Tidarfelagi.com

ቅቤ የሌለው ሽሮ…

ሰውዬው እቤቱ ሲገባ ባለቤቱ ያቀረበችለት ሽሮ
ምግብ ምንም ሊጥመው አልቻለም።
አንዳች ነገር ጎድሎታል። አሰበ አሰበና አገኘው። ቅቤ የለውም። «ምነው?» አለ። «ቅቤ አልቋል» ተባለ። የተዘረጋውን ማዕድ ትቶ ወጣና ወደ ጎረቤቱ ገባ። «አያ እገሌ ዛሬ ምን አግር ጣለህ» አለና ጎረቤቱ አባ ወራ ተቀበለው። «ባክህ አንዳች የሚበላ ነገር ካለ ብዬ ነው» አለ እንዳኮረፈ መሆኑን በሚያሳብቅ ድምፅ። «ውይ በሞትኩት» አለችና የጎረቤቱ ሚስት እንጀራውን በመሶብ ሞልታ ፊቱ ላይ አቀረበችለት። የምግብ አምሮቱ ተነቃነቀ። ወጡን በእንጀራ ሲያጠቅሰው ግን ያ መጣሁ መጣሁ ያለው አምሮት እልም ድርግም አለ።

እዚህም ያለው ወጥ አንዳች ነገር ጎድሎታል። «ቤት ያፈራውን ብላ እንጂ ጨው አለቀ ብላ ብዙም አላደረገችበት። ለረሃብ ይሆንሃል ብላ» አለው አባ ወራው። አልቻለም። ነካክቶ ተወውና ተሰናብቶ ወጣ። ወደ ሦስተኛው ጎረቤቱ አመራ።
የሦስተኛው ጎረቤት አባ ወራ ከጎጆው ውጭ መደብ ላይ ተቀምጦ አንዳች ነገር ይበላል። «አይዋ እገሌ እስቲ ጠጋ በል። እግርህ ርጥብ ነው» አለና አጎዛውን አስተካከለለት። ተቀመጠ። የጎረቤቱ ሴት ልጅ የጣት ውኃ ይዛ መጣች። ታጠበ እና ቀረበ። ጎረቤቱ እንጀራ በአዋዜ ነው የሚበላው። «እቴዋ ገበያ ሄዳ ወጥም አለተሠራ፤ ብላ ምንም አይልህም» አለው እንጀራውን ወደፊቱ እያደረገ። ጥቂት ቀማመሰና ተሰናብቶ ወጣ። «እንዴው የሚጣፍጥ ምግብ በሠፈሩ ሊጠፋ ነው»

እያለ ወደ አራተኛው ጎረቤቱ ቤት አመራ። ማዕድ ቀርቦ ቤተሰቡ እየተመገበ ነው፡ «ሲበሉ አድርሰኝ ሲጣሉ መልሰኝ ማለት ይሄኔ ነው» አለችና እማወራዋ ተቀበለችው። አባወራውም ወንበር ለቀቀለት። እጁን ታጥቦ ቀረበ። «በርበሬ ስላላስፈጨን አልጫ ነው። ግን ይጣፍጣል ብላ» አለው አባወራው። በይሉኝታ ተመቻችቶ ቀረበ። እርሱ እቴ በርበሬ ለሌለው ወጥ መች ወስፋቱ ይከፈትለታል። ለምላሱ ሳይሆን ለሆዱ ቀመሰ።

ጥቂት ተጫወተና ወጥቶ ወደ አምስተኛ ጎረቤቱ አመራ። አቦል ቡና ላይ ነበር የደረሰው። እማወራዋ ወደ ጓዳ ገብታ እንጀራውን አጠፈችና ፊቱ ላይ ዘረጋችው።ወጡ በሰታቴ ቀረበ። በምላሱ አጣጣመና ቅር አለው። አባወራው ገባውና «ምን እዚህ ቤትኮ ሽንኩርት የገባበት ወጥ ከተሠራ ቆየ፤ እኔም ይህንኑ ነው የበላሁት» አለው። እንዴው ለላንቲካው ጎራረሰ። እስከሁለተኛው ቡናውን ጠጣና ወጣ።እንዲህ እያለ መንደሩን ሁሉ ዞረው። አንዱ ቤት እንጀራውይጠቁራል፤ አንዱ ቤት እንጀራው ይደርቃል፣ አንዱ ቤት ወጡ ያርራል፣ አንዱ ቤት ወጡ ይጎረናል። አንዱ ቤት ቅመም አይኖረውም፣ ሌላው ቤት በሚገባ አይበስልም። የተሟላ ማዕድ አላገኘም።

