Tidarfelagi.com

‹‹ቆንጅዬ›› 

(የታሪክ መዋቅር እና ሃሳብ- የቼታን ባጋት ‹‹ዋን ኢንዲያን ገርል››) 

እንደ እህቴ ቆንጆ አይደለሁም። ሕይወቴን ሙሉ በተደጋጋሚ የሰማሁት አንድ ነገር ቢሆን እንደ እህቴ ቆንጆ ያለመሆኔን ነው።
የሁለት አመት ታላቄ ናት። ትምህርት ቤት እያለን ጀምሮ የአባትና የአያታችንን ስም ሰምቶ እስኪያረጋግጥ፣ አንድ ቤት ውለን ማደራችንን እስኪያውቅ ድረስ፣ በመልክ መራራቃችንን የሚያውቅ ሰው ሁሉ እህትማማች መሆናችንን አያምንም ነበር።

‹‹የሆነ ነገራችሁ ግን ይመሳሰላል…አለ አይደል…ደማችሁ›› እያሉ ሊያፅናኑኝ የሚተጉ ሰዎች አንዳንዴ ይከሰታሉ። እኔ እና እህቴ በደም እንኳን ብንመሳሰል ከፎቶሾፕ በፊት እና በኋላ ነው የምንሆነው። በፊቱ እኔ…በኋላዋ እሷ። በዚህ ላይ እህቴ ራሷን መጠበቅ፣ ውበቷን መጨመር ታውቅበታለች። እኔ አጎፍሬው ስዞር ቅንድቧን መቀንደብ የጀመረችው አስራ አምስት ሳይሞላት ነው። እኔ በቋሚነት በሄርባንድ አፖሎ አሲዤው ስሄድ ለታክሲ የሚሰጠንን ገንዘብ አጠራቅማ ፀጉሯን መተኮስ የጀመረችው ዘጠንኛ ክፍል እንደገባን ነው።

እንደ እህቴ ቆንጆ አይደለሁም። ግን ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። መደበቂያዬ ትምህርት እና መፃህፈት፣ ብቸኛ የውዳሴ ምንጬ ጉብዝናዬ ስለነበር ትምህርቴ ላይ ቀልድ አላውቅም ነበር። ገናና ተማሪ ነበርኩ። ከሴክሽን አንደኛ የምወጣ፣ እህቴ ተንጠልጥላ ስታልፍ ደብል የምመታ።

የእህቴ ምኞት አንዱን ሃብታም በጊዜ አግብታ የድሎት ኑሮ መኖር ነበርና ሃያ ሁለት አመት ሳይሞላት አገባች። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በህግ (ያው በከፍተኛ ማእረግ ተመርቄ) ከእሷ ጋር የመነፃፀር ዘመኔ አበቃ ብዬ እፎይ ባልኩበት ጊዜ ግን የእማዬ ‹‹ምናለ እንደሷ ብትሆኚ›› ንዝንዝ ጭራሽ ባሰ።

ለእማ የእኔ በማእረግ ተመርቆ የብዙ መስሪያ ቤቶች ‹እኛ ነን ምንቀጥራት›. ሽሚያ ብዙ አላኮራትም። በተመረቅኩ በቀናት ውስጥ ቤት ተቀምጠን እንዲህ አለችኝ።
– በይ አሁን አንቺም እንደ እህትሽ ቶሎ አግቢ
– እንዴ! ማስተርሴን ሳልሰራ? አልኳት
– ማግባት በወጣትነት ይሻላል በተለይ ለእንዳንቺ አይነቱ…..አለችኝ….
በተለይ ለእንዳንቺ አይነቱ ማለት ምን ማለት ነው? በዚህ ማስጠላትሽ ላይ እድሜ ስትጨምሪበት እንኳን የሚያገባሽ በእንጨት የሚነካሽ አታገኚም ማለት ነው?

ተውኳትና ማስተርሴን ሰራሁ። ኢንተርናሽናል ሎው ነው የተማርኩት። ኤ ደርድሬ ከመመረቄ በፊት ነው ስራ ያገኘሁት። ያውም የኮራ የደራ ኢንተርናሽናል ኤንጂኦ። በዜሮ አመት ልምድ 27050 ብር ስቀጠር በድንጋጤ እንጥሌ ዱብ ሊል ምንም አልቀረው። ለእነእማ ስነግራቸው ሌንጬጫቸው እስኪንጠለጠል ድረስ ደነገጡ። አባዬ ጎበዝ አለኝ። እማ ግን ከድንጋጤዋ መለስ ስትል ገንዘብ ብቻውን ምን ይሰራል? ይልቅ ቶሎ አግቢ ነው ያለችኝ።

ኤንጂኦ!

