Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 16)

‹‹ ኢያሱ እቤት እንደተቀመጠ ወጣሁና ….እንጀራ ገዝቸ ተመለስኩ …በቅቤ እብድ ያለ ፍርፍር ሰራሁና … (ኢያሱ ፍርፍር እንደሚወድ የሆነ ጊዜ ሲናገር ሰምቸ ነበር) አቀራረብኩ … ቡና አፈላሁ(አላሳዝንህም አብርሽ…. ኢያሱ እንዳይሄድብኝ መንከባከቤኮ ነው በቃ ሽር ጉድ አልኩ ) …
በየመሃሉ ኢያሱ ያወራኛል ….‹‹ ልእልትየ ….ባክሽ አትቸገሪ እኔ ናፍቀሽኝ አንችን ላወራሽ ነው የመጣሁት…ድምፅሽ የዋህነትሽ ሳቅሽ …ሁሉ ነገር ነው ያናፈቀኝ ›› ይለኛል ….እንዳልሆነ ባውቅም ውስጤ ግን ደስ አለው … አየህ የብቸኝነት ገደል ውስጥ ተንኮታኩተህ ከወደክ የሚላክልህ እጅ የማንም ይሁን ትጨብጣለህ …. ከገባህበት ገደል መውጣት ብቻ ነው ህልምህ ….ኢያሱ ሲያወራኝ ደስ እያለኝ እሰመዋለሁ …እሱም ካለወትሮየ የሰጠሁት ፊት አደፋፍሮት ዝም ብሎ ያወራልኛል …

‹‹ሌሊት ድንገት ትዝ አልሽኝ በቃ …ይች ልጅ ማን ጋር ትውላለች…ማን አላት … እያልኩ አስባለሁ …ስንት ነገር የለመደች ልጅ ሰው ከቧት ያደገች ልጅ ብቻዋን ባዶ ቤት ….. ዛሬማ ሳላያት አልውልም ብየ ‹በቃ እናንተ ቃሙ እኔ ዛሬ ልእልትየ ጋር ነኝ› ብያቸው መጣሁ ወንዴን ና እንሂድ ስለው አልሄድም አለኝ …የራስህ ጉዳይ ብየው መጣኋ …እንኳን መጣሁ ሳይሽ እንዴት ደስ እንዳለኝ ……ልክ ነኝ አይደል እንዴ ….በዚህ ሁኔታ ሰው የሚያስፈልግሽ አንች ነሽ ልእልትየ …ብቸኝነትን አውቀዋለሁ ….››
እያወራ ያለው ኢያሱ ነው ….ይታይህ ኢያሱ ተንኮለኛ በሌላ ነገር የሚፈልገኝ ነገረ ስራው ሁሉ እንደሂሳብ ስሌት የተሰላ መሆኑን አውቃለሁ …. በኢያሱ ህይዎት ውስጥ አጋጣሚ ብሎ ነገር የለም !! ምናልባት ዛሬ እኔ ጋር እንደሚመጣ ከነሰአቷ …ከአስራ አምስት ቀን በፊት ይሆናል ያሰበው …ቢሆንም አመንኩት !

