Tidarfelagi.com

ቅንጥብጣቢ የአስመራ እና ምፅዋ ወግ

አስመራ- ከተወራላት በላይ የምታምረው ከተማ

‹‹እናት ብዙ ሻንጣ የለሽም አይደል? እባክሽ ይህቺን ስኳር ያዢልኝ? የእኔ እህት….ኪሎ በዝቶብን ነው…ይህችን ቡና ትይዥልኛለሽ?….እመቤት… ያንቺ አልሞላም አይደል…እባክሽ እነዚህን ጫማዎች ያዢልን…›› እያሉ ብዙ ሰዎች ያዋክቡኛል። ቦሌ አየር ማረፊያ አስመራ የሚወስደኝን አውሮፕላን ለመሳፈር ሻንጣ ማስረከቢያው ጋር ቆሜያለሁ። የማንን ወስጄ የማንን እንደምተው ለመወሰን ስቸገር ትርምሱ ይበልጥ ባሰ። ብዙ ላስቲክ ንብርብር እንጀራዎች፣ የቆዳ ጫማዎች እና ጃኬቶች፣ ቅንጡ የአበሻ ልብሶች፣ ቡና፣ ስኳር፣ በላውንደሪ ላስቲክ የተጠቀለለ ከነመስቀያው ያለ ሙሉ የወንድ ልብስ….እቃ በአይነት አይነት ካንዱ ሻንጣ ተቀንሶ ሌላው ውስጥ በግድ ይጠቀጠቃል። በሃይል ይጎሰራል። ይተርፋል። ደግሞ ይወጣና ወደሌላ ሻንጣ ይወሰዳል።

ምንድነው ይሄ ሁሉ ሸክም?

ሻንጣዬን ካስረከብኩ በኋላ ተራዬ ደረሰና የኢሚግሬሽን መስኮቱ ጋር ፓስፖርቴን ሰጥቼ ቆምኩ።
– አስመራ ነው የምትሄጅው? አለችኝ ሚጢጢዋ ክፍል ውስጥ የተቀመጠችው የኢሚግሬሽን ሰራተኛ፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ትህትና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ጭራሹን ይህችን ማህተም የመምታት፣ ፎቶ የማንሳትና ፓስፖርትን የመመርመር አፍታ በ ትንንሽ ጨዋታ ወደ መሙላት ፍላጎት አድጓል።
– አዎ አልኩኝ ቶሎ ብዬ
– ዘመድ አለሽ እዛ?
– የለኝም።
– እና ዝም ብለሽ?
– አዎ…ለጉብኝት…የድሮ ሃገራችን አይደል ብናየው ደስ አይልም?
– እሱስ ደስ ይላል…

የሂጂ ማህተም ተመቶልኝ አለፍኩ። አስመራን ልጅ ሆኜ በአባቴ ወሬ፣ አደግ ብዬ በበአሉ ግርማ ኦሮመይ፣ አሁን አሁን ደግሞ በቴሌቪዥን እንጂ ረግጫት አላውቅም። ግን አውቃት ይመስል፣ ዘመድ ያለኝ ይመስል ሌላ ቦታ ስሄድ ከሚኖረኝ ስሜት የተለየ ስሜት እያስተናገድኩ ነው። በአብዛኛው ጉጉት ነው። የበአሉ ግርማ አስመራ እንደ ጠበቅኳት አግኝቻት ታስደስተኝ ይሆን ወይስ ከግምቴ አንሳ ቅር ታሰኘኝ? በአንድ ሰአት ተኩል ውስጥ አውቃለሁ።
—-
አስመራ አለም አቀፍ አውሮፕላን ከማረፋችን እልልታው ቀለጠ።
እልልታው ዛሬም ከአመታት በኋላ ከዘመድና ወዳጅ ጋር ለመገናኘት የቋመጡ ሰዎች መሳፈራቸውን ነገረኝ። ከአውሮፕላን ስወጣ ደስ የሚያሰኝ ነፋሻማ አየር ተቀበለኝ። የአስመራ አየር ማረፊያ ትንሽና በዘመናዊነት ስሌት ቢታይ ሚዛን የማይደፋ ነው። ግን ንጹህ ነው። ተሳፋሪዎች ኢሚግሬሽን በር ጋር ደርሰን ሰልፍ ልንይዝ ስንል ሁለት ወጣት ሴቶች ፓስፖርት እንድንሰጣቸው ጠየቁን። ሰጠን። አንደኛዋ ባዶ ገፅ ፈልጋ ማህተም ስታደርግ ሌላኛዋ ደግሞ በእስኪብርቶ ቀን እና ሌላ ነገር ፅፋ ፈረመችበት። ፓስፖርቴ ሲመለስልኝ ከፍቼ አነበብኩት። ‹ለአንድ ወር እንድትቆይ ተፈቅዶላታል‹ ይላል።