ኤንጂኦ በእህቴ አይነት ሴቶች የተሞላ ነው። በራሳቸወ አምረው በገንዘብ ይበልጥ የቆነጁ፣ ፉንጋ ሆነው መጥተው በገንዘብ ሃይል ደምግባት ያበጁ ይበዙበታል። ከሚሰሩት በላይ የሚከፈላቸው ሴቶች ቋ ቀጭ ጫማቸውን ሲያንቋቁ ይውላሉ። ውድ ሽቷቸውን በየኮሪደሩ እየረጩ ሲወዘወዙ ያመሻሉ። ሴፎራ ሊፕስቲክ ተለቅልቀው፣ የ700 ብር ፓውደር ፊታቸው ላይ ነስንሰው፣ በሳምንት ሁለቴ የሚተኮስ ውድ የብራዚል ፀጉራቸው ሰክተው፣ በዋክስ ሙልጭ ተደርጎ የተላጩ እግሮቻቸውን በአጭር ቀሚስ አጋልጠው ወዲህ ወዲህ ሲሉ ያመሻሉ- ያነጋሉ።

ይሄን ስራ ይዤ ለመቆየት አካባቢዬን መምሰል ነበረብኝ። እንዴት አድርጌ እንደምመስል ግን መንገዱ ጠፋኝ። እኔ አሁንም ዮኒቨርስቲ ያለሁ ደክራታ ተማሪ ነው ምመስለው። ወፋፍራምና ቀጭን ሰውነቴ ላይ የሚወዛወዙ ሹራቦቼ ከትልቁ መነፀሬ እና ቡላጫ (ቡኒ እና ግራጫ) ሱሪዎቼ ጋር ተደምረው እድሜዬ ላይ 20 አመት ይጨምራሉ። የሰለቻት ለይብረሪያን እንጂ የኤንጂኦ ሰራተኛ አልመስልም።

ስራ በጀመርኩ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከሁሉ ጋር የሚግባባው ቶማስ ቢሮዬ መጣና ‹ኦፊስ ፓርቲ›› ጋበዘኝ።
– መቅረት አይቻልም! አለኝ ማመንታቴን አጢኖ
– እህ…እስቲ ላስብበት
(መቀላቀሉን እፈልገዋለሁ ግን ምን ለብሼ ልሄድ ነው ብዬ ተጨንቄ ነው)
– ማሰብ የለም…መምጣት ብቻ ነው….መምጣት….ብሎ ጥሎኝ ሄደ

ቶማስ በሄደ በደቂቃ ውስጥ አጠገቤ የምትቀመጠውን የዘናጭ ጥግ ጠራኋት።
-ሜሪ….
– ወዬ…
– ልብስ የት ነው ምትገዢው?

ማርቲስ ኮሌክሽን ሂጂ አለችኝ። ከስራ እንደወጣን ሄድኩ።
ልብሶቹን በፍርሃት ከቃኘሁ በኋላ የምትሸጠውን ዘናጭ ልጅ…
– ማታ እራት አለብኝ….ሾፒንግ ሞቴ ነው…እስቲ አማርጪኝ በናትሽ …አልኳት።

ሰባ ምናምን ነገር ሳልሞክር አልቀረሁም። አላበኝ። በመጨረሻ ከጉልበቴ ትንሽ ከፍ የሚል በጣም የሚያምር ብሩህ አረንጓዴ ቀሚስ መረጠችልኝ።
– ሲያምርብሽ! አለችኝ
(የሚከፈላት እንዲህ እንድትል ስለሆነ ከቁብ አልቆጠርከትም)

– እውነት? አልኳት ዝም ላለማለት
– ውይ በጣም…ሰፊ ነገር ለብሰሽ ስትመጪ ወፍራም ትመስይ ነበር…በጣም ያምራል ሰውነትሽ
(ቢከፈላትም ደስ አለኝ…)
– ስንት ነው? አልኩኝ
– 950…ሴል ላይ ነው አለችኝ ፈጠን ብላ

ወይ ሴል እቴ!
ትንሽ አቅማምቼ…
– እሺ በቃ እወስደዋለሁ…አልኩና አንዴ ዞር ብዬ ቂጤን አየሁት። ፍጥጥ ብሏል
– አይዞሽ በጣም አምሮብሻል….ግን…እግርሽን ዋክስ ብታደርጊ ጥሩ ነው….አለችኝ።

