Tidarfelagi.com

‹‹ቆንጅዬ›› (ክፍል ሶስት)

አንዳንድ ሴቶች በቁርጥ ስጋ እና ቱርቦ ተደልለው ወደ አልጋ ይሄዳሉ። አንዳንዶች ውድ ሽቶ ሲሰጣቸው ገና ሳይቀቡት ልብሳቸውን ለሰጪያቸው ያወልቃሉ። አንዳንዶች ለቪትዝ የውስጥ ሱሪያቸውን ያስወልቃሉ። አንዳንዶች ጂ ፕላስ ምናምን ቤት ሲያዩ ጭኖቻቸው ይከፈታሉ። አንዳንዶች ላሳቃቸው ወንድ ገላቸውን ይቸራሉ።

የእኔ ምስ ግን አንድ ነው። ‹‹ቆንጅዬ›› መባል። ‹‹የኔ ቆንጆ›› መባል።

ከእህትሽ ታምሪያለሽ ብሎኝ ለወራት አብሬው የወጣሁት የመጀመሪያ ቦይፍሬንዴ ለአልጋ ዝግጁ የሚያድርገኝን ቃል ጠንቅቆ ያውቀዋል። ወደ አልጋ ሊያስገባኝ ሲፈልግ ውድ ምሳ – ወይ የሻማ እራት አይጋብዘኝም። ወይን አያጠጣኝም። ስጦታ አሽጎ አያመጣልኝም።

ቆንጅዬ ሲለኝ ፍንክንክ እላለሁ።
የኔ ውብ ሲለኝ ወከክ እላለሁ።
የኔ ቆንጆ ሲለኝ ሙክክ ብዬ እበስላለሁ።
ካንቺ በላይ ቆንጆ የለም ሲለኝ ሲራገብ እንደ ዋለ ከሰል ትርክክ እላለሁ። እንኳን ጭኖቼ ሁለንተናዬ ይከፈታል። ብርግድግዴ ይወጣል።

ቆንጆ መባሌ እኔም እንደሴቱ ወግ ደርሶኝ ቦይ ፍሬንድ ኖሮኝ- የአልጋ ላይ ንግስት መሆንን ብቻ አይደለም የሰጠኝ። እሱ ቆንጆ ባለኝ ቁጥር ተጨማሪ የራስ መተማመን በመርፌ እንደተወጋ ሰው ያደርገኛል። እነቃለሁ። እነሳለሁ። ወደ ፊት እራመዳለሁ።

ቆንጅዬ ሲለኝ የደስታ ክተባት እንደተከተበኩ ሁሉ ሁለንተናዬ እየሳቀ፣ እየተፍነከነከ ቀኔን ጀምሬ እጨርሰዋለሁ።

ያኔ ነው አለምም በራሳቸው ለሚተማመኑ የምትመች ቦታ መሆኗን ያወቅኩት። እንዴት ?

በእንዲህ ያለው ቀን በቦይፍሬንዴ ተስሜ፣ በፍቅር ተሸሞንሙኜ ውዬ ከቤቱ ሰወጣ ሰበር ሰካ እል የለ? ከአንገቴ ቀና፣ ከትከሻዬ ነቀል፣ ከእግሮቼ ፈንጠር እያልኩ እሄድ የለ?

