Tidarfelagi.com

ቂም የሸፈነው እውነት

“መለያየት እፈልጋለሁ። ፍታኝ?” አልኩት በመኪናው መስኮት አሻግሬ ዓይኖቹን እየሸሸሁ።

“እሺ!!” ነበር መልሱ:: ቢያንስ ‘ለምን?’ ብሎ እንዴት አይጠይቀኝም?

“መች ነው እንዲሆን የምትፈልጊው? አሁን? ነገ? ከሳምንት በኋላ? መቼ?” ቀለል አድርጎ ቀጠለ። ቀጥዬ የምለው ጠፋኝ። ለራሴ ምክንያት መስጠት እፈልጋለሁ። ተናዶ እንዲናገረኝ እሱ ላይ እንከን ማግኘት አጥብቄ እፈልጋለሁ።’ፈታችው’ ከመባል ሌላ ቅጥያ ተጨምሮበት ‘ስላናደዳት ፈታችው’፣ ‘ስለመታት ፈታችው’……… ብቻ ምክንያቱ ከሱ ቢመጣ ደስ ይለኛል።

“ካለቀልን ዛሬም ብንፋታ ደስ ይለኛል።”

“ከዛሬ በኋላ ተፋተናል። የግድ በህግ መፋታት የለብንም። እኔን መፍታት አይደል የፈለግሽው? ስለወደድኩሽ እንጂ ማንም ስለፈረመ እና ምስክር ስለተጠራ አላገባሁሽም።” ብሎኝ ከመኪናው ወረደ እና የኔን በር ከፈተልኝ። ቤታችን ደጅ ደርሰን ነበር። ተናደድኩ።

“የንብረት ክፍፍሉ……..” አላስጨረሰኝም።

“የትኛውን ንብረት ነው የምትፈልጊው?” የአጥሩን በር ከፍቶ በእጁ እንድገባ አሳየኝ።

“ድርሻዬን::”

“ህምምምም…….. ቅር ካላለሽ ትንሿን መኪና ልውሰዳት ሌላውን ንብረት አልፈልገውም። ከዛሬ በኋላ ባልሽ አይደለሁም። ምንም ንብረትም የለኝም።” ብሎኝ ‘ትንሿ’ ያላት መኪናው ውስጥ ገብቶ ተመልሶ ሄደ።

ምን እንደምፈልግ ግራ ገባኝ። ካሳሁንን ሳላገባው በፊት ነበር የምፈታው ቀን የሚናፍቀኝ። ሳላገባው ፈትቼዋለሁ። እሱ ያገባኝ የመሰለው ቀን እኔ አግብቼም ፈትቼዋለሁ።ታዲያ ለምን አገባሁት? እሱን አላገባሁትም። ገንዘቡን እንጂ። ወንዶች ‘ሴት ልጅ ገንዘብ ያለው ወንድ ትወዳለች’ ሲሉ ሳቄ ያመልጠኛል። ወይ ሰውየው ማርኳታል ወይ ገንዘቡ ማርኳታል። ለአንዳቸው ቅድሚያ ትሰጣለች።ለገንዘቡ ብላ ከሆነ ገንዘቡን እንጂ እሱን አትወደውም። ገንዘቡ እስካለ ወይም የምትፈልገውን እስክታገኝ ድረስ አለች። እነሱ ግን ራሳቸውን ሳይሆን ገንዘባቸውን ያቀርቡላታል። ምክንያቱም የቁስን ያህል ራሳቸውን አያምኑትም። ስለዚህ ከቁሳቸው ይልቅ ራሳቸውን ተወዳጅ አድርገው ማቅረብ ሲሳናቸው ለገንዘቤ ብላ ነው የወደደችኝ ይላሉ እንጂ ገንዘቤን ነው የወደደችው አይሉም። ሰውየውን ከወደደችው ለገንዘቡ ብላ፣ ለቁመናው ብላ፣ ለወዙ ብላ…. የሚሉት ቀልድ አይጥመኝም። በቃ ሰውየውን ነው የወደደችው።

የዛን ቀን ምሽት አልመጣም። ጠበቅኩት። እውነቱን እንደሆነ ገባኝ። ካሳሁን ፈቶኛል። ሁለተኛው ቀን መሸ ።አልመጣም። አልደወለም። ሶስተኛ ቀን ሆነ……… አራተኛ ቀን መጣ… … አስር ቀን ሞላው። አልመጣምም። አልደወለምም። የገባኝ ግን ቢመጣ ደስ እንደሚለኝ ነው።እሱን መፍታት ያስደስተኛል ብዬ ያሰብኩትን ያህል አልነበረም የደስታዬ መጠን።

“አልወደውም። ከሀብቱ እንጂ ከእርሱ ጉዳይ የለኝም።” ለራሴ ብቻዬን አነበነብኩ። ስልኬን እልፍ ጊዜ ልደውልለት አነሳሁ። እልፍ ጊዜ ተውኩት። በአስራአንደኛው ቀን ስልኬ ጠራ። እሱ ነበረ። ለምን ደስ አለኝ? አብሬው መኖር የማልፈልገው ሰው ድምፁን መስማቴ እንዴት አስደሰተኝ?

“ደህና አደርሽ ሰብሊ? …… ላግኝሽ?”

“እሺ:: የት እንገናኝ?”