አብርሽ እውቀት ሁልጊዜ ጉልበት አይሆንም ….ማጨስ ይጎዳል ሁሉም ሰው ይሄንን ያውቃል …መጠጣት ይጎዳል ህፃን ልጅም ያውቃል …ግን እውቀትህን ተጠቅመህ ከሚመጣው ችግር ለመዳን ጉልበት ያስፈልግሃል ….ሰው ደግሞ ያንን ጉልበቱን በተለያየ ምክንያት ይቀማል ይነጠቃል …. እኔም ተቀምቻለሁ ወንዴ ከነጓደኞቹ ባዶ ቤት እንደምናምንቴ ጥለውኝ ሂደው በራስ መተማመኔን …. ሁሉ ነገሬን ሰልበውኛል ….ትንሽ ንፋስ ቢነካኝ የትም የምወድቅ አቅመቢስ አድርገውኛል ….
ልእልት ስታወራኝ ተመስጨ እሰማታለሁ ….አንዴ ምን ታድርግ እያልኩ …ደግሞ መልሸ የፈለገ ቢሆን ኢያሱ ጋር ምንም ነገር መፈጠርማ የለበትም እያልኩ (ኧረ እንደውም ኢያሱ ጋር የሆነ ነገር ቢከሰትስ ብየ እንደቅናት ሁሉ ጀመረኝ …እስቲ ምን ባይ ነኝ ባሏ እያለ )ልእልት በየወሬው መሃል የሚዘረገፍ እንባዋን እየጠራረገች ቀጠለች
‹‹ …..ቤቱ የበፊት ድምቀቱ ተመለሰ ….የቡናውና የእጣኑ ጭስ ተቀላቅሎ ሙዚቃው ለሰስ ብሎ ተከፍቶ በዛ ላይ የኢያሱ የማፅናኛ ወሬ ሲዘንብ(መቸም ወሬ ይችላል) በብቸኝነት የደረቀ ልቤ እያንዳንዱን የቃሉን ጠብታ እንደደረቀ መሬት ዝናብ እንደናፈቀው … ይመጠዋል ….ኢያሱ ምን መናገር እንዳለበት ያውቃል …ምሳ ስንበላ አጎረሰኝ …. እያጎሰኝ ያወራኛል …..እያወራኝ ያጎርሰኛል ….የንግግሩን የእጁን ፍጥነት መቋቋም ሁሉ አልቻልኩም ….ኢያሱ ፈጣን ነው !

ምሳ በልተን ስንጨርስ …..ጫት አቀበለኝ ተቀበልኩ !! ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደቃመ ሰው ጫቱን አላምጨ ጭማቂውን ስውጠው …ምሬቱ አንገሸገሸኝ ….የተጨቀጨቀ ግራዋ በጉሮሮየ የተደፋ ነበር የመሰለኝ …. ቢሆንም የረሳሁት ምሬት የረሳሁትን ጣፋጭ የፍቅር ጊዜ ጎትቶ ውስጤን ሞላው … ድባቡ ውስጤን አገለባበጠው …..ከምንም በላይ ደግሞ ኢያሱ ሲሄድ ወደዛ አሰቃቂ ብቸኝነቴ አንደገና እንደምመለስ ሳስብ ሳላስበው እንባየ ተዘረገፈ …!