ቪዛዬ ይሄ ነው? ለቪዛ እንደማንከፍልም እንደማንጉላላም ቢነገረኝም ይሄን ያህል ይቀላል ብዬ አልገመትኩም ነበር። በቅለቱ ተገርሜ ወደ ፊት ገስግሼ ልሄድ ስል ቀድመውኝ ከሄዱ ሰዎች ጀርባ እንድሰለፍ ተነገረኝ።

ተሰለፍኩ።

ሰልፉ አይሄድም።

ብዙ ደቂቃዎች አለፉ።

ሰልፉ አሁንም አይሄድም።

ከ20 ደቂቃ በላይ ከቆምኩ በኋላ ተራ ደረሰኝና ከመስታወት ጀርባ ለተቀመጠችው ሌለ ወጣት ሴት ፓስፖርቴን አስረከብኩ። ቀና ብላ አየችኝና ፓስፖርቴን ከፍታ ምልክት የተደረገበትን ቦታ መፈለግ ጀመረች።
ወዲያው ፊት ለፊቷ በተቀመጠው በፕላስተር በተለጠፈ ኮምፒውተር ላይ በግራ እጇ ፓስፖርቴን ከፍታ እንደያዘች በቀኝ እጇ አንድ አንድ ፊደል እየለቀመች ቀስ ብላ መተየብ ጀመረች።

ጉጉቴን አልተረዳችም። ተቁነጠነጥኩ።
ቃ–ቃ….ቀና ብላ እይት…ቃ….ቃ….ቀና ብላ እይት…ቃ…ቃ….ፓስፖርቴን እይት።

ዘልአለም የቆምኩ መሰለኝ።

ምንድነው ይሄን ሁሉ ሰአት የምትፅፈው? ለምን በሁለት እጆችዋ አትፅፍም? ሃሳቤን ሳልጨርስ ድንገት ቀና አለችና ቶሎ ቶሎ በትግርኛ ታወራኝ ጀመር።
‹‹ሕይወት….xxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxx?….››ከስሜ በስተቀር አንዲት ቃል አልያዝ ብሎኝ እንደ ቂል ዝም ብዬ አያታለሁ።

– ትግርኛ አልችልም እናት…አልኩ እና አቋረጥኳት።
የሚያምር ፈገግታ ፈገግ አለችና….
– ካዲሳባ ነው? አለችኝ።
– አዎ…ካዲሰባ…አልኩ ደስ ብሎኝ።
– የት ነው የምትገቢው? አማርኛዋ ይጣፍጣል።
– አስመራ…አልኩ ቆፍጠን ብዬ…
– አይደለ….ዘመድ አለ ወይስ ሆቴል?
– እ…ዘመድ የለም። ሆቴል። ሆቴል ነው ምገባው።

ጎንበስ አለች። እንደገና ልትተይብ ነው?

ቃ–ቃ….ቀና ብላ እኔን እይት…ቃ….ቃ….

አሁንም ድንገት ፓስፖርቴን እንደያዘች ተነሳችና ከጀርባዋ ያለችውን ትንሽ በር ከፍታ ሄደች።

እንዴ? ምንድነው ነገሩ?

ሁለት ደቂቃ ቆይታ ተመለሰችና እንደገና መተየብ ጀመረች።

አዬ! ማደሬ ነው።

ሌሎች ሰልፎች እየተንቀሳቀሱ ይሆን ብዬ ግራና ቀኝ አየሁ። ያው ነው። ሌሎቹ መስኮት ውስጥ ያሉት ሴቶችም እንዲሁ ፓስፖርት ይዘው ሲወጡ አየሁ። ቆይቶ ክፍላቸው ውስጥ ፓስፖርት ስካን የሚያደርጉበትም ሆነ ሌላ መሳሪያ ስለሌለ ለፎቶ ኮፒ ወይ ስካን ለማድረግ እንደሚሄዱ ገመትኩ።

ጉልበት በሚቆጥብ አኳሃን ቆሜ ሳለ ማህተሟ ጓ! ሲል ሰማሁ።

በመጨረሻ ግቢ ተባልኩ።
– አመሰግናለሁ አልኳት ፈገግ ብዬ።

እሷም ፈገግ ብላ ‹‹ መልካም ጊዜ! ›› አለችኝ።

ከአውሮፕላን ማረፊያው ስወጣ አየሩን በረጅሙ ሳብኩ። አዲስ ሃገር ስሄድ የከተማውን ሽታ ለማወቅ የማደርገው የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ ከተሞች አበባ አበባ ይሸታሉ። አንዳንድ ከተሞች ቅመም ቅመም ይሸታሉ። አንዳንድ ከተሞች ባህር ባህር ይሸታሉ። አንዳንድ ከተሞች ደግሞ ብዙ አይነት ነገር ይሰነፍጣሉ።

አሰመራስ? አስመራ ንፁህ ንፁህ ነው የምትለው። ንፁህ ንፁህ ብቻ። አብርሃም አፈወርቂ አስመራ ፃእዳ እያለ ሲዘፍን ውሸቱን አልነበረም። አስመራን ያየ ሁሉ ስለንፅህናዋ አውርቶ የማይጠግበው አለነገር አይደለም ብዬ ገመትኩ።

ስሜን ይዞ ይጠብቀኛል ያልኩት ሰው መዘግየቱን ያወቅኩት ንፁሁን ሽታ ምጌ ምጌ ስጨርስ ነው። የት ሄደ?
በምሽት በሰው ሃገር ለማን ትቶኝ ሄደ?