ይሄን ጊዜ የማያየኝ ወንድ የለም። ይሄን ጊዜ የማታየኝ ሴት የለችም። ፀጉሬን በእጆቼ ወደ ግራ ወይ ወደቀኝ መታ አድርጌ፣ደረቴን ነፋ አድርጌ በጎዳና ላይ ሽር ብትን ስል የሚያዩኝ ስራ ፈትተው- ዛሬ ደግሞ ምን እናድርግ- ማንን እንልከፍ ምናምን ብለው ብቻቸውን የቆሙ ቦዘኔ ወንዶች ብቻ አይደሉም።
ከሴት ጋር የቆሙ፣ ከሴት ጋር የተቀመጡ፣ ከሴት ጋር የሚበሉ፣ ከሴት ጋር የሚጠጡ፣ ከሴት ጋር የሚራመዱ ወንዶች ሁሉ አፍጥጠው ያዩኛል።
ከሴት ጋር ስል ዝምብለው ቱታ ወይ ድሪያ ለብሰው፣ ሻሽ ሸብ አድርገው የወጡ ሴቶችን አይደለም። ቦርጫም ወይ ብጉራም፣ ቂጣቸው ከጭናቸው ጋር የተቀላቀለ አይነት አይስቤ ሴቶችንም አይደለም።
ቂቅ-ቋ ብለው የወጡ፣ በከፍተኛ ሂል ጫማ ላይ የቆሙ፣ በሂውማን ሄር ያበዱ፣ አንጀታቸው ሙትት..ቂጣቸው ውጥት ያሉ ቆንጆ ሴቶችን ማለቴ ነው። እንዲህ አይነቷ ሴት ጋር ያሉ ወንዶች ናቸው እኔን ለማየት የሚዞሩት። የሚሰርቁት። አይኖቻቸውን የሚያንከራትቱት። እህቴን የሚመስሉ ሴቶችን ወገብ አቅፈው የሚሄዱ ወንዶች ናቸው አንገታቸውን አዙረው እኔን አይተው ከንፋቸውን እንደ ምግብ የሚልሱት።

ነገሮች ፍጹም ተለዋውጠዋል። የቁንጅና ጣኦት፣ በየጎዳናው የምመለክ ጣኦት ሆኛለሁ።

ከእነዚያ ውብ ሆነው ከተወለዱ የኤንጂኦ ሴቶች ጋር ምሳ ስወጣ (በ‹‹ ማን ይበልጥ ያምራል ›› አደራደር ቃተኛ ተኮልኩልን ተምጠን) ምድረ-ሃብታም ወንድ ምግቡና አጠገቡ ያለች ሴቱን ትቶ አይኑን እኔ ላይ ይሰካል። እጆቼን ልታጠብ ቋ ቀጭ እያልኩ ስነሳ የሰራው ጉርሻ አፍርሶ እየተደናበረ ይከተለኛል።

ሰከርኩ። በመፈለግ፣ በፍላጎት በመታየት፣ ብዛት ብስብስ ብየ ሰከርኩ። በራስ መተማመኔ በዝቶ በዝቶ ወደ ትእቢትነት ለመቀየር እስኪደርስ ድረስ በወንዶች የአድናቆት ብዛት ሰከርኩ።

አንዱን ቀን ከቢሮ ሴቶች ጋር እራት ልንበላ አንዱ ቤት ተቀምጠናል። ከገባን ጀምሮ በመጥቀስና በማፍጠጥ መሃከል ባለ ሁኔታ የሚያየኝ ብዙም የማያምር ግን ወንዳወንድ ልጅ ከእኛ ቀጥሎ ያለውን ወንበር ዘሎ ያለው ወንበር ተቀምጡዋል። አላየውም እል እና አየዋለሁ። አይኖቻችን ሲገናኙ ወሬ እነደያዘ ሰው ወደ ጓደኞቼ እመለሳለሁ። ደግሞ አሁንም አያየኝ ይሆን ብዬ አስብና ቀና ብዬ አየዋለሁ።

አሁንም እያየኝ ነው።

ምን ፈልጎ ነው?

ትቼው ጨዋታውን ቀጠልኩ።
– ስሚ አለችኝ ከሰባቱ አንዷ የጎረሰችውን ጥብስ ፍርፍር ጨርሳ ሳትውጥ
– እ…አልኩ ሃሳቤ ከወንዳወንዱ ልጅ ሳይላቀቅ።
አላየውም። አላየውም። አላየውም።

አየሁት።

እንዳፈጠጠ ነው።
ተሸኮረመምኩና አይኖቼን ሰበርኩ።
ሆ!

– ….እና ስልኳን ካልሰጠሸኝ ብሎ ወጥሮኛል…ልስጠው? አለችኝ ሜላት።
ልጁን ሳይ ያለቸውን ሁሉ አልሰማሁም።
– ምን? አልኳት እያየኋት
– እንዴ…አልሰማሽኝም እንዴ?
– አዎ…ሶሪ…ማነው ስልኳን ያለሽ….