“ስራ ቦታ:: አራት ሰዓት ላይ መጥቼ ወስድሻለሁ።”

ስራ የመግባት ፍላጎት አልነበረኝም።ቁምሳጥኑን ከፍቼ ሊያቆነጀኝ ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ ልብስ ሞከርኩ። ላማልለው? ወይስ ከሱ በመለየቴ አለመከፋቴን ለማሳየት? ለራሴ የምሰጠው ምክንያት ባይኖረኝም በሱ ፊት ቆንጆ ሆኜ መታየት ፈለግኩኝ። አምስት ዓመት በትዳር አብሬው ስኖር ይሄ ግድ ሰጥቶኝ አያውቅም ነበር። በጥንቃቄ ስዋብ ብዙ ሰዓት ፈጅቼ ደረስኩ። ተጋብተን ብዙም ሳንቆይ ነበር ካሳሁን እቤት ከምትውዪ ብሎ ለንግድ ተስማሚ የሆነ ቦታ ላይ ትልቅ የሴቶች ፀጉር ቤት የከፈተልኝ ። በሩ ላይ ሲደርስ የት ይዞኝ ሊሄድ እንደሆነ እያሰብኩ ነበር። ብዙም ግድ ያልሰጠው ሰላምታ ሰጥቶኝ የመኪናውን በር ከፍቶ አስገባኝ። በሚከብድ ዝምታ መኪናውን መንዳት ጀመረ። ላገኘው እንዳልቸኮልኩ። ተጨነቅኩኝ።

“የት ነው የምንሄደው?” አፌ ይሄን ይበል እንጂ የትም ብንሄድ ግድ አልነበረኝም።

“የምንጨርሰው ጉዳይ አለን።”

ባንክ ቤት በር ጋ ስንደርስ በሁለታችን ስም የነበረውን የባንክ አካውንት ሊያዛውርልኝ መሆኑን ነገረኝ። በተዘባረቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ የሚጠበቅብኝን ፈፀምኩ። እድሜውን ሙሉ የሰራው ገንዘብ መሆኑን እያወቅኩ ‘አንተስ?’ ብዬ እንኳን አልጠየቅኩትም። ነገር ዓለሙ ዞረብኝ። ምንም ሳንነጋገር ፀጉር ቤቱ በር ጋር ደርሰን።በር ሊከፍትልኝ ከመድረሱ ዘልዬ ከመኪናው ወረድኩ። በሌላ ትህትናው መቁሰል አልፈለኩም።

“የት ነው ያለኸው?” አልኩት

“ቤት እስካገኝ ሆቴል ነው ያረፍኩት::”

“ለጊዜው እኮ እቤት መሆን ትችላህ::”

“በሚቀጥለው ሳምንት በአንዱ ቀን የቤት ባለቤትነቱን ስም አዛውርልሻለሁ:: ሰሞኑን ስራ ስለሚበዛብኝ የምችል አይመስለኝም።” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገብቶ ሄደ። ራሴ የሚፈነዳ መሰለኝ።የማብድ የማብድ መስሎ ተሰማኝ። ወደቤቴ ሄድኩ።

የደስታዬ ጫፍ ይሆናል ብዬ የማስበው ቀን ሲመጣ እርካታን ሳይሆን ባዶነትን ተሸክሞ ነው የመጣው። የምፈልገው ሁሉ ኖረኝ።የማስበው ሁሉ ሰመረልኝ። ግን ትርጉም አልባ፣ ደስታ የለሽ ሙት ሆነብኝ።

**************
እንደማንም ያልነበረው ልጅነቴ፡-
ሰዎች ስለልጅነታቸው ሲያወሩ ‘እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ…..’ ሲሉ እገረማለሁ:: ‘ማንኛውም ኢትዮጵያዊ’ እኔን ያቀፈ ማዕቀፍ ይሆንን?

በቀን አንዴ ትርፍራፊ ለመቅመስ መስገብገብ፣ ጎዳና ላይ በገነባቻት የላስቲክ ቤት አጠገብ ተቀምጣ የምትለምን ወፈፍ የሚያደርጋት እናት፣መለመኛ የሆኑ መንታ ታናናሽ እህትና ወንድም፣ አስር ሳንቲም ለመመፅወት የሚመፃደቅ ሂያጅ፣ በባዶ እግርና በእኮዮች ምፀት ታጅቤ የምዳክርበት ትምህርት ቤት…….. ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለየ ልጅነት ነው።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እናቱ ልመናን ተናዛለት አባት አልባ ህፃናት መንገድ ዳር አስታቅፋው አልሞተችም።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እናቱ የሚበር መኪና ውስጥ ገብታ ስትሞት የሚሰማውን ከእብደት ያልተለየ ስሜት አያውቀውም።

የኔ ልጅነት ‘እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ’ የሚባለው ማዕቀፍ ውስጥ የማይገባው ልጅነት የሚባለው ዘመኔ በአስር ዓመቴ አክትሞ የሁለት አመት ጨቅላ መንታ ታናናሾቼን እየለመንኩ ማሳደግ ግዴታዬ ስለነበር ነው። ዓለም ስትከረፋብኝ፣ በርሃብ ከሚጮሁ ታናናሾቼ ጋር ኡኡኡ ብዬ ሳለቅስ “እንደእናቷ ጠሸሸች” እተባልኩ አራት ዓመታትን ጎዳና መግፋቴ ነበር።

አንድ ምሽት ታናናሾቼን አስተኝቼ ነትቦ እርቃኔን ያጋለጠውን ልብሴን እየሳብኩ ከላስቲክ ጎጆአችን ፊት ለፊት ቆሚያለሁ። መኪና ሲጢጥ ብሎ ሲቆም ሰማሁ። የሰከረ ወንድ ድምፅ ተከትሎ ተሰማኝ።

“እሙዬ ነይ እስኪ……”

ቂም የሸፈነው እውነት (ክፍል ሁለት)

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...