባ ልጅ… በባሬላ አሸዋና ስሚንቶ አግዥ …. ›› እየተንገዳገደ ተነስቶ ቆመና እጁን በዛቻ ለረዝም ደይቃ አወዛወዘብኝ …. ‹‹ውሻ›› ብሎ መረቀበት ! አባትየው በቁጣና በንቄት አስተያየት ገልመጥ አድርገውኝ …
‹‹በሩን ክፈችው እንጅ ምን ቁመሽ ታይኛለሽ ›› አሉኝ …. በወንዴ አጠገብ ወደበሩ ሳልፍ ስካር ባዝለፈለፈው እጁ በቃሪያ ጥፊ ሰንዝሮ ፀጉሬ ላይ ያሰርኩትን ሻሽ በተነው …. (መናቅ ፅዋዋ ሞላ ) … በሩን ከፍቸ ልክ እንደዘበኛ እነወንዴ እንዲገቡ ጥጌን ይዠ ቆምኩ
….
‹‹አልገባም ….አባባ አንተ ጋር ነው የማድረው …. አባቴ ናፍቀኸኛል ….አንተ ጋር እያወራሁ ማደር ነው የምፈልገው …ጋብቻ አልጋው ንፁህ ነው ይላል ቃሉ ….የኔ አልጋ ቆሸሸ ውሾች አቆሸሹት ……አባቴ ጋር ነው የማድረው ….›› አለ ወንዴ

አባባ እሽ ብለው ደግፈውት ደረጃውን መውረድ ጀመሩ….. ጎረቤቱ አስከሬን እንደሚሸኝ ሰው ከኋላ እየተንኳተተ ተከተለ … ወንዴ ቆም ብሎ በዛቻ እጁን ነቀነቀብኝና ‹‹ ደውይና ያንን የሌባ ልጅ ጥሪው …ድግሪውን ደሞ …የሰርጉን ፎቶ አውጥተሸ ጣይና ፍሬሙ ውስጥ ስቀይለት ….ለመሃይም ድግሪ ተአምር ነው …..ውሻ›› ብሎኝ እየተወላገደ የአባቱን ትከሻ አቅፎ ቁልቁል ወረደ ….
እታች ወንዴ ወደአባቱ መኪና ሲገባ ጎረቤቱ እንደአስከሬን መኪና ጥቁሩን ቢኤም ደብሊው አጅቦ እንደቆመ ልክ እንደህልም ይታየኛል … መኪናዋ ተነስታ በቀስታ ከግቢ ወጣች …. ጎረቤቱም በቆመበት ሰብሰብ ብሎ የሚያወራውን እንጃ አፉን በጋቢው ከልሎ ይንሾካሾካል …እያዘገሙም ደረጃውን ወጥተው ‹‹በሉ ሰላም እደሩ ›› እየተባባሉ ተራ በተራ በራቸውን ሲዘጉ ይሰማኛል …ከበር አዘጋግ እና ከአነጋገር ፍጥነታቸው እኔን ማናገር እንዳልፈለጉ ይገባኛል ተፀይፈውኛል!! የውጭ መብራቶች ተራ በተራ ጠፉ …. …ከነፍሳት ሲርሲርታና አልፎ አልፎ ከሩቅ ከሚሰሙ የውሻ ጩኸቶች በስተቀር ሁሉም ነገር ፀጥ አለ …ረጭ !!

ከቆምኩበት በረንዳ …. ቀና ብየ ፊት ለፊት የተዘረጋውን ሰፊ ጥቁር ሰማይ ተመለከትኩ …. ሙሉ ጨረቃ ሰማዩ ላይ ፏ ብላ ወጥታለች …..ስታምር … እና የምታፅናናኝ መሰለኝ የምታዋራኝ …..ሁልጊዜ ሙሉ መሆን የለም ነገ ከነገ ወዲያ ተሸርፋ ግማሽ ትሆናለች ሙሉነቷ በጥቁር ደመና ይሸፈናል …. ንፅህናዋ በደመና ግርዶሽ ይቆሽሻል …በጨለማም ይዋጣል … ግን ከየትኛውም ከባድ ግርዶሽ ኋላ ጨረቃ ያው ሙሉ ናት ! አይናችን ጠንካራውን ግርዶሽ አልፎ የጨረቃን ሙሉነት ማየት ሲያቅተው ‹‹ ግማሽ ጨረቃ›› የሚል ግማሽ እውነት እየነገረ ሊያሳምነን ይሞክራል ..እውነታው ግን በዚች ምድር ከየትኛውም ግርዶሽ ወዲያ አልፎ ማየት የሚችል ሙሉ አይን ያለው ፍቅር ብቻ መሆኑ ነው !! አይን የራሱን ድክመት ሲሸፍን ‹‹ፍቅር እውር ነው ›› የሚል ተረት ፈጠረ !

ስልኬን አየሁት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አልፏል … ህይዎቴም እንደዛው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት የሆነ ህይዎት …. በዛች ቅፅበት ከጨረቃው በላይ ከጥቁሩ ሰማዩ በላይ …. ከአስራ ምናምን አመት በፊት የሞተ አባቴ ጠንካራ እና ሞቃት ክንዶቹን ዘርግቶ ታየኝ …. ጠረኑም ሸተተኝ … በጎርናና ድምፁም ‹‹የእኔ ልእልት ምነው ብርድ ላይ ግቢና ተኝ ›› ሲለኝ ተሰማኝ ….
እንባየ ጉንጨ ላይ እየፈሰሰ ነበር … ጨለማ እፈራለሁ …. ያኔ ግን ወደድኩት …ከሰው አይን እቅፍ አድርጎ የደበቀኝ መሰለኝ … ባይነጋ ብየ ተመኘሁ …. የኔ የምነለው ሰው ከሚፈፅምብን በደል በላይ አስፈሪ ጨለማ በምድር ላይ የለም … አሁንም እንባየ ጉንጨ ላይ ዝም ብሎ ይፈሳል ….. ጨረቃ ድንቡሽቡሽ ያለች ህፃን ልጅ መሰለችኝ …እንባየን በፈገግታ የምትጠባ . . .

….ይቀጥላል ……

2 Comments

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...