Tidarfelagi.com

ቅንጣቢ የምፅዋ ወግ

‹‹የት ነው የሚሄደው? ›› ይሉኛል መአት ሰዎች እየተፈራረቁ። በትግርኛ ነው የሚጠይቁኝ። በግምት ነው የምመለሰው።

ከንጋቱ 11.45 ላይ አስመራ አውቶብስ ተራ ላይ ያረጀ ኮሰተር አውቶብስ ውስጥ ብቻዬን ተቀምጬ ሲያገኙኝ ሌላ ምን ሊጠይቁኝ ይችላሉ?

ከአዲስ አበባ አውቶቢስ ተራ ጋር ሲነፃፀር በውክቢያም በስፋትም እጅግ ያነሰውን አውቶቢስ ተራ ውስን ትእይንት እያየሁ በተጠየቅኩ ቁጥር ‹‹ምፅዋ›› እያልኩ ያለመታከት እመልሳለሁ። ደብረዘይት የተመረተ ብስኩት፣ ትግራይ ላይ የታሸገ ውሃ፣ አዲስ አበባ የተቆላ ዳቦ ቆሎ፣ አስመራ ላይ የተዘጋጀ አምባሻ፣ ሌላም ሌላም በየፈርጁ የሚሸጡ ልጆች የሚሸጡትን ነገር እያስተዋወቁ በሻንጣቸው ወይ በብጣሽ ካርቶን ሰልፍ ይዘው በትእግስት የሚጠብቁትን ተሳፋሪዎች ይዞራሉ።

የምፅዋ መኪና ላይ ያለምንም እንግልት ያስገባሻል ተብሎ ገንዘብ እንድሰጠው የተነገረኝ ልጅ እዚህ እንኳን ሊሞላ ከእኔ በቀር አንድ ሰው ያልጫነ አሮጌ መኪና ውስጥ ጥሎኝ ከሄደ 30 ደቂቃዎች በማለፋቸው መንቆራጠጥ ጀምሬያለሁ። ፈልጌ አላገኘው እቃዬን ለማን ትቼ? ደውዬ አላዋራው ስልክ ከየት አባቴ አምጥቼ ?(ኤርትራ ስገባ ሲም ካርድ ለማግኘት ብፈልግም እንደ ብዙ መንግስት የሚያቀርበው አገልግሎት እንኳን ለውጪ ሰው ለሃገሬውም ሰው ብዙ ጣጣ ፈንጣጣ እንዳለው ስሰማ ተውኩት).. የኤርትራን መሬት ከረገጥኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የባይተዋርነት ስሜት ተሰማኝ።

ሆድ ሊብሰኝ ሲጀምር ሁለት ለአውቶብስ ተራ በሚበዛ መልኩ የዘነጡ ሰዎች አውቶብሱ በር ጋር መጡና በተለመደው ሁኔታ የት ነው አሉኝ። ‹‹ምፅዋ›› ብዬ መለስኩ። የአውሮፓን ብርድ ታሳቢ በማድረግ የተሰራ የሚመስል ውፍራም ሱፍ ካፖርታ የለበሰው ጠና ያለው ረጅምና ቀይ ሰውዬ (እድሜውን ስመለከት ልክ እንደ ነፃነት መለሰ ዘፈኑ ሰውዬ ውብ ካፖርታ ያደረገ ከመሆኑ ባሻገር በጊዜው ዶጅ የነዳ እና አረንቻታ የጋበዘ የሚመስል) ተጨማሪ ነገሮች በትግርኛ ጠየቀኝ።

– ትግርኛ አልችልም አልኩ በሃፍረት ፈገግ ብዬ።
– ኢትዮጵያዊ ነሽ? አለኝ ትክ ብሎ እያየኝ
– አዎ….
መልስ ሳይሰጠኝ አብራው የነበረቸውን ሌላ ዘናጭ ሴት ይዞ ወደ አውቶብሱ ገባና ከፊቴ ባለው ወንበር ላይ ተደላድለው ተቀመጡ። ውድ ሽቷቸው አወደኝ።

ተመስገን…ሶስት ሆንን!