ኢያሱ ተጠጋኝና እጁን ትከሻየ ላይ አስቀመጠ ሲነካኝ ስቅቅ አለኝ … እሱም በሰውነቴ መንቀጥቀጥ ሳይደነግጥ አይቀርም … አብርሽ እኔኮ ከወንዴ ውጭ ሰውነቴን ነክቶት የሚያውቅ ወንድ አልነበረም …‹‹ምን ሆንሽ ልእልቴ ችግር አለ …ንገሪኝ እኔ ወንድምሽ ማለት ነኝ ›› እያለ ነዘነዘኝ ኢያሱ …..በቃ አልቻልኩም በእኔና በወንዴ መሃል የተፈጠረውን ነገር ሁሉ ዝርግፍ አድርጌ ነገርኩት ….ዝም ብሎ ሲሰማኝ ቆየና
‹‹ …አውቄ ነበር …የሆነ ነገር መፈጠሩን አውቄ ነበር ….ልጠይቅሽ አስብና ግን በእናተ ትዳር ጣልቃ መግባት እንዳይመስልብ እያልኩ ዝምታን መረጥኩ …ይገባኛል ልእልቴ እንደበፊቱ እንዳልሆንሽ በደንብ አውቂያለሁ ያ ውብ ፈገግታሽ የት አለ…ያ ደስታሽ የት አለ …..አንድ ቀን ግን አላስችለኝ ብሎ ….ወንዴን ‹ለምን ልጅቱን በብቸኝነት ትቀጣታለህ …ዋ በኋላ ወጣ በትል እነዛን ውብ እግሮቿን ስሞ የሚቀበላት ወንድ የምታጣ እንዳይመስልህ አንተን ብላ ነው …እቤት ታሽጋ የምትውለው …..አንተን ብላ ነው እኩዮቿ ሲዝናኑ …ሲደሰቱ ልእልትየ ቤተሰቦቿ ጋር እንኳን የማትሄደው አንተን ብላ ነው አልኩት ….ጫቱን እያመነዠከ … ‹ትሂዳ› አለኝ ›› አለና ኢያሱ ፍራሹን በቡጢ ጠልዞ …‹‹በቃ በዚች ቃሉ ወንዴ ጋር ተጣላን ጫታቸውን ወርውሬላቸው ከዛ ቤት ቀረሁ …በስንት ልመና ጓደኞቻችንን ሁሉ ልከው ሲነዘንዙኝ ነው የታረቅነው ››
‹‹ትሂዳ አለ ወንዴ ›› ብየ ኢያሱን ጠየኩት ….የሆነ ነገር ውስጤ ድቅቅ ሲል ተሰምቶኝ ነበር ….
‹‹ልእልትየ አንች እንደማታደርጊው አውቃለሁ ግን ወንዴ ያው አስተሳሰቡ ትንሽ አስቸጋሪ ነው ……ለብር ብለሽ እንደቀረብሽውና …ለቤተሰቦችሽ በድብቅ ብር ስትልኪ እንደማያውቅ ዝም እንደሚልሽ ጭራሽ አሁን ደግሞ …. ቤት መኪና ምናምን በስምሽ እንድትገዝለት ምናምን እንደፈለግሽ ነው የነገረን ››
ዝም ብየ በእልህ ጫቴን መቃም ጀመርኩ … ኢያሱም ከዛ በኋላ ብዙም አላወራኝም …. ድንገት ቡናው ገንፍሎ ምንጣፉን ሲያጥለቀልቀው ነው የባነንኩት …ተነስቸ በሩን ከፈትኩና መወልወያ አምጥቸ ምንጣፉን ወለወልኩ ….መወልወያውን መልሸ ከምድጃው ላይ የተነሳው ጭስ እንዲወጣ በሩን ገርበብ አድርጌ ተውኩት …..
ነገሩ ግን አንገበገበኝ ….ወንዴ እኔን ‹‹ትሂዳ ›› አለ ….ማለቱንስ ይበል ምናልባት ዛሬ ‹‹ትሂዳ ›› ካለ ነገ ‹‹ሂጅልኝ ›› ካለኝ የት አባቴ ነው የምሄደው …. መቸም እናቴ ጋር አልሄድም … እንደገና ውርደት እንደዛ ምድር መሬት ጠቦኝ በኩራት የወጣሁ ልጅ …እዚሁ አዲስ አበባ ተቀምጣ ‹‹አንዳንዴ እንኳን ብቅ ብለሽ እይኝ እንጅ መኪና አላችሁ ›› እያለች ስትለምነኝ እንኳን ደጇን መርገጥ የከበደኝ እኔ ….ዛሬ እንደተባረረች የቤት ሰራተኛ ልብሴን አንጠልጥየ ወደ እናቴ ቤት ስሄድ …..ኤጭ!

