Tidarfelagi.com

ቅንጥብጣቢ የካናዳ ወግ (ክፍል ሁለት)

የቶሮንቶ የህዝብ ጎርፍ ገባሩ ብዙ ነው። አለም አቀፍ ነው።

የአባይ ልጆች።
የቀይ ባህር ልጆች።
የአትላንቲክ ዳር ልጆች።
የህንድ ውቅያኖስ ልጆች።
የጥቁር ባህር ልጆች…

ጎላ ድስት የሆነ ከተማ ነው። ካርታ ላይ የሌለ ሀገር እዚህ ሀገር አውቶብስ ውስጥ ተሳፍሮ ይገኛል።
በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ የሚናገሩት “አደጋ ላይ የወደቀ” ልሳን በቶሮንቶ ባቡሮች ላይ ይሰማል።

ኢትዮጵያውያን ከነ አማርኛቸው፣ ከነኦሮምኛቸው፣ ከነትግርኛቸው፣ ከነወላይትኛቸው፣ ከነ ጉራጊኛዋ፣ ከነ ሱማሊኛቸው….፣
ከነቅላታቸው፣ ከነ ጠየምነታቸው፣ ከ ነጥቁረታቸው፣
ከነ ሰልካካነታቸው፣ ከነ ጎራዳነታቸው፣
ከነ ዞማ እና ከነ ኪንኪ ፀጉራቸው፣
ቶሮንቶን ያደምቋታል።

ጠንክረው ይሰሩባታል።
ለፍተው ይማሩባታል።
ጥገኛ ተህዋስያን ሆነው ደጉን መንግስት ይቦጠቡጡቧታል።
ፖለቲካ ያፋፍሙባታል።
መፅሀፍ ይፅፉባታል።
ዳንኪራ ይረግጡባታል።
ባንዲራቸውን ያውለበልቡባታል።
ቤተክርስትያን ይሳለሙባታል።
መስጅድ ይረግጡባታል።

ሁሉን ይሆኑባታል።

ዲያሰፖራ ብዙ አይነት ነው። ቡራቡሬ ነው። “ዲያስቡራቡሬ” እንዲል አዳም ረታ።

ቅዠታም አለ። ባለህልም አለ።
ባንዲራውን ማየት የሚያሰለቅሰው አለ። ባንዲራውን ማየት የሚያስመልሰው አለ።
ስለማያውቀው የሚቀባጥረው፣ ስለሚያውቀው ትንፍሽ የማይለው።
ሀገሩ የራበችው ምድሩ የጠማችው፤ ሀገሩን “ሀክ እንትፍ!” ብሎ የተወው፣
ብዙ አይነት ነው።

ዲያስፖራ ደግ ነው። ዲያስፖራ ክፉ ነው።
ሀበሻ እያሳደደ የሚያቅፍ፣ ሀበሻ እያሳደደ የሚያደናቅፍ።
“ዛሬም ናና ከረሜላ አለ?” ብሎ የሚጠይቅ
ስለ አረንቻታ ጠርሙስ የሚያትት፣
ቀልድ ልንገርሽ ብሎ…
“ሹፌር ትወዳለች መባሉን ሰምቼ፣
ሞቼልሽ ነበረ ብስክሌት ነድቼ” ብሎ ከንጉሱ ጋር የወደቀ ቀልድ ነግሮ ራሱ ፍርፍር ብሎ የሚስቅ።

እትብቱ እና ልቡን ኢትዮጵያ ትቶ በባዶ ቀፎ ላይ ታች የሚል፣
የአለበትን ሀገር መስሎ ባለበት ሀገር የሚኖር።

ብዙ አይነት ነው ዲያስፖራ።

አርረውም ያልበሰሉ፣
ምድረ በዳ አንጎሎች፣ የእድሜ ሽማግሌዎች
የሃሳብ ጮርቃዎች

የእንጨት ሽበቶች አሉ።

እነኚሆቹ ያቅራሉ።
ይልጋሉ።

አለኝታ ሊሆኑ ሲችሉ የትም ባክነው የቀሩ፣
በሀሳብ የመጠቁ፣ በተግባር የበረቱ፣
መሄዳቸው ሀገሬን ያጎደላት፣
ህዝቤን ያስቀረበት፣
አሉ።

እነኚኞቹ ይጥማሉ።
አነኚኞቹ ያስቆጫሉ።

“አንዱን ባለስልጣን በስናይፐር የማትሉት…”