እንደገና አየሁት። አየኝና ተነሳ። ቁመቱ መአት ደልዳላ ነገር ነው።
የት ሊሄድ ነው?
ሜላት ታወራለች።
በአይኔ ተከተልኩት።
– እና ልስጠው? አለች ሜላት
– ስጪው…አልኩና ብድግ አልኩ።
የት ልሄድ ነው?
አየሁት። ወደ መታጠቢያ ቤት ነው የሚሄደው።

ተከተልኩት።
ኮሪደሩ ጋር ስደርስ ቆሞ አገኘሁት።
እምም።

– በጣም ታምሪያለሽ…..አለ። ድምፁ ቁመናውን የሚመጥን ነጎድጓዳማ ነው።
በቆምኩበት ፈገግ አልኩ።
– አመሰግናለሁ አይባልም እንዴ? አለኝ
– …ይባላል። አመሰግናለሁ። ሽንት ቤት ልገባ ነው አንዴ….
በቆመበት በቄንጥ እየተራመድኩ ጥዬው ሄድኩ። አይኖቹ ቂጤ ላይ ተለጥፈው ይሰሙኛል። ድንገት ዞር ብዬ አየሁት። ልክ ነበርኩ።

– እጠብቅሻለሁ…አለ ጮክ ብሎ
(አዎ። ትጠብቀኛለህ።)

ያልመጣ ሽንቴን አልሸና ነገር። ሊፒስቲኬን አስተካክዬ እጆቼን ታጥቤ ወጣሁ። እዛው ቆሟል።
– የምር ጠበቅከኝ አይደል…..አልኩ አጠገቡ ስደርስ
– የእኔ ቆንጆ አንቺ ካልተጠበቅሽ ማን ይጠበቃል ታዲያ?

(እውነት ነው። እኔ ካልተጠበቅኩ ማን ይጠበቃል?)

ስልኬን ሰጥቼው ወደ ወንበሬ ተመለስኩ።

– ስልክሽ ሲጮህ ነበር አሉኝ።
አየሁት። ቦይፍሬንዴ አራት ጊዜ ደውሏል። አንድ ቴክስትም አለኝ። ቴክሰቱን ከፈትኩ።
– ቆንጅዬ ናፈቅሽኝ…ማታ አትመጪም?
ለመጀመሪያ ጊዜ መልስ ሳልሰጠው ስልኬን አስቀመጥኩና ሜላትን እያየሁ
– ማነው ስሙ ስልኬን የምትሰጪው ለጅ? አልኳት
– እንዴ…ያን ሁሉ ስለፈለፍ አትስሚም ነበር እንዴ…እንዴ ቆይ ደግሞ…ማንነቱን ሳታውቂ ነው ስልኬን ስጪው ያልሽኝ እንዴ? አለችኝ በመገረም።

(ከፈለገኝ ማንነቱ ምን ያደርግልኛል? ቆንጆ ናት- ስልኳን አምጡልኝ- ከኔ ጋር እንድትሆን ልልፋ- ልድከምላት ካለ እኔ ምን ቸገረኝ? )

– እ….ጫጫታው አላሰማ ብሎኝ ነው…አልኩና ዋሸሁ
– ቢኒያም ነው…ያ ዶክመንተሪ የሚሰራልን ልጅ…አለች ሜላት

ቢንያም ያሚ !
ከማማሩ ብዛት ቢሮ ውስጥ በአባቱ ስም የሚጠራው የለም። ሴቶቹ ሁሉ ቢንያም ያሚ ነው ምንለው። ቢንያም ጣፋጭ…..

ቢንያም ያሚ እኔን ፈለገኝ?…ከዛ ሁሉ ውበት መሃል እኔን መረጠኝ?

ቦይፍሬንዴ ደወለ።
ዘጋሁበት።

ጭካኔ ሊመስል ይችላል ግን ‹‹ማንም አይወደኝም- አስቀያሚ ነኝ›› ብላ ታስራ ትሰቃይ የነበረች የሴትነት ነፍሴን በአንዲት ቃል ከፈታት ወንድ ጋር ታስሬ መቆየት አልፈልግም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...