ሰው ዝም ብሎ ቆንጆ ሴት መሄጃ አታጣም ይላል ….እዚች አገር እንደቆንጆ ሴት መሄጃ የሌላት ፍጥረት የለችም ….የት ትሄዳለች ….የሄደችበት ሁሉ ማንም ሰውነቷን እንጅ ሴትነቷንም ሰው መሆኗንም አስታውሶ የሚቀበላት የለም …የት ትሄዳለች ያልተማረች ብር የሌላት ቆንጆ የት ትሄዳለች….ወንድ አባረረኝ ብላ ሌላ ወንድ ጋር ? ወይስ ….ቡና ቤት ? እንደቆንጆና ደሃ ሴት ዋስትና የሌላት ፍጥረት የትም የለችም ….
በውድ መኪና ጋቢና ተቀምጨ ስቀማጠል ተሰልፈው ታክሲ የሚጠብቁ ሴቶች ቀንተውብኝ ይሆናል …. ለዚች አገር ብዙ የሰሩ ላባቸውን ጠብ ያደረጉ ሰዎች በውስጣቸው እነሱ ጠብ በማይል ከወር እስከ ወር ደመዎዝ ተራራ ችግሯን ሲገፉ …..ምንም ሳንሰራላት እኔና መሰሎቸን በማቀማጠሏ በአገራቸው አዝነው ይሆናል ….ግን አገራቸውና አገሬ ዛሬ አየር ረግጨ ከወጣሁበት ከፍታ ስምዘገዘግ መውደቂያ ሜዳዋን ከማዘጋጀት ውጭ ምንም ልታደርግልኝ እንዳልቻለች ባዩልኝ !! ከፍቅር የተሰናበተች ሴት ምን ሊዘጋጅላት ነበር ድሮስ …ጡረታ አይዘጋጅ ነገር !
ወንዴን እወደዋለሁ ….ሁሉም ነገር ይቅር ብሩም ምኑም ይቅር እኔም ዛሬውኑ ሂጀ ጎዳና ልውደቅ ግን ….በዚች አለም አለኝ የምለው አንድ ነገር እሱም ለወንዴ ያለኝ ፍቅር እንዲህ በቀላል አለመግባባት እንደእቃቃ ቤት ፍርስርስ ብሎ ሲወድቅ ….የውጭ ሰው ባይገባው እንኳን ፍቅሬን እንዴት ወንዴ እውቅና ይንሳው ???
ወንዴን ነፍሴ እስኪወጣ እወደዋለሁ …..ይሄን ሁሉ ጊዜ መንሰፍሰፌ ለብሩ እንደሆነ ነበር ማለት ነው የሚያስበው …ይሄን ሁሉ አመት እጆቸ የማንን እጅ ጨበጡ …ይሄን ሁሉ ዘመን ወጣ ብሎ እስኪመለስ አይኖቸ ማንን ተርበው ጠበቁ …ይሄን ሁሉ ዘመን ማንንም ያለመደ ሰውነቴ ለማን ተጎተተ የማንን እቅፍ ናፈቀ ….ከውስጤ ተፈንቅሎ የሚወጣ ሳቄና ደስታየስ በማን ነበር …. ወንዴኮ አገባኝ ሳይሆን አሳደገኝ ነው የምለው አብርሽ ….››
ልእልት ስርቅርቅ አለች በቁጭት …በፀፀት
ያንን ሁሉ ውድ ሬስቶራንት ይሄን ሁሉ ውድ ልብስና ጌጣጌጥ ማን ገዛልኝ ማን አሳየኝ …..ወንዴ ነው …. እኔማ ተራ ካፌስ የት አባቴ አውቅ ነበር ….እንኳን ግዛልኝ ልለው ከነመኖሩም ሰምቸው የማላውቀውን ልብስ ጫማ ሁሉ ወንዴ ነው እያመጣ የቆለለው ወንዴ ነው ካለበሽ ብሎ እንደህፃን ልጅ ከተቀመጥኩበት አንስቶ እያለበሰ የራሴን ሰውነት እንደሌላ ሰው ሰውነት በግርምት እንዳየው ያደረገኝ ..…
ውጭ ቆይቶ ሲመጣ ልጇን እንዳገኘች እናት ይዞልኝ የመጣውን ነገር ሳይሆን ወንዴን በናፍቆት ተንሰፍስፌ ስጠመጠምበት ያች ቤታችን አፍ አውጥታ ብትመሰክር ስንት ነገር ትል ነበር …… ገዝቶ ያመጣልኝ ልብስ ከነፌስታሉ አስቀምጨ ሳምንት ዙሬ ባለማየቴ ወንዴ ስንት ቀን ተበሳጭቶብኛል ! አንድ ቀን ቻፕስቲክ እንኳን ግዛልኝ ብየው ካወኩ እግዚአብሔር ምስክር ነው … … በገዛልኝ ስልክ እንኳን ከወንዴና ከቤተሰቦቸ ስልክ ቁጥር ውጭ የአንድ ሰው ስልክ ‹ሴቭ› አድርጌ አላውቅምኮ ….ማንንስ አውቃለሁ ከወንዴ ሌላ …የሃይስኩል ጓደኞቸን ገና በፊት ነው እርግፍ አድርጌ የተውኳቸው ….…ወንዴ አለሜ ነበርኮ አብርሽ !!
በእርግጥ ለወንዴ ምንም አድርጌለት አላውቅም (ምን አለኝና ምን አደርግለታለሁ) ግን ማፍቀሬስ እንዲህ ከቁም ነገር የማይፃፍ ተራ ነገር ነው ማለት ነው ?….ውለታው ይከብደኛል … አብርሽ እኔና ወንዴ ከተጋባን ጀምሮ ለቤተሰቦቸ ሰባራ ሳንቲም ሰጥቻቸው አላውቅም … ሰባራ ሳንቲም !! ብር ስለነበራቸው ነው ? የእኔን እርዳታ ስለማይፈልጉ ነበር ?አይደለም ….ግቢያችን ውስጥ አባባ ሳይሞት ያሰራቸው ሁለት ሰርቪስ ቤቶች አሉ ….እህቴና እናቴ እነዛ ሰርቪሶች ውስጥ እየኖሩ ዋናውን ቤት አከራይተው በዛች ኪራይ ነው እማማና እህቴ የሚኖሩት በቃ !ሌላ ቤሳቤስቲን የሚረዳቸው ዘመድ የለም !