“ለምን አንዱን የወያኔ ባለስልጣን በስናይፐር አትሉትም….?”አለኝ አንዱ- አንድ አበሻ ምግብ ቤት ቁጭ ብለን ወሬያችንን ስናደራ፡
“እ..?” አልኩ እጠጣው የነበረው ሻይ ትን ሊለኝ እየታገለኝ።
ደገመልኝ።
“ወያኔን እኮ እሹሩሩ የምትሉት እናንተው ናችሁ። አንዱን በስናይፐር ብትሉት ፈርክስክሱ ይወጣል” ጮክ ብሎ ተናገረኝ።
ግርምቴን በቀዘቀዘ ሻዬ አወራረድኩና፤

‹<እህ…እናንተስ?” አልኩት::
“እ…?” አለ በተራው::
“እናንተስ…?ማለቴ እናንተ ለምን አትሉትም?”
“እኛማ ሩቅ ነን። እንዴት ብለን….?” ወንበሩ ላይ አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደ ቀኝ እያለ መለሰልኝ።

“የእኛንስ መቅረብ ማን ነገረህ?” አልኩት ትኩር ብዬ እያየሁት።
“ቀልዱን ተይ…እውነቴን ነው። ወኔ ያለው ሰው ጠፋ እንጂ ወያኔ እኮ እንኳን 25 አመት 5 አመት አትቀመጥም ነበር….ጣልያንን እንኳን ያኔ መሳሪያ በሌለን ዘመን ይህን ያህል አላስቀመጥነውም”
“ይቅርታህን እና ጣልያን ፤ ውስጥ ባሉ አርበኞች እንጂ ሰሜን አሜሪካ ተቀምጠው በል በል ባሉ ሰዎች የተባረረ አይመስለኝም…ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ከመጣ መምጣት የሚችለው ውስጥ ባለው ሰው ነው። ..ሌላው እንኳን…” ብዬ ሌሎቹን ሰዎች መመልከት ጀመርኩ።
ዝም አለ።
ፀጥታው እና ትርጉሙ ያስፈራቸው አብረውን የተቀመጡ ሌሎች ሰዎች ሌላ ወሬ እያነሱ ለመጣል ቢሞክሩም በአጭር አተካራችን የፈጠርነውን ድባብ ሊያሸንፉት አልቻለም።
ብዙ ሳይቆይ መለስ አለና፤
“በነገርሽ ላይ ውጪ ያለ ሰው…ዲያስፖራ ለሀገሩ ለውጥ ማምጣት አይችልም ይሉት ድምዳሜ የእውቀት ማነስ ነው” አለኝ።

“እንዴት” ሳልቀየም ጠየቅኩ።

“እዚህ ሆኖ ውስጥ ያለውን ማነቃቃት፣ እዚህ ሆኖ ስለሀገሪቱ ሁኔታ ለአለም መንገር ስራ አይደለም…?አያግዝም?”
ረገብ አልኩ።
“እሱ ልክ ነህ…ግን ያ ሚና …ውስጥ ግንባሩ እና ደረቱን ሰጥቶ ከሚታገለው ሰው ጋር ሲወዳደር ምንም ነው። ያም ሆኖ ሀገር ውስጥ ባለው ህዝብ ላይ ለመመፃደቅ የሚያበቃ ሚና አይደለም…እዛ ሆኖ እናንተ የምትሉትን የሚል ሰው አነሰም በዛም የትግሉ እሳት ውስጥ ነው። …እናንተ እኮ ባብዛኛው የትግሉ ጭስ ያባረራችሁ ናችሁ…አንዳንዴ ሳሰበው….” አልኩና ድንገት አቀምኩ።
“አንዳንዴ ስታስቢው ምን…?”
“እ..ላስቀይምህ አልፈልግም…ምሳችንን በሰላም እንብላ”
‹<ኖ…ኖ…ጨርሺው…አንዳንዴ ስታስቢው ምን?”
“አንዳንዴ ሳሰብው የብዙዎቻችሁ ነገር እዚያ ያለው ደሃ ይታገል ይታገል እና እንዲለወጥ የምንፈልገው ስርአት ሲወድቅ ገብተን አዲስ መንግስት እናቆማለን ነገር ነው…ከመሞት መሰንበት ላይ የተመረኮዘች ብልጣብልጥ ዘይቤ ትመስለኛለች….” አልኩኝ ፊቱን ለስሜት ለውጥ እያጠናሁ።
ዝም አለኝ።
ብዙም ሳንቆይ እኔም እሱም የሌለብንን ቀጠሮ አለብን ብለን ቡድኑን ከበተንን በኋላ ተበታተንን። ነገሩ ግን ሲነዘንዘኝ አመሸ።