አስጠቅልዬ ወጣሁ።

– ፐፐፐ! ሌላ ሰው መስለሽ የለ እንዴ! ዛሬ ላይብረሪ የምትሄጂ አትመስይም አለኝ ቶማስ ገና ሲያየኝ።
አስራ ምናምን ከሚሆኑ የስራ ልጆች ጋር እንደ ተቀመጥኩ አስተናጋጅ መጣና-
– ምን ልታዘዝ? አለኝ
– ሁላችንም ቮደካ ይዘናል…ቮድካ አትጠጪም? የሚል ድምፅ ሰማሁና ወደ ቀኝ ዞርኩ። አይቼው የማላውቅ የሚያምር ልጅ ነው። እኛ ቢሮ ነው የሚሰራው?
– አይ….መጠጥ ብዙ አይደለሁም …ቶሎ እሰክራለሁ….አልኩ ትኩር ብዬ ማየቴን ሳላቋርጥ
– አይዞሽ…ባንዴ እኮ አንድ ብርጭቆ ነው ሚያመጣልሽ…አለና ፈገግ አለ። የፈጣሪ ያለ! በእነዚህ ጥርሶቹ እህል አላምጦ ያውቃል? ነ….ጭ…..ናቸው።

ትንሽ ተከራክረን ወይን- ጣፋጭ – ቀይ ያገር ውስጥ ወይን አዘዝኩ።
– የት ዲፓርትመንት ነው የምትሰሪው አለኝ ወይኑ እንደመጣ
ነገርኩት።
– እኔ ኮሚኒኬሽን ነኝ ግን ልለቅ ነው….

(ውይ….ለምን? )
– የተሻለ ነገር አግኝቼ ነው…ዩ ኤን ዲፒ ልሄድ ነው አለኝ፡ ፊቴን አይቶ ለምን እንዳልኩ ገብቶት ነው?
– አሪፍ…አልኩና ወይኔን ጎንጨት አልኩ
– ቀሚስሽ በጣም ያምራል አለኝ በጣም ተጠግቶኝ…
– አመሰግናለሁ …አልኩ ፀጉራም እግሮቼን እንዳያይ ቀሚሱን ያላቅሙ ወደ ታች እየጎተተኩ
– ዋገውም ያምራል….አለኝ አሁንም ተጠግቶኝ ድምጹን ዝቅ አድርጎ
ባንድ ጊዜ ፊቴ የምጠጣውን ወይን መሰለ።
ምንም ሳይለኝ እጆቹን ወደ አንገቴ ጀርባ ልኮ ረስቼው የነበረውን የዋጋ ወረቀት በጠሰው።

ሽምቅቅ አልኩ።
በሚያምሩ ጥርሶቹ ሳቀና
– አዲስ ነው ማለት ነው…አለ
ዝም ብዬ ያዘዝኩትን ጥብስ በጣቶቼ ማማሰል ቀጠልኩ።
– ምግቡ ብዙ አልተመቸሽም መሰለኝ…አለ
– እ….አልኩ
– ምን አይነት ምግብ ነው ምትወጂው?
( ለምንድነው ድምፁ እንዲህ የሚያምረው?)
– እኔ?
– አዎ…አንቺ…
– ሽሮ….አልኩ የግዴን ቀና ብዬ እያየሁት
(ለምንድነው መልኩ እንዲህ የሚያምረው?)

– አዲሳባ አለ የተባለ ሽሮ ቤት እወስድሻለሁ….መቼ ይመችሻል?
(እወስድሻለሁ? ማለት…ለብቻችን….? ፈልጎኝ ነው….ደስ ብዬው ነው? )

– ማለት…በቡድን? አልኩ ትንሽ ተርበትብቼ
(ለምንድነው እንዲህ አድርጎ የሚያየኝ?)

– ኖ…እኔ እና አንቺ….
– እሺ….. ሆዴ ተገለባበጠ።
– መቼ ይመችሻል ታዲያ?
– አ…ዛሬ ምንድነው….?
– አርብ…
– ሰኞ?…ከስራ በኋላ?
– አሪፍ…በቃ ሰኞ እንሄዳለን….
– እሺ…
– ግን አደራሽን….
ቀና ብዬ አየሁት። ምኑን ነው አደራሽን የሚለው?
– ምኑን? አልኩት ወይኔን ብድግ አድርጌ እየተጎነጨሁ።
– ለዛም ቀን አዲስ ቀሚስ እንዳትገዢ….

ትን ሊለኝ ነበር።

– ቀልዴን ነው…አለና ትከሻዬን እንደቀልድ ነካኝ።
(ወይኑ ነው እጁ ይሞቃል? )

– ገባኝ…አልኩ እንደምንም…
– ኦኬ…ስልክሽን ስጪኛ….
ስልኬን ለጥናት ቡድን ካልሆነ፣ ለግሩፕ አሳይመንት ካልሆነ ለወንድ- ለአንድ ወንድ- ያውም እራት ሊጋብዘኝ የፈለገ ቆንጆ ወንድ ሰጥቼ አላውቅም።

ሰጠሁት።

ይሄ ሊጎነጎን የደረሰ የእግሬን ፀጉር ቅዳሜ ወይ እሁድ ዋክስ መደረግ አለብኝ። እንደ ሴቶቹ ሙልጭ አድርጌ መላጨት አለብኝ።

‹‹ቆንጅዬ›› (ክፍል ሁለት)

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...