ደቂቃም ሳይቆይ ሁለቱም ጀርባቸውን ከሰጡኝ አቀማመጥ ዞር አሉና ያዩኝ ጀመር። ምን ፈልገው ነው?
– ኢትዮጵያ ከየት ነሽ? ማለቴ ከየት ስቴት? አለኝ ሰውየው። ስቴት? ይቀልዳል እንዴ?
አማርኛው በከባድ የእንግሊዝኛ ተፅእኖ ውስጥ የወደቀ ነው። ኤርትራዊ ዲያስፖራ እንደሆነ ገመትኩ።
– አዲሳባ…አልኩ
– ኦህ! ናይስ…እኔ አሜሪካ ነው ምኖረው…ኦርጅናሊ ፍሮም ኤርትሪያ! ዚስ ኢዝ ማይ ሲስተር! አለና ሞቅ ያለ ፈገግታ እያሳየኝ እጁን ለሰላምታ ዘረጋልኝ።

ሁለቱንም በደንብ ተዋወቅኩና ወሬ ጀመርን።
ጨዋታቸው ቢጥመኝም የሰአቱ መግፋት ግን አሳሰበኝ። ሰአቴን አየሁ። አስራ ሁለት ተኩል አለፏል። ሌላ ሰው አልገባም። ምፅዋ ከአስመራ በርቀት ቅርብ ብትሆንም በመንገዱ ከባድነት ግን ሩቅ እንደሆነች በተደጋጋሚ ተነግሮኛል። 105 ኪሎሜትር 3 ሰአት የሚፈጅበት መንገድ ነው። ያለኝ አንድ ቀን ነው። መወሰን ነበረብኝ።

ጓዜን ያዝኩና
– ሌላ አውቶብስ ልፈልግ ነው። ይሄ የሚሄድ አይመስለኝም…አልኳቸው
በሃሳቤ ተስማምተው አብረን ከወረድን በኋላ ቀድሞ ይሄዳል የተባለውን መደበኛ አውቶብስ ለመሳፈር ሰልፍ ያዝን። ከብዙ ጥበቃ እና ድካም በኋላ ሶስት ሰአት ሊሞላው ትንሽ ሲቀረው የተሳፈርንበት አውቶብስ ጉዞውን ጀመረ።

መንገዱ በደህና ደረጃ ያለ አስፋልት ቢሆንም እጅግ ጠመዝማዛ ስለሆነ ጉዟችን ጥንቁቅና ቀስታ የበዛበት ነው። ደስ የሚለው አስፈሪ መጠማዘዝ በሚጠይቅ መንገዶች ላይ በሙሉ ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጡ መኪናዎችን ቀድሞ የሚያሳይ መስታወት ተተክሏል። ( ደስ የሚልና ኢትዮጵያም ቢለመድ ብዙ ሕይወት የሚያተርፍ ነገር ነው። የእኛ ነገር ነቅለን ቤታችን ካልወሰድነው…መቼስ በየጉርባው ላይ የሚቆም መስታወት ጠባቂ ወታደር አንቀጥር ነገር…..)