መጨረሻ ላይ በጣም ወደሚቀርበው ጎረቤተሩም ወዳጁም ወደ ሆነ ሰው ቤት ገባ። «እኔ እዚህ ቤት የመጣሁት የሚጣፍጥ ነገር ፈልጌ ነው» አለ ዘና ብሎ።
«ይጣፍጥ አይጣፍጥ እንጃ፤ የሚበላ ግን አይጠፋም» አለችና እማወራዋ አቀረበችለት። ምን የመሰለ ጥብስ። ምን ዋጋ አለው ታድያ ያለ መጥበሻ ቅጠል ነው የተጠበሰው። አዘነ። መርገምት ያለበትም መሰለው። ጠጋ አለ ወደ ወዳጁ። «አንተዋ፤ እኔ ከቤት የቀረበልኝን ጥዬ የወጣሁት የተሻለ አገኛለሁ ብዬ ነበር። ሁሉም ቤት ቀመስኩ። ሁሉም ቤት ጎደሎ አለ። ጨው ያለው ሽንኩርት፣ ሽንኩርት ያለው ጨው፣ ዘይት ያለው፣ ቅመም፣ ቅመም ያለው ዘይት፣ በርበሬ ያው ቅቤ፣ ቅቤ ያለው በርበሬ፣ እንጀራው ሲያምር ወጡ፣ ወጡ ሲያምር እንጀራው፣ አንዳች ነገር ይጎድላል። «እንዴው የተሟላ ነገር የት ነው የሚገኘው?» አለና አዋየው። «የትም» አለው ወዳጁ። «እንዴት እንዴት?» «ሁላችንም ጎደሏችንን እናሟላለን እንጂ ሙሉ የት ይገኛል። ሁሉም ቤት ጎደሎ አለ። ልዩነቱ የጎደሎው ዓይነት ነው።

አንተ ቤት የጠፋው እኔ ቤት፣ እኔም ቤት የጠፋው አንተ ቤት ይገኛል። ያ ማለት ግን ሙሉ ነው ማለት አይደለም። «ሰው ሁሉ ትዳሩን የሚያማርረው ይህንን ባለማወቁ ነው። እርሱ ቤት የጎደለውን እዚያኛው ቤትሲያየው ያኛው ቤት የተሟላ ይመስለዋል። እዚያም ቤት እሳት አለአሉ አለቃ ገብረ ሐና። «ታድያ ምን ያዋጣናል» «የሚያዋጣንማ የየራሳችንን ጎደሎ ማሟላት ነው። ምሉዕ የሆነች ሚስት፣ ምሉዕ የሆነ ባል፣ ምሉዕ የሆነ ትዳር የት ይገኛል። ሁሉ እየተሟላ ይሄዳል እንጂ። ትዳር ማለት በጎደለው ነገር መጨቃጨቅ፣ መነዛነዝ፣ መጣላት እና መኳረፍ፣ መለያየት እና መፋታት አይደለም።

ትዳር ማለት የሚጎድለውን እየሞሉ መቀጠል ማለት ነው። ሙሉ ባል ወይንም ሙሉ ሚስት የሉም። ሊሟሉ የሚችሉ ባል እና ሚስት ግን አሉ። «ቆይ ግን ሁላችንም እዚያ ማዶ ያለው ነገር የሚያምረን ለምንድን ነው?» «እዚያ ማዶ ስናይ ጎደሎው ስለማይታየን ነዋ፤ የሚታየን ከኛ የሌለው እዚያ መኖሩን ነው። እስቲ እይ አንዳንድ ሰዎች ሌሎች ባለ ትዳሮች ቤት ደርሰው ሲመጡ የራሳቸውን ያማርራሉ። እነዚያ የተሻሉ መስለው ይሰማቸዋል። ባልም ሚስቱን ሚስትም ባልዋን እንደዚያኛው ቤት እንዲሆኑ ይመኛሉ፤ ይመክራሉ።

እነዚያኞቹንም ብትሰማ ቸውኮ በነዚህኞቹ የሚቀኑ ናቸው። ወዳጄ ሁሉም የየራሱን ጎደሎ እያሰበ ያማርራል እንጂ ለመሙላት አያስብም። «ለመሆኑ አንተ ለምን ነበር ምግቡን ጥለህ የወጣኸው?» «ቅቤ የለውማ» «ቀላሉ መንገድኮ ቅቤ ገዝቶ የራስህን ወጥ ሙሉ ማድረግ ነበር። አንተ ግን ቅቤ ያለው ስትፈልግ ጨው የለለው መጣብህ፣ ጨው ያለው ስትፈልግ፣ ሽንኩርት ያነሰው መጣ፣ ሽንኩርት ያለው ስትፈልግ በርበሬ የሌለው መጣ፤ እንዲህ እንዲህ እያልክ ስትዞር ትኖራለህ እንጂ ያልጎደለው ወጥ የት ይገኛል።«ተመለስ ወዳጄ፣ ቅቤውን ግዛና ግባ። ያኔ የራስህ ጎደሎ ይሞላልሃል።»

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...