Tidarfelagi.com

‹‹ሻይ በምሬት››

ዛሬ በጠዋቱ አስቸኳይ ጉዳይ ገጠመኝና ስራ ከመሄዴ በፊት አንድ ወዳጄን ለማግኘት አስፋልት ዳር ካለ የሰፈር ካፊቴሪያ ተቀምጬ ቅመም ሻዬን በብርድ እጠጣለሁ። ወሬ አያለሁ። ነፋሱ ይጋረፋል። ብርዱ ያንዘረዝራል።
በትንሽ ብርጭቆ የቀረበልኝ ሻይ ስላልጠቀመኝ ሁለተኛ አዘዝኩና ፕላስቲክ ወንበሬ ላይ እየተመቻቸሁ ወደ ጎን ዞርኩ።

እኔ ያለሁበት ካፊቴሪያ አጠገብ የሚገኘው ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ ገና በማለዳ ቄጠማውን ጎዝጉዞ (አሁን አሁን ሁሉም የአዲሳባ ስጋ ቤቶች መለያ ሆኗል)፣ ደማቅ መብራቶቹን ከጥግ እስከጥግ የሰቀለው የስጋ ግድግዳ ላይ አብርቶ ደንበኛ ይጠብቃል።

ቢላውን ደጋግሞ የሚሞርደው የሉካንዳ ቤቱ ሰራተኛ ሲሞርድ የሚያወጣው ድምፅ ደምበኛን ከአስፋልት ጠልፎ ያስገባlt ይመስል ሳያቋርጥ መሳሉን ቀጠሏል።
‹‹እስቲ አሁን ገና ሁለት ሰአት እንኳን ሳይሞላ ማነው ስጋ ቤት መጥቶ ቁርጥና ጥብስ የሚያቀላጥፍ…? በዚህ ያበደ ኑሮ ማነው እንዲህ የደላው…›› በሚል ሃሳብ ከመያዜ አይኖቼን ከባለሞረዱ ሰው ዝቅ ሳደርግ በቄጠማ ከተሸፈነው የቤቱ በረንዳ ወለል ላይ ከተቀመጡ ስምንት የሚሆኑ ፕላስቲክ ወንበሮች አራቱ በሰው እንደተያዙ ሳይ ገረመኝ።
ከዚያ ደግሞ በማን እንደተያዙ ስመለከት ይባስ ገረመኝ።
አራቱም በእድሜ የገፉ ሰዎች ናቸው።ሁለቱ ደግሞ ነጠላ እና ወፈር ያለ ሹራብ ቢጤ የደረቡ እናቶች ናቸው። አንደኛው አዛውንት ምርኩዝ ይዘዋል።
አራቱም አንድ ጠረጴዛ ከበው ይቀመጡ እንጂ አንድ ላይ የመጡ አይመስሉም። ከሚታየኝ አይነጋገሩም።
እየበሉም እየጠጡም አይደለም። ጠረጴዛቸው ባዶ፣ እጃቸው ቁሩን ሽሽት እኪሳቸው፣ ወይ ደግሞ ከነጠላቸው እና ስር ነው።
ግራ ተጋባሁ።
በእኔና በእነሱ በረንዳ መሃከል ሰፊ ርቀት ስላልነበር ብቻዬንም ከምሆን፣ ጉጉቴም በከንቱ እንዳይቀር ታስተናግደኝ የነበረችውን ልጅ ጠራሁና፤
‹‹እሙዬ…እዚያ ጋር ብሄድ ችግር የለውም አይደል…ሻዩን እዛ አታመጪልኝም?›› አልኳት።
‹‹ችግር የለውም ሂጂ…! የእኛው ማለት ነው›› ስትል አፍታም አልወሰደባት።
ተንስቼ ሄድኩና አጠገባቸው ካለው ጠረጴዛ አንዱን ወንበር ጎትቼ እየተቀመጥኩ…
‹‹እንዴት አደራችሁ….? በጣም ይበርዳል አይደል…?›› ብዬ ወሬ ለመጀመር የመጀመሪያውን ሙከራ አደረግኩ።
አራቱም በየተራም፣ በአንድ ጊዜም ባልጠበቅኩት ጉጉት፤ ‹‹እግዛሄር ይመስገን….እንዴት አደርሽ ልጄ….አዎ…ይበርዳል…በጣም ይበርዳል .›› የሚሉ ቃላትን መልሰው ወረወሩልኝ። ሁኔታቸው የዝምታቸውን አጥር የሚያፈርስ ሰው በማግኘታቸው የተደሰቱ ያስመስልባቸዋል።