…መልከአ ምድሩ ሰሜን ኢትዮጵያን፣ መንገዱ ደግሞ ዝነኛው ሊማሊሞን አስታወሰኝ። ተራራ እየወረድን ነው። በምጥ እንዞራለን። በምጥ እንታጠፋለን። በዝግታ እንሄዳለን። ተራራው አለቀ ሲባል ሌላ ተራራ ላይ ነን። ወረድን ስንል አሁንም ከፍ ያለ ቦታ ነን። ደግነቱ መንገዱ በመኪናዎች አልተጨናነቀም። ባሁኑ ጊዜ የኤርትራ ኢኮኖሚ ከወደብ ይልቅ በማእድን ማውጣት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ስለሰማሁ ምናልባት በዚያ ምክንያት ይሆናል ብዬ ገመትኩ። ምናልባት ይሄ መንገድ ወርቅ እና ዚንክ ወደሚታፈስበት የሃገሪቱ ክፍል አይመራ ይሆናል የሚል ግምት ወሰድኩ።
ግማሽ ሰአት አካባቢ ከሄድን በሁዋላ አየር ንብረቱ ከደጋ ወደ ወይና ደጋ፣ የእፅዋቱም አይነት እንዲሁ ተቀየሩ።
ብዙዎቻችን የማናውቀውን እኔም አሰመራ ውስጥ የተዋወቅኩትን የኤርትራ የቱሪዝም መሪ ቃል አስታወስኩ። <<Eritrea: three seasons in two hours>> ይላል። ‹‹በሁለት ሰአታት ሶስት ወቅቶችን ይዩ›› አይነት ነገር። ምፅዋ ስደርስ ይሄ መሪ ቃል አውነት እንደሚሆን አልተጠራጠርኩም።

ሹፌራችን ለትዝታም ለዝላይም የሚሆኑ ሙዚቃዎችን ቀላቅሎ እያጫወተልን ነው። የአማርኛ ሙዚቃዎች ይበዙታል። ኤፍሬምና ጥላሁን እንዲሁም ኤፍሬምና ጥላሁንን አስመስለው የዘፈኑ ዘፋኞች ደጋግመው ይመጣሉ። ከአንድ ሰአት ተኩል የውረድ እንውረድ የቁልቁለት አስቸጋሪ ጉዞ በኋላ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ100 ኪሎሜትር ጉዞ ለቁርስ ቆምኩ።

ጋህተላይ ትባለለች ከተማዋ። በረድፍ ከተደረደሩ ቁርስ ቤቶች እና በርከት ያሉ የገጠር መንደር ቤቶች ውጪ አይን የሚገባ ብዙ ነገር የላትም። አሁንም አሁንም ነፋስ እየተንደረደረ ከሚያፍን አቧራዋ በተጨማሪ በሃይል ትሞቃለች። ወደ ሶስተኛው ወቅት መግቢያ መሆኗን ጠረጠርኩ። ተሳፋሪው በሰልፍ ሲወርድ እኔ ጋር ግቡ እኔ ጋር ግቡ ብለው የሚሻሙ ባለ ቁርስ ቤቶች መጡ። እኔም አብዛኛው ሰውና ሹፌሩ የሚገቡበት ቤት ተከትዬ ሄድኩና ለነፍስ የቀረች የምትመስል አንዲት ብቸኛ ዛፍ ስር ካለ ፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀመጥኩ። በዛፏ ምክንያት ትንፋሽ ባገኝም ሙቀቱን ግን አልቻልኩም። ከአስመራ ጀምሮ ስቀንስ የነበረውን የልብሴን ድርብርብ በአንድ ቀነስኩና ሙቀቱን ማማረር ጀመርኩ። አጠገቤ የተቀመጠው ባለ ካፖርቱ ሰውዬ ( ካፖርቱን ከ50 ኪሎ ሜትር በፊት አውልቋል) ‹‹በዚህ ከተማረርሽ ምፅዋ ምን ልትሆኚ ነው?›› አለና ፈገግ አለ።
እውነቱን ነው። ዛሬ የሙቀት መጠኗ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሆነ የተተነበየላት ምፅዋ ስደርስ ምን ልሆን ነው?