እርግጥ ነው፤ሀገራቸው ሆነው ለለውጥ ሲተጉ ወንጀል እንደ ጥብቆ በልካቸው እየተሰፋላቸው፣ እጣቸው ወይ እስር ቤት ወይ ስደት በመሆኑ ሳይወዱ በግድ ሀገራቸውን፣ ትዳራቸውን፣ ልጀቻቸውን፣ ሕይወታቸውን በቅጡ ሳይሰናበቱ የተሰደዱ ብዙ አሉ። በነዚህ ላይ ፍርድ ለመስጠት አይቃጣኝም።
እኔን የሚከክነኝ ግን …“ስናይፐር” ወይ “ጨረር” ተጠቅሞ ባለስልጣናት ለምን አይገድልም ብሎ በስንቱ የሚታሸውን ህዝብ፣ አየተበደለ በመንግስት አንቀልባ ላይ እንቅልፉን እንደሚለጥጥ ጨቅላ ማየቱ ነው። መስቀሉ የበዛን ህዝብ በአንድ አረፍተነገር ማንቋሸሹ ነው።
ይህ ደግሞ አሳምነው ገብረወልድ እንዳለው “ለአብዛኛው (ዲያስፖራ) ኢትዮጵያ ማለት ካርታዋ፣ ባንዲራዋ እና የባህል ልብሷ” መስሎ መታየቱ ነው። ስለዘንድሮ ኢትዮጵያዊነት ግንዛቤ ማጣት ነው። ጠልቆ አለመግባት ነው።
(አብዛኛው ዲያስፖራ) “ሙሾ የሚያወርደው ለዚህ ምስል እንጂ ከምስሉ ባሻገር ላለው የእለት ተእለት የወገኑ ኑሮን በማወቅ፣ በመቆርቆር አይደለም።
አብዛኛው ነገር ከከበሮ ድለቃ፣ ከድንፋታ እና ከእርግማን አይዘልም። እዚህ ያለውን መንግስት መኮነን ወይ መርገም ብቸኛው የኢትዮጵያዊነት ምልክት ስለሆነ ሁሉም በእውር ድንብር ዘው ይልበታል።

“እንዴት ናችሁ?” ብሎ የሚጠይቅ
ተደራጅቶ የሚያደራጅ
ነቅቶ የሚያነቃ
ግን የለም። ቢኖርም አይዘልቅም።

“ኤርትራ የማን ናት?”

በአንዱ የኳስ ጨዋታ ቀን፤ በብዙ አይነት የአንድ ኢትዮጵያ ባንዲራዎች ባሸበረቀው ሰታዲየም ቁጭ ብያለሁ።

ኳሱ ከመጀመሩ በፊት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ቀሚስ የለበሱ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቲሸርት ያጠለቁ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የእጅ አምባር እና የጆሮ ጌጥ ያደረጉ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሻሽ ሸብ ያደረጉ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኮፍያ ያጠለቁ…እንደው ባጠቃላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ብቻ የሆኑ ሰዎች ሲተራመሱ አያለሁ።