ቀረብ ብዬ ሳያቸው ኑሮ የሞላላቸው፣ የደላቸው፣ በጠዋት ሉካንዳ እና ግሮሰሪ የሚያስመጣ ምቾት ያላቸው አለመሆኑን ከፊታቸው ተረዳሁ እና ይበልጥ ግር ብሎኝ፤ እርግጠኛ ሳልሆን…‹‹እንዴት በዚህ እድሜያችሁ በዚህ ጠዋት ስጋ ልትበሉ እና መጠጥ ልትጠጡ መጣችሁ?›› ብሎ መጠየቅን ፈርቼ፣
‹‹በጠዋቱ እንዴት ነው እዚህ….›› ብቻ አልኩ።
‹‹ሰልፉ ሳይበዛ…ሰዉም ሳይነጋጋ እንድረስ ብለን ነዋ!›› አሉ ወፈር ያሉት እናት ፈጠን ብለው።
ምንድነው ያሉት?
ሰልፉ ሳይበዛ…ሰዉም ሳይነጋጋ እንድረስ ብለን ነዋ?
‹‹የምኑ ሰልፍ?›› አልኩ አሁንም በበዛ ጥንቃቄ አራቱንም እያየሁ።
‹‹የዚህ ነዋ ልጄ…!›› አሉ የቅድሟ ሴትዮ አሁንም ፈጠን ብለው በአመልካች ጣታቸው በጎን በኩል ከጀርባቸው ወዳለው ግድግዳ እየጠቆሙ። አይኔ ጣታቸውን ተከትሎ ሄደ። ፓስታ ቤት። ካፍቴሪያውም፣ ሉካንዳ ቤቱም ያሉበት የኮንዶሚኒየም ህንፃ ስር ያለ ፖስታ ቤት።
ነገሮች በፍጥነት ተያያዙልኝ።
እነዚህ አራት አረጋውያን በዚህ ጠዋት፣ በዚህ ብርድ ሉካንዳ ቤት ደጃፍ የተቀመጡት ጮማ ሊቆርጡ፣ ቢራ ሊጠጡ አይደለም። በፖስታ ቤት በኩል የሚሰጣቸውን የጡረታ ገንዘብ ሊቀበሉ ነው።
‹‹ልጁ ስለሚያውቀን ከምንቆም ያስቀምጠናል…የተባረከ ልጅ ነው….›› አሉ ሌላኛዋ ሴትዮ የሚቀጥለውን ጥያቄዬን ሳልጠይቅ።
ያልጠበቅኩት ስለገጠመኝ፣ ወሬውን በምን እንደምቀጥል ሳሰላስል ልጅቱ ሻዬን ይዛ መጣችና ሁሉንም በየጊዜው እንደምታያቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ አይታ፣ በቀልድ ለዛ ወፍረሟን ሴትዮ እያየች፤
‹‹ እማማ… ዛሬ መቼም ተቀብለው ኪሎ ቁርጥ ሊበሉ ነው አይደል…?ብቻ ሳይጋብዙኝ እንዳይሄዱ…›› አለች እየሳቀች።
አራቱም ከት ብለው ሳቁ። እኔም ፈገግ አልኩ።
እማማ በቅድሙ ፍጥነታቸው ‹‹አይ እናቴ…ቁርጡን እንኳን ተይው….በህልሜም አልመኘው….ይመስገነው…ቢያንስ ይህችን ሶስት ቀን ያቺን ቡናዬን በስኳር እጠጣለሁ…›› ብለው እንደገና ሳቁ። አሁንም ልጅቱም፣ ሶስቱም አዛውንት አጀቧቸው።
እኔ ግን አንጀቴ በሃዘን ታጠፈ።
የቀልዳቸው ምሬት እንኳን ከእነሱ ጋር ሊያስቀኝ የውሸት ፈገግታ ፊቴ ላይ መሳል ስላላስቻለኝ ፈገግ ለማለት እየታገልኩ ልጅቱ እንዳትሄድ በእጄ አቆምኳትና አራቱንም እያየሁ በእኔ ግብዣ ሻይ ቡና ይሉ እንደሆን ጠየቅኩ። ሁሉም በትህትና እምቢ አሉ።
እህም።
ዝም-ቅዝዝ አልኩና ሻዬን ለመጠጣት አነሳሁ። አሁን ግን ቅድም የጣፈጠኝ ሻይ… በስኳር ፋንታ የእማማ የኑሮ ምሬት የገባበት ይመስል ክፉኛ መረረኝ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...