ቀዝቃዛ ኮካ እና ስልስ በዳቦ አዝዤ ተቀመጥኩ። አንዲት እርምጃዋ ሸክም እንደተሸከመ ሰው ሁሉ ቀስ ያለ ጠና ለለች ሴት ይዛልኝ መጣች።
– አመሰግናለሁ አልኳት
በትግርኛ ብዙ ነገር አለችኝ። ቋንቋ እንደማልችል ስታውቅ እየታገለች፣ በጣም በተቆራረጠ ሁኔታ በአማርኛ ታወራኝ ጀመር። እንግድነት እንዳይሰማኝ በመጣሯ ደስ አለኝ።
– ከአዲስ አበባ ነው የመጣሁት አልኳት ከየት መጣሽ ስትለኝ
– እኔ አዲስባ አላውቅም…ሕይወቴ ሙሉ እዚህ …አለችኝ
– አሁንስ አትመጪም? አልኳት ፈገግ ብዬ
– አይ…እሱ እግዜር ያውቃል..እናንተ ግን እንኳን በደህና መጣችሁ….
– አሜን
– የእኔ አማርኛ ጠፋ…
– አረ ጎበዝ ነሽ…ለመሆኑ እንዴት ቻልሽ? አልኩ ኮካዬን እያጣጣምኩ።
– ለነፃነት ታጋይ ነበርኩ…የደርግ ወታደሮች አስተማረኝ። ምርኮ ወታደር። …ኢትዮጵያዊ ከሆንሽ ደግሞ በነፃ እጋብዛለሁ…የበራድ ቡና አለ ይዤልሽ እመጣለሁ….አለችና ጥላኝ ሄደች።

ኮካዬን አስቀምጬ እንደ ማነከስ እያለች ስትሄድ አየኋት። ጊዜ ግን የሚገርም ነገር አይደለም? መኖር ግን የሚደንቅ ነገር አይደለም?
እኔ፣ አባቴ የኢሰፓ አባል የነበረ ኢትዮጵያዊት፣
እኔ የጥላሁን ገሰሰን
‹‹አባረህ በለው ያንን አመፀኛ ተገጣይ ወንበዴ፣
ልኩን አሳየው አስኪደው በዳዴን›› በህጻንነት ጆሮዬ እያዳመጥኩ ያደግኩ ኢትዮጵያዊት
እኔ፣ በጉረምስናዬ ዘመን ከኤርትራ ጋር ስንዋጋ የክፍሌ ልጆች ለኢትዮጵያ ሊሞቱ በሰልፍ ሲሄዱ ቆሜ ያነባሁ ኢትዮጵያዊት፣
እኔ፣ አሸባሪው ሻእቢያ፣ የሻእቢያ ተላላኪዎች፣ የአስመራ መንግስት ቡችሎች…የሚሉ የፕሮፓጋንዳ ቃላትን ስሰማ የጎለመስኩ ኢትዮጵያዊት..

በአንዲት ሚጢጢ የኤርትራ የገጠር ከተማ፣ ኤርትራን ለመገንጠል ከታገለች የሻእቢያ ወታደር ቁርስ ቤት ተቀምጬ ስልስ በኮካ እየበላሁ፣ ኢትዮጵያዊ ‹‹ጥቁር እንግዳ›› በመሆኔ ደግሞ ነፃ ቡና ልጋበዝ ነው።

በእኔ እና በእሷ መሃከል ሰባ ሺህ ሰዎች ረግፈዋል። በእኔ እና በእሷ መካከል ሃያ የጠብ አመታት አልፈዋል። በእኔ እና በእሷ መካከል ሊነገር የሚቀፍ በደል እና ስቃይ ተከናውኗል።

ግን ያ ሁሉ አልፎ ቡና ልትጋብዘኝ ነው።

ጊዜ ግን የሚገርም ነገር አይደለም? መሰንበት ግን የሚደንቅ ነገር አይደለም?

(ይቀጥል ይሆናል…)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • Selatialbahra@gmail.com'
    selatial bahra commented on February 22, 2019 Reply

    ሂዊ ምናለ እኔንም ይዘሽኝ ብትሄጅ ኖሮ ምርጥ ፅሁፍ ምርጥ ምናብ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...