በቆይታዬ ያየሁት ሌላ ነገር ይሄ ነው።
አንድ ነገር የኢትዮጵያን ባንዲራ ከያዘ ልቡ የማይጨክነው ዲያስፖራ ለፍቶ ያገኛትን ዶላር ያለርህርሄ ይገብራል። የማይፈልገውን ዣንጥላ ይሸምታል። ደግሞ የማይለብሰውን ኮፍያ ይገዛል። ቤት የሚጥለውን ቁልፍ ማንጠልጠያ ሰፍ ብሎ ይወስዳል።
ለባንዲራው ባለው እውር ፍቅር ለብልጣብልጥ ነጋዴዎች ሲሳይ ይሆናል።
በዚህ ሁሉ ግርግር መሃል ፤ ከፊት ለፊቴ ያለው መቀመጫ ላይ አንድ ለየት ያለ የአንገት ልብስ የያዘ ጎልማሳ ሰውዬ አየሁ። ፅሁፍ አለው። ለማንበብ ጓጉቼ ጎንበስ ስል እና ቀና ብሎ ሲያየኝ አንድ ሆነ።
“ይቅርታ…ፅሁፉን ለማንበብ እየሞከርኩ ነበር” አልኩት አፍሬ።
“ይሄው እይው…“ይህች ናት ሀገሬ!” ነው የሚለው” አለኝ በፍፁም ኩራት።
ተቀበልኩት እና አየሁት።
እንዳለው “ይህች ናት ሀገሬ!” የሚል ፅሁፍ ሲኖረው ከኤርትራ መቆረጥ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ካርታንም ይዟል።
“ሆ ሆ” አልኩኝ ሳላስበው።
ሰውየው በፍጥነት “ምነው…ችግር አለ?” አለኝ እንደመቆጣት ብሎ። ድምፅ ማውጣቴን ያወቅኩት ያኔ ነው።
‹…እ…አረ የለም…እንካ ስካርፍህን…አመሰግናለሁ” አልኩ የአንገት ልብሱን መልሼ እየሰጠሁት።
“ታዲያ ምንድነው ሆሆው …?” አለኝ አሁንም እንደተቆጣ
“አይ…ምንም አይደለም አልኩ እኮ”
“ምነው ሀገርሽ ይቺ አይደለችም?”
‹< እንዴ…እንደዛ ማለቴ አይደለም…” ነገሩ መካረሩ አሳሰቦኝ መለስኩ።
“ታዲያ ምንድነው…?”
“እንግዲህ…ኤርትራን ያካተተ ካርታ ሳይ ነው…ማለቴ ካርታው ልክ አይደለም…”›
“ስሚኝ እህት…የእኛ ሀገር እስከ ቀይ ባህር ነው። ድንበራችን ያ ነው። ወያኔ ነሽ መሰለኝ…!.” ይሄ ሰውዬ ይሄን የኳስ ሜዳ ቦክስ ሳጥን ሊያደርገው ነው እንዴ!
‹ስማኝ የኔ ወንድም፣ ኤርትራ ከተገነጠለች 25 አመት ሞላት። የፈሰሰ ባህር አይታፈስም” አልኩት እልህ ተጋብቼ።
አይኔን ቢያፈሰው ደስ ይለው ይመስለኛል። ግን አብራኝ የነበረችው ጓደኛዬ እጄን እየጎተተች ከቦታው አራቀችኝ። የማልሰማውን ነገር ሲያጉተመትም እየሰማሁ ራቅን።

የዚህ ሰውዬ ሁኔታ ሳይለቀኝ…በነጋታው ማታ የአስቴር አወቀን ኮንሰርት ስንገባ ወንዲ ማክ የተባለ ወጣት ዘፋኝ በየዘፈኑ መሃል “ኤርትራ የማናት?” እያለ ለኮንሰርት የመጣውን ሰው ፖለቲካዊ ጥያቄና መልስ ሲያቀርብለት አመሸ።

“ኤርትራ የማናት?” ይላል በ“ባለ አደሷ ነይ” ዘፈኑ መሃከል።
“አስመራ የማናት?” ይላል“ኢትዮጵያ” በሚል ሙዚቃው ማብቂያ ላይ።

ገሚሱ ሰውም፤ “የእኛ ናት…!” እያለ፣ የያዘውን እየተጎነጨ በደስታ ይመልሳል።

ሊገለጥልኝ ያልቻለ ሚስጥር ነው።

ጅማ ባለበት፣ አዳማ ባለበት፣ ባህር ዳር ባለበት፣ ሶዶ ባለበት፣ አሶሳ ባለበት…ብዙ አገር ባለበት፣ ጥላን ከሄደችው አስመራ ጋር የሚያቆራኘን ስሜት ሊገባኝ ያልቻለ ሚስጥር ነው።
ካሁን ወዲህ፤ በፖለቲካ ሳይሆን በጂኦሎጂአዊ እንቅስቃሴ ሊመለስ ከሚችለው ቀይ ባህር ጋር የሚያጣብቀን ስሜት ሊገባኝ ያልቻለ ሚስጥር ነው።
ኢትዮጵያን እንደ ዶሮ አስራ ሁለት ቦታ ከፋፍሎ የእያንዳንዱ አጤ ገዢ ካልሆንኩ እያለ የሚፎካከረው አብዛኛው ዲያስፖራ፣ ከኤርትራ ጋር ያለው ፍፁማዊ ፍቅር ሊገባኝ ያልቻለ ነገር ነው፡
(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...