Tidarfelagi.com

ቅንጥብጣቢ የካናዳ ወግ

(የጉዞ ማስታወሻ)

የኢትዮጵያ…

በሀገሬ ለመኩራራት በየሄድኩበት ጉራዬን ከምነዛበት ነገር አንዱ አየርመንገዳችን ነው።

ስማችንን እና ባንዲራችን ይዞ ከደመና በላይ የሚበረው አየር መንገዳችን።

ቋንቋችንን ከቋንቋዎች ሁሉ አስቀድሞ ከየትም የአለም ጥግ የመጡ መንገደኞቹ ጆሮ የሚያስገባው አየር መንገዳችን።

“የአፍሪካ ሀገር አየር መንገድ በሰማያችን አይታይ፣ በአየራችን አይብረር፣ በምድራችን አይረፍ” ብለው የከለከሉት ምእራባዊያን ሀገሮች፤ ሰማያቸውን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሚያደምቅ፣ አየራቸውን እንጀራ እንጀራ የሚያሸት፣ በርበሬ የሚያጥን፣ ምድራቸውን በጠይሞቹ ኢትዮጵያውያን በኩራት የሚያስረግጠው አየርመንገዳችን።

ለዚህም ነው አንዳንዱ ነገር ባይጥመኝም፤ የሀገር ነገር ባይጥምም ጥም ይቆርጣል እና ከሌሎች አየር መንገዶች የኢትዮጵያን የምመርጠው።

ዛሬም አስራ ሶሰት ሰአት ለሚበላው የቶሮንቶ ጉዞዬ በደልቃቃው ድሪም ላይነር አውሮፕላናችን ተሳፍሬያለሁ። ጢም ብሎ ሞልቷል። ሰው የሌለባት አንዲት ትርፍ ወንበር፣ ሻንጣ ያልተወሸቀበት የአውሮፕላኑ ሻንጣ ቋት የለም። ጢም።

ረጅሙ ጉዞ አንደተጀመረ ከፊቴ ባለው ቴሌቪዥን ላይ ለምርጫ የቀረቡልኝ የመዝናኛ አማራጮች ቴሌቪዥኑን በጣቴ እየደነቆልኩ ማየት ጀመርኩ።

በሙዚቃ፤ ከአዴል እስከ ሃሊማ አብዱራህማን፣ ከ አቡሽ ዘለቀ እስከ አንጀሊክ ኮጆ፣ ከአብርሃም ገብረመድህን እስከ ሰማኸኝ በለው።

ከኮሜዲ ፊልም ከቢግ ባንግ ቲዎሪ እስከ የቻይና “ፊዚካል” ኮሜዲ ። ከወጥ ፊልም ደግሞ ከቤን ስቲለር እስከ ደበበ እሸቱ አዲስ ፊልም ተሰድሯል።

አስራ ሶስቱ ሰአት ሊያንሰኝ ነው።

የዘር ያንዘረዝር የለ! ሚዛን ደፋብኝ እና የደበበ እሸቱን አዲስ ፊልም “ቀያይ ቀንበጦች” ወይም“ ሬድ ሊቭስ”ን ከፈትኩ።

በአድናቆት ፈዝዤ፣ በደስታ ረስርሼ ባላለቀ እያልኩ አልቆብኝ ጨረስኩት።

መቼም የደበበ እሸቱ የትወና ብቃት ከዚህ እስከዚህ የሚባል አይደለም። የፊልም ፅሁፉ እፁብነት፣ ለመጨበጥ የማይከብደው ጭብጥ፣ የዝግጅቱ አስደማሚነት፣ የአጃቢ ተዋናያኑ ብቃት ተትቶ ማለት ነው።

የሚያሳዝነው ነገር ይሄን የመሰለ ድንቅ ፊልም በዚህች ሚጢጢ ስክሪን፣ በተመረጡ ጥቂት እድለኞች ብቻ መታየቱ ነው።

ብዙ ሰው ቢያየው እመኛለሁ።

እንዲህ እንዲህ …ቆነጃጅቱ አስተናጋጆች እንግዳ በሆነ እና “እሰይ ተሸሻሉ” በሚሰኝ ቅልጥፍና እና ትህትና ሲያበሉ እና ሲያጠጡኝ ቆይተው፣ የጣመኝን ፊልም ስጨርስ፣ ያልጣመኝን ሳቋርጥ፤ ከታምራት ንጉሴ ኦሮምኛ ወደ ትርሃስ ትግርኛ ፣ ከቴዎድሮስ ታደሰ ወደ ኒና ሲሞን፣ ከሲናትራ ወደ የከፋ ዘፈኖች እንደፌንጣ ስዘል፤ ረጅም ያልኩት ጉዞ አጥሮ ቶሮንቶ አረፍን።

……………

ራሴን “ጌይ ፓሪድ” መሃል አገኘሁት

……

በበነጋው፤ እንቅልፌ ተስተካክሎ ከተማውን ለማየት ከወንድሜ ጋር ወጣሁ። የኢሊባቡር ጫካን የሚስንቅ አረንጓዴነት እና ዛፋምነትን አቋርጠን ሹል እና ረጃምም ህንፃዎች ወዳሉበት “ዳወን ታወን ቶሮንቶ” ወሰደኝ።

ከባቡር ወርደን አስፋልት ስንወጣ ከዚህ በፊት የማውቀውን የጌይ ሰዎች ሰንደቅ አላማ፤ አንዴ ትልቅ አንዴ ትንሽ ባንዲራ፣ አንዴ ገምባሌ፣ አንዴ ፊኛ፣ አንዴ ቁምጣ፣ አንዴ ቦርሳ፣ አንዴ ኮፍያ፣ አንዴ ደግሞ መነፀር ሆኖ ከመቶ የማያንሱ የሚተራመሱ ሰዎች ላይ አየሁት።