ታናሽ እህቴ <ይንቨርስቲ> ውጤት ሲመጣላት ወንዴን ነግሬው …ያኔም የነገርኩት እንዲሁ ዩኒቨርስቲ መግባቷ በደስታ አሳብዶኝ እንጅ ምንም አስቤ አልነበረም … ምን አስባለሁ እኔ ሰው ዩኒቨርስቲ ሲገባ ምን ይያዝ ምን ይተው ምናውቃለሁ አብርሽ… እና ያኔ ብዙ ልብስ ገዝቶላታል ብርም ሰጥቷታል .ስልክ የገዛላትም እሱ ነው … ወንዴ ለእኔም እኔ ለምወዳቸውም ሁሉ አድርጎ አይጠግብም ነበር …በእህቴም ውጤት አንደእኔ እንደውም ከእኔ በላይ ነበር የተደሰተው …ይሄው ነው ከዛ በኋላም ቢሆን ወንዴ በየጊዜው ብር እየሰጠኝ ላኪላት ይለኛል እልክላታለሁ … ከወንዴ ተደብቄ የሆነ ነገር ማድረግ ቀርቶ የብር ጥቅም ሁሉ ሳይጠፋኝ አይቀርም ….በወንዴ ፍቅር አብጀ ነበር ….በዚች ምድር የእኔ ብቸኛ ሃብት የወንዴ ፍቅር ነበር !!

