Tidarfelagi.com

ሽልማቱ

“በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ ያመቱ ኮከብ ተሸላሚ ማሞ መንገሻ “ ብሎ ለፈፈ ፥ የመድረክ መሪው
አዳራሹ በጭብጨባ ተርገበገበ
የማሞ ልብ በሀይል መምታት ጀመረ፥ ተሸላሚነቱን ከሰማ ጊዜ ጀምሮ መኪና እሸለማለሁ የሚል ሰመመን ጭንቅላቱን ተቆጣጥሮት ቆይቷል፤ ምን አይነት መኪና ይሆን እሚሸልሙኝ የሚል ሀሳብ ጠመደው፤
ወደ ሽልማቱ አዳራሽ የመጣው የሰፈሩን ላዳ ሹፌር አስቸግሮ ነው፤ በሰፈሩ የታወቀውን የላዳ ሹፌር ከዚህ በሁዋላ ማሞን በዱቤ ላለማጓጓዝ ምሎ ነበር፤ ይሁን እንጂ ማሞ ለሽልማት የታጨበትን መጥርያ ሲያሳየው ተረታ፤ ደንበኛው” ገንዘብ ከሸለሙኝ እስከዛሬ ያለብኝን እዳ እጥፍ አድርጌ እከፍልሀለሁ፤ መኪና ከሸለሙኝ ላንድ ወር ራይድ ትሰራባታለህ” የሚል ተስፋ ሰጥቶታል፤
ማሞ ከወንበሩ ተነስቶ ወደ መድረኩ አቅጣጫ ለመራመድ ሲቃጣ የፕሮግራሙ መሪ “ ማሞን ወደ መድረኩ ከመጥራታችን በፊት ለዚህ የሽልማት እውን መሆን ከፍተና ደጋፍ ያደረጉ ስፖንሰሮቻችንን እናስተዋውቃለን፤ “ ብሎ ጀመረ” ጌድዮን ሪል ስቴት ለድርጅታችን ቢሮ እንደሚሰጠን ቃል ስገባ እናመሰግናለን! ጠንበለል ቢራ አንድ ሚሊዮን ብር ስላበረከልን ደስታችን ወደር የለውም፤ እባካችሁ ጭብጨባ ያንሳል”
ጭብጨባው አዳራሹን ነቀነቀው፤
የፕሮግራሙ መሪው ዝርዝር ውስጥ ያልተጠቀሰ የንግድ ድርጅት የለም፤ ማሞ በቆመበት እግሮቹ ሊክዱት ሲያንገራግሩ ተሰማው ፤ ከዚህ በሁዋላ ሁለት ደቂቃ ከቆምኩ ዊልቸር እንጂ መኪና አያሰፈልገኝም ‘ ብሎ አሰበ፤
ሁለት ቆነጃጅት ሴቶች አጅበው ወደ መድረክ ወሰዱት፤ ከመድረኩ ጫፍ እስከ ሸላሚው ድረስ ያለው ርቀት አገር አቁዋራጭ ሆነበት ፤ መሸለሚያው ላይ ሲደርስ ሁለት ግላድያተር እሚያካክሉ ወጠምሾች የብረት ሙቀጫ እሚያክል ዋንጫ መዳፉ ላይ አስቀመጡለት፤
ወደ ወንበሩ ሲመለስ ጋዜጠኞች አንገቱን በየማእዘኑ እየጠመዘዙ የካሜራ ብርሀን ነሰነሱበት፥
የፕሮግራም መሪው ሌሎችን ተሸላሚዎች አንድ ባንድ መጥራት ቀጠለ፤ ባዳራሹ ውስጥ ያሉ ካሉት ታዳማዊዎች መካከል ዘጠና በመቶው ተሸላሚዎች ሳይሆኑ አልቀሩም፤ ማሞ የመዳፉ መስመሮች እስኪደበዝዙ ሲያጨበጭብ ቆየ።

የመድረኩ ወከባ በረድ ሲል አንድ ዘፋኝ መድረክ ላይ ወጦ እንደ ድንገተኛ ዝናብ ታዳሚውን መበትን በሚችል ድምጽ መዝፈን ጀመረ፤ ማሞ ቀስ ብሎ ዋንጫውን እንደ ግንድ ጉማጅ ትከሻው ላይ አድርጎ ካዳራሹ መሰስ ብሎ ወጣ፤ ትንሽ እንደተራመደ። የቤትና የጉዋዳ እቃዎችን የሚሸጥ ሱቅ ተመለከተ፥
“ይሄንን ስንት ትገዛኛለህ?” አለው ባለሱቁን
“ምንድነው?” አለ ባለሱቁ ሽልማቱ ላይ አፍጥጦ፥
“ዋንጫ“
“ይሄማ ዋንጫ ሊሆን አይችልም”
“ታድያ ምንድነው? “ አለና ማሞ፤ የተሸከመውን ሽልማት እንደገና እየቃኘ
“ባለ እጄታ ዳምቤል ነው የሸለሙህ” ባለሱቁ ዘለግ ያለ ሳቅ ሳቀ፤
“እሺ ስንት ትገዛኛለህ?” ማሞ በቅጡ በማይሰማ ድምጽ ቀጠለ፥
“በነጻ ብትሰጠኝ ንክች አላደርገውም፤ ያንድ ደርዘን ስኒ ቦታ ይይዝብኛል፥ ለምን ጂም ቤት አትሞክርም፤ ?”
ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ ማሞ ራሱን የሞላ ምኒባስ ውስጥ አገኘው ፤
ወያላው ትከሻውን ሲነካው ቀና አለ፤
“ጀለስ!“ አለው ወያላው ማሞን ቁልቁል እያየው፥
“አቤት”
“ለእቃው ትከፍላለህ”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...