ደንገጥ ብዬ፣ “የት ነው ያመጣኸኝ…ይሄ ምንድነው?” አልኩት።

ከአሰር አመት በላይ ቶሮንቶ የኖረው ወንድሜ ቅምም ሳይለው ፤“ ኦህ…ረስቼው! ይሄ ወር የጌይ ፕራይድ ወር ነው። ዛሬ ፓሬዳቸው ነው…” አለኝ።

“ጌይ ፕራይድ?” መልሼ ጠየቅኩት::

“አ…አዎ…እዚህ ሀገር በየአመቱ ጌይ ፕራይድ ወር አለ….አንዱ ቀን ደግሞ እንደህ ያለ ሰልፍ ይወጣሉ…ጌይ ፓሬድ ይሉታል” አለኝ፡:

“ማለት…በጌይነቴ እኮራለሁ ምናምን ብለው ማለት ነው?”

“አዎ” በአጠገባችን የሚያልፉትን ሰዎች መንገድ እንዳንከለክል እጄን ይዞ ወደ አንዱ ጥግ እየወሰደኝ መለሰ።

“ቆይ…ካናዳ ጋብቻቸውን እንከዋን ከፈቀደች ከአስር አመት በላይ ሆኖ የለ…?ይሄ ሁሉ ጋጋታ ምን አስፈለገ?” እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ “ጥንዶችን” እያየሁ ጠየቅኩት።

“ብዙ ብር አላቸው…አድቮኬሲ ነገር ነው…በዛ ላይ እንደ ቶሮንቶ ባህል ነው ሚቆጠረው አሁን..አለ አይደል…እንደ በአል”

“እና በየአመቱ ተገናኝተው እመት አመት ያድርሰን ተባብለው ነው የሚለያዩት በለኛ! ለመሆኑ ለአመት በአሉ ማን ማን ነው የሚጠራው?” አልኩት::

“ሁሉም ይመጣሉ…ጌይ ያልሆነውም ሰው ይመጣል…ለድጋፍ…አሁን ትዝ ሲለኝ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይመጣል…አለ መሰለኝ ኦሮዲ…”

“እኔ ምልህ”

“እ…?”

“እነዛ ሱቆች፣ ባንኮች፣ ቡቲኮች፣ ላይብረሪው…በሙሉ የነሱን ባንዲራ የሚያውለበልበው ለዚህ ነው?”

“አዎ…እንደዛ ካላደረጉ ቢዝነሳቸውን ቦይኮት ያስደርጉባቸዋል…በጣም ሀይለኛ ብር አላቸው…በጣም ጉልበት አላቸው”

ወቸ ጉድ!

ሃያል የምእራብ ብራም ባንክን እጅ የሚጠመዝዝ የብር ጉልበት።

አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከአንድ ሚሊዮን አንድ ስራው አስነስቶ እያክለፈለፈ ዳወን ታወን የሚያመጣ የፖለቲካ ጉልበት።

እነሱን የማይደግፍ ንግድን በሰአታት ውስጥ የሚያሽመደምድ ማህበራዊ ጉልበት።

በጊዜ ቆይታም እንደተረዳሁት ፤ ኢትዮጵያውያን ወላጆችን ልጆቻቸውን ፍፁም ካናዳዊ አድርጎ በማሳደግ እና በኢትዮጵያዊ ወግ በማሳደግ መካከል ሰንጎ የሚይዝ ፣ ታላቅ ፈተና የሆነ ጉልበት።

“ እህ…እና ይቆያሉ ብዙ ሰአት…?ማለቴ እዚህ” አልኩ እንደ መተከዝ ብዬ።

“አዎ የተወሰነ ሰአት…በሌላ መንገድ አቋርጠን መሄድ ግን እንችላለን…የደበረሽ መሰለኝ…” አለኝ ዞር ብሎ እያየኝ።

“ወይ ታሪክ…!ግዴለም ትንሽ ልይ እስቲ.. ” ብዬ ሳልጨርስ በሕይወት እስካለሁ ልረሳው የማልችለውን ትእይነት አየሁ።

ህጻናት ሴት ልጆቻችን ልደታቸውን ሲያከብሩ ፣ ወይ ደግሞ ሰርግ ላይ ሻማ ያዥ ሲሆኑ የሚለብሱት በልማድ “የሙሽራ ቀሚስ” የምንለው አንዳንዴ በሮዝ አንዳንዴ በነጭ ቀለም የሚመጣውን ቡፍ ያለ ላባ መሰል ነገር ያለውን ቀሚስ ታውቁት የለ?

ሚጢጢ ሴት ልጆች እሱን ቀሚስ ሲለብሱ፣ ፀጉራቸው ባይበጠርም፣ ንፍጣቸው ቢዝረበረብም፣ አመዳም ቢሆኑም፣ ጣፋጭ ይሆኑ የለ?

አንድ እድሜው አርባ የሚሆን ባለ ብዙ ጡንቻ ወንድ እሱን ቀሚስ በሮዝ ቀለም ለብሶ፣ ልጥፍ ጫማ አድርጎ ሰዉን ሁሉ በፈገግታ “ሀይ…ሃፒ ፓሬድ!” እያለ በአጠገቤ ሲያልፍ አየሁ።

የሎጥ ሚስትን የሆንኩ፣ በሰው ሀገር የጨው አምድ ሆኜ የቀረሁ መሰለኝ።

ከድንዛዜዬ ስነቃ፣ ወደ ወንድሜ ዞር አልኩና፤ “አቋራጩ መንገድ በየት በኩል ነው?” አልኩት።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...