በቃ እንባየ ተዘረገፈ …አብርሽ እንደዛን ቀን አልቅሸ አላውቅም ..ኢያሱ እንደህፃን አቅፎ አባባለኝ .. የኢያሱን ኢያሱነትም ወንድነትም ረስቸ ደረቱ ላይ ልጥፍ ብየ እስኪበቃኝ አስነካሁት …. እራሴ ሊፈነዳ ደረሰ ….
እኔኮ ለወንዴ ህፃን ነበርኩ … የወንዴ እንክብካቤኮ ዝም ብየ ሳስበው ከአባት እንኳን ይበልጥ ነበር …
ታውቃለህ አብርሽ …‹ማንስትሬሽን › ላይ ስሆን እንደትልቅ ህመም ቤቱ በጁስና በፍራፍሬ ይሞላል …ወንዴ ከአጠገቤ ቢሞት አይርቅም …. ቁጭ ብሎ አይን አይኔን ሲያየኝ ይውላል እንደውም ኩርምት ሲል አንጀቴ ይንሰፈሰፍለት ነበር … በአንድ ሰዓት አራት ጊዜ ‹‹አሁንስ አንዴት ነሽ ያምሻል ›› ይለኛል ….በቃ ጭንቀት ነው ! ›› ልእልት በሚያሳዝን ፊት ትክ….ዝ ብላ ለረዥም ደይቃዎች ቆየችና በረዥሙ ተንፍሳ … እነዛን አሳዛኝ ውብ እና ገራገር አየኖቿን አይኖቸ ላይ ተክላብኝ ለራሷ በሚመስል እና በታከተው ሰው ድምፅ ….
‹‹ወንዶች …ቢያንስ ስትንከባከቡት የቆያችሁትን ፍቅር አንስታችሁ ስታፈርጡት ምን ላይ ያርፋል ብላችሁ እንኳን አትጨነቁም ….ምናይነት ልብ እንዳደላችሁ ግን !!›› አለችና እንባዋ እንዳይፈስ ወደላይ ወደኮርኒሱ ቀና አለች …ጥርት ያለ አንገቷ ላይ በጣም ቀጭን የወርቅ ሃብል አስራለች … አንገቷ ከአገጯ ወደታች በስርአት ተቀርፆ ይወርድና ቀኝና ግራ የተሰመሩ የሚመስሉ አጥንቶቿ አጥረውት እንደውሃ ጉድጓድ ስምጥ ያለ የትከሻዋ ጉድጓድ ላይ ተተክሎ ሲታይ ውብ የእብነበረድ አምድ ይመስላል …
ልእልት ውብ ናት…. አንዳንዴ የእግዚአብሔር ጥበብ ይገርመኛል ….ሁሉም ቁንጅና የራሱ መስእብ ቢኖረውም እንዲህ አይነቱ የልእልት ቁንጅና ላይ አንዳች አስደማሚ መንፈስ የጨመረበት ነው የሚመስለኝ ….ይህን ውበት የሚረብሸው ታሪክ ጦርነት መሰለኝ ….የተሰናከለ ፍቅር ውብ የጥበብ ከተማን ከሚያጠፋ ጦርነት እኩል ነው ! ጦርነትም የተሰናከለ ፍቅርም የበለጠ ለሴቶች ሰቆቃ ነው !
አይኖቿን ከጣራው ስትመልስ ….በጣም በወረደ ፀፀት እና ሃዘን በተሞላበት ድምፅ እንዲህ አለችኝ ….
‹‹ ያኔ … አልቅሸ ወጥቶልኝም ከእያሱ ደረት ላይ ቀና አላልኩም ….ዝም ብየ በሃሳብ ነጎድኩ ….. አንጀቴ ውስጥ ገብቶ የሚያንሰፈስፈኝ ነገር ነበር …ብዙ ነገር ነበር … ግንብ ልደገፍ እያሱን ልደገፍ ጉዳየ አልነበረም ብቻ መንቀሳቀስም ማሰብም መተንፈስም ጭምር አስጠልቶኝ ዝም ብየ ነበር …..በዚች ቅፅበት ቡናው ሲገነፍል ቤቱን የሞላው ጭስ እንዲወጣ ብየ ክፍቱን በተውኩት በር ከሰማይ ይውረድ ከመሬት ይውጣ እንጃ ወንዴ ሰተት ብሎ ገብቶ ፊታችን ተደነቀረ !! ….
ኢያሱ ደረት ላይ እንደተለጠፍኩ አይኔን ብቻ ቀና አድርጌ እንደሰመመን አየሁት ወንዴን ….ህልም ነው የመሰለኝ …እግዜር ይፍታው ይሄን ህልም …
…ይቀጥላል ….

4 Comments

  • WANOFI commented on August 4, 2018 Reply

    betam des ylal gn lemn alchereskewm, mechereshawn lemawek guaguchalehu

  • wanofi commented on August 4, 2018 Reply

    ታሪኩ ደስ ይላል በናትህ ጨርሰዉ ,አሌክሰ አብርሀም

  • value commented on August 15, 2019 Reply

    የማንን ልብ አንጠልጥለህ ትቀራለህ ጨርሰው

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...