አስር ደቂቃ በላይ ጠብቄው ሲቀርብኝ አንዱን ወዲህ ወዲህ የሚል ረጅምና ቀይ ወጣት ጠጋ ብዬ
– ይቅርታ…አማርኛ ትችላለህ? አልኩት
– ሰላም እህቴ…አዎ እችላለሁ…ምን ላግዝሽ ? አለኝ ቅልጥፍጥፍ ባለ አማርኛ።
ጎሽ!
– ታክሲዬ ቀረብኝ…ስልክ ትደውልልኛለህ? አልኩት በማስተዛዘን።
– ምን ችግር አለ? ቁጥሩን አምጪ…አለኝ ቶሎ ብሎ።
ቁጥሩን ሰጥቼው ስልኩን የሚስጥር ቁጥር ሲያስገባ የስልኩ ስክሪን ሴቨር የጠቅላይ ሚንስትሬ ፎቶ መሆኑን ሳይ ፈገግ አልኩ።
ደውሎ በትግርኛ ሲያወራ የሚለውን ለመገመት እየሞከርኩ አየዋለሁ።
ኢትዮጵያ ትግርኛ ትንሽ ትንሽም ቢሆን ይገባኛል ብዬ አስብ ነበር። የኤርትራው ይለያል ልበል?
ጨርሶ ዘጋ።
– እ? እየመጣ ነው? አልኩት
– አዎ…ትንሽ ዘግይቶ ነው…ይመጣል…ያዲሳባ ልጅ ነሽ? አለኝ
– አዎ…
– አዲስ እንዴት ናት?
– ምንም አትል አልኩ የሰሞኑን ነገር እያሰብኩ…
– እኔ አዲሳባ ነው የተወለድኩት…አለኝ ቶሎ ብሎ
– ተው ባክህ! የት አካባቢ? በጉጉት ጠየቅኩት
– ቄራ! ጦርነቱ ሲመጣ ነው እዚህ የመጣሁት…
– ፐ! ታዲያ አሁን አትመጣም?
– አዎ እመጣለሁ…ገንዘብ እያጠራቀምኩ ነው። አለኝ ወደ ቢጫ ታክሲ መኪናው እያሳየኝ። ዘናጭ ሁንዳይ ናት።
ሳቅ ብዬ ዝም ስል
– ኤረፖርት ስራ የሚደርሰን በሁለት አመት አንዴ ነው….ስራ ስላለኝ ተቼሽ ልሄድ ነው ይቅርታ….አለኝ
ግር አለኝ።
– በሁለት አመት አንዴ? ለምን? አልኩ ሳይነግረኝ እንዳይሄድ ተጣድፌ
– ዘጠኝ መቶ ምናምን መኪና ነው ያለው…ብዙ ስራ ስለሌለ በሁለት አመት ነው ሚደርሰን…ለአስራ አምስት ቀን…ቆይ.. መጣሁ አንዴ….

ሄደ።

ባለፈው የቦሌ ቢጫ ታክሲዎች በሳምንት ሁለቴ ስሩ ሲባሉ ለአቤቱታ ኢቲቪ መሄዳቸውን አስታውሼ በንፅፅሩ ተገረምኩ።

ከሌላ 10 ደቂቃ በኋላ ፊልሞን መጣ። ፊልሞን አስመራን ሊያሳየኝ የተዋዋልኩት ወጣት ነው።
ስለመዘግየቱ ይቅርታ ጠይቆኝ በቀይ መርቼዲሱ ፍስስ እያልን ወደ ከተማ ገባን።

አስመራን በጭለማ ተዋወቅኳት። ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶቿን፣ ሶቶ ተያይዘው የሚሄዱ ጥቂት ወጣት ፍቅረኞቿን፣ መንገድ ላይ በዝተው የሚታዩ ባለ ከዘራ አዛውንቶቿን፣ ሰፋፊ ሻማ ቀሚስና ነጠላ ለባሽ አሮጊቶቿን፣ ብዙ ቢጫ ታክሲዎቿን፣ ቀይ አውቶብሶቿን እና እነዛ ዝነኛ ዘምባባዎቿን ለመጀመሪያ ጊዜ አየኋቸሁ። ነግቶ በብርሃን እስካገኛቸው በጭለማ ተዋወቅኳቸው።

ቅንጥብጣቢ የአስመራ እና ምፅዋ ወግ (ክፍል ሁለት)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...